በኢትዮጵያ ህገ መንግሥት መሰረት ምርጫ በየ5 ዓመቱ የሚካሄድ ነው ። 6ኛ አገራዊ ምርጫም በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ለአንድ ዓመት ተራዝሞ በመጪው ሰኞ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓም ይካሄዳል ፡፡ በዚህ የምርጫ ውድድር ላይ 49 የፖለቲካ ፓርቲዎች ከቦርዱ ፍቃድ አግኝተው ለመወዳደር ቀርበዋል። ፍቃድ ካገኙት መካከል 47ቱ የምርጫ ምልክት ወስደው የምርጫ ክርክር ሲያካሂዱም ቆይተዋል።
በጸጥታ ችግርና ከፖለቲካ ፓርቲዎች በቀረበ ቅሬታ ምክንያት በ27 የምርጫ ክልሎች ምርጫ እንደማይካሄድም ምርጫ ቦርድ ማሳወቁ ይታወሳል። በሌላ በኩልም በ 27ቱ የምርጫ ክልሎች፣ ማለትም በሶማሌና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ (ለሕዝበ ውሳኔ) ጳጉሜ 1 ድምጽ ይሰጣልም ተብሏል ።
በትግራይ ክልል ካለው የህግ ማስከበር ዘመቻ አለመጠናቀቅ ጋር ተያይዞ አጠቃላይ ምርጫው አይካሄድም። በዚህም ምክንያት 38 የተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) ወንበሮች ክፍት ይሆናሉ ማለት ነው። ከምርጫ ማስፈጸሚያ ደንቦች አንዱ የአገር ውስጥና የውጭ ታዛቢዎችን ማሳተፍ እንደመሆኑ በዘንድሮው ምርጫ ላይም 45ሺ ታዛቢዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። ምርጫውን ለመታዘብ ባጅ ከወሰዱት መካከል 167 ቱ የሲቨል ማኅበራት ናቸው፡፡
በአገር አቀፉ ምርጫ ላይም 37 ነጥብ 4 ሚሊዮን መራጮች ተመዝግበው ካርዳቸውን የወሰዱ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ እብዛኛው ዜጋ ድምጹን ለሚፈልገው ፓርቲም ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።
በምርጫ 2013 የፖለቲካ ፓርቲዎች 547 መቀመጫዎች ባሉት የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) መቀመጫ ለማግኘት ይወዳደራሉ፡፡
በሶማሌ ክልል በሁሉም ምርጫ ክልሎች፣ በአማራ ኤፌሶን፣ አንኮበር ማጀቴ እንዲሁም በአርማጭሆ፣ በቤኒሻንጉል ደግሞ መተከል እና ከማሺ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓም መራጮች ድምፅ የማይሰጡባቸው የምርጫ ክልሎች ናቸው ። ከመራጮች ምዝገባ እና ከጸጥታ ችግር እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታ ጋር በተያያዘ ድምፅ የማይሰጥባቸው እነዚህ አካባቢዎችም በቀጣይ ውሳኔ የሚያገኙ መሆኑንም ምርጫ ቦርድ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
እኛም በተለይም ምርጫን ለማስፈጸም የወጡት ህጎች ምን ይላሉ? ተፈጻሚነታቸውም ምን መምሰል አለበት? ስንል የህግ ባለሙያና ጠበቃ የሆኑትን አቶ ሰመረ አሰፋን አነጋግረናቸዋል።
አዲስ ዘመን ፦ለምርጫ ስኬት የተቀመጡ የምርጫ ህጎች ምንድን ናቸው?
አቶ ሰመረ ፦ የምርጫ ህጎች መነሻቸው የአገሪቱ ህጎች ሁሉ ምንጭ የሆነው ህገ መንግሥት ነው። ይህንንም መሰረት አድርገው የወጡ በርካታ ህጎች አሉ ።ከነሱም በተጨማሪም ምርጫ ቦርድ በህግ በተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት መሰረት ያወጣቸው መመሪያዎች አሉ ። እነዚህን መሰረት በማድረግም 6ተኛው አገራዊ ምርጫ ህጉን ተከትሎ ይካሄዳል ።
በሌላ በኩል ደግሞ ተፎካካሪዎች እንዲሁም በምርጫ ጉዳይ ላይ ውሳኔ እንዲያሳልፉ የሚፈቀድላቸው የህግ አካላት እነዚህን ህጎች መሰረት አድርገው የምርጫን ጉዳይ ይዳኛሉ ውሳኔ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ሲያጋጥሙም ውሳኔያቸውን ያስተላልፋሉ።
አዲስ ዘመን ፦ ከእነዚህ ህጎች አንጻር በምርጫው በቀጥታ የሚሳተፉት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ያሉባቸው ኃላፊነቶች እንዴት ይገለጻሉ?
