አስቴር ኤልያስ
ብዙዎች ኢትዮጵያ ላይ እንዳሟረቱባትና እነርሱ በፈለጉት መንገድ እንደሚገፏት ሆና ባለመገኘቷ አግራሞታቸው ከቀን ወደቀን እየበረታ ስለመምጣቱ የማይታበል ነው። እርሷ በነደፈችው ትክክለኛ ጎዳና ላይ ናት። የትኛውም አካል ጠልፎ ሊጥላት ቢያሴርም ጉርብጥብጡን መንገድ በዜጎቿ ትብብር እያለፈች ዛሬ ላይ ደርሳለች። በቀጣይም የምትሰራውን ጠንቅቃ ስለምታውቅ የትኛውም ጩኸት እያቆማት አይደለምና ምርጫውንም ልታካሂድ በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ቀርተዋታል። ብዙ ፍጭትና ውይይትን እያስተናገደ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም ሁለተኛው ዙር ውሃ ሊሞላ የዝናቡን መምጣት ብቻ እየጠበቀ ይገኛል። እኛም በተለይ ሰንደቅ ዓላማችን የሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የተለያዩ ጥያቄዎችን በማንሳት ቀደም ሲል የምስራቅ ናይል ቴክኒካል አህጉራዊ ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የድርድሩ ተሳታፊ ከነበሩት ከውሃ ሀብት አስተዳደር ባለሙያው አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገን እንደሚከተለው አጠናቅረነዋል። መልካም ንባብ ይሁንልዎ።
አዲስ ዘመን፡– በህዳሴ ግድቡ ላይ በተከታታይ እየተደረገ ያለውን አይነት ውይይትና ጭቅጭቅ በሌሎቹ ግድቦች ላይ አለመደረጉን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፤ በህዳሴ ላይ ይህ መሆኑ ከምን የመነጨ ነው ይላሉ?
አቶ ፈቅአህመድ፡– ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሰረተ ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ በጣም በርካታ የቴክኒክ ውይይቶች እንዲሁም ድርድሮችም ሲካሄዱ ነበር። በዚህ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ትኩረት የተሰጠበት ዋናው ምክንያት የመጀመሪያ የሚሆነው ግድቡ የሚገነባው በአባይ ወንዝ ላይ በመሆኑ ነው ። የአባይ ወንዝ ደግሞ የናይልን ውሃ 62 በመቶ አበርክቶ ያለው ወንዝ ነው። ስለዚህም በዚህ ወንዝ ላይ ግብጾች ከድሮም ጀምሮ የይገባኛል ጥያቄ በተደጋጋሚ ሲያነሱ የነበረበት ነው። በርካታ የተለያዩ የህግ ማዕቀፎችን ከተለያዩ አካላት ጋር በመፈራረም አልፎ አልፎም አገራትን በማስፈራራትና በማዳከም ራሳቸው ብቻ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በርካታ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ስለነበረ በአባይ ወንዝ ላይ የሚሰራውን ግድብ በቀላሉ አላዩትም።
