የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ባለፉት ዓመታት የመንግሥትን ተቋማት የፋይናንስና የክዋኔ ኦዲት ግኝቶች በማቅረብና በየመሥሪያ ቤቶች ያለውን የኦዲት ህጸጽ በማውጣት ግንቦት በመጣ ቁጥር ሲጮህ ነበር። ድምጹ/ጥሪው በሚፈለገው ደረጃ ሰሚ ባያገኝም፤ መንግሥት ችግሮቹን ለማረም ባይችልም፤ ተቋሙ ዛሬም የተበላሸውን ለማረም ሥራውንም ጩኸቱንም ቀጥሏል። በዛሬው ዕትማችን ከዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ ጋር ቃለ መጠይቅ አድርገን ባለፉት ዓመታት ስለነበረው ሁኔታ፤ የ2010 በጀት ዓመት ኦዲትና በቀጣይ መደረግ ስላለበት የሰጡንን ሀሳብ እንደሚከተለው አቅርበናል።
አዲስ ዘመን፡- የ2010 በጀት ዓመት ኦዲት አፈፃፀም በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
አቶ ገመቹ፦ የ2010ን በጀት ዓመት የኦዲት ሥራ እያጠናቀቅን ነው። ይሁን እንጂ፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከነበረው የጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ በእቅዳችን መሰረት ጥር 30 ቀን 2011 ዓ.ም ማጠናቀቅ አልቻልንም። አሁን ላይ እስከ የካቲት 15 ቀን 2011 ዓ.ም ለማጠናቀቅ እየሠራን ነው ያለው።
አዲስ ዘመን፡- በኦዲት ሂደት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ካጋጠሟችሁ ችግሮች በተጨማሪ በሌሎች ተቋማት ያጋጠማችሁን ዘርዝረው ቢያብራሩልኝ?
አቶ ገመቹ፡- በኦዲት ሂደት ሌሎች መሰረታዊ የምላቸው ችግሮች የሉም። ተቋማት በወቅቱ ሂሳባቸውን ዘግተው ለኦዲት ዝግጁ አድርገዋል። የገንዘብ ሚኒስቴርም ሂሳብ እንዲዘጉ አድርጓል። በህጉ መሰረት ተቋማት ሂሳባቸውን ዘግተው ለኦዲት ክፍት ማድረግ ያለባቸው መስከረም 30 ነው። ከጥቂት ተቋማት በስተቀር ሁሉም በሚባል ደረጃ ሂሳባቸውን ዘግተው ለኦዲት ዝግጁ አድርገዋል። በመሆኑም ሥራችን አልተስተጓጎለም። በከተማ ውስጥ ያሉ ተቋማት ሁሉም በዚህ ረገድ ችግር የለባቸውም። ከከተማ ውጪ ያሉ፤ በገቢዎችና ጉምሩክ የሞያሌ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት፣ ጅግጅጋ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኦዲት ለማድረግ ገብተን ከጸጥታ ጋር በተያያዘ ችግር ምክንያት ወጥተናል። ከዩኒቨርሲቲዎችም የደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ለኦዲት ዝግጁ ማድረግ አልቻለም። እስካሁንም ችግር ያለበት ነው። የቀብሪ ደሀር ዩኒቨርሲቲ ሂሳቡን መዝጋት አለመቻሉ ሌላው ችግር ነው። ሚዛን ቴፒና አሶሳ ዩኒቨርሲቲዎችም ያለመረጋጋት ነበር። እንዲያም ሆኖ ሠራተኞች ኃላፊነት ወስደው በመሥራታቸው ከተያዘው እቅድ ትንሽ ቀን ቢንፏቀቅም ኦዲቱ ይጠናቀቃል።
አዲስ ዘመን፡- በፋይናንስና ህጋዊነት እንዲሁም በክዋኔ ኦዲት በዘንድሮው በጀት ዓመት ምን ያህል ተቋማትን ኦዲት አደረጋችሁ ?
አቶ ገመቹ፡- ባጠቃላይ 174 ተቋማትን የፋይናንስና ህጋዊነት ኦዲት እናደርጋለን። በአሁኑ ሥራችን ሁሉንም የፌዴራል ተቋማት ኦዲት አድርገናል። 24 አዳዲስ የክዋኔ እና 6 የክትትል ኦዲቶችን ለማድረግ አቅደናል። የያዝናቸው አዳዲስ የክዋኔ ኦዲቶች ሁሉም እያለቁ ናቸው። የክትትል ኦዲቱ ከአንዱ በስተቀር በሁሉም ተጠናቅቋል።
አዲስ ዘመን፡- ቀጣይ ሥራችሁ ምንድን ነው የሚሆነው ?