አቶ ሰመረ ፦ ምርጫ በዋናነት የአንድን አገር መንግሥት በዴሞክራሲያዊ ሁኔታ ህዝብ የሚመርጥበት ስርዓት ነው። ይህ ደግሞ በተለያዩ ጊዜያት ሲካሄድ የመጣ ሂደት ነው። ይህ ሂደት መጥቶ መጥቶ ደግሞ ዘንድሮ 6ተኛውን አገራዊ ምርጫ ማካሄድ ላይ ደርሰናል። ወደፊትም በርካታ ምርጫዎች ይመጣሉም ብለን ተስፋ እናደርጋለን ። በመሆኑም ምርጫ የሂደት ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የዛሬን ብቻ በማየት ዛሬ በሚያደርጉት የምርጫ ፉክክር ማሸነፍና መሸነፋቸውን ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ማበብ አንድ እርምጃ ወደፊት መራመድ ከዚህ ቀደም ከነበሩት የምርጫ ጊዜያት በተለየ መልኩ ምርጫው ከውጤቱም በኋላ ቢሆን ሰላማዊ ሆኖ እንዲቀጥል የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው።
በምርጫው የሚሳተፉ አካላት የአገሪቱ የምርጫ ሂደት አቅጣጫ ገንቢ ወደሆነና የአገራችንን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት በሚገነባና ሁሉም ነገር ሰላማዊ ሆኖ የአገርን ቀጣይነት መሰረት ባደረገ መልኩ መንቀሳቀስ አለባቸው ። የትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ኃላፊነት በአንድ ምርጫ ከመመረጥ ጋር የሚያያዝ መሆን የለበትም። ይልቁንም ፓርቲዎች ቢያሸንፉም ቢሸነፉም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ ሂደት ውስጥ ማለፋቸው በራሱ ድል መሆኑንና በተለይም ለዜጎች መልካም መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።
ዜጎችን ምረጡን እንምራችሁ የሚል ማንኛውም ፓርቲ የምርጫውን ውጤት በጸጋ የመቀበል ኃላፊነት አለበት። የህዝብን ውሳኔ የማክበር ኃላፊነት አለበት ። ይህንን ማድረግ ካልቻለ ግን መጀመሪያውንም የእነዚህ ፓርቲዎች አላማ ስልጣን እንጂ የህዝብን ውሳኔ ሰጪነት አላመኑም ማለት ስለሚሆን ገዢው ፓርቲም ይሁን ተፎካካሪዎች የምርጫውን ውጤት በጸጋ መቀበል ማለት እንምራህ የሚሉትን ህዝብ ማክበር መሆኑን መገንዘብ ይገባል።
በተለይም ውጤትን ከምርጫ ቦርድ ውጪ ለመግለጽ መሞከር የማይገቡ ድርጊቶችን በመፈጸም ህዝብን ማነሳሳት ከዚህ ቀደም ይደረጉ የነበሩ ስህተቶችን መድገም ስለሚሆን በተቻለ መጠን ከዚህ ዓይነቱ ተግባር በመራቅ ለአገራቸውም ለህዝባቸውም ያለባቸውን ኃላፊነት መወጣት ይገባቸዋል።
አዲስ ዘመን ፦ እዚህ ላይ መንግሥትም በምርጫው አንዱ ተፎካካሪ ፓርቲ ነውና የእርሱስ እንዲሁም ምርጫውን ለማስፈጸም ስልጣን የተሰጠው ምርጫ ቦርድ ኃላፊነታቸውን በምን መልኩ ነው ሊወጡ የሚገባው?