ግድቡ ያው ግድብ ነው ፤ የተለየ ምንም አይነት ባህሪ የለውም። ምናልባትም ግብጾች ከአስዋን ግድብ በዓመት የሚያተኑት ውሃ ቢጠራቀም ግድቡን ከአራት እስከ ስድስት ዓመት መሙላት ያስችላል። እነርሱ በሚያባክኑት ውሃ የህዳሴ ግድቡን መሙላት ይቻላል። በግዝፈት የምናይ ከሆነ ደግሞ አስዋን ግድብ ከህዳሴ ግድብ በላይ በእጥፍ ነው ውሃ የሚይዘው። የሚያጥለቀልቀው ቦታ ደግሞ ከህዳሴ ግድብ አራት ጊዜ ይገዝፋል። ያፈናቀላቸው የህዝቦችና ያደረሳቸው የአካባቢ ተጽዕኖዎች ቢታይ ደግሞ የአስዋን ግድብ ያደረሰው ተጽዕኖ ከህዳሴ ግድብ ጋር ሲነጻጸር የህዳሴ ግድብ ኢምንት ነው ማለት የሚቻል ነው።
ብዙ ውይይትና ድርድር መፈጠሩ ሌላ ነገር ኖሮት ሳይሆን ኢትዮጵያ በዚህ የውሃ ሀብቷ እንዳትጠቀምና ወደፊትም ለመጠቀም እንዳትሞክር ወደፊት ጭራሽ ግድብ የሚባል ነገር እንዳታስብ ለማድረግ ያቀዱትን ዓላማ ለማሳካት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ነው እንጂ የህዳሴ ግድቡ የተለየ ነገር ኖሮት አይደለም።
ሌሎች ግድቦቻችን ላይ ግን እንዲህ አይነት ችግር አልነበረም፤ በእርግጥ ተከዜ ላይ የተወሰነ ነበር። ነገር ግን መጠናቸው ሲታይ የግድቦቹ መጠን በጣም ከፍተኛ ካለመሆኑ የተነሳ እምብዛም የህዳሴ ግድብ አይነት ግፊት አልነበረም ።
አዲስ ዘመን፡– ምዕራባውያኑና አሜሪካውያኑ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማድረስ ብዙ ሙከራ እያደረጉ ነው፤ ለዚህ ሙከራዎቻቸውም ሆነ ጫናውን ለመመከት ምላሽ መሆን የሚገባው ነገር ምንድን ነው ብለው ያስባሉ?
አቶ ፈቅአህመድ፡– ይህን ነገር በሁለት ከፍለን ብናይ መልካም ነው፤ በተለይም ከህዳሴ ግድብ ጋር የተያያዘውንና ከዚያ ውጭ ያለውን እንክፈለው። የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ ሶስተኛ አካል ማስገባት ከመጀመሪያውም ጀምሮ ቢሆን ትክክል አይደለም ። ትክክል አለመሆኑን ደግሞ በተገኘው ውጤት መረዳት ችለናል። ስለዚህ ሶስተኛ ወገን ተብለው ከመጀመሪያውም ጀምሮ መግባት አልነበረባቸውም፤ ከገቡም በኋላ ደግሞ በታዛቢነት መቆየት ነበረባቸው።
ይሁንና እነርሱ ከታዛቢነት አልፈው ድርድሩን እስከማመቻት፣ እስከመደራደር እንዲሁም ከዚያም አልፈው ስምምቱን ላይ እስከመነጋገር የሄዱበት ሁኔታ ነው የነበረው። ይህ አይነቱ ሁኔታ ግን መፈቀድ አልነበረበትም።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ስለአሜሪካ የተለያዩ ነገሮችን ማንሳት ይቻላል። አንደኛው ከግብጽ ጋር ተያይዞ ያደረጓቸው ስምምነቶች አሏቸው፤ በተለይ ግብጽ እስራኤል የካምፕ ዴቪድ ስምምነት እኤአ በ1978 ሲፈርሙ ግብጽና አሜሪካ ሌላ የጎንዮሽ ስምምነቶች ነበራቸው። ከካምፕ ዴቪድ ስምምነት ግብጽ ከአሜሪካ፣ እስራኤልም ከአሜሪካ ጋር ስምምነት ነበራቸው። በግብጽና በአሜሪካ መካከል የተፈጸመው ስምምነት በጣም በምስጢር ነው የሚያዘው፤ ነገር ግን በዛ ስምምነት አሜሪካ በግብጽ ላይ አለኝ የምትለውን የውሃ ድርሻ ወይም መብት እውቅና ሳትሰጣት አትቀርም ተብሎ ነው የሚታማው። እሱም ብቻ ሳይሆን ይህንንም መብቷን እንድትከላከል በዓመት እስከ አንድ ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የጦር መሳሪያ እርዳታ ለመስጠት በወቅቱ አሜሪካ ቃል ገብታለች። ስለዚህ አሜሪካ ይህንን ስምምነት የማስፈጸም ግዴታ ስላለባት ገለልተኛ ሶስተኛ አካል መሆን አትችልም። እንግዲህ አንዱ ይህ ይመስለኛል፤ አሜሪካ ያንን ያህል ከመንገድ ወጥታ በጣም የፈጠጠ ድጋፍ ለግብጽ የመስጠቷ ጉዳይ።
