
ኢትዮጵያ እንደሀገር ከምትታወቅባቸው ማህበራዊ እሴቶች አንዱና ዋነኛው የተለያዩ እምነት ተከታዮች በአንድነትና በፍቅር አብረው የሚኖሩባት ምድር መሆኗ ነው። ህዝቦቿ ከምንም በላይ ፈጣሪያቸውን የሚፈሩና የሚያከብሩ፤ የእምነታቸውን አስተምህሮ አክብረው የሚያድሩም ናቸው። ይህ ማህበራዊ እሴት በተለያዩ ጊዜያት በውጭም ይሁን በውስጥ ጠብ ጫሪ ምክንያት ሲተነኮስ ኖሯል። የሁሉም ሴራና ተንኮል ትንኮሳው ከሚፈጥረው አነስተኛ የግጭት ሰለባ ውጭ በህዝቦች አብሮነት ላይ የጣለው አንዳችም ነገር አልነበረም፤ አይኖርምም።
በአሁኑ ወቅትም ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በፈጠሩት ህዝባዊ ቁጣ የተጀመረው አገራዊ ለውጥ የአብዛኛውን ህዝብ ይሁንታ የማግኘቱን ያህል፤ ጥቅማቸው ተነክቶባቸው የደነገጡ አካላት ነገ ከሚመጣባቸው ተጠያቂነት ለማምለጥ የማይጠነስሱት ሴራ እንደሌለም ዕለት ዕለት መልካቸውን እየቀያየሩ ከሚሰሩት ሥራ እየተገነዘብን ነው።
የሚታይ ልዩነቱን በውበትነት ይዞ የቆየውን ማህበረሰብ የመለያያና የመከፋፈያ ሰበብ አድርጎ እርስ በእርስ ከማነካከስ ጀምሮ ወልደው ከብደው ከኖሩበት አካባቢ እስከማፈናቀል የደረሰ ችግር ፈጥረዋል።
ይህ ችግር የመፍጠር ሙከራ ዛሬም አልቆመም። አንዱ ተንኮል ሲከሽፍ ወይም አልሰራ ሲል ሌላ የሚያማትሩት እኒህ እኩያን ወገኖች ሁሉን ቁሳዊ፤ አካላዊና ምድራዊ ገጽታ አካልለው የሚፈልጉት ማባላት አልሆን ሲላቸው፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በማይደራደርበት ጉዳይ ላይ ማተኮር ይዘዋል። በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በሚባል ደረጃ እምነትን ማዕከል ያደረገ የጠብ ድግስ ጀምረዋል።
ይህ በየአካባቢው እንደሚመቻቸውና እንደመረጡት መንገድ የሚገለፀው የተለያዩ የእምነት ተከታዮችን የማጋጨት ተግባር፤ አሁን አሁን ሆኖ በማይታወቅ ደረጃ ቤተዕምነቶችን በማቃጠል ጭምር ይገልፁት ጀምረዋል።
እንደእውነቱ ከሆነ የትኛውም እምነት ሰውን ያህል በአምሳለ ፈጣሪ የተገኘ ፍጡር ግደሉ የሚል አስተምህሮ የለውም። የዚያኑ ያህል አምልኮ መግለጫ የሆኑትን የእምነት ቤቶች አቃጥሉ የሚል ዕምነትም ሆነ አስተምህሮ የለም። ይህ ከየትኛውም እምነት ያፈነገጠ ምግባር የጎደለው፤ ምናልባትም ሰይጣናዊ ተብሎ የሚገለጽ ተግባር ነው። እንዲህ ዓይነቱ ምግባረ ብልሹነት በሁሉም ሊወገዝ ይገባል።
