ከከተሞች መሰረታዊ መገለጫዎች መካከል የጽዳት ጉዳይ አንዱ ነው:: ጽዳቱ ያልተጠበቀ ከተማ ለነዋሪዎቹ የጤና ጠንቅ ከመሆን ባለፈ ለኑሮም ሆነ የአገርን መልካም ገጽታ ጥላሸት ይቀባል፡፡ ከዚህ አንጻር አዲስ አበባ ከተማ ለነዋሪዎቿ ጽዱና ምቹ ትሆን ዘንድ የተለያዩ ጥረቶች ይደረጋሉ:: በእርግጥ እነዚህ ጥረቶች መልካም ውጤቶችን እያስገኙ ቢሆንም አሁንም የከተማዋ ጽዳት ብዙ ትኩረት የሚፈልግና ብዙዎች ኃላፊነታቸውን ሊወጡበት የሚገባ ጉዳይ ነው::
ኢትዮጵያ የአካባቢ ተፈጥሮ ደህንነትን የሚያስጠብቁ ደንቦች፤ ሕጎች እና መመሪያዎችን በዝርዝር ያወጣች ሀገር ብትሆንም የደረቅም ሆነ ፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ጉዳይ ዛሬም አነጋጋሪ ነው። በፋብሪካ አካባቢ የሚገኙ ወንዞች በፍሳሾች መበከላቸው፤ በየቦታው ፕላስቲክን ጨምሮ ሌሎች በካይ ነገሮች መጣላቸው በአካባቢው ተፈጥሮ ላይ ከሚደርሱት ብክለት በተጓዳኝ የጤና ጠንቅም ሆነዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ኤጀንሲ ከመኖሪያ ቤቶች፣ ከተቋማት እና ከልዩ ልዩ ድርጅቶች የሚመነጨውን ደረቅ ቆሻሻ በማሰባሰብ፣ በማጓጓዝና በማስወገድ እንዲሁም በአስፓልት መንገዶች ላይ የሚመነጨውን ደረቅ ቆሻሻ በሰው ኃይልና በዘመናዊ ማሽነሪ ታግዞ በማፅዳት ከተማዋን ፅዱ፣ ውብና ለኑሮ ተመራጭ እንድትሆን የማድረግ ጥረቱ አጠናክሮ ቀጥሏል።
ሆኖም የፅዳት ተግባር በተቋማት ጥረት ብቻ የሚሳካ ባለመሆኑ ሁሉም የበኩሉን ይወጣ ዘንድ ደግሞ ግድ የሚልም ነው። ደረቅ ቆሻሻ በአግባቡ ከተያዘ ሀብት፤ ካልተያዘ ደግሞ የጤና ጠንቅ በመሆኑ ከቤትም ሆነ ከድርጅት የሚመነጩ ደረቅ ቆሻሻዎች አካባቢን ሳይበክሉ መወገዳቸውንም ማረጋገጥ እንደ ዜጋ ከሁላችንም የሚጠበቅ ሀላፊነት ነው::
እኛም የአዲስ አበባ ደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ ከሆኑት ከወይዘሮ ሀይማኖት ዘለቀ ጋር እየተከናወኑ ባሉ ስራዎች ዙሪያ ቃለ ምልልስ አድርገናል::
አዲስ ዘመን፦ ኤጀንሲው ከተማዋን ጽዱና ውብ እንዲሁም ለመኖሪያ ምቹ ከማድረግ አንጻር ምን ምን ተግባራትን አከናወነ?
