ሰሞኑን ከምኖርበት ሰፈር አቅራቢያ ባለ መንደር ስዘዋወር ነበር:: የአካባቢው ቤት ኪራይ ዋጋ በአንፃራዊነት ከሌሎች ሰፈሮች አነስ ማለቱን ሰምቼም ነበርና እዚያው ሰፈር ቤት መፈለግ ውስጥ ገባሁ:: ጉዳዩንም አካባቢውን ለሚያውቅ አንድ ወዳጄ አዋየሁት፤ ምላሹ ግን አስገረመኝና ለዛሬ ወጌ መነሻ አደረኩት:: ቤት ልቀይር አስቤያለሁና ትረዳኛለህ ያልኩት ይህ ወዳጄ “ከምርጫ በኋላ ብትቀይር መልካም ነው አለኝ” አባባሉ ብዙ አሳሰበኝ::
ወዳጄ! ስንቱን ነገር ከምርጫ በኋላ እያልክ ስትቀጥርና ስታስቀጥር ከረምክ? እርግጠኛ ነኝ ብዙዎቻችንም በዚህ በወዳጄ መንገድ ሄደናል::
“ይሄን ሰፈር ልቀይር ፈልጌ ነበር፤ ከምርጫ በኋላ ብዬ ነው፤ አዲስ ስራ ልጀምር አስቤ ነበር፤ ከምርጫ በኋላ ላድርገው…” እያልን በተደጋጋሚ በየቀጠሮና እቅዳችን መሀል ስናወራ ከርመናል ፤ ሰንብተናል:: አቤት ስንቱን ከምርጫ በኋላ አደርጋለሁ እያልን አራዘምን? ይሄው ከምርጫ በኋላ ብለህ የቀጠርከውንም ፣ያስቀጠርካቸውንም ጉዳዮች ፈፅም፤ ሁሉም ሰላማዊ ሆኖ ተጠናቋልና አልኩት::
በእርግጥ የወዳጄን አባባል ንቄ አላለፍኩትም፤ ምክንያቱም አንድ እውነት አለዋ:: ነገር ግን እኔ ሁሌም በዚህ አምናለሁ:: ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ሲሉ ምንም ነገር እንደሚያደርጉ:: ሰላማቸውን ጠብቀው አገራቸው እንድታሸንፍ ሁሌም በጋራ ቆመው እንደሚሰሩ::
ወዳጄ ልኬት ታውቃለህ? እርስዋ ከአንተና ከእኔ የተለያየ ሀሳብ እጅግ ከፍ ያለች ከሁላችንም የምትልቅ ግዙፍ ናት፤ ኢትዮጵያ:: የህዝብዋን ስነ ልቦና ጠንቅቀህ ማወቅ ደግሞ ለሁሉ ነገር ይጠቅማል:: ኢትዮጵያዊያን ከሁሉም በላይ አገራቸውን ያስበልጣሉ፤ አገራቸውን በትክክልና በእውን እንድትቆም ደግሞ የማያደርጉት እንደሌለ ማወቅ ተገቢ ነው::
የኢትዮጵያ ህዝብ አርቆ የሚያይ ነገሮችን በጥልቀት የሚመረምር ነው:: አገሩን የሚጎዳውንና የሚጠቅመውን ለይቶ የሚያውቅ:: እርግጥ አፍሪካዊያን የዲሞክራሲ ባህላችንን ብዙ ይቀራዋል፤ እንዲያም ሆኖ ግን በራሳችን ቀለምና በተለየ ባህላችን ወደ ሌሎችም ቢሻገር አሁን ካለው በተሻለ ለሰው ልጆች መብት እና ፍትህ የሚያላብስ ባህል አለን:: ነገር ግን የእኛን ጥለን ይጠቅማል ብለን የምራባዊያንን ባህል ተቀብለን፣ የኛን በትክክል ሳንተገብረው ምዕተ አመታትን አሳለፍን::
