ኢትዮጵያ ተቆጥሮ የማያልቅ የማዕድን ሃብት ባለቤት እንደሆነች ለዘመናት ተነግሯል። ይህን የማዕድን ሃብት ግን በአግባቡ ተጠቅማበታለች የሚለው ጥያቄ የሚነሳበት ጉዳይ ሆኖ ዘልቋል። በተለይ በክልሎች ላይ በዘርፉ የሚከናወነው ሥራ የአካባቢውን ማህበረሰብ ሳይሆን ግለሰቦችን ብቻ ተጠቃሚ ያደረገ እንደነበር የዘርፉ ባለሙያዎች ይስማሙበታል። በአፋር ክልል በተመሳሳይ ማዕድን ልማት በኮንትሮባንድ እና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የሚፈለገውን ያክል ውጤት ሳያስገኝ በርካታ ዓመታት ቆይቷል።
በክልሉ ከመሬት በላይና በመሬት ውስጥ የሚገኝ ሰፊ
የማዕድን ሃብት እንዳለ ጥናቶች ያመለክታሉ። በዚህ ረገድ፤ ኢንቨስተሮችን በመሳብ፣ የገበያ አማራጭ በማስፋት እና ችግሮችን በመቅረፍ
እና የማዕድን ሃብቱን በአግባቡ ለመጠቀም ምን አይነት ስራዎች ተከናወኑ የሚሉ ጉዳዮችን አንስተን ከአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
ማዕድን ሃብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገዶ ሃሞሎ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፡– በአፋር ያለው የማዕድን እምቅ ሃብት በዝርዝር ይታወቃል፤ ዝርዝር የማዕድን ሃብቶችስ በመረጃ በተደገፈ ስርዓት ለመያዝ ምን አይነት ጥረት ተደርጓል?
አቶ ገዶ፡– በማዕድን ዘርፉ በመጀመሪያ ምንድን ነው ያለን የሚለውን ስናይ አፋር ክልል የበርካታ እምቅ የማዕድን ሃብት እንዳለ ይታወቃል። አካባቢው በእሳተ ጎመራ ምክንያት የተፈጠሩ ገጸምድሮች ያሉት በመሆኑ ሰፊ የማዕድን ሃብት ከመሬት በላይም ሆነ በመሬት ውስጥ ይዞ ይገኛል።
ከለውጡ በኋላ ባሉት ጊዜያት በቅድሚያ ያተኮርነው የተጀመሩም ሆነ አዳዲስ ሥራ የሚጠይቁ ጥናቶችን ማከናወን ነው። ከግምት ባለፈ በተጨባጭ ምን አለን የሚለውን ከግምት ያስገባ ሥራ ማከናወን ተችሏል። ክልሉ በእርሱ አቅም፤ በጀትና የሰው ኃይል ማስኬድ የሚችለውን በመለየት የዳሰሳ ጥናቶችን አካሂደናል።
የተለያዩ አካባቢዎች ላይ አለኝታ ቦታዎችን የመለየት ሥራ ተከናውኗል። በዳሰሳ ጥናቱ መሰረት በሦስት ዘርፎች ማለትም በኢንዱስትሪ ማዕድናት፣ በጌጣጌጥ ማዕድናት እና በኮንስትራክሽን ማዕድናት የተለያየ ሃብት እንዳለ ማረጋገጥ ተችሏል። ከእነዚህ ውስጥ ትልቁና እንደሃገርም ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ላለፉት ዓመታት በተለያዩ ድርጅቶች ሙከራ እየተደረገበት ያለው የፖታሽ ማዕድን ነው።
በሌላ በኩል ወርቅ እና የከበሩ ማዕድናትም በክልሉ የሚገኙበት ቦታ መኖሩ ተጠንቷል። የኢንዱስትሪ ማዕድናት በተመለከተ ጨው ለተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ግብአት የሚውል በመሆኑ አንዱ የማዕድን ምርት ነው። በተለይ በአፋር አፍዴራ፣ በራህሌ እና ዳሎል እንዲሁም ዶቢ በተባለ ስፍራ ላይ ትልቅ የጨው ምርት ሃብት አለ።
ኮፐር፣ ወርቅ፣ ማንጋኔዝ ፣ ፖታሽ ምርት፣ ቤንቶናይት እና የተለያዩ የኮንስትራክሽን ግብአት የሚውሉ ማዕድናት በአፋር ክልል መኖራቸውን ባደረግነው የዳሰሳ ጥናት መለየት ችለናል። እያንዳንዱ ማዕድን ሀገርን በሚጠቅም መልኩ ሊለማ የሚችልበት መንገድ ላይ በተከታታይነት ለመስራት ዝግጁነት አለ።
አዲስ ዘመን፡– እንደአፋር ክልል ባለው የማዕድን ሃብት ልክ መጠቀም ያልተቻለበት ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው?
