
ሸበዲኖ፦አረንጓዴ ዐሻራ ከተጀመረ ወዲህ የክልሉ የደን ሽፋን አምስት በመቶ ማደጉን የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ አስታወቁ።
በሲዳማ ክልል ሸበዲኖ ወረዳ ዲላ-አፈራራ ቀበሌ የክልሉ 3ኛው የአረንጓዴ ዐሻራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በተካሄደበት ወቅት አቶ ደስታ እንዳስታወቁት ፣ አረንጓዴ ዐሻራ ከተጀመረ ወዲህ የክልሉ የደን ሽፋን አምስት በመቶ አድጓል።
በቀጣይ 10 ዓመታት ውስጥ የክልሉን የደን ሽፋን በ2011 ዓ.ም ከነበረበት 17 በመቶ ወደ 30 በመቶ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።ለዘንድሮው መርሐ ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው 270 ሚለዮን ችግኞች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።በክልሉ በአንድ ጀንበር 15 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል መታቀዱንም አመልክተዋል።
የአንድ ሀገር ብቻ መበልጸግና መልማት ለአየር ንብረት መዋዠቅ ዋስትና ሊሆን አይችልም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ፤ለጎረቤት ሃገራት 500 ሚሊየን ችግኝ በክልል ደረጃ ለማበርከት ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
በክልሉ የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ መስፍን ቃሬ በበኩላቸው ፣የአረንጓዴ ዐሻራ ፕሮግራም ለክልላችን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ እስችለዋል ብለዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ የግብርና ምርትና ምርታማነት የጎላ አስተዋጽኦ ስላለዉ ህብረተሰቡ ከደጃፉ ጀምሮ የተለያዩ ችግኞችን በመትከል ድርሻውን ሊወጣ ይገባልም ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው፣ የአረንጓዴ ዐሻራ ዘመቻ የኢኮኖሚ ዕድገታችንን ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና እንዳለው አስታውቀዋል ።
የውጭ ጣልቃ ገብነትን መቀነስ የምንችለው ውስጣዊ አንድነታችን የተጠናከረ ሲሆን ነው ብለዋል።
የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን፣ አረንጓዴ ዐሻራ የአካባቢ ሁኔታን ከመቀየር እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ የሚፈጥረውን የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ከመከላከል ባለፈ ምርት እና ምርታማነትን ያሳድጋል ብለዋል።
የማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ እና የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ጨምሮ የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን ፣የአካባቢ፣ ደን እና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፈቃዱ በየነን ጨምሮ ከፍተኛ የፌዴራል እና የክልል የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 9 ቀን 2013 ዓ.ም