ወይዘሮ ሀይማኖት፦ ኤጀንሲው የተቋቋመበትም ሆነ በአዋጅ የተሰጠው ተልዕኮ አዲስ አበባን ጽዱ ማድረግ ነው:: በተለይም እንደ ኤጀንሲ ደረቅ ቆሻሻን በማንሳት ረገድ ያለውን ሁኔታ በተገቢው ሁኔታ ከየቤቱ፣ ከተቋማት፣ ከንግድ ድርጀቶች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት፣ ከገበያ ቦታዎችና ከሀይማኖት ተቋማት መሰብሰብ፣ ማጓጓዝ፣ ማስወገድ እንዲሁም መልሶ ጥቅም ላይ መዋል የሚችሉበትን ለማድረግ ሀላፊነታችንን እየተወጣን እንገኛለን::
ዘንድሮ በተለይ ነዋሪውን ያንቀሳቀሱ ሰፋፊ ንቅናቄዎችን በማድረግ በወር ይካሄድ የነበረውን አገር አቀፍ የጽዳት ዘመቻችንን ከታህሳስ ወር ወዲህ ዘመቻውን በየሳምንቱ በማድረግ ስራው ተደራሽ እንዲሁም የአካባቢን ጽዳት በማስጠበቁ በኩል ትልቅ ሚና ያለው እንዲሆን አድርጓል::
በዚህ የጽዳት ዘመቻ ላይ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤን ጨምሮ ሌሎች የስራ ሃላፊዎች፣ የከተማዋ የካቢኔ አባላት፣ የቢሮ ሃላፊዎች፣ የብልጽግና ፓርቲ አስተባባሪዎችና ሌሎችም በየደረጃው ያሉ አመራሮች የተሳተፉበት ነበር:: ይህ የሆነበት ዋነኛ ምክንያት ደግሞ እነዚህ ሰዎች ህዝብ ጋር ሲደርሱ የማንቀሳቀስ ሀይላቸው የተሰሚነት መጠናቸው በቀላሉ የሚታይ ባለመሆኑ ራሳቸው በአርአያነት የጽዳት ስራውን እየመሩ ሌላውን እንዲያንቀሳቅሱ ነው::
በሌላ በኩልም የኪነጥበብ ሰዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የስፖርት ቤተሰቦችና በተለያየ ምክንያት ህብረተሰቡ የሚያደምጣቸውና የሚሰማቸውን ግለሰቦች በሙሉ በመምረጥ የጽዳት አምባሳደር አድርገን በመሰየም በእነሱ ጭምር ነው ስራዎች እየተሰሩ የነበረው:: በዚህም አዲስ አበባ ውስጥ ኤጀንሲው ባለው መረጃ መሰረት ስድስት ሺ 885 ብሎክ አለ፤ በየብሎኩ እነዚህ የጽዳት አምባሳደሮችና አመራሮቻችን አርዓያ ሆነው እንዲያጸዱ በማድረግ በተለይም ባለፉት ሶስት ወራት ከተማዋ ላይ በጽዳቱ ዘርፍ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ መጥቷል ::
የዚህ ማሳያው ደግሞ በየአንዳንዱ ቀን 3ሺ ቶን ያህል ቆሻሻ ይወገዳል:: ይህንን ቆሻሻ ለመሰብሰብም የወጣው ህዝብ ቁጥር ስድስት ነጥብ ስምንት ሚሊየን ህዝብ ይሆናል:: በ11 ክፍለ ከተሞችና በ125 በየሳምንቱ 150ሺ ሕዝብ ወረዳዎች ወጥቶ አጽድቷል የሚል መረጃ ነው ያለን፡፡ ይህ ደግሞ የሚያሳየው እንቅስቃሴው የተሻለ መሆኑን ነው :: ይህንን የኤጀንሲውን ጥረት ደግሞ የከተማዋ ነዋሪም መገናኛ ብዙኃንም እየመሰከሩ ከመሆኑም በላይ የሚታይና ተጨባጭ ስራ ተሰርቷል ብሎ መውሰድ ይቻላል::
አዲስ ዘመን ፦ እንደ ሞዴል ሊነሳ የሚችል ስራ ካለ?