አቶ ገዶ፡– ከማዕድን እንደክልልም ሆነ እንደሀገር ካየን መጠቀም ያልተቻለው ሃብቱ ስለሌለን ነበር ወይንስ በአግባቡ መጠቀም ስላልቻልን ነው የሚለውን ማየት ያስፈልጋል። በየአካባቢው የተለያየ ማዕድን አለ፤ ይሁንና አጠቃቀሙ ነው ችግር ቆኖ የቆየው።
ዘርፉ ለኮንትሮባንድ ንግድ ተጋላጭ ሆኖ በመቆየቱ የሚፈለገውን ውጤት አላስገኘም። አሁን ይሄን ለመቀየር የሚያስችል አሰራር እየተተገበረ ነው። በሌላ በኩል የማዕድን ዘርፍ የእራሱ ፖሊሲ እንኳን የለውም ነበር። ከለውጡ ጊዜ በኋላ ግን ከአምስቱ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ውስጥ አንዱ የማድን ዘርፍ በመሆኑ የእራሱ ፖሊሲ እንዲኖረው ተደርጓል።
አንድ ኢንቨስተር ለማልማት ሲነሳ እኮ በመጀመሪያ ያች የሚሄድባት አገር የማዕድን ፖሊሲ አላት ወይንስ በዘፈቀደ ነው የሚሰራው? የሚለውን አጥንቶ ነው። ስለዚህ ፖሊሲ መዘጋጀቱ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ አሁን አመቺ ሆኗል።
በአንጻሩ ደግሞ ማዕድኑን የሚመሩ ተቋማትም አልተጠናከሩም ነበር። ከዚህ በፊትም የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የሚባል ነበር፤ ስራውን ግን በአግባቡ እያከናወነ ስላልነበር ዘርፉን ጎድቶታል። አሁን በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ዘመን ተቋሙ ተጠናክሮ የቁጥጥር እና የክትትል ስራዎቹንም አጠናክሯል።
ህገወጥ አሰራሮችንም በመከታተል ፍቃድ ይዘው የማይሰሩትንም ከመስመር እያስወጣ ነው። ስለዚህ የነበሩ ውስብስብ ችግሮች ናቸው ዘርፍን የያዙት አሁን በተሻለ መስራት የሚያስችል ሁኔታ ስላለ መልካም አጋጣሚ ነው ማለት ይቻላል። እንደ አፋር ክልልም እንደአርብቶ አደርነቱ ካሉት የእንስሳት ሃብቶች በበለጠ መጠቀም እና በፍጥነት ማደግ የሚቻለው የማዕድን ሃብቱን መጠቀም ሲቻል ነው በሚል እየሰራን እንገኛለን።
አዲስ ዘመን፡– በየማዕድናቱ ዘርፍ ለወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠርና የገበያ አማራጮችን ለማስፋት ምን አይነት ጥረት አደረጋችሁ?
አቶ ገዶ፡– በኮፐርም ሆነ በጨው ምርቶች ላይ ወጣቶች ናቸው ተደራጅተው እየሰሩ የሚገኙት። በኮፐር ምርት ብናይ እስካሁን የየአካባቢው ወጣቶች ተደራጅተው በሚሰሩት ሥራ 4000 ኩንታል ምርት ተገኝቷል።
ምርቱ ግን ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚቀርብ ሳይሆን የውጭ ገበያ መቅረብ ያለበት በመሆኑ ባለሃብቶች እስኪገዟቸው ይጠብቃሉ። የገበያ ትስስር ባለመፈጠሩ ግን ምርቱን አከማችተው ይዘውታል። ማንጋኔዝም በተመሳሳይ ወጣቶች እያመረቱት ነው፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ገበያ መፍጠር ይጠይቃል።
ቀደም ብሎ ምርቶቹን ከወጣቶቹ ላይ ይገዙ የነበሩ የውጭ ሀገራት ገዥዎች በኮቪድ በሽታ ምክንያት እየመጡ አይደለም። እኛም እንደክልል ገበያ በማፈላለግ ባለሃብቶችን እየጋበዝን ነው። ምርቶቹን ትላልቅ ካምፓኒዎች መጥተው እንዳይገዙት እና እነሱም ለማልማት እንዳይነሳሱ በማዕድናቱ ያለው እምቅ ሃብት ጥልቀትና መጠን መታወቅ አለበት።
እኛ እንደክልል ያከናወነው የዳሰሳ ጥናት ምርቶቹ በየት አካባቢ ይገኛሉ የሚለውን እና የተወሰኑ ዝርዝር ጉዳዮችን ነው። ለስንት ዓመት የሚሆን?፣ በምን ያክል ጥራት እና ጥልቀት አለ የሚለውን? ለመለየት ግን ቀጣይ የጂኦፊዚክስ ጥቅል ጥናት ያስፈልጋል። የክልሉን አለኝታ የመለየት ጥናት መነሻ አድርጎ ዝርዝር ጥናት የሚሰራ ካምፓኒ ሲመጣ ደግሞ የበለጠ ለወጣቶቹም የገበያ እድል የሚፈጠርበት እድል ይኖራል።
በተጨማሪ የተለያዩ ኤግዚቢሽኖች ላይ በመካፈል እና በክልል ያለውን የማዕድን ምርት በማስተዋወቅ የተዘጋጁ ማዕድናትም ሆኑ መሬት ውስጥ ያሉትን በማስተዋወቅ የገበያ አማራጮችን የማስፋት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡– በአፋር ከሚገኙ ማዕድናት አንዱ የሆነው የፖታሽ ማዕድን ብዙ የተባለለት ቢሆንም ውጤታማነቱ ላይ ግን እስካሁን ተጨባጭ ነገር ተገኝቷል ማለት እንችላለን?
