የሰዎችን የእለት ተዕለት እንቅስቃሴ ከሚያሳልጡና የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የንግድ እንቅስቃሴን ከሚያቀላጥፉ የመሰረተ ልማት አውታሮች መካከል የመንገድ መሰረተ ልማት በግምባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ በተለይ የመንገድ መሰረተ ልማት በከተሞች አካባቢ ፋይዳው የጎላ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህም ምክንያት በርካታ ሀገራት ለመንገድ መሰረተ ልማት ልዩ ትኩረት በመስጠት መንገዶችን ገንብተዋል፡፡
ኢትዮጵያም ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራቻቸው ካሉ የመሰረተ ልማት አውታሮች ውስጥ መንገድ ዋናው ሲሆን በተለይ ከቅርብ ግዜ ወዲህ በርካታ አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በከተሞችና በገጠር እያከናወነች
ትገኛለች፡፡ አሮጌና በእድሜ ብዛት ያረጁ መንገዶችንም አፍርሳ በአዲስ መልክ አስፋፍታ እየገነባች ነው፡፡ በከተሞች አካባቢ ያለውን የመንገድ ሽፋን ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት እያተደረገ ነው፡፡ እጅግ አስደናቂ በሆነ ፍጥነት ተሰርተው ለትራፊክ ክፍት የሆኑ የመንገድ ልማቶችን በምርቃታቸው ወቅት ለማየት ችለናል።
በተለይ ደግሞ አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫና የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማትና ዲፕሎማቶች መቀመጫ እንደመሆኗ መጠን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ አዳዲስና ግዙፍ የመንገድ ፕሮጀክቶች ተጀምረዋል፡፡ ከፊሎቹም ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ለትራፊክ ክፍት ሆነዋል፡፡
በአሁኑ ግዜ ግንባታቸው እየተከናወነ የሚገኙት የከተማዋ አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶች በቀጣይ ተጠናቀው ለትራፊክ ክፍት ሲሆኑ የከተማዋን ገፅታ ከመቀየር በዘለለ የትራንስፖርት እንቅስቃሴውን በማሳለጥ ረገድ ሚናቸው የጎላ እንደሚሆንም
ይጠበቃል፡፡ እየተከናወኑ የሚገኙት አብዛኛዎቹ የመንገድ ፕሮጀክቶችም የከተማዋን የወደፊት አቅጣጫ ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውም ይታወቃል፡፡
በመንገድ መሰረተ ልማት ግንባት ሂደት ከሚያጋጥሙ ችግሮች መካከል አንዱና ዋነኛው የወሰን ማስከበር በመሆኑ ይኸው ችግር የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣንን በተደጋጋሚ ፈትኖታል፡፡ በዚሁ ችግር ምክንያት አንዳንድ ፕሮጀክቶች ተጓተዋል፡፡
የመንገድ ፕሮጀክቶች በሚያልፉባቸው አካባቢዎች ላይ የሚገኙ መኖሪያ ቤቶች፣ ህንፃዎች፣ የንግድ ፣ የግልና የመንግስት ተቋማት፣ የውሃ፣ ቴሌኮምና የመብራት መሰረተ ልማቶችና ሌሎችም በግዜ ባለመነሳታቸው በከተማዋ ለመንገድ መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች መዘግየት ምክንያት ሆነዋል፡፡ ይህም ችግር ከባለስልጣኑ አቅም በላይ ሲሆን ታይቷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ እያሱ ሰለሞን እንደሚሉት፤ የወሰን ማስከበር ችግር ሲባል በአንድ አዲስ ወይም የነባር መንገድ ማስፋፊያ መሰረተ ልማት ግንባታ ፕሮጀክት ዲዛይን የመንገድ ወሰን ተብሎ በተለየው ቦታ ውስጥ የሚገኙ የመኖሪያ ቤቶችን፣ የግልና የመንግስት ድርጅቶችን እንዲሁም የውሃ፣መብራትና ቴሌኮም መሰረተ ልማቶችን ያጠቃልላል፡፡ የወሰን ማስከበር ስራም አዲስ በሚገነባው ወይም ደግሞ ማስፋፊያ በሚደረግበት የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ የሚገኙትን እንቅፋቶች የማስነሳት ተግባር ነው፡፡
