የጥፋት መንገድን ለማስቆም!

እንደ ሀገር ዘመናትን ተሻግረን የመጣነው ሀገራዊ አንድነታችንን ማስጠበቅ በሚያስችል አብሮነት ነው። ይህ አብሮነት ማኅበረሰባዊ መስተጋብሮቻችንን እያጠናከረው የጋራ ትርክት እና ከዚህ የሚመነጭ የጋራ ማኅበራዊ እሴቶች ባለቤት አድርጎናል። ይህ በራሱ የቀደመ አንድነታችንን እያጠናከረ አሁን ላይ አድርሶናል። በቀጣይም አንድነታችንን ጠብቀን መጪ ዘመናትን እንድንሻገር ሀገራዊ አቅም እንደሚሆነን ይታመናል።

ይህ ማለት ግን ከሀገረ መንግሥት ምስረታችን ጀምሮ እንደ ሀገር ያለን ታሪክ ፈተና ያልነካው ወይም አልጋ በአልጋ የነበረ ነው ማለት አይደለም ። ማኅበረሰባዊ አንድነታችንን የሚፈታተኑ ፤ እሱን መሰረት አድርገው በብዙ የተፈታተኑን የጥፋት ክስተቶች አጋጥመውናል ። በታሪካችን ጥቁር ጠባሳዎችን ጥለው ያለፉ፤ ያልተገባ ዋጋ ያስከፈሉን መዘናጋቶችን አሳልፈናል። ዛሬም ቢሆን ይኸው እውነታ ጥላ ሆኖ እየተከተለን ፤ የለውጥ ተስፋችን እየፈተነ ነው።

ይህ ጠላቶቻችን ከቀደመው ዘመን ጀምሮ እንደ ሀገር ሊያንበረክኩን ፤ እንደ ሕዝብ ሊያፈርሱን በተንቀሳቀሱባቸው ጊዜያት ሁሉ፤ ለከንቱ ህልማቸው ትልቅ ስትራቴጂክ አቅም አድርገው የሚወስዱት ፤ የሕዝባችንን አንድነት የሚያፋልሱ ፤የልዩነት ፣የስጋት እና የጥፋት ትርክቶችን በሕዝባችን ውስጥ መዝራት፤ በዚህም የኃይላችን ፣የአልበገር ባይነታችን እና የነጻነታችን ምንጭ የሆነውን ብሔራዊ አንድነታችንን መሸርሸር ነው ።

በርግጥም ለጠላቶች ሃሳብ የተሸነፍን በመሰሉ የታሪክ ክስተቶች ሆነ ፤እንደ ሀገር ብዙ ያልተገባ ዋጋ በከፈልንባቸው የታሪክ ምዕራፎቻችን የሚስተዋለው እውነት ከዚህ የተሻለ አይደለም። ብሔራዊ አንድነታችንን በጸና መሰረት ላይ ማስቀጠል ሲሳነን ፤ ስለ ሀገራዊ ተስፋችን የጋራ ቋንቋ እና ቁርጠኝነት ስናጣ፤ ራሳችንን ከጠላቶቻችን የተለመደ ወጥመድ ማስምለጥ ሲያቅተን በተለመደ ፈተና ውስጥ ለማለፍ ተገደናል።

የኢትዮጵያን መዳራሻ ያወቁ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት በብዙ ፈትነውናል። እንደ ሀገር የጋራ ተስፋ እና የተስፋ ቋንቋ እየተናገርን መደማመጥ አቅቶን በከፋ የግጭት አዙሪት ውስጥ አልፈናል ። ለጠላቶቻችን ዘመን ተሻጋሪ የጥፋት ተልዕኮ ሁሌም አዲስ እየሆንን ትውልድ ተመሳሳይ እና ያልተገባ ዋጋ በሚከፍልበት ሀገራዊ የታሪክ አውድ ውስጥ አልፈናል፤ ዛሬም እያለፍን ነው ።