አቶ ሰመረ ፦ ምርጫ ቦርድ እስከ ዛሬ ድረስ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በጣም መልካም ሊባልና ሊበረታታ የሚገባው ገለልተኝነት ታይቶበታል። ይህ ከውስጥ ጥንካሬያቸው የሚመነጭ እንዲሁም መንግሥት የፈጠረውንም አስቻይ ሁኔታ የሚያመላክት ነው።
መንግሥት በገዢነቱ በአገሪቱ ውስጥ ህግና ስርዓትን የማስከበር ሰላም የማስፈን ምርጫም ይሁን ሌላ አገራዊ ሁነት በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ የማድረግ ኃላፊነት ያለበት ሲሆን በተፎካካሪ ፓርቲነቱ ደግሞ ለምሳሌ የምርጫ ውጤትን በጸጋ የመቀበልና ሌሎችንም ለምርጫው ፍትሀዊነትና ታማኝነት የሚረዱ ተግባራትን የማከናወን ግዴታ አለበት።
የምርጫ ቅስቀሳው ከትላንት በስቲያ ማብቃቱ ይታወቃል። ስለዚህ ከዚህ በኋላ የምርጫ ቦርድ የሚያወጣቸውን የምርጫ ማስፈጸሚያ ደንቦች እንደ ገዢ መንግስት ሳይሆን እንደ ተፎካካሪ ፓርቲ እኩል አክብሮ የመንቀሳቀስ ኃላፊነት አለበት። ከዚህ ጎን ለጎን ግን እንደ መንግሥት ደግሞ ህግና ስርዓትን የማስከበር ኃላፊነቱን በመወጣት ህዝቡን መጠበቅ ይኖርበታል።
ምርጫ ቦርድና ፍርድ ቤት እንደ ጅማሮ እያደረጉ ያሉት ነገር በጣም ደስ የሚል ነው፤ ምርጫ ቦርድም እስከ አሁን ድረስ በገለልተኝነት የተለያዩ ውሳኔዎችን እየወሰነ አሳይቶናል ፤ ውሳኔዎቹም በፍርድ ቤት ውድቅ የሆኑበትም የጸኑበትንም ሁኔታ ደግሞ ታዝበናል። በተለይም ምርጫ ቦርድ ውድቅ የተደረጉበትን የፍርድ ቤት ውሳኔዎች አክብሮ ለመፈጸም ያሳየው ተነሳሽነት በአገራችን የህግ የበላይነትን ለማስፈን እንዲሁም ለህግ ስርዓቱ መልክ መያዝ ትልቅ ተስፋ የሰጠም ነው። ቦርዱም ሊመሰገን ይገባዋል።
አዲስ ዘመን ፦ አንድ ምርጫ ሲካሄድ ከሚመጡ ነገሮች መካከል የምርጫ ታዛቢነት ነውና እነዚህ ታዛቢዎች ደግሞ ከአገርም ከውጭም አገር የሚመጡ ናቸው፤ ህጉ ስለእነሱ እንቅስቃሴ ምን ይላል?
አቶ ሰመረ ፦ እኛ ምርጫ እናደርጋለን ስንል በዋናነት ለራሳችን ብለን ነው። ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለዚህች አገር ያስፈልጋታል ብለን ነው ምርጫ
የምናካሂደው ፤ የምርጫውንም ውጤት ወሳኙ የኢትዮጵያ ህዝብ ነው። ሂደቱ በአግባቡ ተከናውኗል ውጤቱ ተገቢ ነው አይደለም የሚለውን የሚፈርደው ህዝብ ነው። የትኛውም የውጭ አካል ይሁንታ ወይንም ደግሞ ተቀብያለሁ አልተቀበልኩም የሚለውን ነገር ለእኛ መሰረታዊ ነገር አይደለም።
ሆኖም ዓለም ላይ እንዳለ አገር የምርጫ ሂደት ሌሎችም አካላት ምርጫውን ታዝበው ውጤቱ ላይ አስተያየት ቢሰጡ ምንም ክፋት የለውም ። ነገር ግን ይህንን ሥራ ለሌላ ድብቅ አላማ ማስፈጸሚያ ማድረግ ትክክል አይደለም። ዞሮ ዞሮ በዚህች አገር ላይ የምርጫውን ሂደት የመፈጸም ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም አለ እርሱም ኃላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣት ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው ። የኢትዮጵያ ህዝብም ትኩረቱን ሊያደርግ የሚገባው ተቋሙ ምርጫውን በአግባቡ አከናውኗል፣ ውጤቱም ይህ ነው እስከሚል ድረስ መጠበቅ ነው።
በዚህ መሰረት ደግሞ ምርጫውን ያሸነፈው አካል ስልጣኑን በህግ አግባብ በመቀበልና የመረጠውን ህዝብ ማስተዳደር ላይ ትኩረቱን አድርጎ መስራት ነው። እዚህ ላይ ግን ህዝቡ የምፈልገው አካል ወደ ስልጣን አልመጣልኝም ካለ ሰላማዊ የሆኑና በቀጣይ ሊከናወኑ የሚችሉ ሂደቶችም ስላሉ ያንን በሰላማዊ መንገድ መቀጠል ይቻላል ። እንደ አገር ካሰብንና አገራችን ትቀጥል ካልን መጪው ትውልድንም ካሰብን ደግሞ ቀጣዩን ምርጫ መጠበቅ ነው የሚሻለው።
አዲስ ዘመን ፦ እዚህ ላይ ታዛቢዎች በገለልተኝነት ምርጫውን ከመታዘብ ጎን ለጎን አንዳንድ ችግሮች ሲመለከቱ በምን ዓይነት መንገድ ነው እንዲገልጹ ህግ የሚፈቅድላቸው?