የወሰን ማስከበር ስራ በተለይ እንደ አዲስ አበባ ላሉና ቀድመው በተገነቡ ከተሞች የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታን ለማከናወን ትልቅ ተግዳሮት ነው፡፡ አዳዲስና የማስፋፊያ የመንገድ ፕሮጀክቶች በሚከናወኑበት ወቅትም በፕሮጀክቱ ወሰን ውስጥ የሚገኙ ግንባታዎች፣ ቀድመው የተገነቡ የውሃ፣ መብራትና የቴሌኮም መሰረተ ልማቶች በስፋት ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ባልተነሱበት ሁኔታ በአዳዲስም ሆነ በነባር መንገዶች ላይ የሚደረጉ ማስፋፊያዎችን ለማከናወን አዳጋች ያደርገዋል፡፡ ይህም ጉዳይ ልዩ ትኩረት የሚፈልግና በተደጋጋሚ ለመንገድ ግንባታ ስራዎች ተግዳሮት ሆኖ ቀጥሏል፡፡
አዲስ አበባ ቀድማ የለማች ከተማ ናት፡፡ ቀድሞ በለማ ከተማ ውስጥ ያለው የመንገድ መሰረተ ልማት ሲታይም አስቀድሞ በተገነባበት ዘመን ከነበረው አጠቃላይ የከተማዋ የትራፊክ እንቅስቃሴና ከሌሎች ጉዳዮች አንፃር በቂ ሆኖ ሊታይ ይችላል፡፡ ይሁንና ከተማዋ በፈጣን እድገት ውስጥ የምትገኝና የነዋሪዎቿም ቁጥር በየጊዜው እያደገ በመምጣቱ፤ ከዚህም ጋር ተያይዞ የትራንስፖርት አገልግሎቶ አገልግሎቶችና ሌሎችም ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ከዚህ አኳያ ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ ሁልግዜም የመንገዶችን ደረጃዎች የማሻሻል እንዲሁም የመንገድ መረብ ሽፋንን የማሳደግ ስራዎች ይጠበቃሉ፡፡ አቋራጭና አንዱን ከሌላኛው መንገድ ጋር የሚያስተሳስሩ አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶችም ይገነባሉ፡፡ በተለይ አዳዲስ የመኖሪያ መንደሮችና ሌሎች አካባቢዎች እየለሙ የመጡበት ሁኔታ በመኖሩ ከዚህ ጋር በተያያዘ የመንገድ መሰረተ ልማቶች ያልደረሰባቸው ቦታዎች ላይ ተደራሽ የማድረግ ስራዎችም ያስፈልጋሉ፡፡
እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ ባለስልጣኑ እነዚህን የመንገድ መሰረተ ልማት ስራዎችን ሲያከናውን እያገጠሙት ካሉ ተግዳሮቶች ውስጥ አንዱና ዋናው የወሰን ማስከበር ችግር ነው፡፡ ይህም በዲዛይን ውስጥ መንገዱ የተያዘለትን ወሰን ውስጥ ያሉ ግንባታዎች፣ ቀድመው የተገነቡ የውሃ፣ መብራትና የቴሌኮም መሰረተ ልማቶችን ያጠቃልላል፡፡ ችግሩ በዋናነት የሚከሰተውም ቀደም ሲል የነበሩ አሮጌና ጠባብ መንገዶችን ለማስፋትና አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በአዳዲስ ቦታዎች ላይ ለመገንባት በመንገዱ ክልል ውስጥ ያሉትን እንቅፋቶች ለማስነሳት በሚደረገው ጥረት ነው፡፡
በዚህ ሂደትም በርካታ ቤቶች በፊት ከነበራቸው ይዞታ ይነሳሉ፡፡ የቤት ጉዳይ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች አንዱና ትልቁ ጥያቄ በመሆኑ ምትክ ቦታ ማዘጋጀት በራሱ ሌላ ፈተና ሲሆን ይህም በመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ ተጨማሪ አሉታዊ ተፅእኖ ያሳድራል፡፡
በዚሁ በጀት አመት የግንባታ ስራቸው ተጠናቆ ለምረቃ የሚበቁትን መንገዶች በፍጥነት ለማጠናቀቅና ለትራፊክ ክፍት ለማድረግ በባለስልጣኑ ሰፊ የወሰን ማስከበር ስራዎች ይጠበቁ ነበር፡፡ በዚሁ መነሻነትም በበጀት አመቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራቶች በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ ለሚገነቡ መንገዶች ከወሰን ማስከበር አንፃር 1 ሺ 852 ቤቶች ከመንገዶቹ ግንባታ ወሰን ክልል ውጪ እንዲሆኑ በእቅድ ተይዞ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በተሰራ ስራ 1 ሺህ 398 ቤቶችን ማስነሳት ተችሏል፡፡
