
ጊንጪ፦ በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ግብርናውን ለማዘመን፣ የእውቀት ሽግግር ለማምጣትና ለወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ ገለጹ። ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ከ22 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበትን ኬኛ የመጠጦች ፋብሪካን መርቀው ከፍተዋል።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ በኦሮሚያ ክልል፣ በምዕራብ ሸዋ ዞን በ110 ሄክታር መሬት ላይ የተገነባው፣ ግዙፉን ኬኛ የመጠጦች ፋብሪካ ትናንት መርቀው ሲከፍቱ እንደተናገሩት፤ የኬኛ መጠጦች ፋብሪካ በአካባቢው መገንባቱ ሌሎች ተጨማሪ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል። የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ግብርናውን ለማዘመን፣ የእውቀት ሽግግር ለማምጣትና ለወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ያስችላሉ። በዚህ ረገድ የኬኛ ፋብሪካ ሚናው የጎላ መሆኑን አብራርተዋል።
ፋብሪካው በዞኑ የሚኖረውን ኢኮኖሚ ያሻሽላል። ከጥሬ እቃ ጀምሮ እስከ ምርት ያለውን የገበያ ሰንሰለት በመጠቀም ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ያደርጋል ያሉት ፕሬዚዳንት ታዬ፤ የከተማዋን የኢንዱስትሪ ማዕከልነት እንደሚጨምር፤ ምርቶችን በጥራት በማምረት የኤክስፖርት ምርትን እንደሚያሳድግም ተናግረዋል። በመሆኑም ማህበረሰቡ ፋብሪካውን ሊጠብቅ እና ሊንከባከብ ይገባል ነው ያሉት።
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ የለውጡ መንግሥት የመሠረተ ድንጋዮችን የሚያስቀምጥ ብቻ ሳይሆን ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ገንብቶ ለአገልግሎት በማዋል የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ይገኛል።
በክልሉ ውስጥ የተለያዩ የልማት ሥራዎች በስፋት እየተሠሩ መሆናቸውን ገልፀው፤ ሕዝቡን ወደ ልማት ለማስገባትና ኢኮኖሚውን ለማጠናከር የሚሠሩ ሥራዎች እንደሚቀጥል ተናግረዋል። በቀጣይም መንግሥት የሀገሪቱን ብልፅግና ከማረጋገጥ አንፃር የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ፕሮጀክቶች በማስፋፋት ህብረተሰብ ተኮር ሥራዎችን በትኩረት ይሠራል ብለዋል።
የኬኛ መጠጦች ፋብሪካ የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ንዋይ መገርሳ የፋብሪካ ግንባታው ስምንት ዓመታትን የፈጀ መሆኑን ተናግረው፤ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን የሥራ እድልን መፍጠር የቻለ ስማርት ኢንዱስትሪ መሆኑን ገልፀዋል።
እንደ ሰብሳቢው ገለፃ ፤ በአሁኑ ወቅት ፋብሪካው ከ250 በላይ የሰው ኃይል ቀጥሮ በማሠራት ላይ የሚገኘው ኬኛ፣ በእሴት ሠንሰለቱን መሠረት ከ1 አንድ ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።
ኩባንያው፣ በተቀናጁ የግብርና መርሃ ግብሮች አማካኝነት አርሶ አደሮች ምርታቸውን እንዲያሳድጉ እንደሚደግፍ አመልክተዋል።
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 8 ቀን 2017 ዓ.ም