የመሰረተ ልማት ግንባታ ቅንጅት አልባ አሰራር በየአካባቢው የሚታይ እና እንደሀገር ልንፈታው ያልተቻለ ችግር መሆኑን በርካታ የዘርፉ ባለሙያዎች የሚናገሩት ጉዳይ ነው። ግንባታቸው ከተጠናቀቀ መንፈቅ ያልሞላቸውና በቢሊዮኖች ብር ወጪ የተደረገባቸው የመንገድ ግንባታዎችን በመቆፈር የውሃ፣ የቴሌ አሊያም የሌላ ተቋም መሰረተ ልማት ለመዘርጋት በሚደረግ ጥረት በርካታ የሀገር ሃብት ይወድማል። የየተቋማቱን የመሰረተ ልማት ቅንጅታዊ አሰራር ለማስተባበር የተቋቋመ የፌዴራል የተቀናጀ የመሰረተ ልማት ማስተባበሪያ ኤጀንሲ ደግሞ ችግሩን ከመከላከል አኳያ የራሱ ኃላፊነት ተሰጥቶት ወደ ስራ ከገባ ጥቂት ዓመታት ተቆጥረዋል። እኛም ከተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ አልማው መንግስት ጋር በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችንና የመፍትሄ ሃሳቦችን በተመለከተ እንዲሁም ተቋሙ እያከናወናቸው ስለሚገኙ ሥራዎች አንስተን ቆይታ አድርገናል። መልካም ንባብ ይሁንልዎ።
አዲስ ዘመን፦ ተቋሙ ከመሰረተ ልማት ቅንጅትና አስተዳደር ጋር በተያያዘ ምን አይነት ኃላፊነቶችን እየተወጣ ይገኛል?
አቶ አልማው፡– በዋነኛው ተቋሙ በአዋጅ የተሰጠው ኃላፊነት የመሰረተ ልማት ሥራዎች ማስተባበር፣ ማቀናጀትና ክትትልና ድጋፍ ማድረግ ነው። ተቋሙ የፌዴራል የተባለው በፌዴራል በጀት የሚሠሩ መሰረተ ልማቶችን መቆጣጠር እና ከካሳ ክፍያ እንዲሁም ሌሎች ፕሮጀክቶችን ከሚያጓትቱ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታትም ይሰራል።
በፌዴራል መንግሥት በጀት የሚሠሩ መሰረተ ልማቶች አብዛኞቹ የሚገኙት በገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል ነው። እነሱን በተገቢው መንገድ እየተከታተልን ቅንጅታዊ ሥራው እንዲሳለጥም እየሠራን እንገኛለን። ለምሳሌ መንገድ እየተሠራ መብራት ኃይል ምሰሶውን ባለማንሳቱ መንገዱ ከሦስት ወራት በላይ የሚቆምበት አጋጣሚ ይፈጠራል፤ ይህንን ችግር የመቅረፍ ኃላፊነት የእኛ ነው።
ሌላው በተለይም በመንገድ መሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ እያጋጠመ ያለው ችግር የተጋነነ ካሳ መጠየቅ ሲሆን፣ ይህም ሥራው እንዲጓተት እያደረገ በመሆኑ ኤጀንሲው በተለያዩ ክልልና ከተማ መስተዳድሮች የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀትና ከአመራሮች ጋር በመነጋገር ጭምር ህብረተሰቡ የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማው ለማድረግ ሰፊ ሥራ ያከናውናል።
በዚህም በካሣ ክፍያ ምክንያት ቆመው የነበሩ በርካታ የመሰረተ ልማት ሥራዎች እንዲጀመሩ ማድረግ የተቻለ ቢሆንም፤ አሁንም ህዝቡ ካለው የመሰረተ ልማት ፍላጎትና ተጀምረው ከዘገዩ ፕሮጀክቶች አንጻር ሲታይ ግን ኤጀንሲው የበለጠ ተጠናክሮ መስራት እንዳለበት ያሳያል።
አዲስ ዘመን፡– ኤጀንሲው መሰረተ ልማት ቅንጅታዊ ሥራ ለማስተባበር የሚረዳ ሀገራዊ ማስተር ፕላን ከማዘጋጀት አኳያ ምን ያህል ርቀት ተጉዟል?