ይህ ብቻ ሳይሆን በዘጠኝ ወሩ በመንገድ ፕሮጀክቶቹ ውስጥ የሚገኙ የውሃ፣ ኤሌክትሪክና ቴሌኮም መሰረተ ልማቶችን ለማስነሳት ከባለድርሻ ተቋማት ጋር በመስራት ከኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት አንፃር ወደ 1 ሺ 287 የኤሌክትሪክ መስመሮችን ለማንሳት ታቅዶ 566 ያህሉን ማንሳት ተችሏል፡፡ ከስልክ መስመር ጋርም በተያያዘ 148 የሚሆኑ መስመሮችን እንዲነሱ ተደርገዋል፡፡ ከውሃ መስመሮች ጋር በተገናኘም ተመሳሳይ ተግባሮች ተከናውነዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ከተማዋ ቀድማ የለማች በመሆኗ ባለስልጣኑ የመንገድ መሰረተ ልማትን በሚያስፋፋበት ወቅት የወሰን ማስከበር ስራዎችን መስራት ትልቁና ዋነኛው ተግባር ሆኗል፡፡ አንዳንድ ግዜ ደግሞ ፈተናም ሆኖ ያለፈበትና ችግሮቹንም ለመፍታት ሰፊ ስራዎችን የሰራባቸው ነው፡፡
በከተማዋ ከወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ ችግር ምክንያት ግንባታቸው ከዘገየና በዚህ በጀት አመት ግንባታቸው ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆን ከነበረባቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ አስራ አንድ ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለውና ከቃሊቲ ማሰልጠኛ ወደ ቱሉ ዲምቱ የሚሄደው መንገድ ሲሆን በዚህ የመንገድ ክፍል ውስጥ ሰፊ የወሰን ማስከበር ስራዎች ከዚህ ቀደም ተከናውነዋል፡፡
ወደ ቱሉ ዲምቱ የሚወስደው የመንገዱ ቀኝ ክፍል አስፓልት እንዲሆን ተደርጎም በተወሰነ ደረጃ አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡ ትላልቅ ስትራክቸር ያላቸው ሶስት መሻገሪያ የማሳለጫ ድልድዮችም ተገንብተዋል፡፡ ይሁንና በመንገዱ የግራ ክፍል በኩል ግንባታውን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ ትልቅ ፈተና ከሆኑ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ በመንገድ ወሰኑ ላይ የሚያልፍና ወደ 10 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ከአቃቂ ክፍለ ከተማ ወደ መሀል ከተማ የሚመጣ ትልቅ የውሃ መስመር መኖር ነው፡፡
ይህ የውሃ መስመር ባለመነሳቱ ምክንያት የመንገድ ግንባታውን በታሰበው ግዜ ለማጠናቀቅ
አልተቻለም፡፡ በመሆኑም የአዲስ አበባ የውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን መስመሩን ለማስነሳት በቅድሚያ ለስራው አጋዥ የሆኑ ማቴሪያሎችን ከውጪ ሀገር ለማስገባት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ከወሰን ማስከበር ችግሮች አንዱ ማሳያ ከሆኑ የከተማዋ የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል ግን አንዱ ይኸው የመንገድ ፕሮጀክት ነው፡፡
