ኢትዮጵያውያን ምርጫን ሲያስቡ የሚጀምራቸው መጥፎ ጭንቀት አለ፡፡ይህ አይነቱ ጭንቀት ፈረንጆቹ ትራውማ ይሉታል፡፡አንድ ሰው ከዚህ ቀደም አንድ ጉዳት ካጋጠመው ለዚያ ጉዳት ያጋጠመው ጉዳይ በመጣ ቁጥር የሚፈጠር ጭንቀት ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ምርጫም ለብዙ ኢትዮጵያውያን የዚህ አይነት መጥፎ ጭንቀት መንስኤ ነው፡፡ ምርጫ 1997 ብዙ ኢትዮጵያውያን በምርጫ ዙሪያ መጥፎ ጭንቀት (trauma) እንዲይዛቸው አድርጎ ያለፈ የታሪክ አጋጣሚ ነው፡፡
በተለይ ድህረ ምርጫ የተፈጠሩት ሁከቶች እስከ ዛሬም ድረስ ብዙ ኢትዮጵያውያን የማይረሱትን ጠባሳ እንዲፈጠርባቸው ያደረገ ነበር፡፡ ከዚያ ምርጫ በኋላ በነበሩ ሁለት ምርጫዎችም ኢትዮጵያውያን የዚያ ምርጫ ጠባሳ ተጭኗቸው ታይተዋል፡፡በ2002 እና በ2007 በነበሩት ሁለት ምርጫዎች ላይ ገዢው ፓርቲ ለኢትዮጵያውያን የ1997ን ጠባሳ እያሳየ በፍርሀት ውስጥ ሆነው ሰላምን ብቻ እያሰቡ ስለ ለውጥ እንዳያስቡ ያደረገበት ኢ ዴሞክራሲያዊ ምርጫዎች ነበሩ፡፡ የዘንድሮው ምርጫ ግን ከዚህ የተለየ ነበር፡ ፡ኢትዮጵያውያን በመጨረሻ ከ97ቱ ምርጫ ቆፈን መላቀቃቸውን ያሳዩበት እና መጥፎ ጠባሳቸው ያሻረበት መሆኑንም ያሳዩበት ታሪካዊ ምርጫ ነበር፡፡
ኢትዮጵያውያን በመጨረሻ ከፍርሀታቸው ተላቅቀው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማድረግ በሚጥሩበት በዚህ ወቅት ግን ሌላ አዲስ ፍርሀት ሊፈጥሩበት የሚፈልጉ ሀይሎች ከየአቅጣጫው ብቅ ብለው ታይተዋል፡፡እነዚህ ሀይሎች ህዝቡ በፍርሀት ውስጥ ሆኖ እንዲመርጥ ብቻ ሳይሆን በተቻለ መጠን እንዲያውም ምርጫው እንዳይካሄድ ህዝቡም ዴሞክራሲያዊ ልምምድ እንዳያደርግ የሚፈልጉ ነበሩ፡፡ለዚህም በአንድ ጎን እንደ ወዳጅ መካሪ እየሆኑ በሌላ ጎን በስድብ እያጣጣሉ በምርጫው ዙርያ ውዥንብር ለመንዛት ሞክረዋል፡፡እስኪ በዚህ ምርጫ ዙሪያ ሲያሟርቱ ከነበሩ ነገሮች መሀከል የተወሰኑትን እናስታውስ፡፡
የዘንድሮውን ምርጫ በተመለከተ በማስፈራራቱ የመጀመሪያ የሚሆነው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ነው፡፡በቃል አቀባዩ ኔድ ፕራይስ በኩል ከምርጫው ቀደም ብሎ ባወጣው መግለጫ ምርጫው የሚካሄድበት አውድን እጅግ በጣም አስጊ መሆኑን ገልጾ በሌላም በኩል ምርጫውን ቅቡል የማያደርጉ ያላቸውን ብዙ ምክንያቶች ዘርዝሯል፡፡የምርጫው መካሄድ እነዚህን ችግሮች እንደሚያባብስ እና ሀገሪቱን ወደለየለት መሰነጣጠቅ እንደሚመራም ስጋቱን ገልጾ ነበር፡፡ምርጫው ላይ ሁከት መፈጠሩ አይቀርም ብሎ የደመደመው መስሪያ ቤቱ በመግለጫው መንግስት ኢንተርኔትን መዝጋት የለበትም በማለትም አሳስቦ ነበር፡ ፡
