
ሰላም የአንድን ሀገር እጣ ፈንታ ለመወሰን ካለው ሁለንተናዊ ተጽእኖ አኳያ ጉዳዩ ለመንግሥት እና ለጸጥታ ተቋማት ብቻ አይተውም። የዜጎች የተቀናጀ ንቅናቄ እንዲሁም ለሰላም የተገዛ ማንነት ያለው ትውልድ መፍጠርን ዋንኛ አማራጭ አድርጎ መውሰድን ይጠይቃል።ለእዚህ የሚሆን ሀገራዊ መነሳሳትንም ይፈልጋል።
በየትኛውም የዕድገት ምዕራፍ ላይ ያለ ማህበረሰብ የዕለት ተዕለት ሕይወቱን ለመምራት እና እንደ ማህበረሰብ ያለውን ቀጣይ እጣ ፈንታም ሆነ፤ የመኖር እና ያለመኖር የሕልውና ጥያቄውን ለዘለቄታው ለመመለስ በእጅጉ ሰላም ይፈልጋል። አምርቶ ለመብላት፣ ወልዶ ለመሳም፣ ልጅን ለወግ ማዕረግ ለማብቃት፣ወዘተ… ሰላም መተኪያ የለውም።
እንደ ሀገርም ቢሆን የአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ወይም ብልጽግና የሚወሰነው በዛች ሀገር ባለው ሰላም እና ሰላሙን ሊፈጥር በሚችለው የዕድገት መነቃቃት ነው። ያለ ሰላም የአንድን ሀገር ብልፅግና አይደለም ሀገረ መንግሥት ማሰብ አይቻልም። ለእዚህ ደግሞ በሰላም እጦት ሳቢያ ከሀገርነት ወርደው የግጭት ማዕከል የሆኑ ሕዝቦችን ማስታወስ ይገባል።
በርግጥ ስለ ሰላም እና የሰላም አለመኖር ስለሚያጎድላቸው ማህበረሰባዊ እና ሀገራዊ እውነታዎች እኛ ኢትዮጵውያን ነጋሪ አያስፈልገንም። በሰላም እጦት ከፍ ካለ ስልጣኔ ወርደን የድህነት እና ኋላቀርነት ምሳሌዎች ሆነና። ብዙ ትውልዶች ብሩህ ነገዎችን እየናፈቁ፤ ተስፋ ያደረጓቸውን እነዚያን ቀናት የራሳቸው ሳያደርጉ ለዘላለሙ አሸልበዋል ።
ከሰላም እጦት ጋር በተያያዘ ያለፉት ዘመናት ትውልዶች እንደ ሀገር ተፈጥሮ የቸራቻቸውን ሀብት ማልማት እና መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል፤ በብዙ የጉስቁልና ሕይወት ውስጥ ለመጓዝ ተገደዋል። በበዛ የሕይወት ፈተና፤ያልተገባ ዋጋ ለመክፈል በተገደዱበት የሕይወት ትርክት ውስጥ ለማሳለፍም ተገድዋል።
ይህ ሀገራዊ ተጨባጭ እውነታ ከእዚህም ባለፈ በየዘመኑ የነበሩ የለውጥ መነቃቃቶችን በማደብዘዝ፤ መላው ሕዝብ የለውጥ መሻቱ ባለቤት እንዳይሆን አድርጎታል። የለውጥ መነቃቃት የነበራቸውን ትውልዶች አንገት በማስደፋት ፤እንደ ሀገር የለውጥ ድባቴ ውስጥ ከቷቸዋል። ሀገር እንደ ሀገር ከትናንት እንዳትሻገር አድርጓል።
ይህ እውነት ዛሬም የሀገራዊ ለውጥ ፈተና ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል። ለለውጡ ስኬት ትልቅ አቅም የሆነውን ሀገራዊ ሰላም ለመገዳደር የተለያዩ ኃይሎች ጠበንጃ አንግበው ፤የራሳቸውን ፣የትውልዳቸውን እና የመላውን ሕዝብ ሰላም በሚፈታተኑ የጥፋት ተልዕኮዎች ውስጥ ተሰልፈው ታይተዋል።
በተሳሳቱ የጥፋት ትርክቶች ጥቂት የማይባል ቁጥር ያላቸው ዜጎች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በለውጥ ተስፋቸው ላይ ጠበንጃ አንስተው፤ የሀገር እና የሕዝብን ሰላም ከመፈታተን ባለፈ፤ ሀገረ መንግሥቱን ስጋት ውስጥ በጨመረ የጥፋት ተልዕኮ ውስጥ ተዘፍቀው፤ እንወክለዋለን ያሉትን ሕዝብ እና ሀገርን ጭምር ያልተገባ ዋጋ አስከፍለዋል።
ሃይ ባይ ባጣ የማህበራዊ ሚዲያ የጥላቻ እና ጽንፍ የረገጠ የጥፋት ፕሮፖጋንዳ ፣ ከንቱ ፉከራ እና ቀረርቶ ፣ በለውጡ ዋዜማ የለውጥ ተስፈኛ የነበሩ ዜጎቻችን ከራሳቸው የለውጥ መነሳሳት ጋር በተቃርኖ ቆመው ላልተገባ መስዋእትነት ተዳርገዋል።
ችግሩን ለዘለቄታው ለመፍታት መንግሥት እና ሕዝብ የተለያዩ የሰላም አማራጮች አቅርበዋል፤ ለተፈጻሚነታቸውም በቁርጠኝነት ተንቀሳቅሰዋል። አማራጩን እንደ መልካም ዕድል በመውሰድም በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በተሳሳተ የጥፋት መንገድ ላይ የነበሩ ብዛት ያላቸው ዜጋች ወደ ሰላማዊ ሕይወታቸው ተመልሰው ሰላማዊ ሕይወታቸውን እየመሩ ነው ።
ይህ ሰላምን እንደ አንድ የትግል አማራጭ አድርጎ የመውሰድ ውሳኔ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በስፋት እየተስተዋለ ይገኛል። አብዛኛው ታጣቂ እየተጓዘ ያለበትን የጥፋት መንገድ በመገምገም፤ መንገዱ ለራሱ፣ እታገልለታለሁ ለሚለው ሕዝብም ሆነ ለሀገር እንደማይጠቅም በአግባቡ እየተረዳ፤ ጠበንጃ እያወረደ ነው። ይህ ከጥፋት የመመለስ መንገድ እንደ ሀገር ለጀመርነው የለውጥ ጉዞ ስኬት ትልቅ አቅም ነው።
በተለይ እንደ ሀገር ሁሌም ከውድቀታችን ውጪ ሰላም እና ዕድገታችንን ለማይፈልጉ፣ እርስ በርሳችን እንድንገዳደል ጠበንጃ ለሚያቀብሉ ፣ ከእያንዳንዱ የጥፋት ሃሳብ እና መንገድ ጀርባ ላሉ፣ መቼም ተኝተውልን ለማያድሩ ፣ አሁናዊ እና ታሪካዊ ጠላቶቻችን ትልቅ መርዶ ነው!
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ.ም