በእርግጥ ይህ ሁሉ ጥፋት በአንድ ጀንበር የተጠነሰሰም፤ የተደረገም አይደለም። ይልቁንም ከትንሹ ጀምሮ ውጤት ሲታጣበት እያደገ የመጣ፤ የህዝቦች መተባበርና መተቃቀፍ ይበልጥ አልበገር ሲል ተንኮሉና ግብሩ የጨመረ፤ የተገኘውን ሁሉ አማራጭ ከመጠቀም አባዜ የመጣ የባህርይ እድገት ነው። መንግሥትም ሆነ ህብረተሰቡ ከዛሬ ነገ ተምረው ይመለሳሉ በሚል የአቃፊነት ስሌት በመታገስ ሲመለከታቸው የተፈሩ ያህል ተሰምቷቸው የተፈጠረ የማንአለብኝነት ስሜትም ነው። በምንም መስፈሪያ ግን ይህ አግባብ አይደለም።
አዎን መንግሥት ሁሌም ቢሆን ሆደሰፊ መሆን አለበት። ያውም እንደኢትዮጵያ ባሉ እምነትና ምግባር ከምንም በላይ የህይወት መርህ በሆኑባትና ዘመናትን የተሻገረ የአብሮነት ታሪክ ባላት አገር ቀርቶ፤ ትናንት ህልውና ባገኙ አገራትም ቢሆን መንግሥት ታጋሽና አቃፊ መሆን ይገባዋል። ይህ ሲባልም ግን ጥቂቶች የአብዛኛውን ኑሮ ሲረብሹ፤ ብዙው ወገን በትንሽ አካላት ህይወቱ ሲመሰቃቀል ዝም ብሎ ይመልከት ማለት አይደለም። እናም መረን የለቀቁ እኩይ ተግባራት ሲፈጸሙ አግባብነት ያለው ህጋዊ ቅጣት ሊወስድ ይገባዋል።
የእምነት አባቶችና ተከታዮችም እንደየሀይማኖታቸው እሴትና አስተምህሮ አጥፊዎችን መክረውና ዘክረው ወደህሊናቸው እንዲመለሱ የማድረግ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል። መቼም የትኛውም አጥፊ በግለሰብ ደረጃም ይሁን በቡድን ሲንቀሳቀስ የወጣው ከቤተሰብና ከማህበረሰብ ነውና እንዲህ ዓይነቱን አካል ገስጾ የመመለስ ተግባር ከቤተሰብና ከአካባቢ ሊጀምር ይገባዋል። ሰው ሁልጊዜም ክፋትና ተንኮል ሲሰራ አይኖርምና የዛሬ ችግር ፈጣሪዎችም ቢሆኑ ወደህሊናቸው ሊመለሱ ይገባል እንላለን።
አዎን ከዚህ በኋላ ሁሉም የተንኮል ጠንሳሾችና እኩይ ተግባር ፈጻሚዎች በቃ! ሊባሉ የግድ ነው። ከዚህ በኋላ ህብረተሰቡ እያንዳንዱን እንቅስቃሴያቸውን ተከታትሎ ለሚመለከተው የፍትህ አካል ሊያሳውቅ ተገቢ ነው። መንግሥትም እስካሁን ደረስኩባቸው ባላቸው አጥፊዎች ላይ አስተማሪ ርምጃ ሊወስድ፤ የወሰደውንም ርምጃ ለሕዝቡ ይፋ ሊያደርግ ይገባዋል። እንዲህ ሲሆን የአጥፊው ቁጥር ይቀንሳል፤ አዲስ አጥፊም አይፈጠርም።
የእምነት ተቋማትና አባቶችም ከመቼውም ጊዜ በላይ የተቀናጀና በምግባር ላይ ያተኮረ ትምህርት የሚሰጡበት ወቅት አሁን መሆኑን አውቀው ለተከታዮቻቸው በየትኛውም የእምነት አስተምህሮ ሰው ግደል ወይም ቤተእምነት አቃጥል የሚል መመሪያ/ትምህርት እንደሌለ ደጋግመው ሊዘክሩ ይገባል። እንዲህ ሲደረግ ለዘመናት ጸንቶ የኖረው የኢትዮጵያዊነት ስነምግባር ይመለሳልና ሁሉም አካል ተረባርቦ እኒህን ምግባረብልሹና ተንኮል ጠንሳሾችን በቃችሁ ሊል ይገባል እንላለን።
I couldn’t stop scrolling and reading, your content is truly one-of-a-kind. Thank you for all the time and effort you put into creating such amazing content.