በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ምርጫ 2013 እነሆ ተጠናቀቀ፡፡ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ሆነው ታሪክ ሰሩ፡፡ ከተራራው ማማ ላይም ወጡ፡፡ ዛሬ እገሌና ታሪክ ሰሪ እገሌ ነው ተወቃሽ የሚባለው ፓርቲም ሆነ ግለሰብ የለም ፤ሁሉም በሚችለው ልክ ለሀገሩ አንድነትና ዴሞክራሲ የበኩሉን ጠጠር ጥሏል፡፡ ብዙዎች ሲያሟርቱበት የነበረው ምርጫ 2013 ያለምንም ኮሽታ ተጠናቋል፡፡ኢትዮጵያውያን ጠላቶቻቸውን አሳፍረዋል፤ወዳጆቻቸውን አኩርተዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ታሪክ እንደሚሰሩም አንዱ ማሳያ ሆኗል፡፡ዛሬ ኢትዮጵያ መሪዎች ተለውጠው እውነተኛ ምርጫ ለማድረግ ተነስተዋል።የትናንቱን ከዛሬ ጋር ስናስተያየው በምርጫ ስም ምን ያህል ሲቀለድብን እንደኖርን የገባኝ ዛሬ ነው፡፡ሀገራችን ኢትዮጵያ ለዘመናት በዚህ እርባና ቢስ ስርዐት ውስጥ ያለፈች ናት፡፡ በዚህም ብዙ ነገራችንን አጥተናል፡፡ ህዝብ ባልቀደመበት፣ ቅድሚያ ለሀገር የሚል እሳቤ ባልተፈጠረበት ሀገርና ህዝብ ውስጥ የሚመጣ ነውጥ እንጂ ለውጥ የለም፡፡ምርጫዎቻችን የጨረባ ተስካር የሚል ስም የሚሠጣቸውን የአንድ ፓርቲ ማዳመቂያዎች ሆነው አልፈዋል፡፡
ስልጣን ለመያዝም ሆነ በስልጣን ለመቆየት የህዝቦች የበላይነት የተረጋገጠበት አብላጫ ድምጽ ያስፈልጋል፡፡ ሀገር በመረጠችው ስትመራና አጭበርብሮ ስልጣን በያዘ ስትመራ አንድ አይነት አይደለም፡፡ ሀገር በመረጠችው ስትመራ መሪና ተመሪ እኩል ያስባሉ፡፡ አንድ አይነት ራዕይ ያያሉ፡፡ አንድ አይነት ህልም ይገነባሉ፡፡ አንድ ልብ፣ አንድ ሀሳብ ይሆናሉ፡፡ ሀገር ለመለወጥ በሚደረገው ማንኛውም ትግል ውስጥ ከፊት በመሰለፍ አሻራቸውን ያሳርፋሉ፡፡
ሀገር ዋሽቶና አታሎ ስልጣን በያዘ ስትመራ ግን ህዝብና መንግስት ሆድና ጀርባ ነው የሚሆኑት፡፡ ለጋራ ጥቅም በጋራ ከመስራት ይልቅ ተለያይቶ መቆምን የሚመርጡ ይሆናሉ፡፡ ከመነጋገር ይልቅ ለምንም ነገር ሀይልን በመጠቀም የሚፈልጉትን በጉልበት ለማስፈጸም የሚተጉ ይሆናሉ፡፡ ከውይይት ይልቅ ጦርነትን በማስቀደም ሀገርና ህዝብ የሚያውኩ ይወጣቸዋል፡፡ አንዱ በአንዱ ላይ ቂም በመያዝ ከልማት ይልቅ ለጥፋት ይነሳሳሉ፡፡
ለምንም ነገር ህዝብ የስልጣን ባለቤት ነው፡፡ መንግስት በህዝቦች የላቀ ተሳትፎ ካልተመረጠ ትርጉም አይኖረውም፡፡ ባለፈው የኢትዮጵያ የምርጫ ስርዐት ውስጥ መንግስት ለመመስረት ህዝብ ስልጣን አልነበረውም፡፡ መንግስት ራሱን የሚመርጠው ራሱ ነበር፡፡ በዘንድሮው ምርጫ ግን ይሄ ሁሉ የለም፡፡ ስልጣን የህዝብ ነው፡፡ ህዝብ ያልመረጠው ፓርቲ መንግስት እንደማይሆን ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ፓርቲዎች ለሀገር የሚጠቅም ሀሳብ ይዘው በነጻነት ሀሳባቸውን ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡ የተሻለ ሃሳብ ያቀረበ ፓርቲ የህዝብን ቀልብ ስለለሚገዛ የመመረጥ ዕድሉም የሰፋ ነው፡፡