ይህ ልማዳችን ደግሞ ሁሌም የማይላቀቀንና በምርጫ ወቅት የምንወዛገብባቸውንና ግጭት የምንፈጥርባቸውን የራሳችን ጉዳዮች በስርዓት የመፍታቱ ልምድ ስለሌለን እኛም ይገጥመን ይሆን እንዴ ብለን መስጋታችን ነው:: በእርግጥም አሁን አገራችን ካለችበት ዘርፈ ብዙ ችግርና የተለያየ ፅንፍ የያዙ የፖለቲካ ሃይሎች መበራከት ጋር ተያይዞ መስጋታችን አይገርምም::
ነገር ግን እዚህ ጋ አንድ እውነት አለ:: ይህቺ አገር ኩሩ ህዝብ አላት:: በአገሩ ጉዳይ የማይደራደር የአገሩን ህልውና እንዴት መጠበቅና በምን መልክ ማፅናት እንዳለበት ጥልቅ የሆነ እውቀት ያለው ኩሩ ህዝብ ነው:: አትስጋ፤ አንተ አገርህን ወደህ በእስዋ ውስጥ ሰላምዋን በመጠበቅና ሰላማዊ የሆነ እቅድህን ብቻ ተግብር::
የፖለቲካ ፓርዎች አሻጋሪና አሸናፊ ሊያደርገኝ የሚችለውን የትኛውን ሀሳብ እንካ ብዬ ህዝቡን ልምራ እያሉ በምርጫ ሰሞን ጭንቅ ጥብብ ማለት ሲገባቸው በተቃራኒው እኛ ይሄ ምርጫ ምን ይዞብን ይመጣ ይሆን እያልን እንሰጋለን:: እንደው አለመታደል ሆኖ እንጂ ህዝብ ሳይሆን ህዝብን እንምራ የሚሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ነበሩ በዚህ ሂደት ሊጨነቁ የሚገባቸው:: ህዝቤ ያምንብኝ ይሆን? ያነሳሁት ሀሳብ ምን ያህል ተቀባይነት አግኝቶ ለድል ያበቃኝ ይሆን እያሉ ማሰብየነበረባቸው እነሱ ነበሩ::
አንዳንዴ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚራወጡ ፖለቲካ ነክ ቀልዶች ትኩረቴን ይስቡታል:: ፖለቲካን ቀለል አድርገን አይተን ፖለቲከኞቻችን የሚመሩትን ስርዓት በሀላፊነት እንዲወጡ ብቻ ስልጣኑን ለእነሱ ብንሰጥ ብዬ አስባለሁ::
ሰሞኑን ከምርጫ ጋር ተያይዞ ብዙ ቀልዶች ተነስተዋል:: በተለይ የፖለቲካ ፓርቲዎች በቅድመ ምርጫው ያደርጉት የነበረውን የምርጫ ቅስቀሳ በተመለከተ ያነሱት ሀሳብ ተነስቶ ብዙ ተቀልዷል:: እያልኩ ያለሁት ግለሰቦችን የማይጎዱትን፣ ሀሳባቸውን ብቻ ነጥሎ ስህተታቸውን ለማመላከት የሚረዱትን ቀልዶች ነው::
እነዚህን ቀልዶች ስመለከት የምሬን አንድ ነገር ተመኘሁ:: ፖለቲካን ሳናከብደው በስርዓት የሚመራበትና እኛም ከስሜት ወጥተን በትልልቅ ሀሳቦች ላይ ብቻ ትኩረት አድርገን የተሻለ ሃሳብ የምንመርጥበት ልክ እንደ ማህበራዊ ሚዲያው የማናቀልበት ጊዜ ናፈቀኝ:: በእርግጥ በአገሬ ህዝብ እተማመናለሁና ይሄን አያለሁ::
ለማንኛውም በዘንድሮው ምርጫ ኢትዮጵያዊያን ህጋዊ መሰረት ያለውና የፍቃዳቸውን ልኬት የሚያሳየውን እንደራሴያቸውን መርጠዋል:: ብዙዎቻችን ተያይዞ ምን ይመጣ ይሆን? ያልነው ምርጫ አሳታፊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተጠናቋል::