እነዚህ የተጠቀሱ ችግሮች ምርጫ አካሂዶ ፤ ህጋዊነት ያለው መንግስት አቋቁሞ ከመፍታት በቀር ሌላ ምን አማራጭ እንዳለ ያልጠቆመው መግለጫው እንዲሁ ምክር የሚመስሉ ብዙ ማስፈራሪያዎችን ዘርዝሮ ነበር ያበቃው፡፡ከመግለጫው ከጥቂት ቀናት በኋላ ግን መንግስት ኢንተርኔት ሳይዘጋ ፤ በምርጫው ዙሪያም በተቃዋሚዎች የከፋ ስሞታ ሳይቀርብ ፤ ህዝብም እነሱ እንደፈሩት ወደለየለት ብጥብጥ ሳይገባ ምርጫው በሰላም ተጠናቅቋል፡፡ምርጫው ከተጠናቀቀ ቀናት ቢያልፉም የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱም ሆነ በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ እስካሁን ወዳጃችን የሚሉት የኢትዮጵያ ህዝብን ሰላማዊ ምርጫ በማከናወን እንኳን ደስ አለህ አላሉትም፡፡
የአውሮፓ ህብረትም እንዲሁ በዚህ ምርጫ ዙሪያ ስህተት ከሰሩት ሀይሎች የሚመደብ ነው፡፡ህብረቱ ምርጫውን ለመታዘብ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በነበረው ውይይት ምርጫውን ለመታዘብ በኢትዮጵያ የቴሌኮም ስርአት ውስጥ የሌለ የኮሚኒኬሽን መሳሪያ እናስገባ ፤ እንዲሁም የምርጫውን ውጤት እኛ ቀድመን እናሳውቅ የሚል ጥያቄ አቅርቦ በኢትዮጵያ መንግስት ውድቅ ከሆነበት በኋላ ምርጫውን አለምአቀፍ ስታንዳርድን የማያሟላ ከደረጃ በታች የሆነ ምርጫ ነው ብሎ በማጣጣል ራሱን ከታዛቢነት አውጥቶ ነበር፡፡ነገር ግን ምርጫው በህብረቱ እንደተገለጸው ከደረጃ በታች ሳይሆን ብዙ ኢትዮጵያውያን በነጻነት የተሳተፉበት እና እስከዛሬ ህብረቱ በኢትዮጵያ ከታዘባቸው የተሻለው ሆኗል፡፡ህብረቱም ዘግይቶም ቢሆን ለምርጫው ታዛቢዎችን መላክ ባለመቻሉ ማዘኑን ገልጿል፡፡
ሌላኛው ማስፈራሪያ ደግሞ ራሳቸውን በኢትዮጵያ ጉዳይ ኤክስፐርት አድርገው ከሾሙ ሰዎች መሀከል አንዱ በሆነው ዊሊያም ዴቪድሰን የተሰጠ ነበር፡፡ ደዴቪድሰን ከምርጫው ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ለዶይቸቨለ በሰጠው አስተያየት ኦነግ ሸኔ በኦሮሚያ የሚካሄደውን ምርጫ እንደሚበጠብጠው ተናግሮ ነበር፡፡Ethiopia’s Oromia region volatile ahead of elections (ከምርጫው በፊት ኦሮሚያ ክልል ያለበት ሁኔታ አስጊ ነው) የሚል የተጋነነ ርእስ በተሰጠው ዘገባ ላይ ዴቪድሰን በኦሮሚያ ክልል የሚካሄደው ምርጫ በኦነግ የተነሳ ብጥብጥ እንደሚጠብቀው ተንብዮ ነበር፡፡ እርግጥ ኦነግ ሸኔ እንደ ሽብር ቡድንነቱ የብጥብጥ ሙከራ ማድረጉ የሚጠበቅ ቢሆንም እንኳ የቡድኑ እንቅስቃሴ ግን በጥቂት የኦሮሚያ አካባቢዎች ብቻ በመሆኑ መላው ኦሮሚያን መበጥበጥ ይችላል ብሎ ማሰብ አይቻልም፡ ፡የሆነ ሆኖ በዘገባው እንደተጋነነው በነዳቪድሰን እንደተተነውም ሳይሆን በኦሮሚያ የተካሄደው ምርጫ በሰላም ተጠናቅቋል፡፡