ከዚህ ባሻገር በሁለቱ መካከል የንግድ ግንኙነቱም አለ፤ በአሜሪካና በግብጽ መካከል ያለው የንግድ ግንኙነት በጣም ከፍ ያለ ነው። ከዚያም አልፎ ከእስራኤል ጋር ከማዕከላዊ ምስራቅ ጋር በተያያዘ በአካባቢው ግብጽ የምታከናውንላቸው ስራዎች አሉ። በተለይ ከቀጣናዊ ደህንነት ጋር በተያያዘ የተለያዩ ሥራዎችን ትሰራላቸዋለች። ምንም እንኳ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ የምታበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ቢሆንም እስራኤል እዛ አካባቢ መገኘቷ አሜሪካ ወደ ግብጽ እንድታደላ ያደረገ ይመስለኛል። እነዚህ ናቸው በአብዛኛው አሜሪካ በዚህ ጉዳይ ውስጥ ገብታ ጫና ከመፍጠር እስከማስፈራራት ከዚያም አልፎ ግብጽ ጥቃት እንድትሰነዝር የማበረታት እና ለኢትዮጵያ እርዳታ ወደማቆም እስከመሄድ የደረሰችው። ለዚህ ሁሉ እንደ መነሻ አድርጌ እኔ የምቆጥረው ካምፕ ዴቪድ ላይ የተካሄደው የጎንዮሽ ስምምነት ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፡– ስለዚህ አሜሪካና ግብጽ በመካከላቸው እንዲህ አይነት የጠነከረ ወዳጅነት ካለ ኢትዮጵያ ጫናውን በመቋቋም የራሷን ሀብት ማንንም ሳትጎዳ መጠቀም የምትችለው በምን አይነት መልኩ ነው ይላሉ?
አቶ ፈቅአህመድ፡– ዋናው የራስን አቅም መገንባት መቻል ነው። የራስ አቅም ማለት በሁለንተናዊ መልኩ አገራዊ አቅምን መገንባት ነው። ትልቁ ነገር አገር ውስጥ ሰላምና መረጋጋት መፍጠር ነው። በተቻለ መጠን ህዝቡን በልማቱ ዙሪያ ማሰለፍ እንዲሁም በህዝቡ መካከል ያለውን ልዩነት በማጥበብ ህዝቡ ተቻችሎ መኖር የሚችልበትን አቅም ማጎልበት ነው። በተለይ በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ አገራዊ አንድነትን ለመፍጠር መሰራት ያለበት ይመስለኛል። የአገሪቷን ኢኮኖሚ ማሳደግም ዋናው ነገር ነው። በዚህም የማስፈጸም አቅምን ጎን ለጎን ማሳደግ ነው። በተለያየ መልኩ አቅማችንን ካሳደግን እንዲሁም ከጎረቤቶቻችን በተለይ ደግሞ ከተፋሰሱ አገራት ጋር የነበረንን ከፍተኛ ቅንጅት እና ከፍተኛ መረዳዳት እንደገና መልሶ ማጠናከር ከተቻለ ጫና እያደረሱብን ያሉትን አገራት ጫና መቋቋም ቀላል ነው የሚሆነው። ከሁሉም በላይ ግን የራስን አቅም ማደርጀት ወሳኙ ጉዳይ ነው። ከዚህ ውጭ ደግሞ የእኛን ፍላጎት የማይረዳና ጫና መፍጠር የሚፈልግን አካል በተቻለ መጠን በታዛቢነት አለማስገባቱ መልካም ነው።
አዲስ ዘመን፡– አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ እያሳደረች ያለው ተጽዕኖ በህዳሴ ግድቡ ላይ የሚያመጣው ጫና ምን አይነት ነው?