አቶ አልማው፦ ለቅንጅታዊ ክንውን የአሰራር ስርዓት ዝርጋታ ወሳኝነት ስላለው ለመሰረተ ልማት ዝርጋታ የሚሆን አገራዊ የቅንጅት ማስተር ፕላን ዝግጅት እያከናወንን ይገኛል።
እንደሀገር የምንመራበት የመሰረተ ልማት ቅንጅትን ማስተር ፕላን ባለመኖሩ መሰረተ ልማት ግንባታ የሚያከናወኑ ተቋማት በተናጠል ይንቀሳቀሳሉ። ከምናስተባብራቸው ሰባት የመሰረተ ልማት ግንባታ ተቋማት መካከል ከምድር ባቡር ተቋም በስተቀር ሌሎቹ በተናጠል የተደራጀ ማስተር ፕላን አዘጋጅተው እየሰሩ አይደለም።
እኛ የተቀናጀ የመሰረተ ልማት ማስተር ፕላን ለማዘጋጀት ስንነሳ የእያንዳንዱን ተቋም ማስተር ፕላን ነበር ወስደን ሀገራዊውን ማዘጋጀት የነበረብን። በአሁኑ ወቅት ግን ተቋማቱ ስለሌላቸው እንደአማራጭ የወሰድነው ከዜሮ ተነስተን የቅንጅት ማስተር ፕላኑን ከየተቋማቱ ጋር በመተባበር እንዲዘጋጅ ማድረግ ነው። በእቅዳችን መሰረት ማስተር ፕላኑ በሶስት ዓመት ተዘጋጅቶ የሚጠናቀቅ ይሆናል።
በ2013 ዓ.ም ዘጠኝ ወራት ውስጥ ከሀገራዊ የመሰረተ ልማት የቅንጅት ማስተር ፕላን ዝግጅት 10 በመቶውን ማከናወን ችለናል፤ ይህ እቅዳችንን ሙሉ በሙሉ ያሳካንበት ሥራ ሆኗል። በዚህ ውስጥም በመጀመሪያ ደረጃ ለስራው የሚያገለግል የፕሮጀክት ፕሮፖዛል የማዘጋጀት ሥራ ይጠይቃል። የፕሮጀክት ፕሮፖዛሉን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመነጋገር ውል ተዋውለን እየሰራው ይገኛል። በቀጣዮቹ ወራት ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ማስተር ፕላኑን ለማሰራት በዓለም አቀፍ ደረጃም ጨረታ እንድናወጣ በቀጣይ የሚያስገድድ ሊሆን ይችላል፤ ይህን ጨረታ ለማውጣት ደግሞ በቅድመ ሁኔታነት ምን አይነት መስፈርቶች ያስፈልጋሉ የሚለው በአግባቡ የሚጠናው በፕሮጀክት ፕሮፖዛሉ ላይ ነው። ስለዚህ ፕሮፖዛሉ በትኩረት እንዲዘጋጅ እየተቆጣጠርን ይገኛል።
በሌላ በኩል በሁለተኛ ደረጃ መረጃዎች ከፌዴራልና ከክልል ተቋማት እንዲሁም ሁሉን አቀፍ መረጃዎችን አደራጅቶ የመተንተን ሥራ ይከናወናል። የተቋማችን መረጃ ዳይሬክቶሬት በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ የተቀናጀ መሰረተ ልማት ለመገንባት የሚረዱ ተቋማትን መረጃዎች ሰብስበዋል፤ አሁን መረጃውን በመተንተን ላይ እንገኛለን። በሶስተኛ ደረጃ ስታንዳርድ የማዘጋጀት ሥራ እየተከናወነ ነው። በዚህ መሰረት ካለፉት ወራት ዋነኛ ሥራችን ከሆነው የቅንጅት ማስተር ፕላኑ ዝግጅት አንጻር በጥሩ ሁኔታ እያስኬድነው ይገኛል።
አዲስ ዘመን ፡– አራቱ ተጻጻሪ ተቋማት እየተባሉ ጭምር በተለይ መንገድ፣ መብራት፣ ቴሌ እንዲሁም ውሃና ፍሳሽ አንዱ የሰራውን አንዱ የማፍረስ ችግር ይስተዋላል፤ ይህ በዋነኛነት ከምን የመነጨ ነው ይላሉ?