አቶ ገዶ፡– ማዕድኑ ቀደም ሲልም ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት በእንግሊዝና ጣሊያኖች ተጠንቶ የተቀመጠ ነው። ይሁንና ወደተግባር የመቀየሩ ጉዳይ ለረጅም ጊዜ ተጓትቶ የመጣ በመሆኑ ላለፉት 10 ዓመታትም የተለያዩ ድርጅቶች እየተፈራረቁ ሲሞክሩት ነበር።
በነበረው የአሰራር ችግርና ክትትል ጉድለት ምክንያት ድርጅቶቹ በወሰዱት ፈቃድ መሰረት ጥናታቸውን አጠናቀው ወደምርት የገቡበት ሁኔታ አልነበረም። በሦስት ዓመት ውስጥ የተሻለ አሰራር ስርዓት በመዘርጋት እና ቁጥጥርን በማጠናከር ዝም ብለው ፈቃዱን ይዘው መስራት ግን ሳይችሉ የተቀመጡትን በመለየት ፈቃዳቸው እንዲሰረዝ ተደርጓል።
በተሻለ ደረጃ የምርመራ ስራቸውን እያከናወኑ የነበሩትን ደግሞ በፍጥነት ወደምርት እንዲገቡ ተደርጓል። ለአብነት ያራ አዳሎ የሚባል ፖታሽ ለማምረት የሚያስችለውን ሂደት አጠናቋል። ፖታሽ በዋናነት ለማዳበሪያ ግብአትነት ይውላል።
ኢትዮጵያ ደግሞ ለግብርና ማዳበሪያ ምርት በየአዓመቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የምታወጣ በመሆኑ በአፋር ያለው የፖታሽ ምርት በሰፊው ሲመረት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጪ ማዳን ያስችላል። ስለዚህ በፖታሽ ምርት ፋብሪካ የሚገነቡበት ቦታ ጠይቀው ለግንባታ የሚሆን ቦታ መረጣና ዲዛይን ዝግጅት ተደርጓል። በጥቂት ጊዜያት የሚጠበቀውን ያክል ውጤት ይመጣል ብለን እንገምታለን።
አዲስ ዘመን፡– በማዕድን ዘርፎች የሚሰሩ ኢንቨስትሮችን ካለመሳብ ምን ጥረት አደረጋችሁ?