አቶ ፈቅአህመድ፡– ምዕራባውያኑ ጫናቸው ከባድ ነው፤ ምናልባት መታየት ያለበት ከእኛ አቅም አኳያ ነው። ኢትዮጵያ እንደሚታወቀው በጣም ድሃ አገር ነች። በአብዛኛው የምግብ እጥረት አለብን። የልማትም ሆኑ የኢንዱስትሪ ግብዓቶቻችን እንዲሁም የማህበራዊ ፍላጎቶቻችንን ሁሉ ለማሟላት እርዳታም ሆነ ብድር የምናገኝበት ሁኔታ ብዙ ጊዜ ከውጭ ነው። በመሆኑም እንዲህ አይነቱ አካሄድ ጫና ከማስመጣታቸው የተነሳ ይጎዱናል።
ይህ ማለት በመንግሥት ደረጃ የተለያዩ ቅደም ተከተሎች አሉ፤ ብዙ ድጋፍ ከውጭ ቢኖር ጠቃሚነቱ አያጠራጥርም፤ ለሌላ የታሰበውን ፋይናንስ በዚህ ድጋፍ ለህዳሴ ግድቡ ማዛወርም የሚቻልበት ሁኔታ ይኖራል። ጫና አድራጊው አካል የሚጠነክር ከሆነ አማካሪውም ኮንትራክተሩም ከውጭ ናቸው። በመሆኑም በእነሱ ላይ የእጅ አዙር ጫና መፍጠር ይችላሉ። ስለሆነም በተቻለ መጠን በብልጠት ይህን ሁኔታ ይዞ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ የሚፈታበትን ሁኔታ እንደ አማራጭ መውሰዱ ነው የሚያዋጣው።
እኛ የሚጣሉብንን ማዕቀቦች የመሸከም ትከሻችን እምብዛም የበረታ አይደለም። በዓለም ላይ ምዕራባውያን የሚያደርሱት ጫና እንዲሁም የሚጥሉት ማዕቀብ እነ ራሽያን እነቱርክን በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደጎዳቸው አሳምረን የምናውቀው ጉዳይ ነው። እነዚህ አገራት ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር ሲነጻጸሩ የተሻሉ የሚባሉ ናቸው። ስለሆነም በተቻለ መጠን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መፍታቱ የሚሻል ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፡– ኢትዮጵያ ባቀደችው መሰረት በሐምሌ ወር ሁለተኛው ዙር ውሃ ከሞላች በኋላ በግድቡ ላይ የሚሰነዘረው ጫና ያቆማል የሚሉ አሉና ይህን እንዴት ይገልጹታል?
አቶ ፈቅአህመድ፡– ግድቡ እስኪሞላ ድረስ ጫናው የሚቀጥል ይመስለኛል። የሚቀጥለው ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ሲካሄድ ምናልባት ግድቡ ውስጥ ገባ የምንለው ወደ 18 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ነው የሚሆነው። እሱ ማለት ደግሞ ግድቡ ከሚያስፈልገው ወደ ሩብ ያህል ውሃ እንደማለት ነው። ስለዚህም በግድቡ ውስጥ መያዝ ከሚችለው ሩብ ያህል ውሃ ገባና ጫናው ይቀንሳል ማለት እኔ በበኩሌ የሚመስለኝ አይደለም። ጫናው እስከመጨረሻው ድረስ የሚቀጥል ነው የሚመስለኝ። ግድቡ እንኳን በሩብ ያህል ብቻ ሞልቶና ከሞላም በኋላ ጫናው የሚቀጥል ነው የሚመስለኝ።
ከዚያ በኋላ ግን ራሱ ግድቡ ዲፕሎማሲ ይሰራል ብለን እናምናለን። ያም ዲፕሎማሲ የምንለው ውሃው ይይዛል፤ ውሃው ከተያዘ በኋላ ጉልህ ጉዳት ካልደረሰ ምናልባትም ህዝባቸው መልሶ ራሳቸውኑ ሊታዘባቸው ይችላል። ያኔ ግን ጫናውም ይቀንስ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ። ዋናው ግን መታየት ያለበት ጉዳይ የግብጽ ዋናው ዓላማ አሁን ካለው እንቅስቃሴ አኳያ ሲታይ ኢትዮጵያ ወደፊት የምትገነባቸው በርካታ ግድቦች አሉ። እነዚህም ግድቦች በአባይም፣ በተከዜም፣ በባሮም፣ በአኮቦም በተለይ በእነዚህ በሶስቱ ተፋሰሶች ውስጥ በርካታ የተዘጋጁ ግድቦች አሉ፤ እነዚያን ግድቦች እንዳታስብ በዚህ በህዳሴ ግድብ ላይ ኢትዮጵያ መከራ በማሳየት እና ጫና በመፍጠር እንዲሁም ከፍተኛ ወጪ እንድታወጣ በማድረግ ሌላ ግድብ እንዳታስብ የማድረግ ሥራ ይመስለኛል። በእርግጥ ግድቡ ሲሞላ ጫናው በተወሰነ ደረጃ ይቀንሳል። ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ የሚጠፋ ሳይሆን እንደሚቀጥልም መታሰብ ይኖርበታል። ለዚህ ደግሞ ከወዲሁ መዘጋጀት የሚጠበቅብን ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፡– የተፋሰሱ አገራት 11 እንደሆኑ ይታወቃልና በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ላይ በምዕራባውያኑና በአሜሪካውያኑ አማካይነት እየደረሰባት ያለውን ጫና ከዳር ሆነው ከመመልከት ይልቅ በምን አይነት ሁኔታ ነው ድምጻቸውን ማሰማት የሚችሉትና የሚጠበቅባቸው ይላሉ?