የላቀ አስተሳሰብ በምርጫ ስርዐት ውስጥ የጎላ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ከጥንት እስከዛሬ ኢትዮጵያውያን ሀሳብ አላጣንም፡፡ ያጣንው አድማጭ ነው፡፡ ያጣነው ከእኔነት የወጣ ህዝባዊ አይን ነው፡፡ ይሄ ሁሉ የሀገራችን ድሮአዊ ጋፍ መልክ በመቀየር ላይ ነው፡፡ ህዝብን ያስቀደመ በሀገር ሉአላዊነት ላይ የማይደራደር ትውልድ በመገንባት ላይ እንገኛለን፡፡ ካለፈው ይልቅ የሚመጣው ቀን እጅግ ብሩህ እንደሚሆን የብዙዎቻችን ተስፋ ነው፡፡ ይህ ተስፋችን አብቦ ፍሬውን እናይ ዘንድ የሁላችንም የጋራ ርብርብ ይጠይቃል፡፡
ምርጫው በሰላማዊ መንገድ ተጀምሮ እንደተጠናቀቀ ሁሉ ፍጻሜውን የማሳመር ኃላፊነት የሁላችንም ነው፡፡ የነገዋ ብሩህ ኢትዮጵያ በዚህ የምርጫ ውጤት ላይ የቆመች ናት እላለው፡፡ ብዙ ነገራችን ልክ የሚመጣው የዚህን ምርጫ ውጤት ተከትሎ ነው እላለሁ፡፡ ለሁላችንም የተስፋ ብርሀን በሆነው በዚህ ታሪካዊ ምርጫ ላይ ተሳትፈናልና ውጤቱም የጋራችን ነው፡፡ምርጫው ሀገራችንን የከፍታማማ እንድትወጣ የሚያስችል ነውና ፍሬውንም በጋራ ለመቋደስ እስከ መጨረሻው በጋራ ዘብ መቆም አለብን፡፡ ትናንትና ከምርጫ ጋር ተያይዘው የተነሱ በርካታ ሀገራዊ መከራዎችን አሳልፈናል፡፡ እኔነት በወለደው ልክ በሌለው የስልጣን ጥም በርካታ ህዝባዊ ኪሳራዎች እዛም እዚህም ነበሩ፡፡
ትናንትና በዛ ሰሞን በነበሩ የይስሙላ ምርጫዎች እዚች ሀገር ላይ ምን ያልሆነ አለ? በውሸት ፕሮፓጋንዳ ህዝብን እያታለሉ፣ በእብለት በማስመሰል ሀገርና ህዝብ ሲበደል ኖሯል፡፡ የሀሳብ የበላይነት መክኖ በአንድ ፓርቲ የበላይነት ብዙ ማጭበርበሮች ደርሰዋል፡፡ ትናንትና ለብዙዎቻችን ዘግናኝ ጊዜ ነበር፡፡ ጸዐዳ ቀኖች ናፍቀውን፣ ብሩህ ማለዳዎችን ስንጠብቅ ነበር፡፡ መጪው ጊዜ የኢትዮጵያ የከፍታ ጊዜ ነው፡፡ ይሄ ስለመሆኑ በርካታ አመላካች ምልክቶች በመፈጠር ላይ ናቸው ፡፡በምርጫው ዕለት የነበረው መተሳሰብና መፈቃቀድ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያስደሰተ ነበር፡፡ ይህ ምርጫ የብዙ ነገር መጀመሪያ
ነው፡፡ ከፍታዎቻችን ሁሉ ከዚህ ምርጫ በኋላ የሚመጡ ናቸው፡፡ ዛሬን የመሰሉ በርካታ ነገዎችን ለመፍጠር ፍትህን የሚሻ፣ ሀጢዐትን የሚጸየፍ እውነተኛ ትውልድ ያስፈልጋል፡፡ በሀገር ጉዳይ ላይ ሁላችንም ሀላፊነት አለብን፡፡ ካለእኔና እናተ መንግስት ብቻውን የሚፈጥረው ተዐምር የለም፡፡ የሁላችንም ጥረት ያስፈልጋል፡፡
ትናንት የተሰራው ታሪክ ነገ የሚዘከር ነው፡፡ የሀገራችን አሁናዊ ቁመናን የተበላሹ ትናንትናዊ መልኮቻችንን የሚያሳምር ነው፡፡ ከ37 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ተመዝግቦ አብዛኛው ድምጽ ሲሰጥ ውሏል፡፡ ሀገርና ህዝብ በአንድ ላይ ነጋቸውን ሊጽፉ