አቶ አልማው፡– በአገራችን በተለይ በከተሞች ላይ ትልቅ ችግር ሆኖ የቆየው አንዱ የሰራውን የመሰረተ ልማት ሌላኛው ተቋም የሚያፈርስበት ጉዳይ ነው። ለዚህ ችግር ትልቁ ምክንያት እንደሀገር የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ስታንዳርድ አለመኖሩ ነው። በእርግጥ ሌሎች ሀገራት ላይ ችግሩ ቢኖርም እኛ አገር ላይ ደግሞ ችግሩ የከፋ ነው።
ይህንን ችግር ደግሞ በአንድ ጊዜ ማስወገድ አይቻልም፤ ደረጃ በደረጃ ለማስወገድ ነው እኛው እየሰራን ያለነው። ለችግሩ መፍትሄ ለማበጀት በተቋማችን የውስጥ ባለሙያዎች አማካኝነት እና ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር ሁለት ወሳኝነት ያላቸውን ስታንዳርዶች አዘጋጅተን በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ምክር ቤት አጸድቀናል።
አንደኛው ሰነድ “ዩቲሊቲ ኮሪደር ስታንዳርድ” ይባላል፤ በተለይ በከተሞች የሚቀበሩ የመብራትም ሆነ የቴሌ እንዲሁም የውሃ መስመሮች የትኛው ከላይ የትኛው ከታች መሆን አለበት የሚለውን ጭምር የያዘ ነው። በምን ያህል ጥልቀትና ስፋት መቀበር እንዳለባቸው የሚዘረዝር እና ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች የተቀመሩበት ስታንዳርድ በመሆኑ ለቀጣይ ሀገራዊ የመሰረተ ልማት ቅንጅት ሥራዎች ወሳኝነት ያለው ነው።
ስታንዳርዱ ለሁሉም ገንቢ ተቋማት ተበትኖ ጭምር በመሆኑ ወደሥራ ገብቷል። ሌላኛው እና ሁለተኛው ስታንዳርድ ደግሞ “የሮድ ከቲንግ” ወይም መንገድ ሲቆፈር እና ስራው ሲያልቅ ምን አይነት ደረጃዎችን መከተል ይገባል የሚለውን የያዘ ነው።
እስከዛሬ ቴሌም ይሁን ውሃ ወይም መንገድ በተለይም የአስፓልት መንገድ ሲቆርጡ እንደፈለጉ ነው የሚቆፍሩት። ምንም እንኳን አዲስ አበባ ላይ ችግሩ የከፋ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን የተወሰኑ መሻሻሎች ታይተዋል። በስታንዳርዱ መሰረት ይበልጥ ሲሰራ ደግሞ የተሻለ ውጤት ይገኛል ብለን እንገምታለን።
ስትንዳርዱ በራሱ ተቋማት አስፓልት በስንት ስፋት ቆፍረው ስራቸውን ሲያጠናቅቁ በምን አይነት ደረጃውን የጠበቀ ምርት መድፈን እና መስተካከል አለባቸው የሚለውን መመሪያ የያዘ ነው። ስለዚህ ከዚህ በኋላ መንገዶች ሲቆፈሩ አግባብ ባለው እና የግድ ለስራው በሚመች መልኩ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ተቋማችሁ ያለአግባብ አንዱ የሰራውን ሌላው በሚያፈርስበት ጊዜ የመቆጣጠር ስልጣን የለውም በሚል ብዙ ጊዜ ችግሮችን የመከላከል አቅሙ ዝቅተኛ ሆኗል፤ ይህን ችግር ለመፍታት ምን እየሰራችሁ ነው?