አቶ ገመቹ፡- ቀጣይ ሥራችን የ2011 በጀት ዓመት የኦዲት ሥራ ዝግጅት እንጀምራለን። እስከ የካቲት መጨረሻም እቅዱ ይዘጋጃል። ከመጋቢት ጀምረን ወደ ሥራ እንገባለን። ሌሎች ሠራተኞች ከየተቋማቱ የተሰበሰበውን ኦዲት የማቀናጀት ሥራ ያከናውናሉ። ከተቀናጀ በኋላ ለምክር ቤት ሪፖርት ለሚያዘጋጀው ቡድን ይሰጣል። ቡድኑም አንኳር የኦዲት ግኝቶችን በመለየት ሪፖርት ያዘጋጃል። በግንቦት ወርም ለምክር ቤቱ ሪፖርት ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- ቀደም ባሉት ዓመታት በኦዲት ሥራችሁ ሂደት የምታቀርቧቸው ቅሬታዎች ነበሩ። ዘንድሮ ይህ ተቀርፏል ?
አቶ ገመቹ፡- በዘንድሮው የኦዲት ሂደት የቢሮ ችግር ብዙም አልታየም። ኦዲት ተደራጊ ተቋማቱ የቢሮ ችግር ያለባቸው ካልሆኑ በስተቀር ችግር አልገጠመንም። የቢሮ ችግር ባለባቸው ተቋማት አቻችለን ሥራችንን ሠርተናል። የመውጫ ስብሰባ በማድረግም ብዙ ችግር አልገጠመንም። አሁንም ችግር ሆኖ የቀጠለው ማስረጃዎችን በወቅቱ የማቅረብ ጉዳይ ነው። አንዳንዶች ማስረጃዎችን በወቅቱ ሳያቀርቡ የመውጫ ስብሰባ ከተደረገ በኋላ ወደዋናው መሥሪያ ቤት ይዘው ይመጣሉ። ይህ ለሥራችን ችግር ሆኖብናል። እኛ የምንሠራው በሰዓትና በደቂቃ ነው። መረጃዎችን በወቅቱ አቅርቦ ኦዲቱን ከማጣራት ይልቅ ጊዜው ካለፈ በኋላ መረጃ ይዞ መጥቶ አስተካክሉልኝ ማለት የእኛን እቅድና ሥራ ያፋልስብናል። ይህ አካሄድ መታረም አለበት። ሌላው ችግር መዋሸት ነው። ባለሙያዎች ኃላፊዎችን ጭምር የማሳሳት ሥራ ይሠራሉ። ባለሙያዎች ያላደረጉትን አደረግን ይላሉ። ከዚህም በተጨማሪ በቂ ማስረጃ ከማቅረብ ይልቅ ምክንያቶችን በመደርደር ያለማስረጃ ለማሳመን የሚደረገው ሙከራ የሚፈጥረው ችግር አሁንም ቀጥሏል።
አዲስ ዘመን፡- የ2010 በጀት ዓመት ኦዲት ጥራት እንዲኖረው ምን የተለየ ጥረት አድርጋችኋል?
አቶ ገመቹ፡- የኦዲት ጥራት እንዲጨምር በተቀመጠው መስፈርት መሰረት እንዲሠሩ ተደርጓል። በእቅድ ዝግጅት ሂደት 50 በመቶ የሚሆነው ፈፃሚ ሠራተኛ ተሳታፊ ነው። ትኩረት የሚያሻቸው ሥራዎች ተለይተው አቅጣጫ ተቀምጧል። የቁጥጥርና የድጋፍ ሥራዎችም እንዲጠናከሩ ተደርጓል።
የኦዲትን ጥራት እኛና ሌሎች አካላት የሚያዩበት መነጽር የተለያየ ነው። እኛ የምንለው የኦዲቱን ጥልቀት በመጨመር የምንሰጠውን ማረጋገጫ ጠንካራ ማድረግ አለብን ነው። ሌሎች የሚሉት ደግሞ፤ ኦዲቱ ትክክል አይደለም የሚል ነው። በእኛ በኩል አንድም ግኝት ያለማስረጃ አናወጣም። ምናልባት በምንሰጣቸው አስተያየቶች ቋንቋ አጠቃቀምና መደምደሚያዎች ላይ ስህተት ሊኖር ይችላል። እንዲያም ሆኖ በተለያዩ አካላት ከዓመት ዓመት እየተገመገመ ነው። ያለንበት ሁኔታም እየተመዘነ ነው። በሂደት ያስተካከልናቸው አሉ። ያላስተካከልናቸውም ይገኛሉ። ካላስተካከልናቸው ውስጥ በኦዲት ብቃትና ጥራት ደረጃ ልክ የመሥራት ክፍተቶች ይታያሉ። ይህንንም ለማስተካክል እየሠራን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ተቋማችሁ በቂ የሰው ኃይል አለው?
