መሪዎቻቸውን ለመምረጥ ከትናንት በስቲያ በየምርጫ ጣቢያዎቹ የተገኙ ኢትዮጵያውያንን ለተመለከተ ሰው በቤቱ የቀረ አይመስልም:: ዜጎች ሰማይና ምድር ሳይላቀቅ በፊት ነው ምርጫ ጣቢያ የተገኙት:: ዘንድሮስ ማንም አይቀድመኝም ብለው በጨለማ የወጡትም በበርካቶች ተቀድመዋል ::
መራጮች ድምጻቸውን ለመስጠት ሰአታትን ጠብቀዋል፤ ወገባቸው እስከሚንቀጠቀጥ፣ እግራቸው እስከሚዝል ቆመዋል፤ ለጸሀይ አልተበገሩም፤ ምሽት አላሸነፋቸውም፤ ለብርድና ቁር እጅ አልሰጡም:: እናቶችና አባቶች አሁንስ ደከመኝ ብለው ወደ ቤታቸው አልተመለሱም:: የልባቸውን አድርሰው ተመስጌን ብለው እንጂ:: በዚህ ቀን ትእግስትና ጽናት ደምቀው ታይተዋል::
ይህን እውነታ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ጭምር መስክረውታል:: መገናኛ ብዙሃኑ ያው የኢትዮጵያ ነገር ባይጥማቸውም ፣ ክፉ ክፉን እየጎተቱ በዘገባቸው እያካተቱም ቢሆን ይህን እውነታ እየተናነቃቸውም ቢሆን ዘግበውታል::
የአልጀዚራ ሪፖርተር መሀመድ አዶው ከአዲስ አበባ ሆኖ በርካታ ኢትዮጵያውያን ምርጫ ጣቢያ የተገኙት በጣም በማለዳ መሆኑን ዘግቦ፣ ድምጽ ሰጪዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስካቸውን አድርገው፣ ብርድ መቋቋም የሚያስችሏቸውን አልባሳት ደራርበው ምርጫ ጣቢያ ተገኝተዋል ሲል ሁኔታውን ገልጾታል::
መራጮች በነቂስ ወጥተው ይወክሉናል ያሏቸውን መሪዎች መምረጣቸውን በአዲስ አበባ ዞር ዞር ያለ ኢትዮጵያዊም ሆነ የውጭ ዜጋ ሊያረጋግጥ የሚችለው ሀቅ ነው:: የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ነዋሪዎቹን ተጠምቶ ጭው ብሎ ውሏል:: ውርውር ከሚሉ መኪኖች በቀር ያ የትራፊክ መጨናነቅ ፈጽሞ አልነበረም::
ሁኔታው መላ አዲስ አበቤ በአለቱ ከምርጫ ውጪ ሌላ አጀንዳ አልነበረውም ያሰኛል:: በድምጽ መስጠቱም የሚገርም ፅናት ታይቷል። እለቱ በታሪክ ማህደር በታላቅ አድናቆት መዘከር ይኖርበታል። ህዝቡ ድምጽ በመስጠቱ ብቻ መርካቱን ከጽናቱ መረዳት ይቻላል:: ዜጎች የተጎናጸፉትን ዲሞክራሲያዊ መብት ለመጠቀም ያሳዩት ቁርጠኝነት በራሱ ይደንቃል።
ይህ የአላማ ጽናት በምርጫ 97 ብልጭ ብሎ ጠፍቶ ነበር፤ ህዝቡ ያኔ ድምጹ ስለተሰረቀበት ባለፉት የይስሙላ ምርጫዎች በግድ እንጂ ወዶ ድምጽ አልሰጠም:: ችግሩ ትቶት ያለፈው ጠባሳ ሰዎች ሁለተኛ የምርጫ ካርድ ለማውጣት መነሳሳት እንዳይኖራቸው አድርጎ ነው ያለፈው:: የዘንድሮው ምርጫ ያ ጽናት መልሶ እንዲመጣ ማድረግ የተቻለበት ሊባል ይችላል::
እዚህ ላይ ቆሜ ቀጣዩ የምርጫ ሂደት ደግሞ ታሰበኝ፤ ምርጫ ሂደት ነዋ፤ ቀጣዩ ሂደት ከምርጫ ውጤት ጋር የተያያዘው ነው:: እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን ብለን የህዳሴ ግድብን እየገነባን እንዳለን ሁሉ ምርጫውንም እንደጀመርነው አሳምረን እንድንጨርሰው በዚህ የምርጫ ሂደት ብዙ ማድረግ እንደሚጠበቅብን ታሰበኝ።