አቶ አልማው፦ የእኛ ተቋም ተቆጣጣሪ ተቋም አይደለም፤ ተቋሙ አቀናጅና አስተባባሪ ተቋም ነው። አዋጃችን ተቋማትን ተቆጣጥረን ቅጣት እንድናስተላልፍ አይፈቅድም። የምናስተባብረውና የምናቀናጀው ደግሞ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት ነው፤ ይህንንም እያከናወንን ይገኛል። ከዚህ ባለፈ የተለያዩ ጥናቶች እያከናወንን ነው።
ከክትትልና ድጋፍ ጋር ተያይዞ ደግሞ ፕሮጀክቶች ላይ እንሰራለን። በአገራችን 300 የሚሆኑ የመንገድ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ነው። ከነዚህ ውስጥ በተለየ መልኩ የቅንጅት ችግር አለባቸው ተብለው የተለዩ 93 ፕሮጀክቶች በአገራችን አሉ። በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ላይ የተለዩት ፕሮጀክቶች ውስጥ 70ዎቹን ተከታትለን የነበሩባቸውን ችግሮች እየፈታን ለመሄድ እጥረት እየተደረገ ነው። በተሻለ ሁኔታ ላይ እንዲገኙ የሚረዳ ድጋፍ ተደርጓል። ከዚህ ውጪ ግን መሰረተ ልማት አቅራቢዎች ሲያጠፉ የምንቀጣበት አሰራር የለንም።
አዲስ ዘመን፡– የመሰረተ ልማት ቅንጅትን ለመምራት ስታንዳርድ ካወጣችሁ ማን ተቆጣጥሮ ሊያስፈጽመው ነው? በዚህ ረገድ ከመዋቅር ጋር ተያይዞ ያለው ችግር ምኑ ላይ ነው?
አቶ አልማው፦ ተቋማችን ላይ የመዋቅር ችግር አለ የሚለው ልክ ነው። እኛም በዚህ ጉዳይ ላይ እንዲስተካከል ጠይቀናል። መዋቅራችን የማስተባበር ብቻ ሳይሆን የቁጥጥር ሥራ መስራት አለበት የሚል ፕሮፖዛል አቅርበናል።
የተቋሙ አቅም መጠናከር አለበት። ይህ ብቻ ሳይሆን ተጠሪነቱን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መሆን አለበት ብለን ነው አስተያየት የምንሰጠው፤ ያስገባነውም እንደዚያ ነው። ቀድሞ ተቋማችን ሲቋቋም ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነበር። በኋላ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሥራ ሲበዛባቸው ተጠሪነቱ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ስር መሆን አለበት ተብሎ ወደሚኒስቴሩ ወረደ። ይህ ውሳኔ ተቋሙ እንዲዳከም አንድ ምክንያት ነው የሆነው።
በሌላ በኩል አዲስ አበባ ከተማ ላይ ብዙ ሰዎችንም ግራ የሚያጋባው ጉዳይ በከተማዋ የሚከናወኑ የመሰረተ ልማት ሥራዎች የሚቆጣጠረው የእኛን አይነት ተቋም ሆኖ በከተማ አስተዳደሩ ስር የተቋቋመው መስሪያ ቤት ነው። የከተማ አስተዳደሩም ለተቋሙ የቁጥጥር ሥራ ጭምር እንዲያከናወን መብት የሰጠው በመሆኑ በመዲናዋ የተሻለ አቅም ያለው ተቋም አለ።
እኛ በአንጻሩ ትኩረታችን በፌዴራል በጀት የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ላይ ነው። አንዳንድ ጊዜ ጌጠኛ ድንጋዮችን (ኮብልስቶን) አፍርሰው ውሃ መስመር አሊያም ሌላ መሰረተ ልማት ሲቀብሩ ወደእኛ ዘንድ መጥተው የመጠየቅ ሁኔታ አለ። ይሁንና እንደዚህ አይነት ጉዳዮች በከተማ አስተዳደሩ ደረጃ ባሉ ተቋማት ነው የሚዳኙት።
ያም ሆነ ይህ ግን አሁን የወጡ ሁለት ስታንዳርዶች አስገዳጅ ናቸው። ስለዚህ ማንኛውም ተቋም ሊከተላቸው የሚገቡ ናቸው። ህጉን የማይከተል ከሆነ ግን ለሚመለከተው የፍትህ አካል የመጠየቅ መብት አለን። ተቋማችን በዋናነት የመቆጣጠር ስልጣን አልተሰጠንም ማለት ግን ችግር ሲኖር አይተን ዝም እንላለን ማለት አይደለም።
ይሄን የመሰረተ ልማት ቅንጅት ስራ ፕሮፖዛል ማን ያስፈጽመዋል የሚለው ወደፊት የሚታይ ቢሆንም ለእያንዳንዱ ተቋም ተብሎ የጸደቀ እና በሀገር ደረጃ ታምኖበት የወጣ በመሆኑ ለህጉ የመገዛት ግዴታ አለብን።
አዲስ ዘመን፡– በተለይ በከተሞች ላይ የሚከናወኑ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ላይ አንዱ የሰራውን አንዱ የማፍረስ ልምድ አሁንም አልቀነሰም፤ ኢትዮጵያ በዚህ ችግር በዓመት ምን ያህል ገንዘብ ታጣለች?