ወይዘሮ ሀይማኖት ፦ እኛ በኤጀንሲ ደረጃ ቆሻሻ ሀብት ነው እንላለን፤ ግን ደግሞ ይህ አስተሳሰብ ነዋሪው ዘንድ ደርሶ ትልቅ ለውጥ እየመጣበት አልነበረም:: ለምሳሌ አዲስ አበባ ውስጥ መልሶ ጥቅም ላይ መዋል ከሚገባው ቆሻሻ መካከል ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው ስድስት በመቶ ብቻ ነው:: በመሆኑም ይህንን ሁኔታ ለመለወጥና መልሶ ጥቅም ላይ መዋል ያለበት ቆሻሻ ሁሉ በአግባቡ የታለመለትን ግብ እንዲመታ ለማድረግ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ነው የሰራነው::
በዚህ ዓመት ብቻ ሦስት ሺ 885 የሚሆኑ ወጣቶች በመልሶ መጠቀም ዘርፍ የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው ሆኗል:: በዘጠኝ ወራትም 114 ሚሊየን ብር ገቢ ማግኘት ችለዋል:: በዚሁ ዘርፍም በተለይም የታሸጉ የውሃ መያዣዎችን በመፍጨት፣ የተለያዩ ብረታ ብረቶችን በማቅለጥና ጥቅም ላይ በማዋል ስራ ላይ የተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች በስራው ተሰማርተው ለአገርም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እያስገቡ ከመሆኑም በላይ በዚህ ዘጠኝ ወራት ውስጥም ስምንት ሚሊየን ዶላር ተገኝቷል:: በመሆኑም ይህ ዘርፍ አዳዲስ ባለሀብቶችን ሁሉ የሚስብ ሆኗል::
በጠቅላላው ዘርፉ ለወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር የገቢ ሁኔታን በማሻሻል እቃዎቹም መልሰው ጥቅም ላይ ሲውሉ ፈጠራ የታከለባቸው ከመሆኑም በላይ ጥራታቸውን ጠብቀው ስለሆነ የሚዘጋጁት ለየት ያለ ተሞክሮ ያመጣንበት ነው፡፡ ዘርፉም ለአገራዊ ኢኮኖሚው የራሱን አስተዋፅዖ ማበርከት ችሏል::
በጽዳቱም በኩል ቢሆን ባህል እንዲሆን ከማድረግ አንጻር ስራው ከዘመቻ ስራነት ወጥቶ ባህል እንዲሆን ከማድረግ አንጻር ትልቅ ስራ የተሰራ ሲሆን ኤጀንሲው በየሳምንቱ የጽዳት ስራን ለመስራት ሲወጣ የመንግስት ተቋማት አርብ አርብ በሰራተኛው እንዲጸዱ ትምህርት ቤቶችም በተመሳሳይ አርብ አርብ ቋሚ ፕሮግራም ይዘው ተማሪዎች በጽዳት ስራ እንዲሳተፉ እየተደረገ መሆኑ ጽዳትን ከታችኛው የእድሜ እርከን ጀምሮ በሁሉም ሰው አእምሮ ውስጥ እንዲሰረጽ በማድረግ በኩል ትልቅ ስራ ተሰርቷል::
በሌላ በኩልም በተለይም ህጻናት ተማሪዎች ጽዳትን ባህል አድርገው እንዲይዙ በትምህርት ስርዓት ውስጥ እንዲካተት ለማድረግም የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው:: ይህ መሆኑ ደግሞ ህጻናት ጽዳትን ባህል ባደረጉ መጠን ለቤተሰቦቻቸውም ሆነ ለሌሎች አርዓያ በመሆን በማስተማር የራሳቸውን ሚና ይወጣሉ ማለት ነው::
በጠቅላላው እንደ ኤጀንሲ ጽዳትን በህብረተሰቡ ውስጥ ለማስረጽ እየተደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ቢሆንም በቀጣይ ደግሞ ባህል ሆኖ ሁሉም የቤቱ፣ የደጁ፣ የአካባቢው፣ አልፎም የከተማው ጽዳት ያገባኛል ይመለከተኛል በማለት እንዲንቀሳቀስ ለማድረግ ሰፊ ስራዎች ይጠብቁናል፡፡ እንደ መነሻ ግን በዚህ ዓመት በየሳምንቱ የጽዳት ስራን በህብረተሰቡ እያሰራን ያለንበት ሁኔታ እጅግ የተሳካ ሆኗል::
አዲስ ዘመን ፦ እንደ ኤጀንሲ ህብረተሰቡ በጽዳት ላይ ያለውን አመለካከት ለመቀየር ሰፋፊ ስራዎች እያከናወናችሁ ነው ነገር ግን የመጣውን የባህርይ ለውጥ ለክታችሁታል? ከለካችሁትስ ምን ያህል ነው?
