
ሞገስ ተስፋ
አዲስ አበባ ፦ በቀጣዩ ምርጫ ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ እድሉን እንጠቀምበት ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባል ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ጥሪ አቀረቡ።
ወይዘሮ አዳነች ለሁለት ወራት ሲካሄድ የነበረው የብልጽግና ፓርቲ የምረጡን ቅስቀሳ የማጠቃለያ ፕሮግራም ትናንት በተካሄደበት መድረክ እንደገለጹት፣ ለእኛ አሸናፊነት ብዙ አብላጫ ድምጽ ብቻ አይደለም።ምርጫውን ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ በማድረግ ጭምር ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ ማድረግ ነው።
በዚህ ታሪካዊ የምርጫ ሜዳ እኩል ተጫውተን ህዝብ አሸናፊ የሚያደርገው ያገለግላችኋል፡፡ ወይዘሮ አዳነች፤ ኢትዮጵያ የምታሸንፈው ሁሉም ሀገሩን በማስቀደም በጋራ በመስራት ለሰላማዊና ዴሞክራሲዊ ምርጫ ሲሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያን የሚያነግሰው የሁላችንም ጥምረትና ስምረት እንደሆነ ያመለከቱት ወይዘሮ አዳነች ፤ አዲስ አበባ የሁላችንም መናገሻና አምባ ናት፣ እንደስሟ እንድታብብ የምናደርጋት ደግሞ ሁላችንም ተጋግዘን ስንሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በሦስት ዓመት ጉዟችን ውስጥ በችግሮች ተፈትነናል፣ ተምረናል፣ ልምድ አገኝተናል ያሉት ወይዘሮ አዳነች ፣ በቀጣይም ዋናው ግባችን ለሚገጥሙን ችግሮች መፍትሔ እየሰጠን በህብረብሔራዊ አንድነት ኢትዮጵያን ማበልጸግ ነው ብለዋል።
እንደ ከንቲባዋ ገለጻ፣ በብዙ ፈተናዎችና የፋይናንስ እጦት ጭምር ውስጥ ስናልፍ በአንድ በኩል ሀገር እንዳትፈርስ ለመታደግ በሌላ በኩል የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ በብዙ መልኩ ሞክረናል።አስደናቂ ውጤቶችንም አግኝተናል።ለዚህም መስቀል አደባባይ ምስክር እንደሆነም ጠቁመዋል።
እኛ ባለስልጣኖች ሳንሆን የህዝብ አገልጋይ ነን፣ ክብራችን ባለስልጣንነት ሳይሆን ህዝብን ዝቅ ብሎ ማገልገልና የደሃ እንባ ማበስ ነው።ፍትህ በማጣት የፍትህ አድራሻ የጠፋባቸው፣ የተጓደለባቸውን ፍትህ መስጠት ክብራችን ነው።ስራችን የፍትህ ጨፍላቂዎችን እያበጠርን አርነት የምታወጣውን እውነት አደባባይ ይዘን መቆም ነው ብለዋል።
ሰርቶ ሀብት ማፍራት ለአፍታም ቢሆን የማንዘነጋው ነው ያሉት ምክትል ከንቲባዋ፣ መተባበር፣ መከባበር፣ አብሮ መስራት፣ ህዝብን ማክበር ኢትዮጵያን እንደሚያበለጽግ በውጤት አይተነዋል።ከዚህ በፊት ሲሸጋገሩ የመጡ መጠነ ብዙ ውስብስብና ውዝፍ ያልተመለሱ ጥያቄዎችን ሁሉ በሶስት ዓመት መመለስ እንደማንችል አውቃችሁ ስለተረዳችሁን፣ ስላገዛችሁን ስለታገሳችሁን በሁኔታዎች ተስፋ ሳትቆርጡ ጊዜ ካገኘን እንደምንጨርስ አውቃችሁ ስለደገፋችሁን እናመሰግናለን ብለዋል።
ኢትዮጵያ ብዙ መሻገሪያ እድሎችን አግኝታ ሳትጠቀምበት እንደቀረች የጠቆሙት ወይዘሮ አዳነች፣ ብልጽግናን ለመምረጥ የማትፈልጉ፣ ለምርጫ ያልተመዘገባችሁ የከተማችን ነዋሪዎች፣ በከተማችን የምትወዳደሩና የምትፎካከሩ ፓርቲ መሪዎች፣ ደጋፊዎችና አባላት ልብ ማለት ያለብን ሀገር ከምርጫና ከፓርቲ በላይ መሆኗን ነው።ስለሆነም እስካሁን ይባላሉ፣ ይበተናሉ ብለው የሚጠብቁን ጠላቶቻችን በጋራ አሳፍረናል ይህንን በምርጫውም ልንደግመው ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ብልጽግና የምርጫውን ሰላማዊነትና ዴሞክራሲያዊነት የሚያውክ ምንም አይነት ተግባር እንደማንፈጽምም በምርጫ ቀስቀሳችን ወቅት አረጋግጠናል ብለዋል።