
ኢትዮጵያ ጥንታዊ የዲፕሎማሲ ታሪክ ካላቸው ሀገራት አንዷ ነች፡፡ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በሃይማኖት በባሕልና በንግድ እንቅስቃሴ ከበርካታ ሀገራት ጋር የጠነከረ ግንኙነት መሠረት የጣለችና በዲፕሎማሲው መስክም ተጠቃሽ ተሞክሮ ማዳበር ከመቻሏም ባሻገር ከንግስት ሳባ እስከ ዘመነኛው የዲጂታል ዲፕሎማሲ ድረስ ዕምቅ ታሪክና ተሞክሮ ያላት ሀገር ነች፡፡
በየዘመናቱ የነበሩ የኢትዮጵያ መሪዎችም ሀገሪቱን ከውጭውም ዓለም ጋር የሰመረ ግንኙነት እንዲኖራትና አልፎ ተርፎም ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገር እንድትሆን ዘርፈ ብዙ ግንኙነቶችን ሲመሠርቱ ቆይተዋል። በዘመነ አክሱም የዲፕሎማሲ ዘመን የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ መሠረቶች ተጥለዋል፡፡
117 ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ዘመናዊ ዲፕሎማሲ በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት አዳዲስ ገጽታዎችን በመላበስ አድማሱን አስፍቶ ቀጥሏል። በተለይም ለቀጣናዊ ግንኙነት የመጀመሪያውን ትኩረት በመስጠት ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የጠበቀ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲኖራት ተደርጓል። ከእዚሁ ባሻገር በርዕዮተ ዓለም ታጥሮ የነበረውን የዲፕሎማሲ ግንኙነት በማሻሻል ከምሥራቁም ሆነ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ጠንካራ የሆነ ግንኑነት መፍጠር ተችሏል ፡፡
ኢትዮጵያ ሁሉንም ባማከለ መልኩ ከሀገራት ጋር ግንኙነት ታደርጋለች። ለሕዝብና ለሀገር እስከጠቀመ ድረስ በገለልተኝነት መርህ ከአራቱም ማዕዘናት ጋር አብራ ትሠራለች፤ ወዳጅነት ትመሠርታለች። በእዚህም ከምሥራቁም ሆነ ከምዕራቡ ሀገራት ጋር ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመመሥረት በሰላምና ልማት ዙሪያ አብራ በመሥራት ላይ ትገኛለች፡፡
ለእዚህ አንዱ ማሳያ የሚሆነው ብሪክስ ነው። ኢትዮጵያ ብሪክስን በመቀላቀል ሰላምን ፣ እድገትን፣ ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ በመጣር ላይ ትገኛለች። በተለይም በአሁኑ ነባራዊ የዓለም ሁኔታ ወቅታዊ እና አንገብጋቢ የሆኑ ድንበር ዘለል ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችም በየትኛውም ተቋም ለብቻ ሊፈቱ ስለማይችሉ እውነተኛ ዓለም አቀፋዊ አጋርነት የግድ ስለሚል ብሪክስን የመሳሰሉ ጥምረቶች ሰላም እና ልማት በማረጋገጥ ረገድ የማይተካ ሚና አላቸው። ኢትዮጵያም ብሪክስን በዋና አባልነት ከተቀላቀሉ ሀገራት ግንባር ቀደም መሆኗ፤ የተከተለችው የዲፕሎማሲ መርህ ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን ማሳያ ነው።
የብሪክስ አባል ሀገራት 40 በመቶውን የዓለም ሕዝብ ይይዛሉ። ቀደም ብለው ብሪክስን የመሠረቱት ብራዚል፣ ሩስያ፣ ቻይና ሕንድና ደቡብ አፍሪካ በጋራ ያላቸው ምጣኔ ሀብታዊ አቅም ደግሞ ዓለምን 26 በመቶ የሚሸፍን ነው። ይህ ምጣኔ ሀብታቸውም በየጊዜው እየጨመረ በዓለም የንግድ ልውውጥ ላይ ተጽዕኗቸው እያደገ ነው። ይህ ሁኔታ ደግሞ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከመደገፍ አንጻር ያለው ፋይዳ የጎላ ነው፡፡
ከምዕራቡ ዓለም ጋርም ኢትዮጵያ ጠንካራ የሆነ ዘመን ተሻጋሪ ግንኙነት አላት፡፡በተለይም ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ተቀዛቅዞ የነበረው የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ሀገራት ግንኙነት ዳግም ታድሷል። በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የነበረው ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት መቋጨቱን ተከትሎ የሀገሪቱን ገጽታ እንደገና በጉልህ ለማሳየት በተሠራው ሥራ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አብቧል። በመሪዎች ደረጃ የሚደረግ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ሲታይ ደግሞ በርካታ የአውሮፓ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች (ለአብነት የፈረንሳይ ፣የጀርመን ወዘተ) ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል። በተመሳሳይ የሀገሪቱ መሪዎችም ወደ በርካታ ሀገራት ሄደዋል። ሚኒስትሮች አሜሪካን ብቻ ሳይሆን የአውሮፓ ሀገራትን ጎብኝተዋል።
ከሰሞኑም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ልዑካቸው በአውሮፓ ሀገራት ጉብኝቶችን እያካሄደ ይገኛል። ከአውሮፓ ሀገራት ጋር ያለው ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዲፕሎማሲ ወደ ላቀ ደረጃ ያድጋል ተብሎም ይጠበቃል፡፡
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማዕከል እንደመሆኗ መጠን፤ አሁን ላይ በየቀኑ የውጭ ሀገር መሪዎች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች ወዘተ ቀን ከሌሊት እያስተናገደች ያለች ሀገር ናት። ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ያላት ግንኙነትና ተሳትፎም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።ይህም ሀገሪቱ የምትከተለው የገለልተኝነት መርህን የተከተለ የዲፕሎማሲ ሥራ ውጤት እያመጣ መሆኑን ማሳያ ነው!
አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 20 ቀን 2017 ዓ.ም