አቶ ፈቅአህመድ፡– ዋናው ነገር የሕዳሴ ግድብ ሲጀመር በተለይ የተፋሰሱ አገራት ከፍተኛ ድጋፍ ሲሰጡ ነበር። እስከተወሰነው መንገድም ድረስ አንዳንዶች አብረውን ተጉዘው እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም። ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ ድምጻቸውንም አሰምተው እንደነበር አይዘነጋም። ሱዳንንም ጭምር ማለት ነው።
ከተወሰነ ጊዜ ወዲህ ግን ከግድቡ ጋር በተያያዘ በሌሎች ጉዳዮች በተወሰነ መልኩ የመራቅ ሁኔታ ነው እያሳዩ ያሉት። ዋናው ነገር በመጀመሪያ አካባቢ እነርሱ የነበራቸው አቋም የህዳሴ ግድቡ መገንባቱን ያዩት እንደፋና ወጊ ነው። ህዝቦቻቸውን በተለይ እነታንዛኒያ፣ ዑጋንዳ እንዲሁም ሩዋንዳ ውስጥ ህዝቡ የኢትዮጵያን አርዓያ መከተል አለብን በሚል በመንግስቱ ላይ በጣም ጫና ይፈጥር ነበር። ኢትዮጵያን እንደምሳሌ ወስደን ወደልማት መግባት አለብን በሚልም መንግሥታቸውን ይወተውት እንደነበር ይታወቃል።
በኋላ ላይ ግን እንዲህ አይነቱ ሁኔታ በተወሰነ ደረጃ እየቀነሰ የመጣ ይመስለኛል። ይኸም ከግድቡ ጋር ብቻ የተያያዘ ሳሆን ሌሎች ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይም ገብተው ያወሳሰቡ ይመስለኛል። አሁን መደረግ ያለበት ነገር ከእነዚህ ከተፋሰሱ አገራት ጋር ተቀራርቦ መስራት ነው። የዲፕሎማሲውን ሥራ አጥብቆ መቀጠልም የሚጠበቅብን ነው የሚሆነው። ከዚህ ባሻገር ደግሞ ሌሎች የሚያገናኙንም ጉዳዮች አሉ፤ በተለይም የናይል ተፋሰስ የትብብር መድረክ አለ። የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት አለ። እነዚህ ስምምነቶች የሚጸድቁበት ሁኔታ እንዲፋጠን በትብብር የመስራት ሁኔታ ይጠበቅብናል። ከተፋሰሱም ውጭ በሌሎችም እንደገበያ አይነት ግንኙነት የምናገኛቸው እንደ ኬንያና መሰል አገሮች ጋርም አብሮ በመስራት መልሶ እነሱን በኛ ላይ ያላቸውን ትኩረት ወደነበረበት የመመለስ ሥራ በስፋት መሰራት ያለበት ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፡– እርስዎም እንደጠቀሱት ሱዳን በመጀመሪው አካባቢ ድጋፏን እስከ ህዳሴ ግድቡ ድረስ በመዝለቅ ስትረዳ መቆየቷ ይታወቃል፤ አሁን ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የአቋም መለዋወጥ አሳይታለች፤ በዚህም ድንበር እስከመውረር ደርሳለችና መላው ምንድን ነው ይላሉ?