አቶ ገመቹ ፡- የሰው ኃይል በቁጥር ደረጃ ብዙ ችግር የለብንም። መቅጠርም እንችላለን። ችግሩ የምንቀጥራቸው ሠራተኞች ብዙም ሳይቆዩ ይለቅቃሉ። የኦዲት ሥራ ከሚማሩት በላይ በሥራ ሂደት በልምድ የሚገኘው ይበልጣል። ከዚህም በተጨማሪ በእቅድ ይዘን ከምንሠራው በተለያዩ ተቋማት ጥያቄ ልዩ ኦዲቶች እንሠራለን። ልዩ ኦዲቱ ለአገርና ለመንግሥት ከሚሰጠው ጥቅም አንፃር በትኩረት እንሠራለን። ከዚህ ጋር በተያያዘ በብቃትና በጥራት በቂ የሰው ኃይል የለንም።
አዲስ ዘመን፡- ምን ያህል ልዩ ኦዲት ሰርታችኋል?
አቶ ገመቹ፡- ከ15 እስከ 20 ልዩ ኦዲቶች ሠርተናል። ያለዕቅድ ስለሚመጣ በመደበኛ ሥራችን ላይ ጫና ያደርጋል። ቁጥሩ ትንሽ ቢመስልም ሥራው ሰፊ ነው። የልዩ ኦዲት ጠያቂዎቹ በርካታ ቢሆኑም ሁሉንም ማስተናገድ አልቻልንም። የሠራናቸውንም ኦዲቶች ከመደበኛው ኦዲት ጋር በማጣጣም ለመሥራት ነው የሞከርነው፤
አዲስ ዘመን፡- በክትትል ኦዲታችሁ ምን ያህሎቹ ተቋማት ጉድለቶቻቸውን አስተካክለዋል?
አቶ ገመቹ፡- ተቋማቱ ጥቂት ነገሮችን ነው ያስተካከሉት፤ አብዛኞቹ እዚያው ባሉበት ነው ያሉት፤ ርምጃ መውሰድ በሚገባቸው ደረጃ አልወሰዱም። የክዋኔ ኦዲት ማስተካከያ ጊዜ ይፈልጋል ብለን ጊዜ ሰጥተን የማስተካከያ ኦዲቱን ለማድረግ ብንሄድም አንዳንዶቹ ረስተውታል። እንደ አገር በመሪዎች መቀያየር ሰበብ ትልቅ የቀጣይነት ችግር አለ። በአጠቃላይ ማስተካከያው አርኪ አይደለም ማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፤ የኃላፊዎች መቀያየር የኦዲትን ግኝት ላለማስተካከል ምክንያት ይሆናል?