ወይዘሮ ሀይማኖት፦ እኛ አሁን እየለካን ያለነው የሚበሰብስና የማይበሰብስ ቆሻሻን ለይቶ በማውጣት በኩል ህብረተሰቡ የቱ ጋር ነው የሚለውን ነው፤ ምክንያቱም የባህርይ ለውጥ የሚጀምረው ከዚህ ነው ብለን ስለምናምን ነው፤ የሚበሰብሰውን ቆሻሻ ወደኮምፖስት ይቀየራል፡፡ ይህንን ለማድረግ ግን ህብረተሰቡ መጀመሪያ ግንዛቤው ሊኖረው ይገባል:: አሁን ላይ ግንዛቤው ተፈጥሯል:: ከዚህ ተነስተን ደግሞ ይህንን የሚበሰብስ ቆሻሻ ወደ ማዳበሪያነት ቀይረው ጥቅም ላይ ሊያውሉ የሚችሉ አንድ ሺ 780 ወጣቶችን በማደራጀት ገቢ እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል:: በየአካባቢው ከ800ሺ በላይ አባወራዎች አሉን ፤ 80 በመቶው ደግሞ ቢያንስ የሚበሰብሱና የማይበሰብሱ ቆሻሻዎችን ለይቶ ከቤቱ ያወጣል ብለን እናስባለን::
በሌላ በኩልም የህብረተሰቡን የግንዛቤ ደረጃ የምንለካው በተለይም በየሰፈሩ መግቢያ ላይ የተለጠፈውን የቆሻሻ ማውጫ ጊዜ በመጠበቅ እያወጣም ነው ብለን ስለምናስብ፤ እስከ አሁን በየሳምንቱ ቆሻሻ አይወጣልኝም የሚል ህዝብ ስለሌለ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከቤቱ አውጥቶ መንገድ ዳር ቆሻሻን የሚወረውር ሰው በመቀነሱ እነዚህን ነገሮች ገጣጥመን ስናያቸው በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው የግንዛቤ ደረጃ ከፍ ማለቱን ያመለክታሉ::
ምንም እንኳን እኛ የያዝነው መረጃ በገለልተኛ ተቋም የተጣራ ባይሆንም ለውጥ ግን መጥቷል ብሎ መናገር ይቻላል፤ ወደፊት ደግሞ ይህ ለውጥ በገለልተኛ አካል ተጣርቶ ያለንበትንም ደረጃ የምናውቅ ይሆናል:: ይህ ለውጥ ግን ተሳስሮና በሁሉም ደረጃ ተግባራዊ ሆኖ ከተመዘገበው ለውጥም በላይ ትልቅ ደረጃ እንዲደርስ የመንግስት ባለስልጣናትን፣ ታዋቂ ሰዎችን፣ የጥበብ ባለሙያዎችን በጠቅላላው በህብረተሰቡ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያላቸውንና ተሰሚ የሆኑ ግለሰቦችን በጽዳቱ ላይ እናሳትፋለን፡፡ ይህ በአንድ ጀምበር የሚያልቅ ስላልሆነ ወደፊትም ተጠናክሮ መሰራት ያለበት መሆኑን ኤጀንሲውም ይገነዘባል::
አዲስ ዘመን፦ ዘርፉ ሰፊ ከመሆኑ አንጻር በዓመቱ ለምን ያህል ሰዎችስ የስራ እድል ፈጥሯል?