አቶ ፈቅአህመድ፡– እግጠኛ መሆን የማይቻለው አዲሱ መንግሥት አለ፤ አዲሱ መንግሥት እንደመጣ ስልጣኑን የያዘው ወታደራዊ መንግሥት ነው። በሌላ መልኩ ደግሞ የሲቪል መንግሥት አለ። ምናልባትም እኛ መልካም ግንኙነት ይኖረናል ተብሎ የተገመተው ከሲቪሉ መንግሥት ጋር ነበር። ወታደራዊው መንግሥት ግን ስልጣን እንደያዘ ቀጥታ የሄደው ወደግብጽ ነው። ስለዚህ የሚሻለው ተመልሰን ሂደቶቻችንን መገምገም ያለብን ይመስለኛል። ከዚያ በፊት ያደርግናቸውን ግንኙነቶች አሁን ላይ መገምገም ይጠበቅብናል የሚል እምነት አለኝ።
አዲሱ የሱዳን መንግሥት ደግሞ ከግብጽ ጋር ከአበረ በኋላ ቀደም ሲል የሱዳኑ ፕሬዚዳንት አልበሽር ኢትዮጵያ የተጣለብኝ ማዕቀብ እንዲነሳልኝ ትረዳኛለች እንዲሁም ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ያለኝን ግንኙነት ታጠናክርልኛለች የሚል እምነት ነበራቸው። ነገር ግን አሁን የመጣው መንግሥት ደግሞ እንዲህ አይነቱን ኃላፊነት ሙሉ ለሙሉ የሰጠው ለግብጽ ነው።
ግብጽ ደግሞ የተሰጣትን ኃላፊነት ለመወጣት እንደቀብድ የያዘችው ሱዳኖች በህዳሴ ግድቡ ላይ ያላቸውን አቋም ደግፈው እንዲቆሙ ቃል ማስገባት ነበረባቸውና በዛ መልኩ ነው ወደፊት እየሄዱ ያለው ይመስለኛል።
ሌላው አዲሱ መንግሥት በተለይ የቀድሞው ፕሬዚዳንት አልበሽር የሚደግፏቸውን ነገር የመቃወም፣ እርሳቸው የሰሯቸውን ነገሮች የማበላሸትና የቀረቧቸውን ሰዎችም ሆኑ አገራትን የመቃወም ብሎም የማራቅ ሥራ ነው እየሰራ ያለው። ከዚህም የተሳሳተ አካሄዳቸው ነው ችግር የሚፈጠረው። አሁንም ቢሆን በኢትዮጵያ በኩል በተቻለ መጠን በደንብ መሰራት አለበት። ሱዳንን ከወታደራዊ መንግሥት ብቻ ሳይሆን የሱዳን ህዝብ ለኢትዮጵያ ያለው አመለካከት በጣም የተለየ ነው። ስለዚህ ከህዝብ ጋር ትብብርን የመፍጠርን ሁኔታ ማመቻቸቱ ተገቢ ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፡- አሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ እያሳደረች ካለው ጫና እና ከጣለችው እቀባ በመነሳት በቀጣናው አካባቢ ስጋት ይነግሳል የሚሉ አካላት አሉ፤ በዚህ ላይ ደግሞ የሱዳንም የግብጽ ሁኔታ ታክሎበት መጓዙ ተጽዕኖውን የሚያበረታ እንደመሆኑ በምን አግባብ ነው ስጋቱን መቅረፍ የሚቻለው ይላሉ?
