
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ አበባ፡- የአረብ ሊግ በውስጡ ብዙ ችግሮችን እያሉበት በአባይ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት መፈለጉ በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት እንደሌለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ትናንት በሳምንታዊ መግለጫቸው እንዳስታወቁት፤ በህዳሴው ግድብ እና በአባይ ወንዝ ላይ የአረብ ሊግ የሚያገባው ጉዳይ የለም። ሊጉ በስሩ በርካታ ችግሮች ያሉበት በመሆኑ እነሱን ለመፍታት ማተኮር እንጂ ወደ ህዳሴው ፊቱን ማዞሩ ተቀባይነት የለውም።
የአረብ ሊግ በደጁ 1000 ችግሮች እያለ ወደ አባይ ግድብ መዞሩ ተቀባይነት የለውም ያሉት አምባሳደር ዲና፤ ስለአባይ ወንዝ የሚያገባቸው እና ባለቤት የሆኑት የተፋሰሱ ሀገራት ብቻ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ኢትዮጵያ በእርሷ የተፈጥሮ ሀብት እንዳትጠቀም የሚከለክላት ነገር እንደሌለ አቋም ይዘዋል ያሉት አምባሳደር ዲና ፣ ይህን መርህ በመከተል ኢትዮጵያም በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ የወንዙን አጠቃቀም እንደምትደግፍ አስታውቀዋል።
አምባሳደር ዲና እንዳስታወቁት፤ የአረብ ሊግ በህዳሴው ግድብ ላይ የሚሰጥ መግለጫም ሆነ አቋም የግብጽን ዓላማ ለማሳካት ነው። አረብ ሊግም የግብጽን ፍላጎት ለማሳካት በሚል የአባይ ወንዝን የመጠቀም መብት የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ብቻ አስመስሎ ያወጣው መግለጫ አግባብ አይደለም።
ግብጽም በአረብ ሊግም ሆነ በተለያየ መንገድ የግድቡን ጉዳይ ዓለም አቀፋዊ በማድረግ ለፖለቲካ ጥቅም ለማዋል ትሰራለች፤ ይህ የግብጽ የተለመደ ተግባር ነው ያሉት አምባሳደር ዲና ፣ የግብጽ አካሄድ በጋራ ለመልማት የሚመች አካሄድ አይደለም። ኢትዮጵያ የያዘችው መንገድ ግን በፍትሃዊነት መልማት እንችላለን የሚል ነው ብለዋል።
በ21ኛው ክፍለ ዘመን ከአባይ ወንዝ 55 በመቶውን ግብጽ ብቻ ትጠቀምበት የሚል የማይሰራ ህግ ተግባራዊ ሊሆን አይችልም። ይህን አውቆ በጋራ ትብብር ላይ የተመሰረተ አጠቃቀምን መከተል እንደሚገባ አስታውቀዋል።
የታላቁ የህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ በመብራት እጦት ውስጥ ለሚኖሩ በርካታ ዜጎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማዳረስ የሚረዳ ነው ብለዋል።
አምባሳደር ዲና በመግለጫቸው እንዳስታወቁት፤ የተለያዩ የኢትዮጵያ ሚኒስትሮች እና አምባሳደሮች በህዳሴው ግድብ፣ በሀገራዊ ምርጫ እና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከተለያዩ የአውሮፓ እና አፍሪካ እንዲሁም የሌሎች ሀገራት መሪዎች ጋር ተነጋግረዋል። በተለይም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ ወደ ቤልጂየም፤ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ወደ ዩጋንዳ፣ ብሩንዲና ደቡብ ሱዳን አቅንተው ነበር።
በተጨማሪ የሰላም ሚኒስቴር ወይሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ የጠቅላይ አቃቤ ህግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ በየሀገራቱ ከሚገኙ መሪዎች ጋር ውይይት አድርገዋል። በውይይታቸው ወቅት በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ፣ ስልህዳሴው ግድብ እና ስለትግራይ መልሶ ማቋቋም እንዲሁም ስለአገራዊ ምርጫው አንስተው ተመካክረዋል ብለዋል።
የአረብ ሊግ አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሰሞኑን በኳታር ዶሃ በተሰበሰቡበት ወቅት በናይል ወንዝ እና ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በግብጽ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ መካከል ያለውን አለመግባባት ለመፍታት ጉዳዩ ወደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እንዲያመራ መጠየቁ ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 10 ቀን 2013 ዓ.ም