የፍልውሃዎች አገልግሎት በዋናነት የሆቴልና የስፓ አገልግሎቶችን ለህብረተሰቡ እየሰጠ የሚገኝ አንጋፋ ተቋም ነው። ሆቴሉ የመኝታ፣ የምግብና የመጠጥ አገልግሎት ሲሰጥ በስፓ አገልግሎቱ ደግሞ የመታሻ፣ የመታጠቢያ፣ የፊዝዮትራፒና የስቲም አገልግሎት እንደሚሰጥ የሚገልጹት አቶ ገብረፃድቃን አባይ የፍልውሃዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ናቸው። የፍልውሃዎች አገልግሎት 99 በመቶ ለሚደርሱ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች አገልግሎቱን እየሰጠ ይገኛል፡፡ አገልግሎቱን ለማህበረሰቡ በተሻለ አቅም ተደራሽ ለማድረግ ድርጅቱ እየሠራ ነው። በተለይም የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ትብብሩን አጠናክሮ ቢቀጥልና ከተማ አስተዳደሩም ከድርጅቱ ጎን ቢቆም ለሀገሪቷ የተሻለ ገቢ በማመንጨት ኢኮኖሚውን መደገፍ እንደሚቻል ዳይሬክተሩ ይጠቅሳሉ።
የላንጋኖ ሪዞርት ሆቴልን ጨምሮ 600 ቋሚና 350 የኮንትራት ሠራተኞችን የያዘው የፍልውሃዎች አገልግሎት ድርጅት በቀን በአማካኝ በስፓ አገልግሎት ብቻ ከ10 እስከ 14 ሺህ ለሚደርሱ ዜጎች የተሟላ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በሆቴል ደግሞ በቀን በአማካኝ እስከ 500 ለሚደርሱ ሰዎች አገልግሎት በመስጠት ላይ ነው። የፍልውሃዎች አገልግሎት ድርጅት ባለፉት ተከታታይ ዓመታት ጥሩ አፈፃፀም እያስመዘገበ የቆየ ተቋም ነው። ይሁን እንጂ ባለፉት ስድስት ወራት የነበረው አፈጻፀም ካለፉት ጊዜያት ጋር ሲነጻፀር ዝቅተኛ የሚባል መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ያነሳሉ። ማሳያቸውም ለደንበኞች የተለያዩ አገልግሎቶችን በመስጠት 39ሚሊዮን ትርፍ ለማግኘት አቅዶ 76 በመቶ ያህሉን ማስመዝገብ ችሏል። በመሆኑም በቀሪዎቹ ስድስት ወራትም ጉድለቱን ለማካካስ ይሰራል ነው ያሉት። ለዕቅድ አፈፃፀሙ መቀነስ ከሚጠቀሱ ምክንያቶች መካከል አንዱ በጸጥታ ችግር ሳቢያ ደንበኞች በመስጋታቸው በፍልውሃዎች አገልግሎት ስር የሚተዳደረውና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ስር ያለው የላንጋኖ ሪዞርት ሆቴል የሚፈለገውን ያህል አገልግሎት መስጠት አልቻለም። ሌላው በአዲስ አበባ ፍልውሃ አገልግሎት የቀዝቃዛ ውሃ ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መሄዱም ይገኝበታል።
አገልግሎቱ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመሆን የቀዝቃዛ ውሃ እጥረቱን ለመፍታት ጥረት እያደረገ ይገኛል። እንዲሁም የላንጋኖ ሪዞርት ሆቴልን በተመለከተ ዘለቄታዊ መፍትሔ ለመስጠት ለሦስተኛ ወገን በሽያጭ እንዲተላለፍ በቀጣይ ስድስት ወራት ወስኖ እንደሚያሳውቅ መንግሥት የልማት ኤጀንሲ ማሳወቁን ይፋ አድርጓል። የብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካና የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት በውጭ ሽያጭ ከፍተኛ አፈፃፀም በማስመዝገብ ለሀገሪቷ የውጭ ምንዛሪን ማስገኘት የቻሉ ተቋማት ናቸው፡፡ ይህም ይፋ የሆነው የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ የዘጠኝ የልማት ድርጅቶችን የስድስት ወራት አፈፃጸም በገመገመበት ወቅት ነው። አቶ አሰፋ ጉያ የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር፤ የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት ከቀረጥ ነፃ አገልግሎቶችና ቀረጥ የተከፈሉባቸውን ሱፐር ማርኬቶች የሚያስተዳድር ድርጅት መሆኑን ገልፀዋል። ድርጅቱ አስር የተለያዩ መደብሮችና አስር የዕደጥበባትና የስነጥበባት መሸጫዎች አሉት።
በተጨማሪም ድል ገበያ ሱፐርማርኬትና አራት የተለያዩ የመጠጥ መሸጫ መደብሮችንም ያስተዳድራል። ድርጅቱ ዘጠኝ ዓይነት ምርቶችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ያሉት ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል የስልክ ስክሪንን ጨምሮ የእንጨት ውጤቶችን፣ ስዕል፣ ሸክላ፣ ሴራሚክና ቀርከሃ ምርቶች ይገኙበታል። እነዚህን ምርቶች ለውጭና ለአገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪን ለሀገሪቱ ያስገኛል። በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራትም 243 ሚሊዮን ብር ለማግኘት አቅዶ 232 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘት ችሏል። በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት የተገኘው ገቢ ካለፈው ዓመት አፈፃፀም ጋር ሲነጻፀር ከፍተኛ ለውጥ የታየበት ነው። በአሁን ወቅት በሀገሪቱ እየሰፈነ ያለውን ሰላም ተከትሎ ዲያስፖራው ወደ ሀገሩ በመግባቱና አጠቃላይ የቱሪስቶች ቁጥርም እየጨመረ መምጣቱ ለገቢው መጨመር ምክንያቶች ናቸው።
