የመኖሪያ ቤት ግንባታ አማራጮች ይስፉ!

በአዲስ አበባ ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ዜጎች ዋነኛው ፈተና የሆነው የመኖሪያ ቤት ችግር ነው። በከተማው የመኖሪያ ቤት እጥረት መኖር የመንግሥት ሠራተኛው የሚያገኘውን ደመወዙን ለቤት ኪራይ እንዲያውለው፤ በተጣበበ ቤት ውስጥ እንዲኖር፣ ከሥራ አካባቢው እንዲርቅ እንዲሁም በደባልነት ሕይወትን እስከመምራት አስገድዶታል።

የመኖሪያ ቤት ችግርን በተለያየ መልኩ ለመፍታት በመንግሥት በኩል እስካሁን ልዩ ልዩ ጥረት ቢደረግም በሚፈለገው ልክ ውጤታማ መሆን አልቻለም። በአሁኑ ወቅት በከተማው ዋናው ችግር ሆኖም ቀጥሏል፤ ዜጎችንም ለከፍተኛ የቤት ኪራይ ወጪ ዳርጓል። ለዋጋ ግሽበት መባባስ ዓይነተኛ ምክንያት እየሆነም ነው።

የከተማዋን ነዋሪዎች ችግር የተረዳው አስዳደሩ ቀደም ባሉት ጊዜያት የቤቶች ግንባታ በመዲናዋ አስተዳደር አቅም፣ በባለሀብቶች ፣ በፌዴራል መንግሥት እንዲሁም ማህበራትን በማደራጀት እና በግል እንዲገነቡ፤ ዜጎች የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሲሠራ መቆየቱ ይታወሳል። በተጨማሪም የግለሰብ ቤት የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ በየጊዜው ጭማሪ እንዳይደረግ የአከራይና ተከራይ አዋጅ በማውጣት ጭምር ችግሩን በዘላቂነት የሚፈቱ ርምጃዎች ለመውሰድ እየሠራ ነው።

ሰሞኑን ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ የመንግሥት ሠራተኞችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል 41 ሺህ የመኖሪያ ቤት ለመገንባት የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል። ከሚገነቡት መኖሪያ ቤቶች ቅድሚያ ለመምህራን የሚሰጥ ሲሆን፤ ቀሪው ደግሞ ለሌሎች የመንግሥት ሠራተኞች እንደሚሆን ተመላክቷል። ክፍያውን 25 በመቶ ሠራተኛው ቆጥቦ እና ከባንኩ ደግሞ 75 በመቶ በብድር የሚሸፈን ሲሆን ባንኩ ለዚህም 120 ቢሊዮን ብር ብድር ማዘጋጀቱን ይፋ አድርጓል።

አስተዳደሩ ይፋ ያደረገው ስምምነት የሦስት ዓመት ፕሮጀክት ሲሆን የግንባታ ጊዜው አንድ ዓመት መሆኑ ተገልጿል። ይሄ በቅድሚያ መምህራንን በሂደት የመንግሥት ሠራተኛውን የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለማድረግ የተያዘ ጥሩ ፕሮጀክት ነው። ፕሮጀክቱ በተባለው ፍጥነትና ጥራት በጊዜው ከተጠናቀቀ አማራጭ ሆኖ ችግሩን በመጠኑም ቢሆን ይፈታል። በመሆኑም ይህንን መሰል ፕሮጀክቶች እና ሌሎችም አማራጮች በአስተዳደሩ እየታቀዱ ተግባራዊ ሊደረጉ ይገባል።

ፕሮጀክቱ የመንግሥት ሠራተኛውን አቅም ባገናዘበ መልኩ በረጅም ጊዜ ክፍያ የቤት ባለቤት የሚያደርግ በመሆኑ የሚበረታታ ነው። ሆኖም ግን ይሄንን መክፈል ወይም ቅድመ ክፍያውን መቆጠብ ለማይችሉ ዜጎችም ከዚሁ ጎን ለጎን ሌሎች አማራጮች መዘጋጀት ይኖርበታል። በመንግሥትም ሆነ በግል ባለሀብቱ ተገንብቶ በአነስተኛ ክፍያ በኪራይ የመኖሪያ ቤት የሚገኝበትን ዕድል ማመቻቸት አንዱ አማራጭ ሊሆን ይችላል። ሌሎች የተሻሉ የሚባሉና ሁሉንም ነዋሪ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ዕድሎችን ማስፋት ከከተማ አስተዳደሩ የሚጠበቅ ይሆናል።

ከመኖሪያ ቤት ግንባታ ጋር ተያይዞም ቀደም ሲል ይታዩ የነበሩ የግንባታ መጓተቶች፣ የግንባታ ጥራት መጓደል፣ የፍትሃዊነት እና የመሳሰሉት የሥነ-ምግባር ብልሹ አሠራሮች በቀጣይ በሚሠሩ የግንባታ ፕሮጀክቶች መታረም አለባቸው። ቀደም ሲል የነበሩ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ መጓተት አንድም መንግሥትን ለተጨማሪ ወጪ ያጋለጠ በሌላ መልኩ ለረጅም ዓመት ገንዘባቸውን ሲቆጥቡ የኖሩ ዜጎችን ለተጨማሪ ወጪ የዳረገ መሆኑ ይታወቃል፤ በመንግሥት ላይ እምነት የሚያሳጣም ሆኗል። የከተማው አስተዳደሩ ይሄንን በሚገባ ተገንዝቦ ከነበሩ ስህተቶችም እርምት ወስዶ የፕሮጀክቶችን አፈጻጸም በጥብቅ ዲስፕሊን መምራት እና ውጤታማ መሆናቸው ን ማረጋገጥ ይኖርበታል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማው ተግባራዊ የተደረጉ ትላልቅ ፕሮጀክቶች አንዳንዶቹ በተያዘላቸው ጊዜ ቀሪዎቹ ደግሞ ከተያዘላቸው ጊዜ ቀድመው ተጠናቅቀዋል። አሁንም በትግበራ ላይ የሚገኙት በተመሳሳይ የሥራ ባህል ውስጥ እያለፉ ናቸው። ይሄ የመንግሥትን የመፈፀም አቅም ማሳያ ነው። በሌሎች ፕሮጀክቶችና የግንባታ ሂደት ላይ እንደታየው አፈጻጸም ሁሉ በቤቶች ግንባታ ዙሪያም ሊተገበር ይገባል። ፕሮጀክቱ በጥራት እና በጊዜው ሊከናወን ይገባል።

አሁን ያለውን የመኖሪያ ቤት ችግር መንግሥት ብቻውን ይወጣዋል ብሎ መውሰድ የማይታሰብ ነው። በመሆኑም በዚህ ዘርፍ ዐሻራውን ማሳረፍ የሚችል ሁሉም አካል የዚህ ጥረት አካል ሊሆን ይገባል። ችግሩ ግዙፍ በመሆኑ በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል እና የመንግሥት ሠራተኛውን አቅም ባገናዘበ መልኩ የመኖሪያ ቤቶቹን በጊዜ ገንብቶ ተጠቃሚ የማድረጉ ጥረት ከሌሎች ኣማራጮች ጋር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል!

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You