አቶ ገመቹ፡- እንደ አገር አንዱ ትልቅ ችግር የተቋም ችግር ነው። ተቋም አሰራር፣ ሥርዓትና ሁሉም ነገር ያለው ነው። የተሟላ ተቋም ካለ መሪ ኖረም አልኖረም ሥራው ይቀጥላል። ነገር ግን በአገራችን በዚህ ደረጃ የሚሠራ ተቋም የለም። መረጃ የሌላቸው ተቋማት አሉ። መረጃ ባለመኖሩም አንዳንድ አዲስ የተመደቡ ኃላፊዎች ለማስረዳት መጥተው ሲጠየቁ አላውቀውም የሚሉ አሉ። ከእቅድ እስከ አፈፃፀም ያሉ ሂደቶችን መዝግቦ የሚይዝ አሰራር በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መዘርጋት አለበት። የዛሬ አስር ዓመት የተሠራ ኦዲት ዛሬ ቢፈለግ ለማቅረብ የሚያስችል፤ ርምጃ መውሰድ የሚገባው ጉዳይም ካለ እንደዚያው፤ ባጠቃላይ መፍትሄ መሰጠት አለበት።
መንግሥትን ባለፉት እየመከርኩት ያለውና ወደፊትም የምቀጥልበት በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የኋላ ታሪክ መረጃዎችን አደራጅቶ የሚይዝ አሰራር መዘርጋት አለበት። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪ በሚል አሰራሩ ተዘርግቷል። ይህ አሰራር በንጉሱም ጊዜ ነበር። ይህ የስራ ክፍል በተቋሙ የሚኖረውን ቢሮክራሲ ይፈታል። ተሿሚ ይመጣል፤ ይሄዳል። በዚህን ወቅት እንዲህ አይነት ስርዓት ቢዘረጋ አሁን በተቋማቶቻችን ያሉትን ችግሮች ይፈታል። ይህ ተቋማዊ አሰራር ተሿሚዎች ተሹመው ቶሎ የመነሳት ችግር ስላለ በተቋሙ አሰራር ላይ መዝረክረክ ይከሰታል። ይህ ካልሆነ ሥራዎች በተከታታይነት መሠራት አለባቸው። አገርን ዋጋ እያስከፈለ ያለው ይህ ነው። ሰዎች በተቀያየሩ ቁጥር የማስተካከያ ሥራ በተቋማት መሠራት አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ዋና ኦዲተር ለፍቶና ጥረት አድርጎ ልፋቱ ወደ ፍሬ አልተለወጠም የሚሉ አሉ። ለዚህ መልስዎ ምንድን ነው?
አቶ ገመቹ፡- ዋና ኦዲተር በሚፈለገው ደረጃ ለውጥ አላመጣም። ቀጣይነት ያለው ጩኽት ጮኸናል። ይህ ለውጥ ማምጣት ነበረበት። ግን በሚፈለገው ደረጃ ለውጥ አልመጣም። ለምሳሌ፤ በፋይናንስ ላይ በሠራነው ሥራ ሙሉ ለሙሉ ስህተት መታረም ባይችልም አውቀው የሚሠሩ ጥፋቶች መቆም ነበረባቸው። ግን አልቆሙም፤ እናም በሚፈለገው ደረጃ ለውጥ አልመጣም።
ያለፉትን ዓመታት የኦዲት ሪፖርት እንመለከትና ካሁኑ ሁኔታ ጋር ሳስተያየው ለውጥ ካላመጣሁ እዚህ ምን እሰራለሁ ብየ ራሴን እጠይቃለሁ። የሚፈለገውን ለውጥና ውጤት አላመጣንም። ሪፖርቱ ጩኸትና ረብሻ ነው። አንድ ጊዜ ሪፖርት አቅርበን ጮኸን ይቀራል። ለዚህ ደግሞ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ። በእኛ በኩል በእርግጠኛነት ኃላፊነታችንን ተወጥተናል። እንደ ዋና ኦዲተር ማድረግ ሲገባን ያላደረግነው አለ ለማለት በጣም እቸገራለሁ። ሁሉንም ጥረት ለማድረግ ሞክረናል። በሚፈለገው ደረጃ እንዲሆንም ሠርተናል።
አዲስ ዘመን፡- ለውጡ ያልመጣው በምን ምክንያት ነው?ለውጥ ከሌለስ ለምን ትለፋላችሁ?