አቶ አልማው፡– አንደኛው እቅዳችን ይሄንን ጥናት ማዘጋጀት ነው። ባለመቀናጀት ምክንያት ምን ያህል ገንዘብ ይጠፋል? ምን ያህልስ ጊዜ ይባክናል? የሚለውን እያየን ነው። አንድ ፕሮጀክት ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ መጠናቀቅ ባለበት ጊዜ ባለመጠናቀቁ ምን ያህል ወጪ እያስወጣ ነው የሚለውን እናጠናለን።
ይህ አንዱ የሰራውን ሌላው እንዳያፈርሰው የሚረዳ በመሆኑ የእያንዳንዱን ፕሮጀክት አፈጻጸም አጥንቶ መለየት ያስፈልጋል። ከጊዜም ሆነ ከበጀት አንጻር ምን ያህል ተጨማሪ ያስወጡ አገራዊ ፕሮጀክቶች አሉ? የሚለውን ሰፊ ጥናት ከፖሊሲና ጥናት ምርምር ተቋም ጋር እያከናወንን ይገኛል።
ሁሉንም ፕሮጀክቶች ይዘን ሳይሆን የተወሰኑ ናሙናዎችን በመለየት የደረሰውን ኪሳራ ነው የምናወጣው፤ ጥናቱ ሲያልቅ በይፋ የምናሳውቀው ይሆናል። በእኛ በኩል ከዚህ ጋር ተያይዞ መረጃ ባይኖርም አንዳንድ ጊዜ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል የሚወጡ አንዳንድ መረጃዎች አሉ።
ከዚህ በፊት የገንዘብ ሚኒስቴር ያወጣቸው መረጃዎች ደግሞ የሁሉንም ትላልቅ ፕሮጀክቶች መረጃ የያዙ ጉዳዮች ናቸው። ከመሰረተ ልማት ቅንጅት ጋር በተተያያዘ ግን አሁን በተጨባጭ ይህን ያህል ገንዘብ ጠፍቷል ይህን ያህል ኪሳራ ደርሷል የሚለውን መናገር አይቻልም።
አዲስ ዘመን፦ ተቋማት በተናጠል ይህን ያህል ውድመት ደርሶብኛል በሚል ለእናንተ የሚያቀርቡት የኪሳራ መጠን ወይም ቅሬታ የለም?
አቶ አልማው፦ በተቋማት ረገድ ብዙውን ጊዜ ቅሬታ የሚያቀርበው እና ወደእኛ የሚመጣው የመንገዶች ባለስልጣን ነው። ባለስልጣኑ በዚህ አካባቢ መንገድ ልሰራ ብነሳም ይህን ያህል የመብራት ይህን ያህል ደግሞ የቴሌ መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎች አሉ፤ ካልተነሱልኝ መስራት አልችልም የሚል ጥያቄ ነው ያላቸው። በጥቅሉ የሚነሳው ቅሬታ የሚያሳየው ችግሩ ለጊዜና ገንዘብ ኪሳራ ይዳርገናል በሚል ነው።
ከዚህ በተለየ በመሰረተ ልማት ግንባታ ቅንጅት ችግር ምክንያት ይህን ያክል ከስረናል ወይም ተጨማሪ አውጥተናል ብለው የሚቀርቡ ቅሬታዎች የሉም። ከዚህ ቀደም ተቋማት በየእራሳቸው ነበር የሚጓዙት፤ መብራት ኃይልም ሆነ ቴሌ ሌላውም በየፊናው ይሰራል፤ አንዱ አንዱን አያዳምጠውም ነበር።
በየእራሳቸው ሲጓዙ ቢቆዩም አሁን ላይ ግን በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ላይ የተቋማቱ የጋራ እቅድ እንዲያዘጋጁ ተደርጎ በዓመት አራት ጊዜ እንገመግመዋለን። በዚህ ጊዜ አንዱ ተቋም በሌላው ላይ ቅሬታ እያረቀበ እና የሌላውን እየገመገመ የሚሄድበት አሰራር ተፈጥሮላቸዋል።