ወይዘሮ ሀይማኖት ፦ በልዩ ሁኔታ በሄድንበት እንኳን የስራ እድል ፈጠራ በሚል አስተዳደሩ 28 ሺ ያህል ሰዎችን የስራ እድል እንድንፈጥር ኮታ ሰጥቶ ነበር:: ከዚህም ውስጥ በልዩ ሁኔታ ከጥቅምት ወር ጀምሮ በሰራነው ስራ አምስት ሺ 500 የሚሆኑ ሰዎችን በሁለት ወር ብቻ ወደ ስራ ለማስገባት ችለናል:: በመደበኛነትም ከ ሁለት ሺ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ እድልን በመፍጠርና ገቢ እንዲያገኙ በማድረግ ተሳክቶልናል:: ይህ ደግሞ ቢሮ ውስጥ ሆነው የሚሰሩትን ሳይጨምር ነው::
አስተዳደሩ በተለይም የመልሶ ጥቅም ማዋል ዘርፍ ገና ጥቅም ላይ ያልዋለ በመሆኑ ወጣቶች ትኩረታቸውን በዘርፉ ላይ አድርገው እንዲሰሩ እየተደረገ ነው:: ለምሳሌ በማህበር ተደራጅተው ማዳበሪያ (ኮምፖስት) የሚያመርቱ አንድ ኪሎ በአራት ብር ነው ለገበያ የሚያቀርቡት፡፡ ከተማ አስተዳደሩ ደግሞ በአንድ ኪሎ ላይ ሶስት ብር ይደጉማቸዋል፤ በተመሳሳይ ወረቀትና ካርቶን መሰብሰብ ላይም በኪሎ ሶስት ብር ይሸጣሉ ከተማ አስተዳደሩ ደግሞ አንድ ብር ከ 50 ሳንቲም በኪሎ ይደጉማል፤ በመሆኑም በዚህ ላይ ወጣቶች በትኩረት ቢሳተፉ የተሻለ ተጠቃሚ ይሆናሉ::
አዲስ ዘመን ፦ ቆሻሻ ሀብት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በተለይም መልሶ ጥቅም ላይ የሚውሉ ቁሳቁሶች ወደውጭ ገበያም ይቀርባሉና በዚህ በኩል ያለው አፈጻጸም የተገኘው ገቢ ምን ይህል ነው?
ወይዘሮ ሀይማኖት ፦የወጪ ንግዱ ለብዙዎች የስራ እድል ፈጥሯል፡፡ በአሁኑ ወቅት ይህንን ስራ የሚሰሩ 15 ድርጅቶች ያሉ ሲሆን በስራቸውም ከመቶ የማያንሱ ሰዎችን ይዘዋል:: እነዚህ ካምፓኒዎችም በተለይ የታሸገ ውሃ መያዣን እየፈጩ ኮምፎርት አልጋ ልብሶች ጅንስ ሱሪዎችና ሌሎች አልባሳትን እያመረቱ ነው:: ግማሾቹም ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪን እያስገቡ ነው:: ከአምና ጀምሮ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የተቀዛቀዘ ቢሆንም በገቢ በኩል ግን ጥሩ የሚባል ደረጃ ላይ ነው ያለው፤ አምና በዘጠኝ ወሩ ስድስት ሚሊየን ዶላር አስገኝቶ የነበረ ሲሆን በዘንድሮው የዘጠኝ ወር አፈፃፀምም ስምንት ሚሊየን ዶላር አስገብቷል::
አዲስ አበባ ከተማ ከስድስት ሚሊየን ህዝብ በላይ ይኖርባታል ተብሎ ነው የሚገመተው፡፡ ከዚህ ውስጥ ደግሞ በሌሎች ጉዳዮች ወደከተማዋ የሚመጡና የሚመለሱ ሰዎች ፤ የአፍሪካ ህብረትም መቀመጫ ናት፤ የቱሪስት መስህብ ፤ ከዚህ አንጻር ደግሞ በርካታ ቆሻሻዎችም የሚመነጭባት ናትና ይህንን ጥቅም ላይ ለማዋል ባለሀብቶች መጨመር አለባቸው::
አዲስ ዘመን ፦ በከተማዋ አረንጓዴ ልማት እየተባለ የተለያዩ ፕሮጀክቶች እየተቀረጹ ወደ ስራ ይገባሉና እንደው የኤጀንሲው ሚና ምንድን ነው?