አቶ ፈቅአህመድ፡- በእርግጥ ጫናው አለ፤ ይህም ይቀጥላል። ሁሌም ቢሆን ስጋትም ሆነ ፍጥጫ ይኖራል። ነገር ግን የዚያን ያህል ደግሞ አብረውን ያሉ አካላት ኃላፊነት የሚሰማቸው ከሆነ ወደባሰ አቅጣጫ የምንሄድ አይመስለኝም። ምክንያቱም እጣ ፈንታችን የተሳሰረ ነው። ከተባበርን አብረን ማደግ እንችላለን። ካልተባበርንና ከተጋጨን ግን ሁላችንም የምናጣው ነገር ይኖራል። የሚታጣው ነገር መጠን ሲለካ ግን የሚብሰው በእነሱ በኩል ነው። ስለዚህ ይህንን በአግባቡ ካስተዋሉት ነገሩን ወዳላስፈላጊ አቅጣጫ ይወስዱታል የሚል እምነት የለኝም።
አንዳንድ ጊዜ መንግሥታት ኃላፊነት ይጎድላቸውና በተለይ ወታደራዊ መንግሥታት የስልጣን ጊዜያቸውን ለማራዘም ወደግጭት የመሄዱን ነገር ይመርጡ ይሆናል። እሱ የሚሆን ከሆነ ደግሞ የመጣውን በማየት እንደአመጣጡ መልስ የሚሰጥ ይሆናል ብዬ አስባለሁ። በእርግጥ ወደእዛ የሚሄድ ከሆነ ግን በመጨረሻ የጉዳቱ ሰለባ የሚሆኑት እነርሱ ናቸው። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ውሃው የሚሄደው ከእኛ ዘንድ በመሆኑ ነው። በኢትዮጵያ ውሃ ላይ እድገታቸው፣ እጣፈንታቸው የተመሰረተ በመሆኑና የድርቅ ሰለባ ስለሚሆኑ ይህንን አሳምረው የሚያውቁት ይመስለኛል። ይህን በአግባቡ የማያውቁ ከሆነ ግን በእኛ በኩል በደንብ በባለሙያ ተተንትኖ ቢቀርብላቸው የተሻለ ይመስለኛል። እነርሱ ወደዛ እንዳይሄዱ የሚከለክሉ መረጃዎች በደንብ ተዘጋጅቶ መለቀቅ ያለበት ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፡– እንደሚታወቀው የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱን የፈረሙት እስካሁን አራት አገራት ናቸው፤ በቅርቡ ደግሞ ደቡብ ሱዳንም ኬንያም እንፈርማለን በማለት ላይ ናቸውና ኢትዮጵያ ከዚህ አንጻር አገራት ወደማጽደቁ እንዲገቡ ምን ያህል እየሰራች ነው?
አቶ ፈቅአህመድ፡– ሰሞኑን የተወሰኑ እንቅስቃሴዎች እንዳሉ ማስተዋል ችያለሁ። እንደተባለውም ደቡብ ሱዳንና ኬንያ አካባቢ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች በመሰራት ላይ ናቸው። ከእነዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ቡሩንዲም አለች። በተለይ ኬንያ ሌላ ፍላጎት አላት። ያንን ፍላጎቷን በማሳካት ስምምነቱን እንድታጸድቅ ማድረግ ተመራጭ ነው። እንደሚታወቀው ደግሞ አራት አገራት አጽድቀውታል፤ የሚጠበቁ ሁለት አገራት ብያጸድቁት አስገዳጅ ህግ የመሆን እድል አለው።
ደቡብ ሱዳንም የኤሌክትሪክ ኃይል ትፈልጋለች፤ በባሮና አኮቦ ተፋሰስ አካባቢ የሚጀመሩ ፕሮጀክቶች ካሉ ተስፋ ይኖራቸዋል፤ እነርሱም ያንን ተስፋ ካገኙ ወደማጽደቁ ይሄዳሉ የሚል እምነት አለኝ። በተለይ ባሮ አኮቦ ላይ የሚሰሩ ሥራዎች ደቡብ ሱዳንን በጣም ስለሚጠቅሙ በዚያ ዙሪያ አብሮ መስራት ይቻላል።
ሌላዋ ቡሪንዲ ነች፤ ከእርሷ ጋር በእርግጥ የድንበር ግንኙነት የለንም። ስለዚህ በዲፕሎማሲው ዘርፍ አንዳንድ ስምምነቶች ቢገቡ ቡሩንዲም ወደማጽደቁ ትሄዳለች የሚል እምነት አለኝ። በመሆኑም በዚህ አካሄድ ሶስቱ አገራት ስምምነቱን ካጸደቁት ጉዳዩ አስገዳጅ ይሆናል ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡– ኢትዮጵያ በተለይ ከህዳሴ ግድቡ ጋር ተያይዞ በዲፕሎማሲው ረገድ እየሄደችበት ያለው አካሄድ እንዴት ይገለጻል?