አቶ ገመቹ፡- እንዲህ ስልህ ምንም ለውጥ አልመጣም ማለት አይደለም። ለምሳሌ፤ የመንግሥት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ጥናት እና ዲዛይን የላቸውም። የመንግሥትን ገንዘብ እያስወጡ በተባለው ጊዜም እየተጠናቀቁ አይደለም። ተጠናቅቀውም የሚገባቸውን አገልግሎት እየሰጡ አይደለም በማለት መጮህ የጀመርነው ከዛሬ አምስትና ስድስት ዓመት በፊት ነው። በወቅቱ እርምጃ አልተወሰደም።
ከብዙ ጊዜ በኋላ ቢሆንም አሁን ላይ መንግሥት ጥናት ሳይደረግ ፋይናንስ አናደርግም ወደማለት ገብቷል። ይህ ለእኔ ውጤት ነው። ዋናው ግን ይህን የሚከለክል አሰራር መዘርጋት ነው። ከዚህ አንፃር ፕላን ኮሚሽንም የጀመራቸው ሥራዎች አሉ። የሚኒስትሮች ምክር ቤትም ደንብ አውጥቷል። የመንግሥት ልማት ፕሮጀክቶች የሚመሩበት መመሪያ በፕላን ኮሚሽን እየተዘጋጀ ነው። ይህ ለእኔ ፍሬ ነው።ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ተሠርተው አያልቁም። ይህ የሚያመጣውን ኪሳራ ደምረን አላየነውም። ፕሮጀክቶች በጊዜ አለመጠናቀቃቸው እንደ አገር ምን ያህል ጉዳት እንደሚያደርስ በዘንድሮው ሪፖርታችን እናካትታለን። በምን ያህል ገንዘብ ተጀምረው በምን ያህል ተጠናቅቀዋል የሚለውንም እናያለን።
የዩኒቨርሲቲዎችንና የሌሎች ችግር ያለባቸውን ተቋማት ለማስተካከል ምክር ቤቱ ልዩ ኮሚቴ አቋቁሞ እየሠራ ነው። ይህ ሌላው ፍሬ ነው። ምናልባት አሰራር መዘርጋት አንድ ነገር ነው። አንዳንዱ አሰራር እያለም የተፈጠሩ ችግሮች አሉ። በኦዲቱ ዘርፍ ተጠያቂነት አሁንም የሚቀርና ያልተሰራበት ጉዳይ ነው። ተጠያቂነትን በማረጋገጥ ደረጃ ለውጥ መጥቷል ብዬ አላምንም። ተጠያቂነቱ ከመጣ ሥራችን እሴት ይጨምራል። ተጠያቂነት መጥቶ እሴት ካልጨመረ መንግሥት ለዚህ ተቋም በዓመት የሚመድበውን በጀት ሦስትና አራት ትምህርት ቤት ቢሠራበት ይሻላል።
አዲስ ዘመን፡- ተቋሙ ከጮኸና ኃላፊነቱን ከተወጣ ፍሬያማ ነው ማለት አይቻልምን? የመስተካከል ተስፋ የለውም ወይ?
አቶ ገመቹ፡- ሥራዎችን በዜሮ እያበዛን አይደለም። የተስተካከሉ ጉዳዮች አሉ። በመስተካከል ላይ ያሉም አሉ። ከዚያ በላይ ለእኔ ትልቁ ተስፋ የሚሰጠኝ ፖለቲካዊ መነሳሳት ይታያል። ጊዜ ሊወስድ ይችላል እንጂ ይለወጣል። ዋናው ፖለቲካዊ ፍላጎት ነው። ይህ ፍላጎት ካለ ተጠያቂነት አይቀርም። ምክንያቱም ሞኝና ወረቀት የያዘውን አይልቅምና የተሠሩ ኦዲቶች በሙሉ በየተቋማት መደርደሪያ ላይ አሉ።
በሌላ በኩል፤ በሚፈለገው ደረጃ አልፈጠንንም እንጂ፤ ከጠቅላይ አቃቤ ህግ ጋር እየተነጋገርን ነው። አልጠየቅም ብሎ የሚያስብ ካለ በእርግጠኛነት መጠየቁ አይቀርም። ታዲያ፤ የረጅም ዓመቱን ሁኔታ ነው እንዲህ ያልኩት እንጂ ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ በምክር ቤቱም፤ በመንግሥትም ደረጃ እየተደረጉ ያሉ ሁኔታዎች ተስፋ ሰጭ ናቸው። ምን አደርጋለሁ ለሚለው፤ አገሬን እንዳገለግል በዚህ እድል ከተሰጠኝ ማድረግ በምችለው ደረጃ ማገልገል አለብኝ ነው የምለው፤ ለውጡ ፈጥኖ እንዲመጣ መሥራት አለ ብኝ ። አሁን ላይ ምክር ቤቱ ከፍተኛ ግምገማ እያደረገ ነው። ከ8 ዓመት በፊት ፓርላማው ይለኝ የነበረው “ምን እርምጃ ወሰድክ?” ነበር። አሁን ይህን አይጠየቁኝም። የዋና ኦዲተር ሀላፊነት ምን እንደሆነ ተረድተዋል። የምክር ቤቱ አባላት በጉብኝት ክትትል ያደርጋሉ። ይህ ትልቅ ነገር ነው። ከዚያም በላይ ሪፖርቱን ሰምተን ዝም አንልም በማለት በምሬትና በቁጭት ልዩ ኮሚቴ አቋቁሟል። ለዚህ ሥራው ለምክር ቤቱ ልዩ ምስጋና አቀርባለሁ! ውጤት አመጣም አላመጣም። ምክንያቱም የመጀመሪያ ትልቅ ስራ ስለሆነ፤ አስፈፃሚውም ቢሆን በካቢኔ ደረጃ ከሶስት ዓመት በፊት ጀምሮ የገንዘብ ሚኒስትር የማስፈፀሚ እቅድ አዘጋጀቷል። የተወሰደውን ርምጃ ለፓርላማውና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እያቀረበ ነው። እኔ በማስበው ደረጃ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አሁን በከፍተኛ ደረጃ ተነሳሽነት አለው። አካሄድ ላይ አልተስማሙም እንጂ እየሄዱበት ነው። ይህ የፖለቲካ ፍላጎት ነው። በመዳረሻችን ብርሃን ይታየኛል። መጠየቅ አይቀርም የምልህ ለዚህ ነው።
ከሁለት ዓመት በፊት ባዘጋጀነው የማጠቃላይ ሪፖርት የህግ ጥሰት ሳይጨመር ወደ 700 ሚሊዮን ብር ይመለስ ብለናል። ያኔ ስናይ 17 ሚሊዮን ብር ነው የተመለሰው። ኦዲተሩ የጠበቀው ከዚህ በላይ ነው። ተስፋ የመቁረጥ ምልክት የለም። እንቀጥላለን።
አዲስ ዘመን፡- ልዩ ኮሚቴው መቼ ተቋቋመ? ምንስ ሠራ?
አቶ ገመቹ፡- ምክር ቤቱ ልዩ ኮሚቴ ያቋቋመው በ2010 ዓ.ም ነው። ከተቋቋመ በኋላ አባላቱ ዕረፍት ሄደው ነበር። ሲመለሱም በምክር ቤቱ አዳዲስ ነገሮች ነበሩ። የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎች ተለዋውጠዋል። የልዩ ኮሚቴው ተግባርና ቆይታ እስከ ጥር 30 ቀን 2011 ይጠናቀቃል የሚል ነበር። ነገር ግን የተወሰነ ጊዜ ዘግይቷል። ልዩ ኮሚቴው አሁን ላይ የሚችለውን ሥራ አከናውኖ ሪፖርት እያዘጋጀ ነው። በሂደቱ ማስረጃ በመስጠት ዋና ኦዲተር ሲያግዝ ነበር። ኮሚቴውም የሚቻለውን አድርጓል። ይህ መልካም ጥረት ነው። ከዚህ በተጨማሪ መንግሥት እየወሰዳቸው ያሉ ርምጃዎች የኦዲት ሥራውን የሚያጠናክሩና ተስፋ የሚሰጡ ናቸው። ለዚህ ሁሉ ኮሚቴው ማጠቃለያ ያቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- ኮሚቴው ምን ውጤት አመጣ?
አቶ ገመቹ፡- ኮሚቴው ለማስተካከል ያሰበውን ሥራ በመፈጸም ረገድ ብዙ ተቋማት ማስተካከያ አላደረጉም። ማስተካከያ ያደረጉ የተወሰኑ ተቋማት ናቸው። ገቢዎች አንድ ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን በእኛ በኩልም ማረጋገጫ ሰጥተናል። የተወሰኑት ተቋማት ስላደረጉት ማስተካከያ ያረጋገጥንላቸው አሉ። አብዛኛዎቹ ተቋማት ግን በሂደት ላይ ናቸው። አሳማኝ ርምጃ አልወሰዱም። መወሰድ አለበት ብለን የመከርነው አስተዳደራዊና ህጋዊ ርምጃ ነው። ህጋዊና አስተዳደራዊ ርምጃ አልተወሰደም። አስመልሱ ያልናቸውን ገንዘብ እንኳን ማስመለስ አልቻሉም። አላግባብ የተሰጠ ገንዘብ «በደብዳቤ ጽፌ ስለሰጠሁ ይህን ማስመለስ አንችልም» ነው የሚሉት፤ አብዛኞቹ ይህን ያደረጉ ሰዎች ደግሞ በቦታቸው የሉም። ሰዎች የወሰዱትን ትርፍ አበል እንኳን አስመልሱ ብለን መክረን ይህን እንኳን ያላስመለሱ ይገኛሉ። በዚህ ብቻ አላበቃም። አሁንም በዚህ ሥራ የገፉበት አሉ።
አዲስ ዘመን፡- ፓርላማው በልዩ ኮሚቴ ማስተካከል ካልተቻለ ወደ ርምጃ እንደሚገባ ተገልጿል፤ በቀጣይ ምን አይነት ርምጃ መወሰድ አለበት ይላሉ?