በመሆኑም በከተማዋ የሚገኙ አብዛኞቹ የመንገድ ፕሮጀክቶች በከተማ የሚገነቡ ከመሆኑ አኳያ ብዙዎቹ በወሰን ማስከበር ችግር ተፈትነዋል፡፡ ከአውቶብስ ተራ ወደ አስራ ስምንት ማዞሪ የሚሄደው የመንገድ ፕሮጀክትም ይኸው የወሰን ማስከበር ችግር ከፈተናቸው ውስጥ ሌላኛው ማሳያ ነው፡፡ በዚህ የመንገድ ፕሮጀክት ወሰን ውስጥ በተመሳሳይ ስፋት ያላቸው የመኖሪያና የንግድ ቤቶች እንዲሁም የመሰረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት መስመሮች ይገኙበታል፡፡ በዚህ የመንገድ ፕሮጀክት የወሰን ማስከበር ስራውን በተወሰነ ደረጃ ለመፍታት ብዙ ርቀት ለመሄድ የተሞከረ ቢሆንም አሁንም ድረስ ያልተፈቱ ችግሮች ስላሉ በተፈለገው ፍጥነት የግንባታ ስራውን ማከናወን አልተቻለም፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በከተማዋ ያሉትን የወሰን ማስከበር ችግሮች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላትና ተቋማት ጋር በመሆን እየፈታ ይገኛል፡፡ እስካሁን ባለው ሂደትም ከ77 ኪሎ ሜትር ርዝመት በላይ ያላቸው 24 የሚሆኑ የመንገድ ፕሮጀክቶችን አጠናቆ በቅርቡ አስመርቋል፡፡ በቀጣይም ተጨማሪ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ለማስመረቅ በትጋት እየሰራ ይገኛል፡፡ ከመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ ጋር ሲታይ ግን የወሰን ማስከበር ስራው ፈታኝ ነው፡፡
በቀጣይ ሌሎች አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶች በከተማዋ መጀመራቸው አይቀርምና ተመሳሳይ የወሰን ማስከበር ችግሮች ሊያጋጥም እንደሚችል ያላቸውን ስጋተ ጠቅሰዋል። ነገር ግን ይህን ችግር ከመፍታት አንፃር ባለስልጣኑ አዳዲስ እየተገነቡ ባሉ መንገዶች ላይ ወደፊት ከተማዋ የሚኖራትን የእድገት አቅጣጫ ታሳቢ ባደረገ ሁኔታ የመንገድ ወሰኖችን አስከብሮ የመሄድ ስራዎችን ይሰራል፡፡
በቀጣይ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች እየገጠማቸው ያለውን የትራንስፖርት አገልግሎት ችግር ለመፍታት የብዙኃን ትራንስፖርት ተደራሽነትን ለማስፋት
ታቅዷል፡፡ በተለይ ፈጣን የአውቶብስ መስመሮችን በስፋት ማከናወን ትልቅ የትኩረት አቅጣጫ ነው፡፡ በመሆኑም ይህን ከማድረግ አንፃር የፈጣን አውቶብሶችን እንቅስቃሴ ሊሸከምና ሊያስተናግድ የሚችል የቢ አር ቲ /Bus Rapid Transit/ ኮሪደሮችን ማልማት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ታሳቢ የሚሆን ከሆነ ደግሞ የመንገድ ወሰኖች አሁን ያለውን የተሽከርካሪ እንቅስቃሴን ብቻ ሳይሆን ወደፊትም የሚኖሩትን የመሰረተ ልማት ዝርጋታ በሚያመች መልኩ የመንገድ ወሰናቸውን በስፋት ማስከበር የግድ ይላል፡፡
ከዚህ አንፃር ከሃይሌ ጋርመንት ወደ ጀሞ አደባባይ በሚወስደው መንገድ ጥሩ ማሳያ ሆኖ የሚጠቀስ ነው። የጎን ስፋት ወደ 120 ሜትር አለው። አሁን ባለው የግንባታ ደረጃ በሁለት አቅጣጫ አስራ አንድ ሜትር የጎን ስፋት ያለውና ሶስት ተሽከርካሪዎች በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚያስችል የአስፓልት ግንባታ ተከናውኖበታል፡፡ በመንገዱ ዳር 20 ሜትር የጎን ስፋት ያለው ቦታም ተትቶለታል፡፡ ይህም በቀጣይ ለሚኖር የመንገድ ትራንስፖርት ማስፋፊያ ስራ ታሳቢ ተደርጎ የተተወ ቦታ ነው፡፡
የሞተር አልባ ትራንስፖርት አገልግሎቶችን፣ የእግረኛ መንገዶችንና የአረንጓዴ ስፍራዎችንም ጭምር ታሳቢ ያደረገ የመንገድ ክፍል አለው፡፡ ከመሰረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት በኩል የሚያጋጥመውን ተናቦ የመስራት ችግር ከመቅረፍ አንፃር ሚናው የጎላና ተቋማቱ ለሚያከናውኗቸው ግንባታዎች ቦታ የተወ የመንገድ ግንባታ ነው፡፡ በሌሎች አካባቢዎች ላይም እንዲህ አይነቱን አሰራርና ስልት በመከተል አዲስ አበባ ከተማ ወደፊት የሚኖራትን አጠቃላይ እድገት ታሳቢ ያደረገ የመንገድ መሰረተ ልማት ለማከናወን ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 18/2013