አቶ ፈቅአህመድ፡– የዲፕሎማሲው ሥራ ሲሰራ ያስቀመጣቸው ግቦች አሉት። እነዚህ ግቦች የሚለኩት በምንድን ነው የሚለው በሚገባ መታወቅ አለበት። የዲፕሎማሲው ጉዟችን ተሳክቷል ወይስ አልተሳካም የሚለውን ለመገምገም ግቡ በደንብ መታወቅ አለበት። ዋናው ነገር በእርግጥ ውጤቱ ነው፤ ውጤቱ ምን ይመስላል ካልን ደግሞ ግቦቹ መታየት መቻል አለባቸው።
ነገር ግን እኔ እንደማስበው በጣም ብዙ የሚቀረን ይመስለኛል። ከዚህ በበለጠ በጣም በብዙ መሰራት ይጠበቅበታል። በአብዛኛው በተለይ የተግባቦት ሥራ ላይ እምብዛም የተሰራ አይመስለኝም፤ ብዙ ነገሮች ታፍነው ነው ያሉት። በጣም በርካታ ሰነዶች መለቀቅ መቻል አለባቸው፤ በጣም በርካታ ምሁራን በግድቡ ዙሪያ ጥናታዊ ጽሁፎችን እያዘጋጁ መልቀቅ መቻል አለባቸው። በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ጋዜጣዊ መግለጫዎች መለቀቅ አለባቸው። አውደ ጥናቶች መዘጋጀት መቻል አለባቸው። የህዝባዊ ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎች በሰፊው መሰራት አለበት። የውሃ ዲፕሎማሲያዊ ሥራ በሰፊው መሰራት አለበት። እነዚህንና መሰል ጉዳዮችን አጠናክረን መሄድ ያለብን ይመስለኛል።
በእርግጥ በርካታ የሚሰሩ ሥራዎች እንዳሉ ይታወቃል፤ ነገር ግን የተቀናጁ አይመስለኝም። ዝም ብሎ ማስተዋል ከተቻለ የእኛ የኢትዮጵያውያን ድምጽ ድብቅ ነው። በዓለም አቀፉ ሚዲያ ላይ ስናስተውል በእኛ በኩል ከእኛ የሚወጣ ብዙ ነገር የለም። በአብዛኛው እነሱ አንድ ጉዳይ ሲያነሱ ያንን ተከትሎ የመሮጥ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ቀድሞ አጀንዳ የማስቀመጥ ነገር ቀድሞ የሚመጡ ነገሮችን አስቀድሞ በመተንበይ ምላሽ የማዘጋጀት ነገር ወይም የማክሸፍ ሥራዎች ቢሰሩ የተሻለ ይመስለኛል። በዚያ ላይ ያሉትን ክፍተቶች በመሙላት ወደፊት መሄድ ከተቻለ የተሻለ ውጤት ማምጣት ይቻላል። ምክንያቱም እኛ የምንናገረው እውነትን ነው። የምንናገረው ስለፍትሃዊነት ነው። በሳይንሳዊ መረጃ ላይ ተመስርተን ነው የምንናገረው።
በእነሱ በኩል የሚነገረው ውሸት በመሆኑ ዓለምን እያወዛገበና እያወናበደ ነው። ውሸት ከግብጾቹ በኩል ሲለቀቅ እኛ ደግሞ ያንን ውሸት በእውነት መመከት ይጠበቅብናል። ከዚህ የምናፈገፍግ ከሆነ ውጤታማ መሆን አይቻልምና በዚህ ላይ ትኩረት ማድረግ ይጠበቅብናል። በዚህ ላይ የዲፕሎማሲ ሥራ የተወሰኑ ምሁራን ወይም ፣መንግሥት ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት ነው። ሁሉም የየራሱን ድርሻ ወስዶ በግልጽ መንቀሳቀስና ባለቤት ብሎም አስተባባሪ አካል ሊበጅለት ይገባል። ይህ አስተባባሪ አካል ደግሞ ሌሎችንም የሚያበረታታ መሆን ይገባዋል።
አዲስ ዘመን፡– ለሰጡኝ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ፈቅአህመድ፡– እኔም በጣም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2013