
ዳግማዊት ግርማ
አዲስ አበባ፡- ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከምን ጊዜውም በላይ ለአገር አንድነትና ሉዓላዊነት ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚሰራ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) አስታወቀ።
ፓርቲው ትናንት የተጠናቀቀውን የምርጫ ቅስቀሳ በማስመልከት ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ከአሁን ወዲህ የሚያደርጓቸው ማናቸውም እንቅስቃሴዎች የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገቡ፣ በሀገር አንድነትና በህዝብ ደህንነት ቅንጣት ታህልም ቢሆን የጥርጣሬ ጥላ ስር የማይከቱ ናቸው።
ምንም አይነት ጫናዎች ቢኖሩም የአገርን ሰላምና አንድነትን በማስጠበቅ ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ እንሰራለን ያለው ፓርቲው፤ ደጋፊዎቹ ሰላማዊ ሂደትን እንዲከተሉ ጥሪ አቅርቧል።ለአባላቶቹ፣ ለደጋፊዎቹና ለመላው ኢትዮጵያውያን እስካሁን ላሳዩት ፍጹም የሰከነ፣ ህጋዊና ሰላማዊ እንቅስቃሴ አመስግኗል ፤ ከምርጫው በኋላም የታየውን ኢትዮጵያዊ ጨዋነት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርቧል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ባለፉት ሦስት ዓመታት አተረፍናቸው ያላቸውን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እና ፍርድ ቤቶች የመሰሉ ተቋማት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ እና በሂደት ገለልተኝነታቸው እና የማስፈጸም ብቃታቸው እያደገ እንዲሄድ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጿል።
የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ እንደተናገሩት፤ በምርጫና በድህረ ምርጫ ወቅትም ደጋፊዎቹ ህጋዊ አማራጭን ሊከተሉ ይገባል።ፓርቲያቸው እየተንቀሳቀሰ ያለው በብዙ ጫናና ተፅእኖ ውስጥ ቢሆንም በምርጫው ሂደት ህጋዊ መንገድን መከተል ያስፈልጋል።ኢትዮጵያ ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ ምርጫው መቀጠሉ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱንም ገልጸዋል፡፡
ከምርጫው ውጤት ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ማናቸውም ቅሬታዎች መጀመሪያ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር ከዚያ ካለፈም በፍርድ ቤቶች ለመፍታት እንደሚሞክርም አመልክተዋል።በምርጫው ሰላማዊ እና ህጋዊ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን እንደሚከተልም ገልጸዋል፤ አባልና ደጋፊዎቹም ለሰላማዊ ምርጫ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የፓርቲው ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ በበኩላቸው ፤ በቅድመ ምርጫ እንቅስቃሴው ኢዜማ የተለያዩ ተጽእኖዎች ቢገጥመውም ምርጫው ሰላማዊ፣ ህጋዊና ዴሞክራያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እየሰራ ይገኛል።ፓርቲው የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በሁሉም አካባቢዎች በሰላማዊ መንገድ የኢዜማን ሃሳብ ለማህበረሰቡ ለማድረስ ሲለፉ ለነበሩ እጩዎቻቸው፣ በየደረጃው ያሉ አመራሮች፣ አባሎቹንና ደጋፊዎቹንም አመስግነዋል።
ፓርቲው በሂደት መገንባት ከሚፈልገው እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አካሄድ እና ሀገራችን አሁን ካለችበት አስቸጋሪ ሁኔታ አንፃር ህጋዊ እና ሰላማዊ ከሆኑ አማራጮች መጠቀም እንደሚያስፈልግ የገለጹ ሲሆን፤ ከሰላማዊ አካሄድ ውጪ ቅሬታዎችን ለመፍታት መሞከር እንደማያስፈልግም አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 10 ቀን 2013 ዓ.ም