ዳቪድሰን አክሎም ምርጫው በትግራይም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ያለውን ችግር እንደማይቀርፍ ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና መንግስታቸው የያዙትን አጀንዳ ለማስቀጠል ተጨማሪ 5 አመታት እንደሚሰጣቸው ይናገራል፡፡ኢትዮጵያን አዋቂ ነኝ የሚለው ዴቪድሰን የተጠቀሱት ችግሮች በህዝብ በተመረጠ መንግስት ካልሆነ በማን እና እንዴት እንደሚፈቱ ግን አይገልጽም፡፡ዴቪድሰን ከምርጫው በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰፊ ልዩነት ማሸነፋቸውን ሲያውቅ ግን ለአልጀዚራ በሰጠው አስተያየት አሁን የተወሰነ ተስፋ ማድረግ እንደሚቻል ተናግሯል፡፡ እንደተለመደው የኢትዮጵያ ችግሮች ናቸው ያላቸውን ከዘረዘረ በኋላም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ብሄራዊ እርቅ ሊጠሩ እንደሚችሉም ትንበያውን አስቀምጧል፡፡
አሌክስ ደዋል በኢትዮጵያ ጉዳይ ሊቅ ነኝ ከሚሉት ሰዎች መሀከል አንዱ ነው፡፡ እሱም ከምርጫው ቀን ቀደም ብሎ ለኤን ፒ አር በሰጠው አስተያየት ኢትዮጵያውያን ወደ ምርጫ ጣቢያ የሚሄዱት ሀገራቸው በእርግጥ በቀጣይ ጊዜያት አንድ ሆና ትሰንብት ወይስ ትፈርስ ይሆን የሚል ጭንቀት በውስጣቸው እየተመላለሰ ነው ብሏል፡፡በእውነቱ ኢትዮጵያን አውቃለሁ የሚል ሰው በምርጫው አለት ኢትዮጵያውያን አእምሮ ውስጥ ከሀገራቸው ህልውና ይልቅ በቀጣዩ አመት ምክር ቤቱ ምን አይነት መልክ ሊኖረው ይችላል የሚለው ሀሳብ ጎልቶ እንደነበር መገመት ይችላል፡፡ በዴንማርኩ የሮስኪልድ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጉዳዮች ምሁሩ ቶቢያስ ሀግማን በበኩሉ ብዙ ኢትዮጵያውያን የምርጫውን ውጤት እንደማይቀበሉት ለኤን ፒ አር በሰጠው አስተያየት ተናግሮ ነበር፡፡በእለቱ እንደታየው ግን ኢትዮጵያውያን መራጮች ብቻ ሳይሆኑ በምርጫው ላይ የተወዳደሩ ፓርቲዎችም ምርጫው እስከዛሬ ከተደረጉት ሁሉ ለመታመን የቀረበው እንደሆነ ሲናገሩ ተሰምተዋል፡፡ እንግዲህ ኢትዮጵያን እናውቃታለን የሚሉት ምሁራን በኢትዮጵያ ጉዳይ እንዲህ አይነት ስህተቶችን ሲሰሩ ነው የከረሙት፡፡