እኛም አንድ ትልቅ ነገር ተፈጥሯል ብለን የምናስበው እነዚህ ተቋማት ፊት ለፊት ተገናኝተው፤ አንዱ ለአንዱ ስራ ሂስ የመስጠት ነገር መጀመራቸው ነው። መስክ ላይ ወጥተው አንዱ ተቋም በሌላው ላይ ጉዳት ከማስከተላቸው በፊት በግምገማው ወቅት እርስ በርስ የት ላይ እንደሚሰሩ እና በምን መልክ መሆን እንዳለበት እየተወያዩ መስራት ጀምረዋል፤ ይህም የተቀናጀ መሰረተ ልማት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት መልካም ነገር ነው። ከዚህ ባለፈ ግን የኪሳራ አሊያም የጉዳት መጠኑ ይህ ነው ብሎ የመጣ የለም።
አዲስ ዘመን፦ እንደአጠቃላይ ከምትመሯቸው ሰባት የመሰረተ ልማት ግንባታና አስተዳደር ተቋማት መካከል ያልተቀናጀ አሰራር በመከተል ተደጋጋሚ ችግር እየፈጠረ ያለው ተቋም የቱ ነው የሚለውን ለመለየት ሞክራችኋል?
አቶ አልማው፦ ሁሉም የራሱን እቅድ ለማሳካት ነው የሚሮጠው እንጂ እንደሀገር ተቀናጅተን ብንሰራ ችግራችንን እየፈታን በጋራ እንስራ የሚለው አስተሳሰብ አልነበረም። የሩብ ዓመት የጋራ እቅድ መገምገም ከጀመርን በኋላ እና ፊት ለፊት እርስ በርስ ሲገናኙ ግን የሁሉም አመለካከት ወደመልካም በመቀየሩ ወደትብብር እየመራቸው ነው።
በርካታ ‹‹የሪሎኬሽን›› ወይም መሰረተ ልማቶችን ከቦታ ወደቦታ የማንቀሳቀስ ሰፊ ሥራ የነበረው መብራት ኃይል ላይ ነበር። በተለይ መንግሥት ሲሰራ እነዚህ ምሰሶዎች ይነሱልን የሚል ነበር ትልቁ የሚያነሱት ጥያቄ። መብራት ደግሞ ከፍተኛ ወጪ ከሚጠይቁ የመሰረተ ልማቶች መካከል አንዱ ነውና በፍጥነት ለመተባበር አንችልም የሚል ሃሰብ ነበራቸው።
አሁን ላይ ግን በጋራ እያቀዱ ሲሆኑ፣ ተግባብቶ የመስራት ልምዱም እየዳበረ መጥቷል፤ ኢትዮ ቴሌኮም ጋር ያለውም ሆነ መብራት ኃይልም ሆነ ሌሎች ዘንድ ያለው አስተሳሰብ ቀና ነው። አንዳንዴ ግን ውሃ መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ ችግር አለ። ውሃ ሥራዎች በፌዴራል ደረጃ ሳይሆን በክልል ደረጃ የተዋቀሩ ናቸው።
የመንገድ ፕሮጀክቶች ለመገንባት ሲታሰብ ደግሞ ዲዛይኑ የሚነካቸው የውሃ መሰረተ ልማት ሥራዎች ላይ የካሳ ክፍያ ይጠየቃል፤ በዚህ ወቅት መንገዶች የሚከፍለው ካሳ የእኛው ሀገር ገንዘብ መሆኑን ያለማወቅ ችግር ስለነበረ መጠየቅ የማይገባቸው ከፍተኛ ገንዘብ ነበር የሚጠይቁት። አሁን ላይ ግን በተደረገ ከፍተኛ ውይይት መሻሻል ታይቷል።
በመሆኑም በአሁኑ ሰዓት ይሄኛው ተቋም አልተቀየረም፤ ይሄኛው ድርጅት የተለየ ችግር አለበት ማለት ባይቻልም ሁሉም ላይ ግን ከመሰረተ ልማት ቅንጅታዊ አሰራር ጋር በተያያዘ በጎ ለውጦች እየታዩ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡– በቅርቡ አዲስ አበባ ውስጥ ሰፋፊ የውሃ መፍሰሻ ትቦዎችን ለመቅበር በሚደረግ ጥረት የየሰፈሩን የመንገድ ግንባታዎች የማፍረስ ችግር ታይቷል፤ ይህን ቅንጅት አልባ አሰራር ማነው መመልከት ያለበት?