አቶ ገዶ፡– እንደአፋር እስአከሁን በማዕድን ዘርፍ ተጠቃሚ አልነበረም። እስከዛሬ ወጥቶ ጥቅም ላይ ሲውል የነበረው አዮዲን ያልተቀላቀለበት ጨው ብቻ ነበር። አሁን ያንን ለመቀየር ሰፊ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።
የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ በተደረገው ጥረት ትላልቅ ካምፓኒዎች ጭምር በማዕድን ዘርፉ እና ማዕድንን ተጠቅመው ኬሚካል ለማምረት የሚፈልጉትን እያወያየን ነው። የጨው ምርትን ተጠቅመው የተለያዩ ኬሚካሎችን የሚያመርቱ ኢንቨስተሮችን በሰፊው የመጋበዝ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።
ባለሃብቶችም በዘርፉ ለመሰማራት ያለው ፍላጎት ከፍተኛ ነው። ወደስራም የገቡ ፋብሪካዎች በአፋር ክልል ቦታ ተሰጥቷቸው እየሰሩ ይገኛል። አንድ የቤንቶናይት ማዕድን ላይ የሚሰራ ካምፓኒ ቦታ ወስዶ ግንባታ እያደረገ ይገኛል። ከአንድ ወር በኋላ ወደሙከራ ምርት ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።
በሌላ በኩል አፍዴራ ሐይቅ ላይ የሚገኘውን ጨዋማ ውሃ እንደግብአት ተጠቅሞ ብሮሚን እና ሶዲየም ክሎራይድ የተሰኙ ኬሚካሎችን ለማምረት ፍቃድ የወሰዱ የቻይና ኩባንያዎች ግንባታ ጨርሰው ወደሙከራ ምርት ተሸጋግረዋል።
ፋብሪካውን በዚህ ወር ለማስመረቅ ዝግጁ ነበርን፤ የድርጅቱ ዋና ባለቤቶች በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ወደኢትዮጵያ መምጣት ስላልቻሉ እነሱ ሲመጡ ምናልባትም በቀጣዩ ወር ፋብሪካው በይፋ ተመርቆ ወደሥራ የሚገባ ይሆናል።
ከአቡዳቢ የመጡ ኢንቨስትሮች የብሮሚንና የክሎሪክ አሲድ ለማምረት የኢንቨስትመንት ጥያቄ አቅርበው ሂደት ላይ ናቸው። በአንድ ዓመት ውስጥ ፋብሪካዎችን በመገንባት ወደምርት እንደሚገቡ እቅድ ተይዟል። በኢንዱስትሪ ማዕድን ዘርፎችም በርካታ ባለሃብቶችን በመሳብ ላይ ነን።
በኮሮና ቫይረስ በሽታ ምክንያት እንደፍላጎታቸው ያክል መጥተው መንቀሳቀስ ባይችሉም ሂደት ላይ የሚገኙ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ስራዎች አሉ። አብዛኛዎቹ ፍላጎት ያሳዩትም ወደሥራ ሲገቡ እንደሀገርም ከማዕድን ዘርፍ የሚገኘው ገቢ ለኢኮኖሚ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እያደገ ይመጣል። ወደፊት አካባቢው የማዕድን ኢንቨስትመንት ኮሪደር ይሆናል ብለን እናስባለን።
አዲስ ዘመን፡– አፋር ክልል በማዕድን ሃብት ልማት ለሚሰማሩ አልሚቆች የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ከማመቻቸት አኳያ ምን ያህል ቅንጅታዊ አሰራር ተግብራችኋል።
አቶ ገዶ፡– አፋር ክልል ላይ እንደሌላው አካባቢ ለኢንቨስትመንት አልሚዎች የሚውል የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር የለም። ምክንያቱን በሌሎች ክልሎች በርካታ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ስላሉ የኃይል ችግር ቢያጋጥምም እኛ ጋር ግን ያለውን የኃይል ክምችት ያን ያህል የሚጠቀም ኢንዱስትሪ በብዛት የለም።
አሁን ባለው ሁኔታ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በጋራ እየሰራን ነው የተሻለ የኃይል አቅርቦትም ለሚመጡ ኢንቨስተሮች ተመቻችቶ ነው የሚጠብቃቸው። ስለዚህ ለአነስተኛ ኢንዱስትሪም ሆነ ለከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚዎች የሚሆን በቂ አቅርቦት ዝግጁ ሆኖ ነው የተቀመጠው።
ከዚህ ባለፈ ግን ማንኛውም አፋር ላይ የሚያመርት ኢንቨስተር ሌላ አካባቢ ከሚያመርተው በተሻለ ተወዳዳሪ የመሆን እድል አለው። ወደፊት ኢንቨስትሮችም ይጠቀሙበታል ብለን የምናስበው የኤርትራ አሰብ ወደብ አለ፣ ታጁራ ወደብና ጂቡቲ ወደቦችም አገልግሎት እየሰጡ ነው። ሦስቱም ወደቦች ከአፋር ያላቸው ርቀት 300 ኪሎሜትር ብቻ ነው።
በአጠቃላይ ከኢትዮጵያ ለወደብ ቅርብ የሆነው ክልል አፋር በመሆኑ ባለሃብቶችም ቢመጡ በወጪና ገቢ ንግዶች ላይ ይበልጥ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችል እያስረዳን ይገኛል። የኤሌክትሪክ አማራጩ መስፋት እና የወደብ ቀረቤታው ለኢንቨስትመንቱን ተመራጭ ያደርገናል ብለን እናስባለን።
አዲስ ዘመን፡– በአፋር ክልል የሚገኘውን የጨው ማዕድን ሃብት ባለው መጠን ልክ እንደሃገር በሚፈለገው ልክ ተጠቅመንበታል ብለው ያስባሉ?