ተረባርበዋል፡፡ በዚህ ምርጫ ላይ የብዙዎቻችን ብሩህ ነገ አለ፡፡ በዚህ ታሪካዊ ምርጫ ላይ የብዙዎቻችን ነገ ተስሏል፡፡ ሀገር የዋጁ፣ ትውልድ የቃኙ የብዙዎቻችን መልካም አጋጣሚዎች ከዚህ እውነታ ውስጥ የሚፈልቁ ይመስለኛል፡፡ ምርጫ የመሪንና የተመሪን ተዐማኝነት ይፈልጋል፡፡ ምርጫ ለሀገር በረከት ይዞ የሚመጣው እንዳለፉት ምርጫዎች በውሸት ተለብጦ ሲቀርብ ሳይሆን በሀሳብ ብልጫ ሲቃኝ ብቻ ነው፡፡
ሁላችንም እንደምናውቀው በኢትዮጵያ ታሪክ እስካሁን ድረስ አምስት የሚሆኑ የምርጫ ስርዐቶች ተካሂደዋል፡፡ ምርጫ የሚለውን ስም ይያዙ እንጂ ምርጫ ለመባል ያልደረሱ እንደነበሩ ብዙዎቻችን ምስክሮች ነን፡፡ ከጥፋትና ከውድመት ባለፈ እነኚህ ምርጫዎች በማህበረሰቡ ላይ ያደረሱት ስነ ልቦናዊ ጫናም እንዲህ በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ምርጫው የተጭበረበረና ቀድሞ የተበላ ዕቁብ መሆኑ ሳያንሰው የበርካታ ወጣት ኢትዮጵያውያንንም ደም በከንቱ አፍሶ ያስቀረ ነው፡፡
ለህዝብ ነጻነትን ስለማንሰጥ፣ ፍትሀዊና ተዐማኝነት ያለው ምርጫ አድርገን ስለማናውቅ ሁሌ ምርጫ በመጣ ቁጥር የንጹሀን ደም ሲፈስ ቆይቷል፡፡ ሁሉም ምርጫዎች ከህዝባዊነት ይልቅ አንድን ፓርቲ መሰረት አድርገው ተጀምረው ያለቁ ነበሩ፡፡ ሁሉም የምርጫ ስርዐቶች ከገለልተኝነት ይልቅ በገዢው ፓርቲ ጣልቃ ገብነት ቅሬታ የሚነሳባቸው ሆነው ያለፉ ናቸው፡፡
ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ግን በብዙ ነገሩ ካለፈው የተለየ ነው፡፡ እንዳውም በኢትዮጵያ ታሪክ የምርጫ ህግና ደንብን የተከተለ የመጀመሪያው ሀገራዊ ምርጫ ነው ብል አጋነንክ እንደማትሉኝ ተስፋ አደርጋለው፡፡ እኔን ጨምሮ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ለሀገር ገጽታ ያለውን ፋይዳ በመረዳት ከሌሊቱ ጀምረን በመሰለፍ ሀገራችንን ለማሻገር ብርድና ቁሩ ሳይበግረን ምርጫችንን አከናውነናል፡፡ በብዙዎቻችን ልብ ውስጥ ያለችውን አዲሷን ኢትዮጵያ ለመፍጠር በዝናብ እየተደበደብን ለውዲቷ እናታችን ኢትዮጵያ አሻራችንን አኑረናል፡፡ ያልተወለደችውን ግን ደግሞ በብዙዎቻችን ነፍስ ውስጥ የተጸነሰችውን የጋራ ምድራችንን ለመውለድ አምጠናል፡፡
የኢትዮጵያ ብሩህ ነገዎች ከእንግዲህ የሚፈጠሩ ይመስለኛል፡፡ የምንናፍቃት ሀገራችን ከእንግዲህ የምትነሳ ይመስለኛል፡፡ ጨለማዎቻችንና ኋላ ቀርነታችን በዚህ በያዝነው የምርጫ ሰሞን የሚያበቁ ይመስለኛል፡፡ ከፊታችን ያለው ጊዜ የኢትዮጵያ የድህነትና የኋላ ቀርነት ማብቂያ ይመስለኛል፡፡ የዘመናት ችግሮቻችን በራሳችን የተፈጠሩ ናቸውና ከእንግዲህ ላይደገሙ አሽቀንጥረናቸዋል፡፡ አሁን ላለንበት መጥፎ የህይወት ገጽ ተጠያቂዎች ራሳችን ነንና ምለን ተገዝተን በድምጻችን አዲሲቷን ኢትዮጵያ አምጠን ወልደናል፡፡
ስር በሰደደ ራስ ወዳድነት ከእኛነት ይልቅ እኔነትን አስበልጠን ድሀ መሆናችንን አውቀን ከእኔነት ይልቅ እኔ የሚለውን ለማጽናት ትናንት ማህተማችንን አጽንተናል፡፡ ለስልጣን ካለን ስር የሰደደ ጥማት ሌላውን ገለን ራሳችንን ስናኖር ከርመናልና ይህንን ላይመለስ ቀብረናል፡፡