የኢትዮጵያን ምርጫ በተመለከተ ከተሰሩት ቅድመ ምርጫ ትንበያዎች ግን ዋናው ኢትዮጵያውያን ከምርጫው በኋላ ወደ ብጥብጥ ይገባሉ የሚለው ሲሆን በዚህ ይህ ግምት ሙሉ ለሙሉ ከሽፏል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ከምርጫው ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ባሰሙት ንግግር ብዙዎች ኢትዮጵያውያን ይበጣበጣሉ ብለው ይጠብቁናል፡፡እኛ ግን ትምህርት እናስተምራቸዋለን ብለው የተናገሩ ሲሆን በእርግጥም በዚህ ምርጫ ኢትዮጵያውያን እንዲህ በቀላሉ የማይተነበዩ ህዝቦች መሆናቸውን አሳይተዋል፡፡
ስለ ዘንድሮው ምርጫ ከተሳሳቱት መሀከል ግን ዋነኞቹ የውጭ ዜጎች ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያኑም ዋነኞች ናቸው፡፡ለምሳሌ ያህል አልጀዚራ ላይ አስተያየታቸውን ያሰፈሩት አወል አሎ እና ፌቨን ግርማይን መጥቀስ እንችላለን፡፡ሁለቱ ግለሰቦች የዘንድሮው ምርጫ ለምን መካሄድ እንደማይገባው ባሰፈሩት ረዥም ሀተታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምርጫውን ከአምና ወደ ዘንድሮ ያሻገሩት ማሸነፍ እንደማይችሉ ስላወቁ ነው ያሉ ሲሆን፤ የዘንድሮውን ምርጫ ለማካሄድም ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ ዝግጅቱም አቅሙም የለውም ብለዋል፡፡በዚህም የተነሳ የዘንድሮው ምርጫ ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት ሁሉ የበለጠ የተበላሸ ይሆናል ብለዋል፡፡ይህ ምርጫ መካሄዱ ሀገሪቱን ወደለየለት ቀውስ ውስጥ እንድትገባ እንደሚደርግም አስጠንቅቀዋል፡፡ይሁንና ከዚህ ቀደም ከነበሩት ምርጫዎች ሁሉ የተበላሸ ይሆናል የተባለው ምርጫ እስካሁን ከተካሄዱት ሁሉ የተሻለው እንደሆነ ተረጋግጧል፡፡ ምርጫው ለሌላ አዲስ ሁከት መነሻም አልሆነም፡፡ እንዲያውም በተቃራኒው ኢትዮጵያውያን አንድ ትልቅ የቤት ስራ ሰርተው እንደጨረሱ እንደተሰማቸው ከሚታየው እና ከሚሰማው ነገር መገመት ይቻላል፡፡ምርጫው እንደጠበቁት ኢትዮጵያውያንን ያስቆጣ ሆኖ ያላገኙት እነ አወል አሁን ፊታቸውን ወደ ምእራቡ አዙረው ምእራባውያን የሆነ ነገር እንዲያደርጉ እየወተወቱ ይገኛሉ፡፡
አሁን ብዙዎች ምርጫውን በተመለከተ የሚሉት ነገር ቢያጡ የትኩረት አቅጣጫቸውን ከምርጫው ወደ ሀገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ ሆኗል፡፡ ነገር ግን በምርጫው ዙሪያ ሁሉም የተሳሳቱትን ስህተት ልብ ብሎ ለሚያስተውል ሰው በእርግጥ እነዚህ ሀይሎች ስለ ኢትዮጵያ ሰላምስ ቢሆን ትክክለኛ ግንዛቤ አላቸው ወይ የሚል ጥያቄ እንዲያነሳ ያደርጋል፡፡እስካሁን ያለው ሁኔታ እንደሚያሳው በተለይ ምእራባውያኑ በምርጫው ላይ የተሳሳቱትን አይነት ስህተት በጸጥታውም ዙሪያ እየደገሙት እንደሆነ ነው፡፡ ምእራባውያኑ የኢትዮጵያን የጸጥታ ተግዳሮቶች የሚያዩት ከሽብር ቡድኑ ህወሓት በተዋሱት መነጽር ይመስላል፡፡ ጆሮዎቻቸውም ህወሓት በሚከፍላቸው ሎቢስቶች ውትወታ የደነዘዘ ይመስላል፡ ፡ሰሞኑን የምእራቡ አለም ሚዲያዎች የኢትዮጵያ ምርጫን በተመለከተ በሚሰሯቸው ዘገባዎች ላይ የሚታየው ሁኔታም ይህን ያመላክታል፡፡
