አቤል
ባለፈው ሳምንት ከህወሓት መንደር አፈትልከው የወጡ መረጃዎች ህወሓት በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያውያን ላይ አዲስ የክፋት ሴራ እየሸረቡ መሆኑን ያመላከቱ ሆነዋል።በእርግጥ ይህ መላው ኢትዮጵያውያን ከሚያውቁት የህወሓት ባህሪ አንጻር አዲስ አስገራሚ ግኝት ነው ባይባልም ነገር ግን ህወሓት የሽብር ቡድን የተባለበትን ምክንያት ፍንትው አድርገው ያመላከቱ ነበሩ።የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከምንጮቹ ደርሶት ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ የህወሓት ትግራይን ከኢትዮጵያ ነፃ የማውጣት እቅድ ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያን በማውደም ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ነው።እስኪ ህወሓት ትግራይን ከኢትዮጵያ የመገንጠል የህወሓታውያን እቅድ በውስጡ ምን ምን ጉዳዮችን ይዟል ብለን የተወሰኑትን እንቃኝ፡-
1) በሀገር ውስጥ የክልሎች እና የብሄሮች የእርስ በርስ ብጥብጥ መፍጠር፣
2) ሆን ብሎ ከአማራ እና ከአፋር ጋር ጦርነት በመፍጠር የትግራይ ህዝብ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከአጎራባች ብሄሮች ጋር ያለው ግንኙነት እንዲቋረጥ ማድረግ፣
3) በኤርትራ መፈንቅለ መንግሥት ማካሄድ እና የኤርትራን ሉአላዊነት መጋፋት፣
4) ግብፅን የህወሓት ደጋፊ ለማድረግ አባይን እንደመደራደሪያ ማቅረብ፣
5) ለአሜሪካ እና አውሮፓ የኒኦ ሊበራሊዝም ርእዮት ፍጹም ተገዢነትን ማወጅ
እነዚህ ከህወሓት ብዙ እኩይ እና አሳፋሪ ሃሳቦች ጥቂቶቹ ናቸው።ታዲያ ከእነዚህ ሃሳቦች ኢትዮጵያውያን የማያውቁት እና ከዚህ በፊት ሲደረግ ያላዩት የትኛውን ነው ብንል መልሱ የትኛውንም የሚል ነው።እነዚህ ሃሳቦች ህወሓት በስልጣን ላይ በነበረባቸው 27 ዓመታት ሲተገበሩ የኖሩ ሃሳቦች ናቸው።ተግባሮቹ በጥቅሉ ሲደመሩ የሚሰጡት ትርጉም ግን ህወሓት አሸባሪ ፤ ባንዳ ፤ የስልጣን ፍቅር ያሰከረው ከሁሉም በላይ ጀግኖ ኢትዮጵያን የሚጠላ ኃይል መሆኑን ያመላክታል።ደግሞስ የእርስ በርስ ግጭትን ከማቀናበር በላይ ምን የአሸባሪነት መገለጫ ምን አለ ? የህዳሴ ግድብን ለግብፅ በእጅ መንሻነት ከማቅረብ በላይስ ምን ባንዳነት አለ ? ለኒኦ ሊበራሊዝም ጽንሰ ሃሳብ እጅ ከመስጠት በላይስ ምን የቅኝ ተገዢነት ማሳያ አለ?
የአሸባሪው ህወሓት እቅድ አስቂኝ ነው።አስቂኝ የሚሆነው ከሁለት መሰረታዊ ነጥቦች አንጻር ነው።አንደኛ ትግራይን ከኢትዮጵያ መነጠል ፍጹም ተግባራዊ ሊሆን የማይችል እቅድ ከመሆኑ አንጻር ነው።ትግራይ እና ኢትዮጵያ ትስስራቸው የስጋ እና የነፍስ ነው።ትግራይ ያለ ኢትዮጵያ ፤ ኢትዮጵያም ያለ ትግራይ ስጋ ያለ ነፍስ ፤ ነፍስም ያለ ስጋ እንደማለት ናቸው።ነፍስ ያለ ስጋ ማደሪያ እንደሌላት ፤ ስጋም ያለ ነፍስ ህላዌ እንደሌለው ትግራይ እና ኢትዮጵያ እንደዚያ ናቸው።አንዳቸውን ከአንዳቸው ለመነጠል የሚደረግ ፖለቲካዊ ቀዶ ጥገና ሁለቱንም በመግደል ይጠናቀቃል።የህወሓትን እቅድ አስቂኝ እና አሳፋሪ የሚያደርገው ሌላኛው ነገር ነፃ ሀገር ትግራይ የሚለውን ቅዥታቸውን ለማሳካት ሊሄዱበት ያሰቡበት መንገድ የቅኝ ግዛት መንገድ መሆኑ ነው። የህወሓት የሽብር ቡድን መንገድ ትግራይን ከኢትዮጵያ ገንጥሎ ግብፅ ላይ የመለጠፍ ፤ አሜሪካ እና አውሮፓ እግር ስር የማንጠፍ መንገድ ነው።መንገዱ ተጋሩን በቋሚነት የዘመናዊ ቅኝ ግዛት ባሮች የማድረግ መንገድ ነው።ነገር ግን እንዲህ ዓይነቱን አሳፋሪ እቅድ ለማቀድ ከህወሓት በላይ ማን የሚመኝ ኃይል አለ? ማንም..