ከእንግዲህ ይሄ ስም ማብቃት አለበት፡፡ ከእንግዲህ ይሄ መጥፎ ገጽታ መታደስ አለበት፡፡ ከእንግዲህ በአዲስ አስተሳሰብ ለአዲስ ነገር የምንነሳበት የብልጫ ዘመን እንዲሆንልን ሁላችንም መስራት ይኖርብናል፡፡ ሀገር ማለት ህዝብ እንደሆነ መማር አለብን፡፡ ሀገር ማለት እኔና እናንተ እንደሆንን ማወቅ አለብን፡፡ ካለ እኔና እናንተ ሀገር ምንም ናት፡፡ ካለ ሀገርም እኔና እናንተ ምንም ነን፡፡ ለምንም ነገር ህዝብ ይቅደም፡፡ ለምንም ነገር ሀገር እንበል፡፡ ከእንግዲህ ባለው የአብሮነት ጊዜአችን ለሀገራችን ምርጡን በማድረግ ሀላፊነታችንን
እንወጣ፡፡ ከፊታችን ብሩህ ዘመን አለ፡፡ በድምጻችን ያጸናናት አዲስ ሀገር ፈጥረናል፡፡ ብዙዎች እንደምንበታተን መርዶ ሲያሰሙና ሙሾ ሲያወርዱ የከረሙ ቢሆንም ጠላቶቻችንን ኩም አድርገን ወዳጆቻችንን አኩርተናል፡፡ አዲሲቷን ኢትዮጵያም አዋልደናል፡፡ሆኖም መርጠን ወደ ቤት መመለስ ብቻ ሳይሆን ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ቤት መስሪያ የሚሆን ምሰሶና ማገር ማዋጣት አለብን፡፡
ሀገር በአንድና በሁለት ሰው ብርታት አትለወጥም፡፡ ለውጥ የአንድነት ውጤት ነው፡፡ ብልጽግና የብዙ እጆች፣ የብዙ ጭንቅላቶች ቅንጅት ነው፡፡ ለሀገራችን እኔም እናንተም እናስፈልጋታለን፡፡ የሀገርና የህዝብ ለውጥ ከእኔና ከእናንተ አስተሳሰብ የሚጀምር ነው፡፡ የብዙዎቻችን ለውጥ ሀገር ይለውጣል፤ የአንዳንዳችን መዋጮ ለሀገር ካስማ ይሆናል፡፡ በዚህ የህይወት ዘይቤ ውስጥ ልዕልና አለ፡፡ እስከዛሬ ትልቅ ሆነን ትንሽ ሆነን ኖረናል፡፡ ለሀገራችን ማድረግ ያለብንን ሳናደርግ፣ ለራሳችንም ሳንበጅ ቀርተናል፡፡ አሁን ግን በአዲስ ሀይል የምንነሳበት ለሁላችን አዲስ ቀን ነው፡፡
አሁን ላይ የብዙዎቻችን ችግር ውስጣዊ ለውጥ በሌለበት ውጪአዊ ለውጥ ለማምጣት መልፋታችን ነው፡፡ አሁን ላይ ሀገራችንም ሆነች ህዝባችን በአስተሳሰቡ የላቀ ማህበረሰብ የሚፈልጉበት ወቅት ላይ ነው፡፡ የላቀ አስተሳሰብ ሀገር ከምትገነባባቸው ማህበራዊ እሴቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ምርጫውን በድል ብንወጣም ቀጣይ የቤት ስራችን የሀገራችንን ልዕልናና ብልጽግና ማጽናት ይሆናል፡፡ምርጫና የላቀ አስተሳሰብ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡ የዘንድሮው ምርጫ ካለፉት የተሻለ የሚሆነውም ሀገሪቱን ወደላቀ ብልጽግናና ልዕልና ለማሸጋገር መሰረት ሲጥል ነው፡፡
ከፊታችን የሁለተኛው የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ይጠብቀናል፡፡ከፊታችን የአረንጓዴ አሻራ የማኖርና የሀገራችንን ህልውና የመታደግ ከባድ ሃላፊነት ተጥሎብናል፡፡የተጎዱና የተረሱ ወገኖቻችንን ልንንከባከብበት በጎ ፈቃድ ስራዎቻችን እኛኑ ነው የሚጠብቁት፡፡ ስለዚህም ያሰብነውንና ያለምነውን ምርጫ ማካሄዳችን እንዳስመሰገነን ሁሉ በዚሁ ሀገራዊ ስሜት ልማቶቻችንን ማፋጠን ይገባናል፡፡
አበቃሁ፡፡ ቸር ሰንብቱ፡፡
ዘለዓለም የሳጥን ወርቅ (የእፀ ሳቤቅ አባት)
አዲስ ዘመን ሰኔ 16/2013