አቶ ገዶ፡– እስከአሁን ባለው ሂደት ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውል ምርት የሚገኘው ከአፋር ነው። በርካታ ፋብሪካዎች የኬሚካል ማምረቻዎችም ሆነ የቆዳ እና ሌሎች ኢንዱስትሪዎች ጨውን ለግብአትነት ይጠቀማሉ።
ጨው ከኢንዱስትሪ ግብአትነት ባለፈ ለምግብነት ስናውለውም ግን በአግባቡ እየተጠቀምንበት ነው ማለት አይቻልም። በአሁኑ ወቅት በአፋር ክልል አፍዴራ አካባቢ ብቻ በገበያ እጦት ምክንያት ለ10 ተከታታይ ዓመታት ተመርቶ የተቀመጠው የጨው ምርት ከ35 ሚሊዮን ኩንታል በላይ አለ። ይህ ምርት ውሃ ውስጥ ያለ እና ወደፊት ሊመረት የሚችለውን የሚጨምር አይደለም።
ክምችቱ ላለፉት ዓመታት በባህላዊ መንገድ ሲመረት የቆየው ጨው ምርት ሲሆን፣ በገበያ እጦት ምክንያት ለተለያዩ አገልግሎቶች መዋል እያለበት በአንድ ቦታ ተከማችቶ የተቀመጠ ነው። ክምችቱን ለመጠቀም ጨው ለማምረት የገቡ ባለሃብቶች ወደዘመናዊ የማቀነባበር ሥራ እንዲሸጋገሩ እየተደረገ ይገኛል።
የገበያ እጥረት በመኖሩ ግን በርካታ የጨው ምርት በአፋር ተከማችቶ ይገኛል። እኛ የጨው ምርት እያለን ለምግብነት የሚውል የተቀነባበረ ባለአዮዲን ጨው ከውጭ ሀገራት መጥቶ በሱፐር ማርኬቶች ውስጥ ይሸጣል። ፋብሪካዎች ለአያያዝ በሚመችና በመጠነኛ ካርቶን ማሸግ ቢቻል የበለጠ የጨው ሃብቱን በተለያዩ የገበያ አማራጮች መጠቀም ይቻላል።
አምራቾች በኩንታል እያቀረቡ በመሆኑ ግን ለቀጣናው ሀገራትም ሆነ ለሌሎች የውጭ ሀገራት ምርት ለማቅረብ በሰፊው እንዲሰሩ አላደረጋቸውም። ይህንን እንዲያስተካክሉ እና ክምችቱን እንዲያነሱ ለፋብሪካዎችም ነግረን ጊዜ ሰጥተናቸዋል። ፋብሪካዎቹ በዘመናዊ አስተሻሸግ የታገዘ ምርት ለማቅረብ ምክንያት እያደረጉ ያሉት የኮቪድ በሽታ እክል እና የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ነው።
ችግሩ እየተቃለለ ሲሄድ ከስድስት ወር በኋላ በኩንታል ብቻ እያሸጉ መሸጥ እንደማይችሉ እኛም ባለንበት የንግድና ኢንዱስትሪ አመራሮችም ባሉበት ተነጋግረናል። ስለዚህ ማሽኖቻቸውን በማዘመን የተለያየ የእሸጋ መጠን ሲኖራቸው የቀጠናውን ገበያ በመያዝ የጨው ክምችቱን በሰፊው የመጠቀም እድል ይኖራል።
አዲስ ዘመን፡– የተወሰኑ ፋብሪካዎች ብቻ በሚያቀነባብሩት የጨው ምርት 35 ሚሊዮኑን ኩንታሉን ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል?