አቶ አልማው፡– አሁን ላይ እንግዲህ በተለይ የእኛ ተቋም አዲስ አበባን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቅንጅትና ቁጥጥር ባለስልጣን ስላስረከብን ከተማዋ ላይ ያሉትን ችግሮች ቆጥሬ አልያዝኳቸውም። አሁን የሚነሱ ችግሮች እንደሚኖሩ ግን እኔም እርግጠኛ ነኝ።
የውሃ እና ፍሳሽ ፕሮጀክቶችም በአብዛኛው በክልል እና በከተማ አስተዳደር በጀት እና ቁጥጥር የሚከናወኑ በመሆናቸው ብዙዎቹን ስራዎች የከተማ አስተዳደሩ አሊያም የክልል መስተዳድር ቢሮዎች ናቸው የሚከታተሏቸው። ስለዚህ እኛ ዘንድ ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ ዝርዝር መረጃ የለም።
አዲስ ዘመን፦ እንደአጠቃላይ ካየነው ኤጀንሲው ከተቋቋመበት አላማ አንጻር ሲታይ የሚጠበቅበትን ተወጥቷል ማለት እንችላለን?
አቶ አልማው፦ እንደማንኛውም የመንግሥት ተቋም ጉድለቶች ይኖሩናል። በተለይ ኤጀንሲው አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሲቋቋምም በደንብ ምንድን ነው መስራት ያለበት፤ ምን ያክል የሰው ኃይል ያስፈልገዋል፤ እንዴት ነው አደረጃጀቱ መሰራት ያለበት የሚለካውን በደንብ ተለይቶ አይያያዘም ነበር ሲቋቋም።
ይሄ በመሆኑ ወደሥራ ሲገባ በርካታ ክፍተቶች ገጥመውናል። በተለይ ደግሞ አደረጃጀቱ ትንሽ ደከም ያለ ስለሆነ ባለሙያዎችን ከገበያው ላይ በምንፈልገው ልክ ማግኘት አልቻልንም። ሥራው ትልቅ ልምድ እና እውቀት ያላቸውን ኢንጂነሮችን እና ትልልቅ ባለሙያዎችን ይፈልጋል። እኛ ደግሞ በአብዛኛው የቀጠርናቸው ጀማሪ ሰራተኞች አሊያም የዩኒቨርሲቲ ምሩቃንን ነው።
የፌዴራል የተቀናጀ የመሰረተ ልማት ማስተባበሪያ ኤጀንሲ በሚያስፈልገው ልክ ባለመደራጀቱ ደግሞ የሚጠበቅበትን ኃላፊነቶች ተወጥቷል ብሎ መውሰድ አይቻልም፤ ጉድለቶችም አሉበት። በሁለተኛ ደረጃ ትልቁ ፈተና የሚገጥመን እኛ የምናስተዳድራቸው ተቋማት ግዙፍ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ነው።
የምናስተባብራቸው ተቋማት መካከል ለአብነት ማንሳት ቢቻል ምድር ባቡርም ቢሆን ኢትዮ ቴሌኮም እና መብራት ኃይል እንዲሁም ሌሎቹም በቢሊዮኖች ገንዘብ ያላቸው እና ከፍተኛ ፕሮጀክቶችን የሚገነቡ ተቋማት ናቸው። ከዚህ ባለፈም ረጅም ዓመታትን ያስቆጠሩ ተቋማት ናቸው። የእኛ ኤጀንሲ ደግሞ ገና አምስት ዓመት ያልሞላው እና አቅሙ ያልተጠናከረ በመሆኑ ድርጅቶቹን ለማስተባበር ያለው አቅም ምን ያህል ነው ብሎ መጠየቅ ቢቻል አስቸጋሪ መሆኑን መረዳት ይቻላል።
እንደአጠቃላይ ግን ኤጀንሲው ሙሉ ለሙሉ ተልእኮውን ተወጥቷል ባይባልም ጥሩ መሻሻሎች እንዲመጡ አድርጓል። የመሰረተ ልማት ቅንጅታዊ አሰራር የሚመራበት ሰነድ ማዘጋጀቱ በራሱ አንድ በጎ ተግባር ነው። ታስቦ እንኳን የማያውቀውን ነገር እንደሀገር አስተዋውቀን ወደሥራ አስገብተናል።
ይህ ሰነድ እንዴት ተተገበረ? ምንስ ውጤት አመጣ? የሚለውን ደግሞ በሚቀጥለው በጀት ዓመት የምንመለከተው ይሆናል። እስካሁን ባለው ግን የሰራናቸው መልካም ሥራዎች እንዳሉ መዘንጋት የለበትም።
አዲስ ዘመን፡– ከመሰረተ ልማት ቅንጅታዊ አሰራር ጋር በተያያዘ የጎረቤት ሀገራትንም ሆነ ያደጉ ሀገራትን ልምድ ለመቀመር ምን አይነት ጥረት አድርጋችኋል?
