ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ለጀመርነው ሀገራዊ የለውጥ ስኬት ወሳኝ አቅም ነው!

ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የመንግሥት ወይም የሆነ ተቋም ኃላፊነት አይደለም። ዜጎች ባላቸው አቅም ሁሉ ሥራ የመፍጠር፤ ከሚፈጠር ሥራ ራሳቸውን እና ወገናቸውን፤ ከዚያም አልፈው ሀገራቸውን የመጥቀም የማይተካ ኃላፊነት አለባቸው። ዘላቂ ለሆነ የኢኮኖሚ እድገትም፤ ዜጎች በሀገር ውስጥ ሊፈጥሩ የሚችሉት ሥራ ወሳኝ እንደሆነ ይታመናል።

በተለይም በአንድም ይሁን በሌላ ለዜጎች ሥራ መፍጠር የሚያስችል አቅም ያላቸው ዜጎች፤ አቅሞቻቸውን አምራች በሆኑ ዘርፎች ኢንቨስት በማድረግ ለዜጎች ተጨማሪ የሥራ ዕድል መፍጠር፤ በዚህም አጠቃላይ ከሆነው የኢንቨስትመንት ተጠቃሚነት ባለፈ፤ ለሀገር እድገት ወሳኝ የሆነውን አምራች ኃይል ወደ ሥ ራ በማስገባት የሀገር እና የሕዝብ ባ ለውለታዎች ሊሆኑ ይገባል።

ለዜጎች አማራጭ የሥራ ዕድል መፍጠር ተጨማሪ ሀብት ከማፍራት ባለፈ፤ እንደ ሀገር ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት በማስፈን፤ የተረጋጋ እና የሰከነ ማኅበረሰብ በመፍጠር ሂደት ውስጥ የሚኖረው ስትራቴጂያዊ አስተዋፅዖ ከፍ ያለ ነው። ኢንቨስትመንትን ስጋት ውስጥ የሚከቱ ማኅበራዊ ግጭቶችን መታደግ የሚያስችል ሁነኛ መፍትሔም ነው።

በተለይም እንደኛ ባሉ፤ ለዘመናት ዜጎች በግጭት አዙሪት ውስጥ ብዙ ያልተገባ ዋጋ ለመክፈል እየተገደዱባቸው ባሉ ሀገራት እና ሕዝቦች፤ ችግሩን ለዘለቄታው ለመሻገር፤ ለግጭቶች አቅም የሆነውን አምራች ኃይል ወደ ሥራ ማስገባት ትልቅ መፍትሔ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ችግሩን በዘላቂ ልማት ለመሻገር ዋነኛ አቅም ከመሆኑም በላይ የሰላም ግንባታ አንድ አካል ተደርጎም ይወሰዳል።

አንድ ሀገር ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ለተሻሉ ነገዎች ግንባታ ተስፋ ሆኖ የመጣውን አምራች ኃይል ወደ ሥራ ማስገባት የሚያስችል አቅም መፍጠር ካልቻለች፤ ለመልካም ነገዎች ተስፋ የተጣለበት ይህ ኃይል በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የጥፋት ኃይል ሆኖ መሰለፉ፤ በዚህም የራሱን እና የሀገሩ፤ ከዚያም አልፎ የመጪውን ትውልድ ዕጣ ፈንታ ማበላሸቱ የማይቀር ነው።

ለዚህ ደግሞ ለዘመናት እንደ ሀገር ያለፍንባቸውን የፈተና ወቅቶች ማስተዋል ተገቢ ነው። በተለያዩ ወቅቶች ለተፈጠሩ ችግሮች በአብዛኛው አቅም የነበረው ሥራ አጥ የሆነው አምራች ኃይል ነው። ይህ ኃይል ከነበረበት ተጨባጭ እውነታ አኳያ የጥፋት ትርክቶች እና መወናበዶች ሰለባ ሆኗል።

በዚህም ሀገር በብዙ ዋጋ በዓመታት መካከል የፈጠረቻቸው ሥራዎች ሳይቀሩ አደጋ ውስጥ ወድቀዋል። ችግሩ ለአምራች ኃይሉ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” በመሆን አምራቹ ኃይል፤ ላልተገባ የጥፋት ተልዕኮ ዋጋ ከፍሏል። ከግጭት ለማትረፍ በብዙ የልብ ድንዳኔ አደባባዮችን የሞሉ ግለሰቦች እና ቡድኖች የጥፋት አጀንዳ ማስፈጸሚያ የሆኑበት ተጨባጭ እውነታ ተፈጥሯል።

ችግሩ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፈጠረው መንገራገጭ ባለፈ፤ በባለሀብቱ ላይ የፈጠረው ጫና ቀልሎ የሚታይ አይደለም። የሁሉንም ማኅበረሰብ የዕለት ተዕለት ሕይወት በመነካካት አሁን ላይ ለተፈጠረው የኑሮ ውድነት እንደ አንድ ምክንያት ተጠቃሽ ነው። በዚህም ሀገር እንደ ሀገር ተጎጂ ሆናለች።

ለዜጎች የሥራ ዕድል የመፍጠር መነቃቃት፤ አሁን ላይ ለሀገር ሰላም እና ዘላቂ ልማት ባለውለታ የመሆን ያህል ነው። በሀገር የሰላም ግንባታ ውስጥ ትልቅ አቅም ሆኖ የመገኘት መልካም አጋጣሚ ነው። ከዚያም ባለፈ እንደ ሀገር ለጀመርነው ድህነትን ታሪክ የማድረግ ጉዞ ተጨማሪ አቅም ሆኖ መገኘት ነው።

ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ሂደት ውስጥ መንግሥት የራሱ የሆነ ኃላፊነት ስላለበት፤ ሥራ ፈጠራን በፖሊሲ ከማበረታታት ጀምሮ ሀገራዊ አቅሞችን አቀናጅቶ ለዚሁ ዓላማ ለማዋል የሚያስችል ዝግጁነት እና ተግባራዊ ሀገራዊ ንቅናቄ በመፍጠር መልካም ውጤቶችን አስመዝግቧል።

ከዚህ በተጨማሪ የግሉ ዘርፍ ባለው አቅም የሥራ ፈጠራን ከማበረታታት ጀምሮ ሥራ በመፍጠር ሂደት ውስጥ ያለውን ግንባር ቀደም ኃላፊነት ለመወጣት ራሱን በተሻለ ዝግጁነት መግራት ይኖርበታል። ዜጎችም የተፈጠረ ሥራ ከመጠበቅ ወጥተው ባላቸው ዕውቀት እና አቅም፤ እንደ ሀገር ከሚፈጠሩ ዕድሎች ሥራ መፍጠርን የዕለት ተዕለት ሕይወታቸው አካል አድርገው መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል።

ይህን ማድረግ ሀገርን ከግጭት አዙሪት ማውጣት፤ አምራች ኃይሉ ለራሱ እና ለሀገሩ ነገዎች ተስፋ መሆኑን በተጨባጭ እውን ማድረግ የሚያስችል፤ እንደሀገር ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ለጀመርነው ሀገራዊ የለውጥ ጉዞ ስኬት ወሳኝ አቅም ሆኖ የመገለጥ ጅማሬ ነው!

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 8 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You