እስትንፋስ የሆኑ የዕድገት ማገሮች

ምርቶችን ወደ ገበያ ለማቅረብ፣ ገበያተኛን ለማገናኘት፤ ወደ ፋብሪካዎች አስገብቶ እሴት የታከለበት ምርት ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የመንገዶች ሽፋን ማደግ ዋነኛው ጉዳይ ነው። መንገድን ጨምሮ ለአንድ ሀገር እድገት መሠረተ ልማት የደም ሥር መሆናቸው አያጠያይቅም። ከየብስ መንገድ ባሻገር፣ የባቡር መስመር ዝርጋታ፣ የአየር እና የባሕር ትራንስፖርት ማሳደግ፣ ኢነርጂ እንዲሁም ዘመኑ የሚጠይቀውን የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂን ማስፋፋት ግድ የሚልበት ዘመን ላይ ተደርሷል።

ይህንን መነሻ በማድረግም የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ስለኢትዮጵያ መሠረተ ልማት እንምከር በሚል ትናንት 20ኛውን መድረክ በድሬዳዋ ከተማ አካሂዷል። በመድረኩ መሠረተ ልማት ላይ የሚመለከታቸው የመንግሥት እና የግል የዘርፉ ተዋናዮች መክረዋል። የኢፌዴሪ ከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ ፣ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ ዶ/ር፣ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው ተገኝተው የተሠራውን ከማሳወቅ ባሻገር ከታዳሚዎች ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ፤ ከትራንስፖርት አኳያ 65ሺህ ኪሎ ሜትር የነበረው የመንገድ ሽፋን ወደ 172 ሺህ ኪሎ ሜትር አድጓል ። ይሁንና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት፤ ካለው ፍላጎት እና ከሀገሪቷ የቆዳ ስፋት አኳያ የተሠራው በቂ አለመሆኑን በማውሳት፤ ከዚህ በላይ መሥራት ያልተቻለበት ዋነኛው ምክንያት የወሰን ማስከበር ችግር እንቅፋት በመፍጠሩ መሆኑን አመላክተዋል።

አንድ ቢሊዮን ብር ለሚጠይቅ የመንገድ ግንባታ፤ ወሰን ለማስከበር እስከ ሁለት ቢሊዮን ብር ወጪ የሚያስፈልግበት ሁኔታ መፈጠሩን አስገንዝበዋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጅነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይልን ለ10 ዓመታት ለጂቡቲ፤ ለስምንት ዓመታት ለሱዳን፣ ለሶስት ዓመታ ለኬንያ ለስምንት ወራት ለታንዛኒያ እየሸጠች መሆኑን አስታውሰው፤ ይሁንና አሁንም የኤሌክትሪክ ኃይል እየሸጠች ቢሆንም አሁን ባለው ሁኔታ ከቀጠለ ከሶስት ዓመት በኋላ ኃይል ከመሸጥ ይልቅ ለመግዛት የምትገደድበት ሁኔታ እንደሚኖር አመላክተዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ፤ 131 ዓመታትን ያስቆጠረው የቴሌ ኮም አገልግሎት ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችል መሠረት መጣሉን አብራርተዋል። ኢትዮ ቴሌኮም በአምስት ኮሪዶሮች ኢትዮጵያን ከሌላው ዓለም ጋር ለማገናኘት እየሠራ መሆኑን በመጠቆም፤ ፍጥነት ቅልጥፍና እና ተደራሽነት ላይ በመመርኮዝ ባከናወናቸው ሥራዎች፤ ከሀገሪቷ ጂዲፒ ስምንት በመቶ ድርሻ ይዟል ሲሉ ተናግረዋል።

በሀገሪቷ የተቋማት የእርስ በእርስ ግንኙነት የብሮድ ባንድ አገልግሎት 66 ሺህ እንደነበር አስታውሰው፤ በአሁኑ ጊዜም ወደ 800 ሺህ መድረሱን ጠቁመዋል። ይህ ለአገልግሎት አሠጣጥ ዕድገት የሚኖረው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑንም ነው ዋና ሥራ አስፈጻሚው ያብራሩት።

ተሳታፊዎቹ በመሠረተ ልማት ላይ መታየት አሉባቸው ያሏቸውን ጉዳዮች ያመላከቱ ሲሆን፤ የከተሞች መስፋፋትን በማንሳት የኤሌክትሪክ የብዙሃን ትራንስፖርትን ማሳደግ ላይ በስፋት ሊሠራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የሃይል መባከንን እና የሕዳሴው ግድብ እየተጠናቀቀ ከሶስት ዓመት በኋላ ኢትዮጵያ ሃይል ለመግዛት ትገደዳለች የተባለበት ምክንያት እንዲብራራላቸው ጠይቀዋል።

የሀገሪቱን በጀት 18 በመቶ የሚወስደው መንገድ መሆኑን በማስታወስ፤ ይሁንና ለመንገድ እና ለድልድዮች ደህንነት የሚሠጠው ትኩረት ማነስ ልማቱን በከፍተኛ መጠን እንደሚጎዳው ተነግሯል። ለመንገድ ጥገና እየወጣ ያለው ወጪም ከፍተኛ መሆኑ ተመላክቷል።

የቴሌኮም አገልግሎትን በተመለከተም የቴክኖሎጂው ማደግ እንደተጠበቀ ሆኖ የደህንነት ጉዳይ ምን ያህል በጥንቃቄ የተያዘ ነው? እንዲሁም በቴክኖሎጂ ዘርፍ ብቃት ያለው የሰው ሃይል ማፍራትን የተመለከቱ እና ሌሎችም ተያያዥ ጥያቄዎች ቀርበዋል።

የሥራ ሃላፊዎቹ በሰጡት ምላሽ በተለይ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ፤ የመንገድ ደህንነት ችግርን ለማቃለል በርካታ አዳዲስ የመፍትሔ አማራጮች መኖራቸውን አስረድተዋል። ቴክኖሎጂዎችን በመግጠም መሠረተ ልማቶቹ ላይ ጉዳት ከመድረሱ በፊት መከላከል የሚቻልበትን ሁኔታ በተመለከተ አስረድተዋል።

የሳይበር ደህንነትን ለማረጋገጥ ኢትዮ ቴሌኮም እየሠራ መሆኑንና የዲጂታል ካውንስል መኖሩን በመጠቆም፤ በቀን ስምንት ቢሊዮን ብር መንቀሳቀስ የቻለው የሳይበር ደህንነት ላይ በአስተማማኝ መልኩ በመሠራቱ መሆኑን አስረድተዋል። ብቁ የሰው ሃይል ከማፍራት አንፃር ሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾ (ካሪኩለም ዲዛይን ተደርጎ) በዩኒቨርሲቲዎች እንዲያስተምሩ በጋራ እየተሠራ ይገኛል ሲሉም ተናግረዋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) እንዳመላከቱት፤ እያደገ የመጣው የሃይል ፍላጎት፣ የማስተላለፊያ እና የማሰራጫ መስመር ግንባታ በቂ አለመሆን፤ ሃይል የሚባክንበት ሁኔታ መኖር በቀጣይ ዘርፉ ላይ እክል ይፈጠራል በሚል ስጋት ያነሱት ሃሳብ መሆኑን አስረድተዋል።

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You