አቶ ሰመረ ፦ የምርጫ ታዛቢዎች በተለይም ከውጭ አገር ሲመጡ የአገሪቱን ህግ ማክበር ግዴታ አለባቸው ። ይህ ለአገር ውስጥ ታዛቢዎችም ይሰራል። የውጭ አገር ታዛቢ ስለሆነ የተለየ መብት ወይንም ደግሞ ህግ እንዲጥስ አይፈቀድለትም። በመሆኑም የአገሪቱን ህግ አክብረው ምርጫውን ይታዘባሉ ፤የታዘቡትን የሚገልጹበት መንገድ ግን የራሳቸው አካሄድ ይሆናል። ይህ ምን ማለት ነው ?ትዝብታችሁን በዚህ በዚህ መንገድ ነው መግለጽ የምትችሉት ብሎ መገደብ አይቻልም። ይህም ቢሆን ግን የታዛቢነት ፍቃድን ከምርጫ ቦርድ ሲወስዱ አብረው የሚገቡት ግዴታና ኃላፊነት አለ። ስለዚህ ይህንን አክብረው መንቀሳቀስ ግድ ነው። ዋናው ነገር ምርጫ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገለጫ አንዱ መንገድ ስለሆነ በዚህ ሂደት ውስጥ የሚሳተፉ ሁሉ ራሳቸውን ከህግ በታች አድርገው መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል።
ታዛቢዎችም ይሁኑ መራጩ ህዝብ እንዲሁም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ህግና ሥርዓትን አክብረው እስከተንቀሳቀሱ ድረስ የትኛውም ፓርቲ አሸነፈም፣ ተሸነፈ አገሪቱ አሸናፊ ሆና የምትወጣበት ነው የሚሆነው። ምክንያቱም ከዚህ ቀደም ያሉ በርካታ ችግሮች አሉብን እነዛን ችግሮቻችንን የምንቀርፍበት ምርጫ ውጤት መገለጽ በኋላ የሚነሱ አለመግባባቶች የሚፈቱበት አግባብ እንዴት ነው ?