አሸባሪው ህወሓት ስለ ኢትዮጵያ ያለው እኩይ ሃሳብ ዛሬ ሳይሆን ጥንትም ቢሆን የታወቀ ነው።ለዚህም ብዙ ማስረጃ መጥቀስ ይቻላል። የአሸባሪው ህወሓት ሰዎች ወደ በረሀ ሲወርዱ አንስቶ ከስልጣን እስከ ተባረሩበት ጊዜ ድረስ ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያዊነት ያላቸው ጥላቻ ስር የሰደደ ነው።የአሸባሪው ህወሓት የትግል መነሻ ዓላማ ኢትዮጵያ አልነበረችም ፤ እነሱ እንደሚሉት ትግሉ ብሄር ብሄረሰቦችን ታሳቢ ያደረገም አይደለም።ለዚህም ምስክርነት የሚሰጡት የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ናቸው።ከማንም በላይ የህወሓት ሰዎችን በማወቅ ቀዳሚ የነበሩት ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ የዛሬ 23 ዓመት በፈረንጆቹ 1999 በፕሪንስተር ዩኒቨርሲቲ ባደረጉት ንግግር ህወሓቶች ኢትዮጵያን ማዕከል ያደረገ እቅድ ፈጽሞ እንዳልነበራቸው ተናግረዋል።ነፃ ሀገር ትግራይ የሚባል እቅድ በተጨባጭ ሊሆን የማይችል እቅድ መሆኑን እንዲረዱ ለማደረግ 10 ዓመት ፈጅቶብናል ብለው ነበር ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር።አሁን አሸባሪዎቹ ህወሓታውያን ራሳቸው በቆሰቆሱት ጦርነት ተሸንፈው ወደ በረሀ ሲመለሱ ወደ በረሀ የተመለሰው አካላቸው ብቻ ሳይሆን አስተሳሰባቸውም ነውና ትግራይን የመገንጠል ያረጀ እቅዳቸውን አቧራውን አራግፈው እንደአዲስ ይዘውት ብቅ ብለዋል።የአሁኑን እቅድ ከያኔው የሚለየው ግን ብዙ ነገር አለ።ከብዙዎቹ ነገሮች አንዱ እና ዋነኛው ኢትዮጵያውያን አሁን ከምንጊዜውም በላይ የአሸባሪውን ህወሓትን እውነተኛ ማንነት የተረዱበት እና ለዚህ ዓይነቱ ተልካሻ እቅድ እጅ የማይሰጡ መሆናቸው ነው።
አሁን ከሰማነው የአሸባሪው ህወሓት እቅድ የምንረዳው የህወሓትን የክፋት መጠን ብቻ አይደለም።ይልቁንም የምንረዳው ነገር ቢኖር አሸባሪው ህወሓት ከጥፋት መንገዱ የመመለስ አዝማሚያ እንደሌለው ነው።አሸባሪ ቡድኑ የቀሰቀሰው ጦርነት የትግራይ ህዝብን እና የኢትዮጵያ ህዝብን ብዙ ዋጋ እያስከፈለ ነው።ዛሬ ላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የትግራይ ወገኖቻችን የመንግሥትን እና የዕርዳታ ድርጅቶችን እጅ የሚመለከቱበት ሁኔታ ውስጥ ገብተዋል።ብዙዎች ሞተዋል።ብዙዎች ቆስለዋል።ብዙ መሰረተ ልማት ወድሟል።ትምህርት ተቋርጧል።የክልሉ መንግሥት ሥራ ተናግቷል።የፌዴራሉ መንግሥት ለብዙ የልማት ሥራዎች ሊያውለው የሚችለውን ሀብት ለጦርነት እና እሱን ተከትሎ ለተፈጠረው ሰብዓዊ ቀውስ ማስታገሻ እያዋለ ይገኛል።ይህ ሁሉ እየሆነ ግን አሁንም የአሸባሪው ህወሓት ጀሌዎች ዛሬም እቅዳቸው ይህን ጦርነት በትግል ስም ማራዘም ነው።
በእርግጥ ለአሸባሪዎቹ ህወሓታውያን እንዲህ ዓይነቱን የእብደት ሃሳብ እንዲገፉበት የልብ ልብ የሚሰጣቸው ብዙ ፀረ ኢትዮጵያ ኃይል አለ።ይህ ኃይል ማን እንደሆነ ይታወቃል።የዚህ ኃይል ዓላማ የትግራይ ህዝብ ሰላም ልማት እና ዴሞክራሲ ፍላጎት መሳካት አይደለም።የዚህ ኃይል ፍላጎት ህወሓታውያን እንደሚመኙት ትግራይ ራሷን የቻለች ነፃ ሀገር ሆና ማየትም አይደለም።ያ ሊሆን እንደማይችል ያውቀዋል።የዚህ ፀረ ኢትዮጵያ ኃይል ዋነኛ ዓላማ አሸባሪው ህወሓትን በትሮጃን ፈረስነት ተጠቅሞ ገብቶ ኢትዮጵያን ማፈራረስ ነው።ከአሸባሪው እቅድ እንደተረዳነውም ደግሞ የትሮጃን ፈረስ ሆኖ የኢትዮጵያን ጠላቶች ለማገልገል ሙሉ ፈቃደኝነቱን አሳውቋል።አሁን ቀጣዩ ምላሽ የኢትዮጵያውያን ነው።ኢትዮጵያውያን አሸባሪው ህወሓት ሊማር እና ሊቀየር የማይችል ኃይል እንደሆነ መገንዘብ አለባቸው።አሸባሪውን በአድራሽ ፈረስነት ተጠቅምው በድርድር ስም ወደ ኢትዮጵያ ፖለቲካ እንዲመለስ የሚፈልጉትን ኃይሎች አይሆንም ማለት የኢትዮጵያውያን ድርሻ ነው።ፈረሱን ባለበት ማቆም ፤ በፈረሱ ሆድ ውስጥ የተደበቁትን አጥፊዎች ማጋለጥም እንዲሁ አስፈላጊ ነው።
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2013