እኛ ኢትዮጵያዊያን ተደጋግሞ እንደሚነገረው እኛ የዛሬዎቹ ትውልዶች የማንጠቀምበት ጥበብ አባቶች አውርሰውናል አይደል። ወዶቼ እኔ የድሮ አባቶች ጥበበኞች ናቸው ሲባል አንድ ጎረቤታችን የነበሩ ጥበቡ የሚባል አዛውንት ናቸው ተደጋግሞ ትውስ የሚሉ። የምር አንዳንዴ ስም ከምግባር ሲገጥም ደስ ይላል። ጋሽ ጥበቡ አምላክ ጥበብን ሲሰጣቸው ቤተሰቦቻቸው ስም ሳያወጡላቸው ቆይተው ጥበበኛ መሆናቸው ጠብቀውና አረጋግጠው “ጥበቡ” ብለው ያወጡላቸው ሰው ሳይሆኑ አይቀርም።
በእርግጥ ከሰውነታቸው ቅጥነት አንፃር እሳቸው ይህቺ ፈታኝ የሆነች ዓለም እንዴት ሊኖሩበት ይችል ነበር። አለ አይደል ሰው ቀጥኖ ኮስምኖ ሲያበቃ በሽሙጥ ሌላ ሸሟጭ ሲያየው “አንተ እፍ ቢሉህ 50 ሜትር ትርቃለህ” ተብሎ በተደጋጋሚ የሚሾመጥ አይነት ሰው ናቸው። ግን ደግሞ ወፍራም ምላስ የታደሉ። ሁሌም ከጡንቻ በላይ የሆነው ምላሳቸውን ስለሚፈራ አንዳች ነገር ደፍሮ የማይላቸው ሰው ናቸው።
ምላሳቸው ስድብን ብቻ ሳይሆን የሰላ መለኛ ሀሳባቸውን የሚያመነጨው ሀሳብ የሚናገሩበትን ሲያወሩ አፍ የሚያስከፍቱበት ነው። ጋሽ ጥበቡ ታያ በምላሳቸው ነገርን ብቻ ሳይሆን ውስብስብ ነገሮችን ፈተው የሚያስረዱ መላን የሚጠቁሙና ለብዙ ችግሮች መፍትሄ የሚጠቁሙ ነበሩና “አባ መላ” የሚሉዋቸውም ይበረክታሉ። ብቻ ጋሽ ጥበቡ በጥበብ ኑሮን እንደ ጉድ ነበር ጢባ ጢቤ የሚጫወቱበት።
እናም ስለ ኢትዮጵያዊያን ጥበብ ተደጋግሞ ሲነገር ጥሎብኝ ጋሽ ጥበቡ ትውስ ይሉኛል። እኔ ምለው በዚህ ትውልድ ግን ጥበቡ የሚባል ሰዎች ስያሜ ካልሆነ በቀር የአባቶቻችን ጥበብ የሚወርስ ቀርቶ የሚተገብር አልሳሳም ትላላችሁ ወገን? ጥበበኛ ባንሆን ከአባቶች የወረስነው ጥበብ እንዴት መተግበር ያቅተናል። ደግሞ ጥበብ ጥበብ ስል አዳሜ የድሮ አያቶቻችን ጥበብ ልብስ አውርደን እንዳንለካ ጎበዝ (ሃሃሃሃ)። እኔ ስለ ብልሀት ወይም ነገሮችን የምናከናውንበት አልያም የምንረዳና የምናስረዳበት ጥበብን ነው። አዎ እሱ ርቆናል።
አዲሱን ትውልድ በፍቅር ገርተን አብሮ እንዲቆም የመግራት ጥበብ ርቆናል። ብዙ ገፍቶ መቶ የሚቀጣን፤ እጅግ ርቆ ነገር ግን የቅርብ ያህል የሚያሳጣንማ ብዙ ጠላት ወዳጅ የማድረጉ ብሂል ጠፍቶናል። ወደን ባደረግነው በፍቃዳችን በፈፀምነው መቀጣት ተደራርቦብናል። አዎን እኛው ወደን የምንቀጣበት ፈቅደን የምንጎደፍበት ጥበብ ስለራቀን ለይተን እንኳን ማወቅ ተስኖናል። ከፍሎ መሞት ማለት ይሄ ነው ወዳጄ።
ያለ ጥበብ ለዘመናት መመራታችን ጎትቶናል ብዙ ጠብቀን ዝቅ ብለን እንድንገኝ አድርጐናል። እንደው ይሰውረን እንጂ ነጋችን እንዳይብሰም ያስፈራል። በእርግጥ አንዳንዴ ይገጥማል ፍሬን አልመው ገለባ የሚሆንበት፤ የተሻለን ፈቶ የባሰ የሚያገቡበት ገጠመኝ አለ።ታዲያ ይህ ገጠመኝ የሚበረክተው በእንደኛ አይነት ስሌትን እያራቀ በሄዴ ማህበረሰብ ብልሀትና ጥበብን በማይጠቀም ነው።
ትውልዱ የአገር ታላቅነት እንዲረዳ ዛሬ ከስርመጀመር ግድ ይለናል። ነገ አገር እንድትፀና የዛሬ ማንነትዋ ታድሶ በሌሎች እንድትፈራ ዛሬ ጥበበኛ ባንሆን የትላንት ጠቢባን አባቶች አገሪቱን ያቆዩበት ጥበብ መውረስ ቢያንስ ይገባል። አገር ማለት ሰው ነው ይባል የለ? ሰው እንስራ ሰው ሰው የሚሸት ስብዕና ያለው ትውልድ እናፍራ። እርግጥ የመናገር ያህል ቀላል አይደልም። ነገር ግን ግድ የሚል ቀዳሚ ተግባር ነው።
ውዶቼ ሰው መስራት ከምንም በላይ ጥንቃቄን ይሻል። ህንፃ ተንጋዶ ቢሰራ ድንጋይ ነውና አፍርስው መልሰው ይገነቡታል። መንገድ ተሰርቶ ቢበላሽ ጭማሪ በጀት ተይዞ መልሶ ጠግነው ለአገልግሎት ያውሉታል። አፍርሰው ሊሰሩ የማይችሉት፤ ጠግነው ሊመልሱት የማይችሉት ሰው ግን አንዴ መንገድ ከለቀቀ ከባድ ነው። አዎ የተንሻፈፈው ሰውና አመለካከቱ ሲሆን ችግር ነው ውዶቼ። አያፈርሱት አይጠግኑት ነገር።
ስብዕና ወይም ሰው መሆን በራሱ ሂደት ነው። ከተበላሸ ትውልድ የሚያነትብ በአንፃሩ ደግሞ በስርዓት ከተገነባ የሰውዬው ዘመን ማብቂያ ድረስ የሚዘልቅ። ሰው በስርዓት ታንፆ ብቁ ሆነ ማለት ብቁና በማንም ተፈሪ አገር ይገነባል። ሰው ሀገር አይደል? ሀገር መገንባት ከስር ነው፤ ሰው መፍጠር ከጅምር ነው። የተቃና ትውልድ የቀናን ሀገር ይፈጥራልና የሰው አዕምሮ ላይ የሚሰራ ስራ ከሁሉ ቀዳሚው እና ትኩረት የሚሰጠው ነጥብ ነው።
አገር በመገንባት ሂደት ውስጥ ቀዳሚው ትኩረት ልጆች ናቸው። የእነሱ መታነጫ ዋንኛ መግሪያ ቦታ ደግሞ ትምህርት ቤቶች ናቸው። በመሆኑም ትምህርት ቤቶች ዋንኛ ትኩረታችን ሊሆኑ ይገባል። ዛሬ ላይ ልጆቻቸው የትኛው ትምህርት ቤትና ማን ጋር እንደምንልካቸው በደንብ አጥርተን ማወቅ ይጠበቅብናል። አገራዊ ሰፊ አስተሳሰብ ተላብሰው ሰፊዋን አገር እንዲያስቡ መዋያቸውን ማመቻቸት መቀረጫቸውን ማደላደል ከእኛ ይጠበቃል።
ጥበበኛ ትውልድ ይህን ማድረግ ይችላል። ስልጡንና ብቁ ዜጋ ያላት አገር ተረክቦ ለሌላ የሚያሻግር ስልጣኔዋም ጥበብዋን የሚያሻግር ይሆናል። አስተማማኝ መሰረት ላይ የፀናች አገር እና ዜጋ ያላት አገር ለመመስረት ደግሞ የጥበብ ማረፊያ ጠቢባን ማምረቻ ዋንኛ ቦታ ላይ ልናተኩር የሚገባን ለዚህ ነው። አዎ የትውልድ መግሪያ ዋንኛ ቦታና መድረክ ትምህርት ቤት።
የመንግስት ትምህርት ቤቶች የተሰጣቸውን ብቁ ዜጋ የማፍራት ሀላፊነት በስርዓት ቢወጡ የግሎችም ከዚያው ባላነሰ መልኩ ትውልዱ ላይ በሀላፊነት ቢሰሩ ለውጥ ይመጣል። ከተማሪ ወላጅ በሰበብ አስባቡ እየነጠቁ ኪሳቸው እንደሞሉት ለወላጆች ቃል ገብተው ልጅህን በስነ ምግባር ኮትኩቼ አስተምሬና አብቅቼ ለወግ ማዕረግ አደርስልሃለሁ ያሉት ቃል ማክበር ግድ ይላቸዋል። የሞሉት ኪሳቸው ያህል የተማሪዎቹን አዕምሮ በሀገር ፍቅር ስሜትና እውቀት መሙላት ይኖርባቸዋል።
አባቶች ያቆዩትን ጥበብ ተረክበን ሌላ ጥበብ አክለን ቀድምን የጀመርነውን ስልጣኔ በአገራችን ህዳሴ ማቃረብ እንደግመው ዘንድ ዛሬ ላይ በጥበብ መጓዝ ነገን አስቦ ዛሬ መስራት የሚያስፈልገው ለዚህ ነው። ለማንኛውም የጠቢባን ምድር የሆነችው አገራችን ጥበብዋን መጠቀም የምንችለው ሁሌም ሰላምዋ ሲበረክት ነውና አገሬ ሰላምሽ ይበርክት፤ አሜን! አበቃሁ ቸር ይግጠመን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሰኔ 25/ 2013