አቶ አልማው፦ አገራዊን የመሰረተ ልማት ቅንጅታዊ አሰራር የሚመራ ስታንዳርድ ስናዘጋጅ ከአፍሪካም ሆነ ከአፍሪካ ሀገራት ውጪ በአደጉ አገራት ያለውን ልምድ ቃኝተናል። በምን አይነት የጥራት መስፈርት እና የደረጃ ልኬት ነው የሚለውን በሙያዊ ትንተና ተመልክተነዋል።
የተቀመሩ የጥናት ውጤቶችን እንዲሁም ተሞክሮዎችን ደግሞ ወደእኛ ሀገር በሚመጥን መልኩ ቀይረን ነው ያዘጋጀነው። ምክንያቱን እንደነሲንጋፖር ባሉ አገራት የመሰረተ ልማት ቅንጅትን የሚመራ ተቋማቸው በሚኒስቴር ደረጃ ነው የተዋቀረው። አንዳንድ ሀገራት ላይ ደግሞ በባለስልጣን ደረጃ ወይም በኤጀንሲ ሆኖ ቢዋቀርም ተጠሪነቱ ለሀገሩ መሪ ሊሆን ይችላል።
የየሀገሩ አሰራር በተለያየ ደረጃ ነው የሚገኘው፤ ይሁንና ለእኛ አገር የሚሆነውን ተሞክሮ ለመቀመር ስንሞክር እንደነዱባይ ያሉ ዘመናዊ ከተሞችን አሰራር ወስደናል። በቀጣይነትም ለእኛ ሀገር የሚበጁ ናቸው ብለን የምናስባቸውን ነገሮች በተለያዩ ሀገራት በመቀመር ለሀገርኛው በሚስማማ መልኩ ለማዋቀር ጥረት እናደርጋለን።
አዲስ ዘመን፦ በቀጣይ በጀት ዓመት በዋነኛነት ለመስራት ያሰባችኋቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው?
አቶ አልማው፦ በቀጣይ በጀት ዓመትም በዋነኛነት እንሰራበታለን ብለን የያዝነው ጉዳይ የተቀናጀ ሀገራዊ የመሰረተ ልማት ማስተር ፕላን ዝግጅት ሥራን ማስቀጠል ነው። ዘንድሮ 10 በመቶውን ሥራ አከናውነናል። በቀጣዩ ዓመት ደግሞ ከማስተር ፕላኑ ዝግጅት 40 በመቶውን ለማከናወን ነው ውጥን የያዝነው።
በሁለተኛ ደረጃ ተጨማሪ ከመሰረተ ልማት ጋር ተያይዞ የሚወጡ ሁለት ስታንዳርዶች ይኖሩናል፤ እነሱንም የማዘጋጀት ሥራ ይኖረናል። እነዚህን በተጨማሪነት አጽድቀን ወደሥራ ካስገባን በዘርፉ ያሉ ችግሮች ደረጃ በደረጃ ይፈታሉ ብለን እናስባለን።
ከዚህ ባለፈ የተቋሙን የሰው ኃይል እና የባለሙያ አቅም ማጠናከር እንዲሁም የተጠሪ ተቋማትን የመሰረተ ልማት ሥራዎች የማስተባበር ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል። በተጀመረው አግባብ መሰረተ ልማት አቅራቢ ተቋማቱን በማገናