የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ሰኞ አመሻሹን ባወጣው መግለጫ የነጠላ የተኩስ አቁም አውጇል።መንግስት በመግለጫው ገበሬው ተረጋግቶ የእርሻ ሥራውን እንዲከውን፣ የእርዳታ ሥራው ከወታደራዊ እንቅቃሴ ነጻ ሆኖ እንዲሠራጭ፣ ሰላምን የሚመርጡ የሕወሐት ርዝራዥ አካላት ወደ ሰላም መንገድ እንዲመጡ፤ ባለማወቅ ርዝራዡን የጥፋት ኃይል የተከተሉ እንደገና ለማሰብና ወደ ሰላማዊ መንገድ ለመምጣት ዕድል እንዲያገኙ ለማስቻል የተኩስ አቁሙን ማወጁን አስታውቋል።ከዚህ የመንግስት ውሳኔ በኋላም አለም አቀፉ ማህበረሰብ ውሳኔውን በማድነቅ የተለያዩ አስተያየቶች ሰጥተዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዚህ የመንግስት ውሳኔ ውስጥ የሚታዩ ብዙ ለትንታኔ የሚበቁ ነጥቦች አሉ።ዋነኛው የትንታኔ አጀንዳ የገበሬው ሁኔታ ነው።ትግራይ ክልል እንደተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል ብዙሀኑ የክልሉ ህዝብ በግብርና ላይ የተሰማራበት ክልል ነው።ኑሮውም የተመሰረተው በእርሻው ላይ ነው።በሌላ መልኩ ይሄው ክልል እንደ አብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል ባለፈው አመት በአንበጣ መንጋ ተወርሮ ከፍ ያለ ጉዳት ደርሶበት ነበር።ኮሮናም የክልሉን ምጣኔ ሀብት እያንገዳገደው ነበር።በነዚህ ሁለት ወቅታዊ የቤት ስራዎች ላይ ነው ይህ ጦርነት የተፈጠረው።ጦርነት በመሰረቱ ጎጂ ነው።ለትግራይ ህዝብ ደግሞ ከዚህም የባሰ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም በብዙ ተደጋጋሚ ጦርነቶች ምድሩም ህዝቡም ብዙ የተጎዳ ነው።በዚሁ ላይ ደግሞ ክልሉ የምርታማነት ችግር አለበት።በዚህም የተነሳ በየአመቱ በሚሊየን የሚቆጠር ህዝብ በሴፍቲኔት እገዛ የሚኖር ነው።በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ደግሞ አምና ማረስ የተቻለው መሬት በአንበጣ ወድሟል።ኮቪድ ሌላ ራስ ምታት ሆኗል።ይህ ሁሉ ችግር እያለ ግን ህወሀት የሰሜን እዝን አጠቃ።የፌደራሉ መንግስት ምላሽ ሰጠ።በሶስት ሳምንት ውስጥ የጁንታው መመኪያ የነበረው ሀይል ፍርስርሱ ወጣ።ይሄኔ የአልሞት ባይ ተጋዳይ መፍጨርጨር ውስጥ የገባው ህወሀት ፊቱን ወደ ገበሬው አዞረ።የፈረደበት ገበሬ ስራውን ትቶ ጁንታውን ተከትሎ መኳተን ስራው ሆነ።በዚህ መልኩ ሰኔም ደረሰ።በወርሀ ሰኔ ውሎና አዳሩ እርሻ ቦታው መሆን የነበረበት ገበሬ በሰኔ መገኛው ዋሻ ሆነ።ይሄ ለጁንታው ራስ ምታት አይደለም።ለመንግስት ግን ሌላ ጣጣ ነበር።በትግራይ ክልል ከሚሰጠው ርዳታ 70 በመቶውን የሚሸፍነው መንግስት አሁን ደግሞ ማሳውን ትቶ ዋሻ ለገባ ገበሬ የመቀለብ ግዴታም ሊኖርበት ነው።አሁን ባለበት ሁኔታ እንኳን የእርዳታ ጠያቂ ህዝብ እጥረት የሌለበት መንግስት አሁን ደግሞ በፈቃዱ የሸፈተ ገበሬ ሲጨመርበት ሸክሙ ከባድ ይሆናል።ስለዚህም ያለው አማራጭ ለጊዜው በጁንታው ላይ የሚደረገው ህግ የማስከበር ዘመቻ ጋብ አድርጎ አርሶ አደሩ ወደ ማሳው እንዲመለስ ማድረግ ነው፡፡
የሚገርመው በዚህ ውሳኔ ከማንም በላይ ተጠቃሚ የሚሆነው የትግራይ አርሶ አደር እና የልማት በጀቱን እያቃጠለ ያለው መንግስት ቢሆንም መንግስት ባወጀው ተኩስ አቁም ግን ዋነኛ ተጠቃሚ የሚመስሉት ከእርዳታው 30 በመቶውን ሰጥተው 70 በመቶውን በመውሰድ ለራሳቸው የሚያቀርቡት የእርዳታ ድርጅቶች ናቸው።በሰሜን እዝ ላይ ለደረሰው ጥቃት አንድም እውቅና ያልሰጡት፤ መንግስት ለሚያደርገው ሰብአዊ እርዳታ አድናቆትም ሆነ አክብሮት ሰጥተው የማያውቁት፤ በእርዳታ ማድረሱም ሆነ በሌላው ጉዳይ ለሚገጥም ማንኛውም ችግር መንግስትን ተጠያቂ የሚያደርጉት እነዚህ ሀይሎች አሁን መንግስት የተኩስ አቁም ሲያውጅ አብዝተው የተደሰቱት የሰላም ዘብ ስለሆኑ ሳይሆን ሌሎች ፖለቲካዊ አጀንዳዎቻቸውን ለማስፈጸም የተሻለው ጊዜ አሁን ስለመሰላቸው ነው።ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ ምክትላቸው በተደጋጋሚ በእርዳታ ስም የሚደረግ ሌላ ፖለቲካው ተልእኮ እንዳለ እና ይህ መቆም እንዳለበት አሳስበዋል።የሆነ ሆኖ ገበሬው ወደ ስራው በፍጥነት እንዲመለስ ሲባል ለጊዜው ጁንታውንም ሆነ የጁንታውን ስንቅ አቀባዮችን መታገስ ግድ ሆኗል።ለምጣዱ ሲባል አይጧን ማሳለፍ ለጊዜው አስፈላጊ ነው፡፡
ሌላኛው የተኩስ አቁሙ ምክንያት ለሰላማውያን ማሰቢያ ጊዜ ለመስጠት እንደሆነ መንግስት በመግለጫው አብራርቷል።ይህም ብዙ ሊባልበት የሚችል ምክንያት ነው።ምክንያቱም ከላይ እንደገለጽነው በትግራይ የሚካሄደው ጦርነት ከመደበኛ ጦርነት ወጥቶ ጁንታው ሰለባ እንዲሆኑ የሚያዘጋጃቸው ንጹሃን ሰዎች የሚጎዱበት ወይም በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ንጹሀንን የሚጎዳ እንደሆነ ታይቷል።ብዙሀን ባለማወቅ ጥቂቶች ደግሞ ተገድደው የጦርነቱ አካል እንዲሆኑ ተደርገዋል።በዚህ መልኩ የገቡ ንጹሀን ደግሞ በጦርነቱ ከፊት የጥይት ማብረጃ እንዲሆኑ እየተማገዱ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።ታዲያ እነዚህ የጠመንጃ አፈሙዝ ጫፍ ላይ የቆሙ ሀይሎች እንደምን ሰላምን ሊያስቡ ይችላሉ? ሰላምን እንዲያስቡ ካስፈለገ ያለው እርምጃ አንድ ነው።እሱም መንግስት ሀላፊነቱን ወስዶ ተኩሱን ማቆም እና ገለል ማለት ከዚያም እነዚህ እግረ መንገዳቸውን ወደ ጦር ሜዳ የገቡ ሰዎች ምን ውስጥ እንደገቡ የሚያስቡበት ጊዜ መስጠት ነው።ይህን ለንጹሀን የሚሰጥ የማሰቢያ ጊዜ ጁንታው ራሱን ለማደራጀት እንደሚጠቀምበት ይታወቃል።ቢሆንም ለንጹሀኑ ሲባል ጁንታውን መታገስ ግድ ነው።ለምጣዱ ሲባል አይጧን መታገስ አስፈላጊ ነው፡፡
የኢትዮጵያ አኮኖሚ ባለፉት ሶስት አመታት ሪፎርም እያካሄደ ነው።በዚህም ተጨባጫ የሚባሉ ስኬቶች እንደተገኙ እየታየ ነው።ይህም በየጊዜው በሚወጡ የምጣኔ ሀብት ሪፖርቶች በግልጽ ማየት ይቻላል።በቅርቡ በማእድን ዘርፍ ሀገሪቱ ያገኘችው በታሪክ ከፍተኛ የሆነ ገቢ ለዚህ ማሳያ ይሆናል።በፋይናንስ፤ በቴሌኮም፤ በሌሎችም ዘርፎች እንዲሁ የሚታዩ ብዙ ለውጦች አሉ።ይሁንና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በዋጋ ግሽበት እየተሰቃየ ነው።የዋጋ ግሽበትን ከሚያባብሱ ነገሮች አንዱ ደግሞ ጦርነት ነው።ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከትናንት በስቲያ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ከዚህ ጦርነት ጋር በተያያዘ 100 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ አድርጋለች፡፡
ይህ ወጪ የፌደራሉ መንግስት በየአመቱ ለሀገሪቱ ከሚይዘው በጀት 20 በመቶ ገደማ ሲሆን ለትግራይ ከሚሰጠው አመታዊ በጀት ደግሞ ከ13 እጥፍ በላይ ነው።ይህ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከባድ ሸክም ነው።ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸውም ላይ መንግስት ከዚህ በላይ ወጪ እያወጣ መቀጠል እንደማይችል ተናግረዋል።ይህ ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ ቀና ቀና እያለ ያለውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መልሶ በአፍጢሙ እንዲደፋ የሚያደርግ ነው።ስለዚህም ከጠቅላላው ህዝብ 7 በመቶ ገደማ ብቻ የሚሆነውን ህዝብ የያዘውን ክልል ለማስቀጠል ሲባል 93 በመቶው ህዝብ የሚደክምበትን ኢኮኖሚ መስዋእት ማድረግ አስፈላጊ አይደለም።በተለይም ይህ የመንግስት ድጋፍ ጁንታውን ለመደገፍ ጥቅም ላይ የሚውል ከሆነ ኢኮኖሚው ላይ የሚወሰደው እርምጃ የማያዋጣ ብቻ ሳይሆን በጣም አደገኛም ነው።ስለዚህም ኢኮኖሚውን ለማዳን ሲባል ይህን ህግ የማስከበር ዘመቻ ለጊዜውም ቢሆን ጋብ ማድረግ አስፈላጊ ነው።ለምጣዱ ሲባል አይጧ እንድታልፍ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡
ኢኮኖሚው ጫና ውስጥ የገባው ግን በቀጥታ ጦርነት ውስጥ በሚወጣው ወጪ ብቻ አይደለም።ጦርነቱን እንደ ምክንያት በተጠቀሙ ነገር ግን በኢትዮጵያ የመጣው ለውጥ ጥቅማቸውን በነካባቸው ሀገራት በሚደርስ ማእቀብም ነው።ይህ እቀባ ብድር ከመከልከል እና ከማዘግየትም በላይ ሀገሪቱ በውጭ ሀገር ያስቀመጠቻቸውን ገንዘቦች እንዳትጠቀም በመከልከልም የሚገለጽ ሆኗል።ይህ ጦርነት በእርግጥ ወዳጅ እና ጠላታችንን እንድንለይ አድርጎናል።ከአንዳንድ ሀገራት ጋር ያለን ግንኙነት ዳግም ምልከታ እንደሚያስፈልገውም አውቀናል።ሆኖም እንደ ሀገር በዚህ ጦርነት ምክንያት እየመጣ ያለውን ጫና በአጉል ድፍረት ብቻ መፍታት አይቻልም።ይልቁንም አንድ እርምጃ ወደኋላ መለስ ብሎ ትንፋሽን መሰብሰብ እና ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራ መስራት ይቻላል።
ይህ የተኩስ አቁም ደግሞ በትግራይ ውስጥ ላለው ችግር ተጠያቂው ማን እንደሆነ በግልጽ ለማሳየት እድል ይሰጣል።ስለዚህም ዲፕሎማሲውን እና አለም አቀፍ ገጽታን ለማስተካከል ሲባል ለተወሰነ ጊዜ ሜዳውን ለጁንታው መልቀቅ አስፈላጊ ነው።ለምጣዱ ሲባል አይጧ ማለፍ አለባት፡፡
ከኢኮኖሚውም ሆነ ከዲፕሎማሲውም በላይ የሚበልጥ ሌላም ወሳኝ ጉዳይ አለ።ያም የመከላከያ ሰራዊታችን ነው።የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ኢትዮጵያን ከውጭም ከውስጥም ጠላት ታድጎ ያቆመ ታላቅ ሀይል ነው።ይህ ሀይል ጀግንነቱንም የጁንታውን መተማመኛ ሰራዊት በሶሰት ሳምንት ውስጥ ከጥቅም ውጭ ማድረግም የቻለ ነው።ይሁንና ከዚያ በኋላ ጁንታው የተከተለው ንጹሀንን ለጦርነቱ የመማገድ ሂደት ከሰራዊቱ ባህሪ ጋር የማይሄድ እና አስቸጋሪ ነበር።ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት መከላከያው ወደ ገጠራማ መንደሮች ሲወርድ የሚያገኘው የተደራጀ እና የሚታወቅ ዩኒፎርም ያለው ጦር ሳይሆን ህዝብን ነበር።ነገር ግን በዚህ ህዝብ ውስጥ ጁንታው ተደብቋል።በዚህም የተነሳ መከላከያው በተደጋጋሚ ያልተዘጋጀበት የጥቃት ሰለባ ሆኗል።
ከዚህም በላይ ጦርነቱ በሺ በሚቆጠሩ ወታደሮች እና እነዚህን ለ20 አመታት የጠበቁትን ወታደሮች እንደ ባእድ በሚመለከት ሀይል መሀከል የሚካሄድ መሆኑ ወታደሩ ባለበት ቦታ የባእድነት ስሜት እንዲሰማው አድርጓል።በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ጦሩን ወደፊት ግፋ ማለት ወደለየለት መተላለቅ ሊመራው ይችላል።ከዚህም በላይ ወታደሩ ህይወቱን በማጣቱ እና የመከላከያው አቅምም በማይሻሻል አዙሪት ውስጥ በመባከኑ ሀገር እጅግ አደገኛ ለሆነ አደጋ ትጋለጣለች።በተለይም ከህዳሴው ግድብ አንጻር ያለንበት አደጋ አሳሳቢ ነው።ስለዚህም ይህን ብሄራዊ አደጋ ለመቀልበስ ወታደሩ እንዲያገግም ማድረግ አስፈላጊ ነው።ለዚህም ሲባል ከጁንታው ጋር ያለበትን ልፊያ ለጊዜው ጋብ ማድረግ አስፈላጊ ነው።ጦሩ ለጊዜው ጠመንጃውን ዝቅ ማድረጉ ጁንታው እንደ ሽንፈት ሊያየው ይችል ይሆናል ቢሆንም ለዘላቂው የሀገር ህልውና ሲባል ለጊዜው መታገስ ግድ ነው፡፡
በሌላ መልኩ የጁንታው ሀይል ከጥቂት ቀናት በፊት የትግራይ ህዝብ እያለቀ እንደሆነ ሲናገር ከርሞ አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትን አሸንፎ መቀሌን መቆጣጠሩን እየተናገረ ነው።ለቢቢሲ የተናገረው የጁንታው አፈ ቀላጤ ጌታቸው ረዳ እንዲያውም ከማሸነፍም አልፎ ወደ ተቀረው የኢትዮጵያ እና ወደ ጎረቤት ሀገር ኤርትራ ገብቶ የመደምሰስ እቅድ እንዳለው ሁሉ ፎክሯል፡፡. ከጥቂት ሳምንታት በፊት የኤርትራ ጦር እና የአማራ ልዩ ሀይል ከክልላችን ይውጡልን ሲል የነበረው ጌታቸው አሁን ጨዋታውን ቀይሮ እንዲያውም ኢትዮጵያንም ኤርትራንም ለመደምሰስ ዝግጅት ላይ እንደሆነ ሲናገር መስማት ለምጣዱ ተብሎ የሚሰጥ ትእግስት በጁንታው ዘንድ አጉል የልብ ልብ እንደሚፈጥር አመላካች ነው።ሆኖም ጁንታው ሲዘጋጅ ከርሞ በ15 ቀናት ድባቅ እንደተመታ ለምናውቀው ኢትዮጵያውያን ፉከራውን ሰምተን ከመሳቅ ውጪ ከቁብም የምንቆጥረው አይደለም፤፤
የሆነ ሆኖ አሁን ጦሩ ትግራይን ለቅቆ ወጥቷል።ከአሁን በኋላ ኳስ በሌላኛው አካል ሜዳ ናት።ለጥፋቱም፤ ለግድያውም ከእንግዲህ ተጠያቂው አሸባሪው ህወሃት እንደሆነ የአደባባይ ጸሃይ ይሞቀዋል።ከእንግዲህ እየገደሉ በሌላው ላይ ማላከክ አይኖርም።እየገደሉ ማልቀስ ጊዜው ያለፈበት ስትራቴጂ ሆኗል።ሆኖም የትግራይ ህዝብ የኢትዮጵያ ህዝብ አካል ነውና ጉዳቱን መመልከት ማንም አይፈልግም። መከላከያ ሰራዊት ለህዝብ ሰላም ሲል ለቆ ወጣ ማለት መንግስት ትግራይ የጁንታው መፈንጫ እንድትሆን ፈቅዷል ማለት አይደለም።በመግለጫው መጨረሻ ላይ አስፈላጊ ከሆነ በማንኛውም ሰአት እንደሚመለስ አሳውቋል።ይህ የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ በኢትዮጵያ የግዛት አንድነት ላይ ምንም ድርድርም አይኖረውም።ነገር ግን የኢትዮጵያ የግዛት አንድነት ሊጠናከር የሚችለው የትግራይ ህዝብ ማሰቢያ ጊዜ ተሰጥቶት ግራ ቀኙን አይቶ መወሰን ሲችል ነው።ውሳኔው የሰላም እና አንድነት እንደሚሆንም እርግጥ ነው፡፡
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ሰኔ 24/2013