ስለጠላቶቻችን የጥፋት ተልዕኮ መሽቶ እስኪ ነጋ እየተነገረን ፤እንደ ሀገር የሚያኖሩንን ማኅበረሰባዊ እሴቶቻችንን በሚያደበዝዙ ፤ብሔራዊ ጥቅሞቻችንን በሚያሳጡ ፤ የትውልዶችን እጣ ፈንታ አደጋ ውስጥ በሚከቱ የጠላቶቻችን የልዩነት የጥፋት ትርክቶች ከተስፋችን ጋር እየተጋጨን / እየተጣላን የምንጓዝበት ይህ ያልተገባ መንገድ ዛሬ ላይ መቋጨትን ይፈልጋል ። ከጠላቶቻችን እኩይ ዓላማ የሚቀዳ የጥፋት አስተሳሰብም ሊታረም ይገባዋል፡፡

ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ልዩነታችን ውበታችን እና ዘመን ለተሻገረው አንድነታችን ተፈጥሯዊ አቅማችን ነው። ከቋንቋ ባለፈ የዘመናት የጠላቶቻችንን መልከ ብዙ ፈተናዎች የተሸጋገርንበት ዋነኛ አቅማችን ነው ። ነገም እንደ ሀገር ያለን ተስፋ ከዚህ በልዩነት ውስጥ የደመቀ አንድነት እና አንድነቱ ከሚፈጥረው ውበታችን የሚመነጭ ነው።

ይህ ትውልድ ከምንም በላይ ፤ይህንን ተጨባጭ ሀገራዊ እና ማኅበረሰባዊ እውነታ በአግባቡ ሊረዳው ይገባል። የትኛውም የልዩነት ትርክት እና ከዚህ የሚመነጭ ማኅበረሰባዊ ስጋት እኛን የማይወክል ፤ ለታሪካችንም ሆነ ለማኅበረሰባዊ እሴቶቻችን ባእድ የሆነ የጠላቶቻችን የጥፋት ተልእኮ መነሻ እና መዳረሻ መሆኑን ሊያስተውል ይገባል ። ሀገር የማፍረስ እና ሕዝባችንን የመበተን ዘመን ተሻጋሪ የጠላቶቻችን የጥፋት ተልዕኮ ትርክት መሆኑንም ለአፍታም ሊዘነጋ አይገባም ።

እንደ ሀገር በብዙ የለውጥ ተስፋ በተነሳሳንበት እና ጅማሬዎቻችን መዳረሻችንን እያመላከቱ ባለበት ዛሬ ላይ ጠላቶቻችን ከያሉበት በራሳቸው ሆነ በገዟቸው ባንዳዎች ድምጻቸውን ከፍ አድርገው የሚያሰሙት ተመሳሳይ የልዩነት እና የጥፋት ትርክትም ሆነ በትርክቱ ሊፈጥሩት የሚሞክሩት ማኅበረሰባዊ ስጋት ጆሮ የሚሰጠው አይደለም ።

እንደ አንድ ከፍ ባለ የለውጥ ምዕራፍ ውስጥ እንደሚገኝ ፤ የለውጥ ተስፋዎችን በተጨባጭ የማጣጣም ጅማሬ ውስጥ እንዳለ ሕዝብ ፤ለተለመዱ የጠላቶቻችን የጥፋት የልዩነት ትርክቶች ጆሮ ባለመስጠት ፤ ውስጣችን ላለው እና ብዙ ትውልዶች ዋጋ ለከፈሉበት ሀገራዊ ለውጥ ትኩረት ሰጥተንና ደግፈን ልንንቀሳቀስ ይገባል። ይህን በማድረግ ዘመን የተሻገረውን የጠላቶቻችን የጥፋት መንገድ ማስቆም ከትውልዱ የሚጠበቅ አሁናዊ ዋነኛ ሥራ ነው!

አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You