እናም ከምርጫ በኋላ እያልክ ምርጫውን ስትጠብቅ የነበርከው ወዳጄ ወደ ተግባር ግባ:: እስከ አሁን ያረከው ነገር ከአሁን በኋላም እንዳይለምድህ ብዬሃለሁ:: ምርጫ ሰላማዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፉክክርና ይህችን ታላቅ አገር በታላቅ ሀሳባቸው ሊመሩት ለፈለጉት ህዝብ ራሳቸውን የሚያቀርቡበት መድረክ ብቻ መሆኑን እንመን::
የኢትዮጵያን ሀያልነት የዘነጋኸው፣ ህዝብዋም ስለአገሩ ያለውን ጥልቅ ፍቅር ያልተረዳኸው፣ ምርጫ ፈርተህ አልያም ደግሞ ምን ይፈጠር ይሆን ብለህ በፍርሃት ተሸብበህ የቆየኸው ወዳጄ ሆይ ኢትዮጵያዊያን ለሚፈልጉትና ላመኑበት ጉዳይ ስርዓት ባለው መልኩ ይሁንታቸውን ሰጥተዋል:: ሀሳብ አይግባህ:: የወትሮ ተግባርህን ቀጥል:: ቀጠሮህን ፈፅም::
በነገራችን ላይ እኔም አገራዊ ሀላፊነቴን መወጣት አለብኝ፣ ለአገሬና ለህዝቤ ይህ ፓርቲ ቢመረጥ መልካም ነው ያልኩትን ለመምረጥ ምርጫ ጣቢያ ተገኝቼ ነበርና በህዝቡ ተገርሜያለሁ:: ህዝቡ እጅግ ስርዓት ባለው መንገድ ይሆነኛል ለሚለው ፓርቲ ረጃጅም ሰልፎችን ታግሶና ጠብቆ ሲመርጥ ሲታይ ለለውጥ ያለው ጉጉት ትረዳለህ::
አሁን ደግሞ ወደ አንድ ጉዳይ ማተኮር ይገባል:: የሚያሸንፉት የፖለቲካ ፓርቲዎች በይፋ ሲታወቁ የተቀበሉትን የህዝብ አደራ ለመወጣት ወደ መዘጋጀት መግባት ይኖርባቸዋል፤ የሚሸነፉት እንድሸነፍ ያደረገን ሀሳባችን በህዝብ ተቀባነት ባለማግኘቱ ነው ብለው ለመጪው ምርጫ መዘጋጀት ብቻ ነው ያለባቸው:: ያሸነፉትም መልካም ምኞታቸውን የሚገልፁበት ጊዜ እየደረሰ ነው:: ይህን የጨዋ መንገድ ደግሞ መመልከት እንናፍቃለን:: ይህን ሁሉ ሊደረግም ሊሆንም ይገባዋል:: ለአገር መፅናት ብለው ሁሉም በጋራ መስራት አለባቸው፤ አገራቸው ስትኖር ብቻ እንዲህ አይነት ሰላማዊ ፉክክር ማድረግ እንደሚችሉ መገንዘብ ይገባቸዋል::
ሁላችንንም የሚያግባባ አንድ ሀሳብ ደግሞ አለ:: ኢትዮጵያ ከሁላችንም ሀሳብ ከእያንዳንዳችን ፍላጎት ከፍ ትላለች:: የሀሳባችን ግዝፈቱ የሚለካው ለእስዋ በሚጠቅምበት ልክ ነው:: ኢትዮጵያን የሚጠቅም ሀሳብ ካሰብን ያ ሀሳብ ትልቅ ነው:: የሀሳቡም ግዝፈት ኢትዮጵያን ነገ በተሻለ ግዝፈት ላይ ሲያስገኛት ደግሞ ዛሬ ያሸነፈውም የተሸነፈውም በእኩል አሸናፊ ይሆናሉ:: ለማንኛውም ወዳጄ ከምርጫ በኋላ ያልከው ጥሩ እቅድ ለአገር ጠቃሚ ከሆነ እንዳትዘናጋ ፤ተግብረው፤አበቃሁ ፤ቸር ይግጠመን::
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሰኔ 17/2013