
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ አበባ፡- በዴሞክራሲ ስርዓት ውስጥ በምርጫ ወደ ሥልጣን የሚመጣና በህዝብ ዘንድ ቅቡልነት ያለውን መንግሥት ጠንካራ ኢኮኖሚን ለመፍጠር እንደሚያስችል የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ገመቹ አራርሳ አስታወቁ።
ዶክተር ገመቹ በተለይም ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ጠንካራ ኢኮኖሚ ጠንካራ መንግሥት መፍጠር የሚችል ቢሆንም ጠንካራ ኢኮኖሚ ያለጠንካራ መንግሥት ሊመሰረት አይችልም።
ጠንካራ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የማህበራዊና የፍትህ ተቋማትን መገንባት ሲቻል ጠንካራ መንግሥት ሊኖር እንደሚችል ያመለከቱት ዶክተር ገመቹ ፤ በዚህ መልኩ የተቋቋመ ጠንካራ መንግሥት ደግሞ በኢኮኖሚው ዕድገት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላል ብለዋል።
ጠንካራ መንግሥት መመስረት የሚቻለው ዴሞክራሲያዊ የሆነ ምርጫ በማካሄድ ነው ያሉት ዶክተር ገመቹ ፤ በምርጫ ጠንካራ መንግሥትን የመመስረትና ያለመመስረት ጉዳይ በኢኮኖሚው ላይም የሚያሳድረው አስተዋጽኦ ቀላል ግምት የሚሰጠው እንዳልሆነ አመልክተዋል።
የፖለቲካ መረጋጋት በራሱ በኢኮኖሚው ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከፍ ያለ መሆኑን ያስታወቁት ዶክተር ገመቹ ፣ ከምርጫ በኋላ በህዝቡ ዘንድ ቅቡልነት ያለው መንግሥት መመስረቱን ተከትሎ አንጻራዊ የሆነ ሰላምና መረጋጋት ይፈጠራል ተብሎ የሚጠበቅ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ምርጫው የህዝቡን ትኩረት ይዞ የነበረውን የሰላምና የጸጥታ ችግር የሚቃለል እንደሚሆን ያስታወቁት ዶክተር ገመቹ፣ ከዚህ የተነሳም ህዝቡ ሙሉ በሙሉ ትኩረቱን ወደ ልማት ያዞራል፡፡ የተረጋጋ መንግስትና የተረጋጋ ፖለቲካ መኖሩን ተከትሎ በሚመጣው ሰላምና ጸጥታም አርሶ አደሩም በሙሉ አቅሙ ሙሉ ጊዜውን ተጠቅሞ ማምረት እንደሚችል፡፡ የመንግስትና የግል ድርጅቶችን ጨምሮ ፋብሪካዎችም የማምረት አቅማቸውን በሙሉ ተጠቅመው ማምረት ሲችሉ በሀገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ በጎ ተጽዕኖ መፍጠር ያስችላል ብለዋል ፡፡ በደሃ ሀገራት ላይ የፖለቲካ አለመረጋጋት ሲኖር የኢኮኖሚ መሰረት ልማት የሚወድምበት ሁኔታ መኖሩን አመልክተዋል፡፡
በምርጫ ወደ ስልጣን የሚመጣ ጠንካራ መንግሥት ሲኖር በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማበርከት ጠንካራ ኢኮኖሚ መፍጠር ይቻላል ያሉት ዶክተር ገመቹ፣ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በኢኮኖሚው ላይ የሚኖረውን ፋይዳ ከፍ ያለ መሆኑ ገልጸዋል፡፡
መንግሥት በዋናነት የሰላምና የደህንነት ሥራ በመስራት ከውስጥም ሆነ ከውጭ የሚነሱ የሰላምና ጸጥታ ችግሮችን መቆጣጠር ተቀዳሚ ተግባሩ ነው ያሉት ዶክተር ገመቹ ፣ ከዚህ ጎን ለጎንም በኢኮኖሚ ላይም ከፍተኛ ሚና እንዳለው አስታውቀዋል ።
እንደማንኛውም የግሉ ዘርፉ በኢኮኖሚው ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ መንግሥት ይሳተፋል ፤ እንደ ኢኮኖሚ ሥርዓቱ ደረጃው ቢለያይም እንደማንኛውም የግል ዘርፍ በተመረጡና የገበያ ክፍተት ባለባቸው ዘርፎች ውስጥ ተሰማርቶ ሊያመርትና ለገበያ ሊያቀርብ ይችላል ፡፡ከዚህ የተነሳም ጠንካራ መንግሥት ሆኖ መመስረቱ በኢኮኖሚው ላይ የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡
በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምርጫ ሲካሄድ ፓርቲው ያቀረበውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመረዳት የሀገሪቷን የኢኮኖሚ ችግር ሊፈታ የሚችል መሆኑን፤ የኢኮኖሚ ልማቱን እንዴት ማስኬድ እንደሚችልና ፓርቲው እያቀረበ ያለውን ፖሊሲና ስትራቴጂ ለማስፈጸም የሚያስችል ተቋማዊ አቅም ያለው መሆኑን እንዲሁም ቁርጠኝነት ያላቸው አመራሮች በፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ስለመኖራቸው በማገናዘብ ህዝቡ ምክንያታዊ ሆኖ መምረጥ ይጠበቅበታል ያሉት ዶክተር ገመቹ፤ በዚህ መንገድ ተመርጦ ወደ ሥልጣን የሚመጣው ፓርቲ መንግሥት ሲመሰርት ለህዝቡ የተሻለ ነገር በመስራት የተሻለና ጠንካራ የኢኮኖሚ ልማትን መፍጠር ይችላል ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 9 ቀን 2013 ዓ.ም