ወይዘሮ ሀይማኖት፦ በእርግጥ ጽዳትና ውበት የተለያዩ ናቸው፤ ውበት እራሱን የቻለ ኤጀንሲ ነው፤ በመሆኑም አረንጓዴ ማልበሱንም እነሱ ናቸው የሚሰሩት፤ ቢሆንም ግን አንድ ጥሩ እድል ያለው እነዚህ በጽዳትና ውበት ዙሪያ የሚሰሩ እኛን ጨምሮ ያሉ ኤጀንሲዎች ቀደም ሲል ተበታትነው የነበረ ሲሆን አሁን አንድ ላይ ተሰባስበው የከተማዋ ማዘጋጃቤታዊ ዘርፍ ስር ሆነዋል:: ይህ ደግሞ በአረንጓዴ አሻራ ማሳረፉ ላይ ኤጀንሲው ሚና እንዲኖረው አድርጓል:: እኛ የማይበሰብስና የሚበሰብስ ቆሻሻ በማለት እንለያለን፤ የሚበሰብሰው ቆሻሻ ላይ ደግሞ ወጣቶች ተደራጅተው ማዳበሪያ (ኮምፖስት) እያመረቱ ነው:: ይህ ምርት ደግሞ በገበያ በኩል እዛው አረንጓዴ ልማቱ ጋር እንዲተሳሰር ሆኗል::
በመሆኑም ለሚሰራው የአረንጓዴ ልማት ስራ እኛ የምንሰራው ማዳበሪያ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው ማለት ነው:: በቀጣይም በአገር አቀፍ ደረጃ በሚተከለው ችግኝ ላይ የእኛ አስተዋጽኦ በጣም ሰፊ ይሆናል፤ ወጣቶቹም ሰፊ የሆነ ገበያ እንደሚያኙ በማሰብ ብዙ ምርት አንዲያመርቱም እየነገርናቸው ነው::
በሌላ በኩል ግን የሚበሰብሱ ቆሻሻዎችን በዚህ መልኩ አምርተን ለገበያ ማቅረባችን አረንጓዴ ልማቱን ጥራቱን በጠበቀ ማዳበሪያ በማከናወን፣ ለወጣቶቹ ሰፊ የገቢ ምንጭ በመፍጠር እና ከዚህ ቀደም በማጠራቀሚያ ቦታዎች ላይ የሚፈጠረውን እንዳይመጣ በማድረግ በኩል ሚናው ላቅ ያለ ነው::
አዲስ ዘመን ፦ ኤጀንሲው ከዚህ በላይ ሀላፊነቱን እንዲወጣና ከተማዋም በሚመጥናት ልክ ውብ እንድትሆን ለማድረግ ከማን ምን ይጠበቃል?