አቶ ሰመረ ፦ አገሪቱ ችግሩ ቢከሰት እፈታበታለሁ ብላ ያስቀመጠችው ህግና ስርዓት አለ። መጀመሪያ እንዲህ ያሉ አለመግባባቶች እዛው በሚመደቡ ምርጫ አስፈጻሚዎች ውሳኔ የሚያገኙ ይሆናል። የቦርዱ ውሳኔም አላረካኝም የሚል ወገን ወደ ፍርድ ቤት ሄዶ የመጨረሻ ውሳኔ የሚያገኝበት ስርዓት አለ። ይህ ስርዓት በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያለውና የትኛውም አገር ችግሮች ሲያጋጥሙት የሚከተለውም ነው። በመሰረቱ በጣም ሰለጠንን ከኛ ወዲያ ዴሞክራሲ በሚሉት እነ አሜሪካንም ከምርጫ በኋላ ሁከቶች ሲነሱም ታዝበናል ነገር ግን እንደዚህ ያለ ስርዓት አልበኝነት አደግን ለሚሉትም ይሁን ኋላቀር ናችሁ ለምንባለውም አገራት የማይጠቅምና አፍራሽ የሆነ ተግባር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ። የየትኛውንም አገር ዴሞክራሲ እንደዚህ አይነቱ ሂደት ገንብቶ አያውቅም።
እንደ ኢትዮጵያም ይህ አይነቱን ችግር የሚፈታ ህግና ስርዓት ስላለን ይህንን ህግና ስርዓት ተከትሎ መሄድ ያስፈልጋል። በተለይም ባለፉት ሶስት ዓመታት በአገራችን የሚንጸባረቁት ስሜታዊነትእና ቡድንተኝነት ያደረሱብን ጉዳት አለ፤ ከጉዳቱ አገግመን ፤ጠባሳችን አልሻረም ። በተለይም ህዝቡ በቂ የህግ ተቋማትና ስርዓትም አለን ብሎ በመተማመን ከሞላ ጎደል ከችግር ነጻ የሆነ የምርጫ ሂደትን ለማስተናገድ መዘጋጀት ይጠበቅበታል።
ነጻና ዴሞክራሲያዊ ወይንም ደግሞ ከችግር የጸዳ ምርጫ እንኳን በእኛ አገር ሰለጠንን ባሉትም አገራት የማይካሄድ መሆኑን በመገንዘብ ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ ፤ነገር ግን ካሉን የህግ አካላት የሚሰጡ ውሳኔዎችን በመጠበቅና በማዳመጥ ኃላፊነታችንን መወጣት ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅም ነው። ይህንን አለማድረግ ግን አገሪቱን ለማያባራ የሰላም መደፍረስ የሚከታት በመሆኑና ይህ መሆኑ ደግሞ ለማንም የማይጠቅም መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፦ የምርጫ ውጤትን በማሳወቅ በኩል የሚነሱ ብዥታዎች አሉ ለምሳሌ የምርጫ ታዛቢዎች ከህግ ውጪ ውጤት የሚገልጹበት ተፎካካሪ ፓርቲዎችም በተመሳሳይ ለደጋፊዎቻቸው ውጤትን ለመግለጽ የሚሞክሩበት ሁኔታ ከዚህ ቀደም ባስተናገድናቸው ምርጫዎች ላይም አይተናልና እንደው የምርጫ ውጤትን የመግለጽ ስልጣንና ኃላፊነት የማን ነው?
አቶ ሰመረ ፦ ህጉ በግልጽ ስልጣንና ኃላፊነቱን የሰጠው ለምርጫ ቦርድ እንደመሆኑ ውጤቱንም መግለጽ የሚችለው ምርጫ ቦርድ ነው። እዚህ ላይ ደግሞ በድምጽ መስጫው ማግስት በየምርጫ ጣቢያዎቹ በር ላይ ውጤቶች ይለጠፋሉ፤ ህዝቡም ራሱ በመረጠበት ጣቢያ ላይ ያለውን ውጤት በዚህ መልኩ ያውቃል። ከዚህ ውጪ ግን አጠቃላይ ቆጠራውና ህጋዊው ውጤት ስልጣን ባለው አካል እስከሚገለጽ ድረስ በትዕግስት መጠበቅ ደግሞ የህዝቡ ኃላፊነት ነው።
ከዚህ ቀደም በርካታ ምርጫዎችን አይተናል ለምርጫም እንግዳ አይደለንም በመሆኑም ውጤቱንም በትዕግስት ለመጠበቅ የምንቸገርበትም ሁኔታ ሊፈጠር አይገባም። ከዚህ ባለፈ ግን ይህንን አጋጣሚ ተጠቅመው አገራችንን ወደማይገባት ትርምስ ውስጥ ለመክተት የሚፈልጉ ሀይላትም አላማ ማስፈጸሚያ እንዳንሆን ይህንን መልካም አጋጣሚም ጉዳት ወደሚያመጣ ሁኔታ እንዳይቀየር መንግሥትም ዜጎችም እኩል የየራሳችንን ኃላፊነት መወጣት አለብን። ይህንን ካደረግን አገራችን አንድ እርምጃ ወደፊት ትሄዳለች። የሚኖሩ ስህተቶችም በቀጣይ ምርጫዎች እየታረሙ የሚሄዱ ይሆናል። መጪው ትውልድም በሰለጠነ መንገድ አገሪቱን እንዲመራ ዛሬ እኛ የምናስቀምጠው መሰረት ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን መገንዘብም በጣም ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን ፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ ሰመረ ፦ እኔም አመሰግናለሁ
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሰኔ 11/2013