በዓመቱ ወደ 500 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት በዕቅድ የተያዘ ሲሆን፤ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ያሳካውን መነሻ በማድረግ በቀሪ ጊዜያት ውስጥም ሙሉ በሙሉ ዕቅዱን ለማሳካት እየተሠራ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ያምናሉ። ድርጅቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪን በማስገ ኘት ኢኮኖሚውን እያገዘ የሚገኝ ነው። መንግ ሥት በዘርፉ ያሉ ችግሮችን በመፍታት ረገድ የተለያዩ እገዛዎችን ሊያደርግ ይገባል የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ አቶ አሰፋ፤ በአሁን ወቅት ድርጅቱ ሊያከናውን በዕቅድ የያዛቸውና ከመን ግሥት ድጋፍ የሚያስፈልጉት ሁለት ትላልቅ ፕሮጀክቶች እንዳሉት ይፋ አድርገዋል። ከእነዚህ ትላልቅ ፕሮጀክቶች አንዱ የኪነ ጥበባት የልዕቀት ማዕከል ግንባታ ነው። በማዕከሉ የተለያዩ ግብዓቶችን ማለትም ሸክላ፣ ቀርከሀና እንጨትን በመጠቀም የተለያዩ ቁሳቁሶችን መሥራት የሚያስችል ሥልጠና የሚሰጥበት ይሆናል። ሁለተኛው ፕሮጀክት ደግሞ ከቀረጥ ነጻ የሆነ ትልቅ የገበያ ማዕከል በመገንባት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ነው፡፡ ይህንንም ለማሳካት ድርጅቱ እየሠራ ይገኛል። እነዚህን ሁለት ትላልቅ ፕሮጀክቶች ዕውን ለማድረግ መንግሥት የሚያደርገው ድጋፍ ወሳኝ ነው የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በተለይም የቱሪዝም ፍሰቱ እየጨመረ የመጣ በመሆኑ የውጭ ምንዛሪን ማስገኘት ያስችላል። በተለይም ሁለቱን ፕሮጀክቶች ዕውን ማድረግ ሲቻል የሀገሪቱን ኢኮኖሚ አንድ እርምጃ ከፍ ማድረግ ያስችላልም ብለዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ሚሊዮን ሄክታር የቀርከሀ ምርት እንደሚገኝ ጥናቶች ያሳያሉ የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ ሀገሪቷ ይህን ምርት ተጠቅማ ወደ ዘመናዊ ምርት በመቀየር ኢኮኖሚው ላይ በጎ ተፅዕኖ ማምጣት ይቻላል። ይሁን እንጂ ይህ ምርት ትልቅ ፋይናንስ የሚፈልግ እንደመሆኑ መንግሥትም ለዘርፉ ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል። ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ በዋናነት የአልኮል መጠጥ የሚያመርት ፋብሪካ ነው። አቶ ኃይለማርያም ግደይ የብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ዋና ሥራ አስፈፃሚ እንደገለጹት፤ ፋብሪካው በስድስት ወራት የአልኮል መጠጥ 359 ሚሊዮን ብር ለመሸጥ አቅዶ 396 ሚሊዮን ብር መሸጥ ችሏል።
ከዚህም 103 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ አግኝቷል። የአልኮል መጠጦችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ 223 ሺህ ዶላር ማግኘት ችሏል። ይህም ድርጅቱ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ለአገሪቱ ኢኮኖሚ የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል። ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ከሚያመርተው የአልኮል መጠጥ በተጨማሪ በተለያዩ ማህበራዊ ኃላፊነቶችንም እየተወጣ ነው፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ፋብሪካው ባለበት መካኒሳ አካባቢ ለሚገኙ የፀጥታ አካላት ማረፊያ ህንጻ ገንብቷል። እንዲሁም ለአካባቢው ማህበረሰብ የውስጥ ለውስጥ የምንጣፍ ድንጋይ(ኮብልስቶን) መንገድ አሠርቷል። ለእነዚህ ማህበራዊ ሥራዎችም ከ400ሺ ብር በላይ ወጪ አድርጓል።
ለሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽንም ለስፖርታዊ ውድድሮች 100ሺ ብር ድጋፍ አድርጓል። እንዲሁም ለመቄዶኒያ አረጋውያን ማህበርም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ጥሪ መሰረት በጥሬ ገንዘብ ግማሽ ሚሊዮን ብር እና ለህክምና የሚያገለግል 200 ሊትር አልኮል በመለገስ ማህበራዊ ተሳትፎ እያደረገ የሚገኝ ፋብሪካ ነው። የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ የዘጠኝ የልማት ድርጅቶችን የስድስት ወራት አፈፃፀም በገመገመበት ወቅት የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከዕቅዱ 143 በመቶ፣ የብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ የዕቅዱን 116 በመቶ፣ የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት የዕቅዱን 112 በመቶ፣ የግዮን ሆቴሎች ድርጅት የዕቅዱን 105 በመቶ እና ሆቴሎች ልማት አ.ማ (ሂልተን) የዕቅዱን 93 በመቶ ከታክስ በፊት ትርፍ በማስመዝገብ የተሻለ አፈፃፀም አሳይተዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 13/2011
ፍሬህይወት አወቀ