ወይዘሮ ሀይማኖት ፦ ዘንድሮ ያየነው ለውጥ በጣም አበረታች ቢሆንም ትምህርትም የሚወሰድበት ነው:: የጽዳት ስራ አያስመሰግንም፡፡ ለአንድ ወር በተከታታይ ተጸድቶና አምሮ በቀጣዩ ቀን በሆነ ምክንያት ቢቋረጥ የአዲስ አበባ ቆሻሻ ምን ሊሆን ይችላል ብሎ ማሰብ በቂ ነው:: በመሆኑም ሁሉም ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ሁሉ ትኩረት ሊሰጡት ይገባል::
ለምሳሌ የከተማ አስተዳደሩ ለዚህ ዘርፍ እንደ ዘንድሮ ትኩረት ሰጥቶ አያውቅም፡፡ ከዚህ በፊት ቢሮ የሚመሩ ሀላፊዎችም ሆኑ ሌሎች ለዘርፉ ትኩረት ነፍገውት ቆይተዋል ይህ ማለት ግን አሁንም ትኩረቱ በቂ ነው ማለት አይደለም::
ቆሻሻ አወጋገድም ሆነ የጽዳት ስራ ትልቅ የጤናና የማህበራዊ ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም ማንኛውም አካል የጽዳቱን ጉዳይ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል:: የፌደራል መንግስትም ይሁን አዲስ አበባ ተቋማቶቻቸውን አርብ አርብ አንዲያጸዱ የተቀመጠ አቅጣጫ አለ፡፡ ይህንን ሀላፊ የማይከታተለው ከሆነ ስራው በተገቢው ሁኔታ አይካሄድምና አመራሮች ይህም የስራቸው አንዱ አካል መሆኑን ተረድተው ልዩ ትኩረት ሊሰጡት ይገባል::
ከዚህ በተጨማሪም የጽዳት ጉዳይ በአንድ ኤጀንሲ ላይ የተጣለ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ሀላፊነት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፤ በዚህም መሰረት ሁሉም የድርሻውን በመወጣትና ህብረተሰቡን በመቅረጽ በኩል ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል::
አሁንም መሻሻሎች ቢኖሩም መሻገር ያልቻልናቸው ነገሮች ግን ህብረተሰቡ የመንገድ ጽዳቶች እንኳን አጽድተው ከሄዱ በኋላ ቆሻሻን ከቤት አውጥተው መንገድ ላይ የመጣል ሁኔታ ይታያል:: በመሆኑም እያንዳንዱ የከተማዋ ነዋሪ ሀላፊነት ተሰምቶት በተቻለ መጠን ቆሻሻን በአግባቡና በተገቢው መንገድ በማስወገድ ሃላፊነቱን መወጣት ይገባዋል::
አዲስ ዘመን፦ ኤጀንሲው የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅዶቹ ምንድን ናቸው?
ወይዘሮ ሀይማኖት ፦ የአጭር ጊዜ እቅዶቹ ቆሻሻን ከየቤቱና ተቋማቱ ሰብስቦ እስከማጓጓዝና እስከ ማስወገድ ድረስ ከዚያም መልሶ እስከመጠቀም ያሉት ሂደቶች የእኛ የእለት ተዕለት ተግባራት ናቸው::
አንድ ከተማ ሰለጠነ የሚባለው ቆሻሻውን በአግባቡ ሲይዝ፣ ሲያስወግድና ሲያስተዳደር በመሆኑ በዚህ ደረጃ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ተጠንተው ተግባራዊ እየሆኑ ይገኛሉ፤ ይህም ከረጅም ጊዜ እቅድ ውስጥ የሚካተት ነው:: ለምሳሌ ረዺ ላይ የተጀመረው ስራ በተለይም ከሁለትና ሶስት አመት በፊት ያጋጠመው አይነት አደጋ እንዳያጋጥም ለማድረግ ከጃፓን መንግስትና ከዩኤን ሀቢታት (UN Habitat) ጋር በመተባበር “ፎኮካ ፕሮጀክት” ተግባራዊ እየተደረገ ነው፤ ይህም ቆሻሻው ተከምሮ እንደቀደመው ጊዜ አይነት አደጋ እንዳያመጣ ማስተንፈስና ጋዙን መልቀቅ ነው፡፡ ይህም በተጠና መንገድ የረጅም ጊዜ እቅድ ሆኖ እየተሰራ ይገኛል::
አዲስ ዘመን ፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ::
ወይዘሮ ሀይማኖት፦ እኔም አመሰግናለሁ
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሰኔ 16/2013