አቶ ገመቹ፡- ፓርላማ ማድረግ የሚችልው ሁለት ነገር ነው። በቀጥታ ርምጃ መውሰድ አይችልም። ይህን እንጂ፤ ፓርላማው ችግሩን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በማቅረብ ርምጃ እንዲወስዱ ማድረግ ይችላል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠንካራ መረጃ ከመጣ ርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆናቸውን ለምክር ቤቱ አባላት ገልጸውላቸዋል። የሚወሰደው ርምጃ አንዱ ይኸ ነው። ፖለቲካዊ እርምጃ በመውሰድ ረገድ ብዙዎቹ ከሹመት ስለተነሱ ብዙም ውጤት የለውም። ተጠያቂ ለማድረግ ካስፈለገ ግን በጠቅላይ አቃቤ ህግ በኩል ህጋዊ መንገድ መጠቀም ይቻላል። በዋናነት መሠራት ያለበት ግን ያለፈውን ተጠያቂ ከማድረግም በላይ ችግሩ እንዳይቀጥል መሥራት ነው። ይህንን ለአዲሶቹ አመራሮችም በደንብ ማስረዳት ያስፈልጋል። በ2011 በጀት ዓመትም ይህ እንደሚሻሻል ተስፋ አደርጋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በአገሪቱ እየታየ ካለው ችግር አንፃር ዋና ኦዲተር ኦዲት ከማድረግ በተጨማሪ የሚያጎድሉ ተቋማትን የመጠየቅ ሥልጣን ቢሰጠው ችግሩን ያቃልለው ይሆን ?
አቶ ገመቹ፡- በዓለም ላይ የኦዲት አሰራሮች ሁለት ዓይነት ናቸው። እነዚህም፤ በአምድ በኩል ኦዲት ብቻ የሚያደርጉ የኦዲት ተቋማት፤ በሌላ በኩል ኦዲት የሚያደርጉና ጉድለት ያለባቸውን ተቋማት ራሳቸው በፍርድ ቤት በመጠየቅ ሁለቱንም አጣምረው የሚሠሩ ናቸው። ይህ ዓይነት አካሄድ ሥራውን ፈጣን ያደርገዋል። ነገር ግን፤ አሁን ባለው አካሄድም ውጤታማ ማድረግ ይቻላል። አሁንም በጠቅላይ አቃቤ ህግ በኩል መክሰስ ይቻላል። ይህን ሥርዓት መዘርጋት ሥራውን ቢያፋጥነውም ለኔ ትልቁ ነገር ብዬ የማስበው ተቋም የመገንባት ጉዳይ ነው። ጠንካራ ተቋም ከተገነባ ህግና ሥርዓት አስከብሮ መሄድ ይቻላል። ተጠያቂነትንም ማረጋገጥ ይቻላል። በመሆኑም ይህ እስከተረጋገጠ ድረስ በየትኛውም ሥርዓት ብንሄድ ችግር አይሆንም።
አዲስ ዘመን፡- በኦዲት ሥራቸው የምታመሰግኗቸውንና ችግር አለባቸው የምትሏቸውን ተቋማት ሊገልጹልኝ ይችላሉ?
አቶ ገመቹ፡- በጋራ ለመግባባት ጥሩ የሆኑትን ጥሩ ናቸው ማለት ይጠቅማል። በኦዲት እሳቤ ግን ዛሬ ጥሩ የሆኑት ነገ ጥሩ ላይሆኑ ይችላሉ። ዛሬ ላይ ጥሩ ናችሁ ብዬ ባሞገስኩበት አፍ ነገ ችግር ሲፈጥሩ ልወቅሳቸው አልችልም። ጥሩና መጥፎ መሆናቸውን የሚናገረው የምናወጣው የኦዲት ሪፖርት ነው። በተከታታይ ንጹህ አስተያየት ካላቸው ጥሩ ናቸው ማለት ነው። በአጠቃላይ ግን፤ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የገዘፈ የኦዲት ችግር አለባቸው። ከእነሱ በተጨማሪ ግዙፍ የመንግሥት ፕሮጀክቶችም ችግር ያለባቸው ናቸው። ከዚህም ባለፈ በጀታቸው ትንሽ ሆኖም አውቀው ጭምር የሚያጠፉ ተቋማትም ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን፡-ኢትዮጵያ በአፍሪካና በዓለም ደረጃ በኦዲት ያለችበት ደረጃ እንዴት ይገለፃል?