አቶ ገዶ፡– የሀገሪቷ ወርሃዊ የጨው ምርት ፍጆታ መጠን ወጥቶለታል። ስለዚህ ከፍላጎት በላይ የሆነ አቅርቦት ወደገበያ እንዳይገባም ሆነ ከፍላጎት በታች የሆነ መጠን እንዳይኖር ቁጥጥር ይደረጋል።
በፌዴራል ደረጃ እያንዳንዱ የጨው ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ምን ያክል መጠን ማቅረብ አለበት የሚለው ተመጥኖ ነው የሚሰጠው፤ ስለዚህ ከስድስት መቶ ሺህ ኩንታሉ ወርሃዊ ፍጆታ ውስጥ በአፋር ብቻ ያሉት ሳይሆኑ በሌሎች ክልልች ላይ የሚገኙ ፋብሪካዎችም ምርት በማቅረብ ተሳታፊ ናቸው።
ስለዚህ ፋብሪካዎቹ በብዛት አምርተው ከፍላጎት በላይ ቢያቀርቡ በቀጣይነት የሚመረት ጨው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያመጣል። በአንድ ወር ብቻ በብዛት ተመርቶ በሌላኛው ወራት ባይመረት በጨው ዝግጅት ላይ የተሰማሩ ወጣቶች ገቢ አጠቃቀም ላይ ችግር ያመጣልና ሂደቱን ጠብቆ በመጠኑ ነው እንዲመረት የሚደረገው።
ይሁንና 35 ሚሊዮን ኩንታል ክምችቱን በአንድ ጊዜ ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል ማለት አይደለም። ማቀነባበሪያዎቹ ለሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ለውጭ ሀገራትም በስፋት እያቀረቡ ሲሆኑ በተጨማሪነት ጨውም በመጠቀም ኬሚካል የሚያመርቱ ፋብሪካዎች በስፋት ሥራ ሲጀምሩ ነው ክምችቱን ማቃለል የሚቻለው።
ጨውን ለምግብነት፣ ጨውን ለፋብሪካ ግብአትንት፣ ለኬሚካልና ለሌሎች ምርቶች ግብአትነት እንዲውል የሚረዱ ፋብሪካዎች እየተገነቡ ነው። ፋብሪካዎቹ ቁጥር እና የማምረት አቅም እያደገ ሲሄድ የተሻለ ውጤት ይገኛል ብሎ መናገር ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡– በሀገር ውስጥ ያለውን የገበያ አማራጭ ለማስፋት እና ክምችቱን ለማቃለል የሚቻልበት መንገድ አልታየም?
አቶ ገዶ፡– ፋብሪካዎቹ በኩንታል እያሸጉ ሲሸጡ አብዛኛው የገጠሩ ህዝባችን ምርቱን ሊጠቀምበት ይችላል፤ ይሁንና ከተማ ላይ ያለውን የገበያ ፍላጎት ለመያዝ ግን በተመሳሳይ በዘመናዊ መልክ በመጠኑ ማሸግ ያስፈልጋል።
ከዚህ ባለፈ ግፍን ለሀገር ውስጥ ገበያም ቢሆን የሚቀርበው የጨው መጠን የተመጠነ ነው። ዋናው ነገር አሁን ባህላዊ ምርት አስቀርተን ፋብሪካዎች በማቀነባበር ሥራ እንዲሳተፉ እያደረግን ነው።
ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ባደረገው ጥናት መሰረት በ2013 ዓ.ም በአጠቃላይ አለ ተብሎ ከሚገመተው 110 ሚሊዮን ህዝብ ለምግብ የሚያስፈልገው የጨው መጠን በወር 600ሺህ ኩንታል ነው።
ይህ የኢትዮጵያ የምግብ ጨው ፍጆታ የተሰላው የተባበሩት መንግሥታት የዓለም አቀፉ የህፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ስታንዳርድ መሰረት ሲሆን፣ አንድ ሰው በቀን ከ15 እስከ 20 ግራም ጨው በቀን ይጠቀማል የሚለውን መርህ የተከተለ ነው። በንግድና ኢንዱስትሪ ስሌት መሰረት የሚመረተው የጨው ምርት እየተመጠነ ወደገበያ እንዲደረግ ይደረጋል።
ትልቅ የጨው ምርት ክምችት ባለበት ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውል በወር 600 ሺህ ኩንታል ምርት እያቀረብን መሄድ የሃብት ብክነትን ያመጣል እንጂ ውጤታማነት አይኖረውም።
በመሆኑም የጨው ምርት ክምችቱን አንድም በፋብሪካ በማቀነባበር አዮዳይዝ በማድረግ ለገበያ ማቅረብ እና ለኢንዱስትሪ ግብአቶች በሰፊው በማዋል ለኬሚካል ምርት እና ለሌሎችም አገልግሎቶች ማዋል እንደሚገባ አቅጣጫ ተይዟል።
አዲስ ዘመን፡– የጨው ምርት ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን እና ከኋላቀር አመራረት የተላቀቀ እንዲሆን ምን ሰራችሁ?
አቶ ገዶ፡– እስከዛሬ ጨው አምራች በሚል ከአፍዴራ ሐይቅ የሚያገኙትን ውሃ በትቦ በመሳብና በፀሐይ በማድረቅ ብቻ ጥሬ ጨው ሲያመርቱ የቆዩ በባለሃብት ስም የገቡ በርካቶች ነበሩ። ካለፉት ሦስት ዓመታት በፊት አንድም ፋብሪካ በጨው ማቀነባበርና አዮዳይዝድ በማድረግ ሥራ የተሰማራ ፋብሪካ አልነበረም።
ችግሩን ለማስተካከል ጨውን በማዳበሪያ በማሸግ ብቻ ለገበያ የሚያቀርቡትን በመለየት ከገበያ እንዲወጡ ተደርጓል፤ ባለሃብት ነን ብለው መጥተው ባህላዊ ሥራ የሚሰሩትን አስቁመናል። በምትኩ የአካባቢው ወጣቶች ተደራጅተው ከሐይቁ ምርት እንዲያዘጋጁ ተደርጓል።
አሁን ባለው ሁኔታ የኢንቨስትመንት ስርዓቱንም በማስተካከል አምራች፣ አቀነባባሪና አከፋፋይ በሚል ተለይቷል። የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ጥሬ ጨው ሲሰበስቡ የነበሩትን በፋብሪካ የማቀነባበር ስራዎች ላይ እንዲሰማሩ ተደርጓል።
ጨውን በአነስተኛ ካርቶኖች በማዘጋጀት እና ቴብል ሳልት በሚባለው መጠን በየሱፐርማርኬቱ ሊሸጥ በሚችልበት መንገድ አዮዳይዝድ አድርገው ወደስራ እንዲገቡ ሰፊ የቁጥጥርና የድጋፍ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።
በፋብሪካ ማቀነባበር ስልት ጨው አዮዳይዝ ተደርጎ ሲመረት ለሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ለውጭ ገበያም ለማቅረብ የሚቻልበት እና ክምችቱን ለመጠቀም የሚያስችል እድል ይፈጠራል። በአሁኑ ወቅትም በጨው ማቀነባበር ሥራ ግንባታቸው ተጠናቆ ወደስራ የገቡ አራት ፋብሪካዎች አሉ።
በተለይ ሁለቱ ከወር በፊት የተመረቁ ናቸው። ፋብሪካዎቹ፣ በሰመራ፣ አፍዴራ እና በራህሌ ከተሞች ላይ እያመረቱ ይገኛል። ሌሎችም ወደስራ ለመግባት ዝግጅት እያደረጉ የሚገኙ ባለሃብቶች አሉ። በዚህም ያለገበያ የተቀመጠውን የጨው ክምችት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገራት ገበያ በማቅረብ ገቢ ለመፍጠር ይረዳል።
በሌላ በኩል ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለፋብሪካ እና ለግለሰቦች በማቅረብ ለጤና ጠቃሚ የሆነ ጨው ገበያው ውስጥ እንዲሰራጭ ያደርጋል። ከዚህ ቀደም እንዲሁ ውሃ አርከፍክፈው ብቻ በመላክ የህብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት ሲያደርሱ የነበሩ አምራቾች ነበሩ። አሁን ሁሉም ጨው አዮዳይዝድ ሆኖ እንዲቀናበር እና በላብራቶሪም ተፈትሾ እንዲወጣ በመደረጉ ችግሩን ቀርፈናል።
አዲስ ዘመን፡– በአፋር ክልል ያለውን እምቅ የወርቅ ማዕድን ለብሔራዊ ባንክ በማቅረብ ረገድ ባለፉት 11 ወራት ምን ተሰራ?
አቶ ገዶ፡– እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በአፋር ክልል የወርቅ ምርት በምን ያክል መጠን ይገኛል የሚለው በውል አይታወቅም ነበር። ምርቱ ቢኖርም በኮንትሮባንድ ነበር ከሃገር የሚወጣው። በአፋር ክልል ስም የተደራጁ እና ፍቃድ ወስደው የሚሰሩ ወጣቶች አልነበሩም።
ያሉትም ግለሰቦች ክልሉን ሳይጠቅሙ ነበር ለግል ጥቅማቸው የሚያሸሹት የነበረው። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ወርቅ ላይም ልክ እንደጨው ምርት ሁሉ ትልቅ ስራ ነው በማከናወናችን ለውጥ መጥቷል። ስንነሳ በመጀመሪያ ያደረግነው ወርቅ የት ቦታዎች ላይ ይገኛል የሚለውን መለየት ነው።