ከትናንት ጧት ጀምሮ የምርጫው ውጤት በምርጫ ጣቢያ ደረጃ እየተገለጸ ነው:: አጠቃላይ የምርጫው ውጤት በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ብቻ ነው የሚገለጸው:: ህዝቡ መጠበቅ ያለበትም የቦርዱን መረጃ ነው።
ዜጎች ድምጻቸውን ሰጡ ወይም የፈለጉትን የፖለቲካ ፓርቲ መረጡ ማለት የምርጫው ሂደት ተጠናቀቀ ማለት አይደለም:: ድምጹ ተቆጥሮ አሸናፊው ተለይቶ መንግስት የሚመሰርተው አካል እስኪለይ ድረስም ሌላ ሂደት አለ።
የምርጫ ውድድር ያው የፖለቲካ ጨዋታ ነው:: ጨዋታ ወይም ውድድር ህግ እንዳለው እናውቃለን፤ ውድድሩ እንደ እስከ አሁኑ ሁሉ በህግ አግባብ ይፈጸማል ተብሎ ይጠበቃል::
የፖለቲካ ጨዋታ ያልኩት የልጅነት ጨዋታችንን አስታወሰኝ:: ጎበዝ ጨዋታ ጨዋታ ብቻ አይደለም ለካ:: የልጅነት ጨዋታ ከቦታ ቦታ ሊለያይ ይችላል:: አላማው ግን ዞሮ ዞሮ አንድ ነው:: በጨዋታ በጨዋታ እያደረጉ መዝናናት ፣ማስተማር::
ያኔ ልጅ እያለን ነው ብያለሁ፤ ልጅ እያለን ስልም አብረውኝ ይጫወቱ የነበሩትንም እያሰብኩ ነው:: አሁን እድሜያችን ወደ ሰላሳዎቹ ገብቷል። ያኔ በርካታ “የልጅነት ጨዋታዎች” ነበሩ። ጨዋታዎቹ አሁንም ድረስ በትዝታ ወደኋላ ይመልሱናል፤ የትውስታ ማህደራችንን ይቆሰቁሳሉ።
ዲሞክራሲያዊነት፣ ፍትሃዊነት፣ ታማኝነት እንዲሁም የሰለጠነ ውድድር የሚሉት ጉዳዮች በአእምሮዬ አሁንም አሁንም ብቅ ቢሉብኝ ወደ ልጅነት ጨዋታችን ተመለስኩ። ኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲንና ፍትሃዊነትን የተማርነው በልጅነት ጨዋታዎቻችን ነው እኮ፤ ግን ስንቶቻችን ይህን እንገነዘብ ይሆን?
ምእራባውያኑ ባስቀመጧቸው ሰብአዊ፣ ዲሞክራሲያዊ፣ ቅብርጥሶ በሚሉ መለኪያዎች ሳይሆን በልጅነት ጨዋታዎቻችን ላይ ተመስርተን ነው እነዚህን ጉዳዮች ማወቅ የጀመርነው። በየአካባቢያችን ሜዳዎች ስንሰባሰብ ዘር፣ ፆታ ቀለም አጭር፣ ረጅም የሚል መስፈርት አልነበረም:: እነዚህን ነገሮች በእነዚህ ሜዳዎች ውስጥ ብትፈልጉም አታገኟቸውም። ሁሉም ልጆች ለጨዋታው ለወጡ ህጎች ራሳቸውን ያስገዛሉ። ዳኛ መርጠው ጨዋታውን ያካሂዳሉ። በሜዳዎቹ ላይ በጨዋታዎቹ አማካኝነት ቦርቀን፣ ተጫውተን፣ ተጣልተንና ታርቀን እንለያያለን። በቃ።
ለምሳሌ “እዝዝሎሽ” የሚለው ጨዋታ ምን ያህል ዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ እንደሆነ ተጫውታችሁ ያደጋችሁ ታውቁታላችሁ:: በጨዋታው ሁለት ተወዳዳሪዎች ጠፍጣፋ ድንጋዮችን ይይዛሉ። አንዱ አስቀድሞ ድንጋዩን ወደ ሜዳው ይወረውራል፤ ሌላኛው ተጫዋች የተወረወረውን ድንጋይ መምታት ትችላለህ ወይ ብሎ ይጠይቀዋል:: አዎን ብሎ ወርውሮ ከመታ የመጀመሪያው ወርዋሪ ተሸንፏልና ሁለተኛውን አዝሎ ድንጋዩ ያለበት ቦታ ያደርሳል፤ ድንጋዩን መምታት ካልቻለ ደግሞ ሁለተኛው ወርዋሪ የመጀመሪያውን አዝሎ ድንጋዮቹ ዘንድ ማድረስ ይኖርበታል፤ ይህ ህግ ነው። ማንም የማይሽረው። ሁሉም ይህን አውቀው ነው ወደ ጨዋታው የሚገቡት:: እዚህ ላይ ማፈር አይሰራም።