አቶ ገመቹ፡- በዓለም ደረጃ አብዛኞቹ የበለጸጉት አገራት የክዋኔ ኦዲት ነው የሚያደርጉት። በክዋኔ ኦዲታቸው የአሁን ብቻ ሳይሆን የቀጣይ አስጊ ሁኔታዎችን ጭምር ይተነትኑበታል። በክዋኔ ኦዲት የተልዕኮአቸውን ስኬት ግምገማ እያካሄዱ ናቸው። በውጤት ሲመዘን የተሻለ ነው። ከዚህ አንፃር እኛ በጣም ሩቅ ነን።
በአፍሪካ ደረጃ ኦዲት ድብልቅ ነው። እኛም ኦዲት በማድረግ ደረጃ ወደኋላ አልቀረንም። በየዓመቱ ሁሉንም ተቋማት ኦዲት በማድረግ የተሻልን ነን። ይህን የሚያደርጉት ጥቂት የአፍሪካ አገራት ናቸው። ይህ ጥሩ ነው። በክዋኔ ኦዲት ደረጃ ሲታይ እኛ የሚቀረን ብዙ ነው። ካለን ሀብት ውስንነት አንፃር ጥልቀት ይቀራል። በርምጃ አወሳሰድ ደረጃ ግን ከእኛ የተሻሉ አገራት አሉ። ከኦዲቱ ተነሰተው ጠንካራ ርምጃ ይወስዳሉ። እኛ ተጠያቂነትን በማረጋገጥ ደረጃ ወደኋላ ነን።
በፓርላማ ክትትል ኢትዮጵያ ጥሩ ደረጃ ላይ ነች። በሌሎች የአፍሪካ አገራት አሰራሩ ችግር ያለበት ነው። የእኛ የተሻለና ለሌሎችም አገራት ትምህርት የሚሆን ነው። ሁሉም ቋሚ ኮሚቴዎች የኦዲት ክትትል ያደርጋሉ። የመንግሥትም የፖለቲካ መነሳሳትም መልካም ነው። ተቋሙን ለመደገፍ የሚያደርገው ጥረት ጥሩ ነው። በህግ ማዕቀፍ ረገድ በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃችን ጥሩ ነው። በህግ ደረጃ አንድ የሚነሳው በአዋጁ የተቀመጡ አንዳንድ ነገሮች በህገ መንግሥት ውስጥ መካተት አለባቸው ብለው የሚከራከሩ አሉ። የእኛ የህግ አረቃቀቅ ያንን አይፈቅድም። ይህን የሚያነሱት አዋጅ በቀላሉ ይሻሻላል ከሚል ነው። በሥራው ላይ ያለው ነፃነት የተጠበቀ ነው። አስተዳደራዊ ነፃነቱን ለማስጠበቅም ከሲቪል ሰርቪስ ተጽዕኖ ውጪ ሠራተኞችን በራሱ ለመቅጠር የሚያስችል አሰራር በፓርላማ ጸድቋል። የበጀት ነፃነትን በህጉ መሰረት ተግባራዊ ለማድረግ እየተሠራ ነው። ከፓርላማው መልካም ምላሽ አለ። እስካሁን ያለው መልካም ነው፤ አሁንም ግን ተቋሙ ለአገር ካለው አስተዋጽዖ በተለየ መልኩ መጠናከር ይገባዋል። የተጠያቂነቱን ሥርዓት ማጠናከርም ያስፈልጋል። ይህን የሚያደረግ ከሆነ አሁን በኦዲት ላይ የሚታየው ጫጫታ እየቀነሰ ይሄዳል። ሙሉ ለሙሉ ግን አይጠፋም። ምክንያቱም ስጋ መሬት ላይ ሲወድቅ ቆሻሻ ሳይይዝ አይነሳም። ኦዲትም እንደዚያ ነው።
አዲስ ዘመን፤ ስለሰጡኝ ቃለ ምልልስ በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ ገመቹ፤ እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን የካቲት 13/2011
አጎናፍር ገዛኽኝ