በጥናታችን መሰረት በራህሌ ዳሎልና አፍሬዳን ጨምሮ አምስት ወረዳዎች ላይ ወርቅ መኖሩን ለየን። በመቀጠል ወርቅ የሚያመርቱ እና የወርቅ አዘዋዋሪዎች በሚል ወጣቶችን አደራጀን። በባህላዊም ሆነ በአነስተኛ መንገድ ሆነ በዘመናዊ መልክ የሚያመርቱትን ወጣቶች 10 ግራምም ይሁን 20 ግራም ምርት የሚገዙ ደግሞ ሌሎች ወጣቶች አሉ። የወርቅ አዘዋዋሪዎቹ ማህበር ደግሞ አሰባስቦ ለብሔራዊ ባንክ ያቀርባል።
ይህን ካደራጀን በኋላ የአካባቢው ማህበረሰብ እና የጸጥታ ኃይል በማስተማር የእራሳቸው ሃብት ነውና በኮንትሮባንድ እንዳይወጣ ተከላከሉ የሚል ሰፊ የግንዛቤ ትምህርት ሰጥተናል። ላለፉት 20 ዓመታት ወርቅ ከአካባቢው ሲጓዝ ቢኖርም ምንም እንዳልተጠቀሙ በማሳየት ህብረተሰቡን ያሳተፈ ሥራ ተከናውኗል።
በዚህ ዓመት ደግሞ የተደራጁት ማህበራትን በማሰልጠን ወደስራ እንዲገቡ አድርገናል። ወደስራ ሲገቡ ግን የተገኘውን ወርቅ አዲስ አበባ ድረስ ወስደን እንዴት እንሸጣለን የሚል ጥያቄ ነበራቸው። በአካባቢያቸው ደግሞ የወርቅ ግዥ ግብይት ለመፈም የሚያስችል የመንግሥት ተቋም ባለመኖሩ ቅርብ የሆነው አጎራባች ትግራይ ሽሬ ድረስ ሄደው ነበር የሚያስረክቡት።
ከኮነባ እና በራህሌ እንዲሁም ሌሎች በረሃዎች ወርቅ ይዘው 600 እና ከዚያ በላይ ኪሎሜትር ተጉዘው መሸጥ ለደህንነትም ሆነ ለወጪ የማያዋጣ በመሆኑ ለችግሩ መፍትሄ አምጡ አሉ። ትክክለኛ ጥያቄ ስለነበር ከብሔራዊ ባንክና ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር አፋር ኮነባ ላይ የወርቅ የግብይት ማዕከል መክፈት ተችሏል።
ይህም አብዛኛውን የኮንትሮባንድ ምርት ወደመንግሥት እንዲገባ ያደረገ ትልቅ ስራ ነው። በውጤቱም መሰረት በዚህ ዓመትም 107 ኪሎ ግራም ወርቅ ገቢ ተደርጓል። በአፋር ታሪክ ይህን ያክል መጠን ያለው ወርቅ ለማዕከላዊ ገበያ ገቢ ሆኖ አያውቅም።
ከፍተኛ የአመራር ክትትል እና ድጋፍ እንዲሁም የህብረተሰቡ ተሳትፎ ለውጤቱ መገኘት አስተዋጽኦ አድርጓል። እንደክልልም እውቅና እንድናገኝ እና ተሸላሚ እንድሆን ያደረገ ሥራ በመሆኑ በቀጣይ ጊዜያትም የበለጠ ምርት ለማግኘት እንሰራለን።
አዲስ ዘመን፡– ቢቀረፉ ዘርፉ ላይ የተሻለ መስራት ያስችለናል የሚሏቸው ችግሮች ምንድን ናቸው?
አቶ ገዶ፡– በማዕድን ዘርፉ ያለው የሰለጠነ የሰው ኃይል ከሚፈለገው አንጻር በጣም ዝቅትኛ ነው። የሰለጠነ የሰው ኃይል ችግራችንን በጊዜ ሂደት መፍታት ይጠበቅብናል። በሌላ በኩል ማዕድን ያለበትንና መጠኑን ለማወቅ በዘመናዊ መሳሪያ የታገዘ ጥናት ይጠይቃል። እኛ ደግሞ ለጥናት የሚሆኑ ማሽኖችም ሆነ ዘመናዊ ላብራቶሪዎች የሉንም።
እንደሀገርም ቢታይ ረጅም እድሜ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ተቋም ላብራቶሪ ነው አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው።ላብራቶሪው ግን በጣም ደካማ በመሆኑ እና ያረጁ መሳሪያዎችን በመያዙ የማዕድን ምርመራ ውጤቶች ሲያስፈልጉ ወደውጭ ተልኮም የሚሰራበት ጊዜ በርካታ ነው።
ወደውጭ ናሙና መላክ ደግሞ ከጊዜም ሆነ ከገንዘብ አኳያ የሚያዋጣ አይደለም። ስለዚህ እንደሀገር ትልቅ የላብራቶሪ ተቋም ያስፈልጋል። በክልሎችም ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ላብራቶሪ ከፍቶ መስራት ቢቻል የማዕድን ዘርፉን በብቃት ለመጠቀም የተሻለ እድል ይፈጥራል የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡– ስለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
አቶ ገዶ፡– እኔም ከልብ አመሰግናለሁ።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ሰኔ 23/2013