በብይና ጠጠር ጨዋታም እንደዚያው ነው። ጎበዙ ካሸነፈ ተሸናፊው በህጉ መሰረት ብይና ጠጠሮቹን ያስረክባል። እዚህም እፍረት የሚባል የለም። አንዳንድ ጊዜ የሚያፍሩ ያጋጥሙናግጭት ይከሰታል። ይሄኔ ደግሞ አንዱ መሀል ይገባል፤ ዳኛ ሆኖ ፍትሃዊ ፍርድ ይሰጣል። እናም ከልጅነት ጨዋታዎቻችን ዲሞክራሲን፣ ፍትህን፣ እኩልነትን፣ ውጤትን በፀጋ መቀበልን እንዲሁም ሁሉም አይነት ሰብአዊነትን እየተገነዘብን አድገናል።
ኢትዮጵያውያን “በምርጫ ወቅት” ሩቅ ሄደን ውጤት በፀጋ መቀበልን፤ በፈለግነው መድረክ ላይ የወደድነውን ዲሞክራሲያዊ ጨዋታ መጫወትን ከምእራባዊያን ለመቃረም መቦዘን የለብንም። የመጣንበትን ህይወት ፣ በልጅነት ጨዋታ ጭምር ያሳለፍናቸውን ልምዶቻችን ማስታወስ ይኖርብናል::
በተለይ መፍትሄ አፍላቂ ነን ብለው በፖለቲካ ጨዋታችን ውስጥ እጃቸውን የሚሰዱትን የውጪ ሀይሎች ገለል ለማድረግ ልምዶቻችንን መጠቀም ላይ ማተኮር ይኖርብናል:: እነዚህ ሀይሎች አስታርቁ ሲባሉ እድሜ ልክ የምንጣላበትን ተክለው የሚሄዱ ናቸው፤ በሀገርኛ መፍትሄ ችግራችንን መፍታት ላይ ማተኮር አለብን።
እንደጠቀስነው ዲሞክራሲ ለእኛ አዲስ አይደለም፤ አብሮን የኖረ ባህላችን ነው፤ ኢትዮጵያውያን የዲሞክራሲን መንገድ ከልጅነታቸው ጀምሮ በጨዋታዎቻቸው ያውቁታል። የውጭ ልምድ ስንቃርም የኛን አግልለን እንጂ ተወዳድሮ ማሸነፍና ሂደቱን በፀጋ መቀበል የኛ የራሳችን ባህል ነው። ዴሞክራሲ እርስ በእርስ እየተገራን ያደግንበት ነው:: በዚህ መንገድ ተገርተን ስላደግን ስናሸንፍ ስንሸነፍ የምናረገውንና የሚደርስብንን እናውቃለን:: ስናሸንፍ እንቦርቃለን፤ ስንሸነፍ ስለቀጣዩ ጨዋታ እንጂ የምናስበው ስለሌላ ጥፋት አይደለም:: ስንሸነፍ አናፍርም::
አሁንም ይሄን ባህላችንን ልምዳችንን መጠቀም ይኖርብናል። መሪዎቻችንን አደባባይ ወጥተን መርጠናል። ቀጣዩ ሃላፊነት ደግሞ ውጤቱን በፀጋ መቀበል፤ የህዝብን ድምፅ ማክበር መሆን ይኖርበታል። “በእዝዝሎሽ” ጨዋታ በልጅነታችን አሸናፊውን በጀርባችን ላይ እንደምንሸከመው ሁሉ ህዝብ ይሁንታ የሰጠውን የፖለቲካ ፓርቲ ያለምንም ማቅማማት መንግስት እንዲመሰርት ማገዝ ይኖርብናል። ብቻ እንዳናፍር እላለሁ። ሲሸነፉ ውጤትን ከመቀበል ይልቅ ማቅማማት ውስጥ መግባት እፍርታም ያሰኛል:: እፍርታም ሲፈጠር እስከ አሁን በመጣንበት የጨዋታ ህግ መሰረት ማረም ፣ መቅጣትም ያስፈልጋል። ሰላም!!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሰኔ 16/2013