ከምርጫው የጠበቁትን አይነት ሁከት እና የስልጣን ሽኩቻ ያጡት ሚዲያዎቻቸው ስለ ምርጫው በሚያቀርቧቸው ዘገባዎች ላይ ሀገሪቱ በሁሉም አቅጣጫ በጦርነት እንደተዋጠች እና ህዝብ በሰሜንም በደቡብም እየሞተ እንደሆነ ፤ ረሀብም እንደተስፋፋ በሰፊው ሲያትቱ ከርመዋል፡፡ ዘገባዎቹ በአብዛኛው በአንድ አላማ ላይ ያጠነጠኑ ናቸው፡፡ይህ አላማም ምርጫውን ማጣጣል ነው፡፡ለምን ምርጫውን ማጣጣል መረጡ ? የዴሞክራሲዊ ስርአት ጠበቃ ነን የሚሉት ሀይሎች ስለምን ምርጫ መካሄዱን አልወደዱትም? የሚለው ብዙ የሚያስብል ስለሆነ ለሌላ ጊዜ እናቆየውና በምርጫ ዘገባዎቻቸው ላይ በሚደነጉሩት የጦርነት እና የረሀብ ዘገባ ውስጥ ግን ብዙ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት እና የህዝቦቿን ማንነት የሚጋፉ መሰረታዊ ሀቁን የካዱ ሀተታዎች በብዛት ይገኛሉ፡፡እነዚህን መስመር የሳቱ መረጃዎች ከየት ነው የሚያገኟቸው ከተባለ ደግሞ ምንጩ ከአሸባሪው ህወሓት እና መፍቀሬ ህወሓት ከሆኑ ሀይሎች ነው፡፡እነዚህ ሀይሎች ፍላጎታቸው ደግሞ ግልጽ ነው፡፡
የሆነ ሆኖ በአውሮፓ ህብረት” ከደረጃ በታች” የተባለው ፤ በአሜሪካ መንግስት ”በአስጊ ሁኔታ ውስጥ የሚካሄድ” ተብሎ የተሰየመው ፤እነ ዊሊያም ዴቪድሰን “ኦነግ ይበጠብጠዋል” ብለው የተነበዩበት ፤ እነ አሌክስ ደዋል “ኢትዮጵያውያን በጭንቀት ውስጥ ሆነው የሚመርጡት ነው” የተባለው ፤ እነ ፕሮፌሰር ቶቢያስ “ህዝብ አይቀበለውም” ብለው የደመደሙበት እንዲሁም እነ አወል አሎ “ከዚህ ቀደም ከነበሩት ምርጫዎች ሁሉ የበለጠ የተበላሸው ነው” ያሉት ምርጫ በሰላም ተጠናቅቋል፡፡ኢትዮጵያውያንም ፓርቲ ወይም ግለሰብ ሳይሆን “ሀገራችን አሸነፈች” ብለው ተደስተዋል፡ ፡ትንበያቸው የከሸፈው ሀይሎች አሁን ዝምታን መርጠዋል፡፡ከምርጫው በፊት የኢትዮጵያ ምርጫን ችግሮች በተመለከተ ብዙ ሀተታ ሲሰጡ የከረሙት ሚዲያዎች እና ምሁራን አሁን የኢትዮጵያ ምርጫ በሰላም ሲያልቅ ግን አንድም የረባ ዘገባ ለመስራት አልመረጡም፡ ፡ለምን ምናልባትም ለዚህ ስላልተዘጋጁ ሊሆን ይችላል ፤ ወይም ስለ ኢትዮጵያ ጦርነት እንጂ ስለ ኢትዮጵያ ሰላም ትንታኔ የሚሰጥ ምሁር ስለሌለ ሊሆን ይችላል ፤ አልያም ደግሞ ስለ ምርጫው ሰላማዊነት መዘገብ ለምርጫው እውቅና መስጠት ይሆንብናል ብለው ሊሆን ይችላል፡፡
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ሰኔ 17/2013