የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሀገራት እጅግ አነስተኛ የኢኮኖሚ ትስስር ካለባቸው አካባቢዎች አንዱ ነው። በሀገራቱ መካከል ያለው የገቢ እና የወጪ ንግድ ግንኙነት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት የሆነው የቀጣናው ሀገራት በመሰረተ ልማት ያልተሳሰሩ መሆናቸው ነው። ይህንን ነባራዊ ሁኔታ ለመቀልበስ እና የአካባቢውን ሀገራት በማስተሳሰር የበለፀገ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሁሉም ነገር ተወዳዳሪ የሆነ፣ የተረጋጋ እና በፖለቲካ የተሳሰረ የምስራቅ አፍሪካን እውን ለማድረግ እንዲሁም በሂደት የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና እውን ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶች ሲደረግ የቆየ ቢሆንም የሚፈለገውን ያህል ትስስር ማምጣት ሳይችል ቆይቷል።
የላፕሴት ፕሮጀክት ይህንን የቀጣናውን ችግር በመሰረታዊነት ሊፈታ ይችላል ተብሎ የሚገመት ፕሮጀክት ነው። የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የንግድ ግንኙነትን ለማቀላጠፍ የላፕሴት ፕሮጀክት በኬንያ፣ በኢትዮጵያ እና በደቡብ ሱዳን መንግስታት እ.አ.አ በ2012 የተጀመረ ትልቁ ቀጣናዊ ፕሮጀክት ነው።
25 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር የሚፈጀው የላፕሴት ፕሮጀክት በፍጥነት መንገድ፣ በባቡር፣ በሀይል ማስተላለፊያዎች፣ የአይሮፕላን ማረፊያዎች፣ በመዝናኛ ከተሞች እና በሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶች አማካኝነት በኢትዮጵያ፣ በኬኒያ እና በደቡብ ሱዳን መካከል እንከን የለሽ ትስስር የመፍጠር ውጥን ያነገበ ነው። በዚህም ፕሮጀክቱ በሶስቱ ሀገራት ውስጥ የሚኖረውን ከ170 ሚሊዮን በላይ የሚሆን ህዝብን ያገናኛል።
ኮሪደሩ ሶስቱን ሀገራት ከማገናኘት በተጨማሪም በሂደት ሌሎች የቀጣናውን ሀገራት ማስተሳሰር የሚያስችል ነው። በረጅም ጊዜ ደግሞ በምስራቅ አፍሪካ በህንድ ውቂያኖስ ዳርቻ ከምትገኘው ላሙ ወደብ በመነሳት ከምዕራብ አፍሪካ የባህር ዳርቻ ዱዋላ ወደብ ጋር የሚያገናኝ ትልቁ የመሬት ድልድይ አካል ነው። ኮሪደሩ የቀጣናው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማሳለጥ የሚያስችል ሲሆን የፕሮጀክቱን ወጪ ሶስቱ ሀገራት የሚሸፍኑት ነው።
እ.አ.አ በ2012 የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት በ2030 የማጠናቀቅ ግብ ያነገበ ነው። የላፕሴት ፕሮጀክት አካል የሆነው የለሙ ወደብ ሰሞኑን በኬኒያው ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬኒያታ ተመርቆ ወደ ስራ መግባቱ ፕሮጀክቱን ያፋጥነዋል ተብሎ ይታሰባል።
የሞጆ-መቂ-ባቱ የፍጥነት መንገድ ምዕራፍ አንድን በቅርቡ መጠናቀቅን ተከትሎ የላፕሴት አባል ሀገራት ሚኒስትሮች ይህንን የፍጥነት መንገድ በጎበኙበት ወቅት እንደተናገሩት፤ የሞጆ መቂ ባቱ ፍጥነት መንገድ መጠናቀቅ ለቀጣናው ትስስር ፋይዳው የላቀ ነው ብለዋል። የቀድሞ የኬንያ ጠቅላይ ሚኒስትርና የአፍሪካ ኅብረት የመሠረተ ልማት ልዩ ልዑክ ራይላ ኦዲንጋ በዚሁ ጊዜ ፕሮጀክቱ ቀጠናውን በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ የተለያዩ የእድገት ምዕራፎች እንዳሉት ጠቁመው፤ ፕሮጀክቱ ለቀጠናው ብቻ ሳይሆን በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ላለው ለአህጉሪቱ የኢኮኖሚያዊ ውህደት መፋጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
በተለይም ደግሞ በቅርቡ ወደ ሥራ የገባው የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና እንደ ‘ላፕሴት’ ያሉ የትስስር መሰረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሚያደርጉ ፕሮጀክቶች ያስፈልጉታል ብለዋል። ይህም አህጉሪቱ በንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም የሰዎች ነጻ ዝውውር እንዲጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ነው የአፍሪካ ኅብረት ልዑኩ ራይላ ኦዲንጋ የገለጹት።
የላፕሴት ፕሮጀክት ሦስቱን ሀገራት በትራንስፖርት በማስተሳሰር ረገድ የያዘውን ውጥን እውን እንዲሆን ሁሉም የዘርፉ ተዋንያኖች በጋራ እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል። የኬንያ ቀጣናዊ የልማት ትስስር ሚኒስትር አዳን ሞሃመድ በበኩላቸው “ፕሮጀክቱን ዓላማ ከግብ ለማድረስ በቅድሚያ ቀጠናዊ ስትራቴጂ መንደፍ ይገባል” ብለዋል።
ይህን በማድረግም ፕሮጀክቱ የዘረዘራቸውን አካባቢያዊ የኢኮኖሚ እቅዶች ማሳካት እንደሚቻል ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቱ የቀጣናው ሀገራት ያላቸውን የኢኮኖሚ ትስስር በማጠናከር እድገታቸውን ያፋጥንላቸዋል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ትራንስፖርት ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ ናቸው። የዚሁ ፕሮጀክት አካል የሆነውና በቅርቡ በኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ የተከፈተው የላሙ ወደብ የኢትዮጵያን የወደብ አማራጭ በማስፋት ትልቅ ጠቃሜታ እንዳለው ገልጸዋል።
የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣና እንዲሁም ለኢትዮጵያ ባለው ፋይዳ ዙሪያ ጥናት ያካሄዱት አቶ ሙሴ ምንዳዬ እንደሚሉት የላፕሴት ፕሮጀክት የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣናን እውን ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ፋይዳው የጎላ ነው። በተለይም የራሷ ወደብ ለሌላት ኢትዮጵያ አዲስ የወደብ አማራጭ ሆኖ የሚያገለግል ነው። ፕሮጀክቱ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ሀገራት ሚናቸውን መወጣት አለባቸው።
የፕሮጀክቱ ዕምብርት ትሆናለች ተብላ የምትጠበቀው የኬንያዋ ላሙ ወደብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከታንዛኒያና ጅቡቲ ወደቦች ከባድ ፉክክር መግጠሙ ተግዳሮት ሆኖ ቆይቶ ነበር። በተለይም ከኬንያ ጋር ወደ ላሙ ወደብ የጋራ ነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ ለመዘርጋት ተስማምታ የነበረችው ኡጋንዳ ሃሳቧን ቀይራ ፊቷን ወደ ታንዛኒያ ወደብ ማዞሯ ለላፕሴት ከባድ ችግር ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 26/2013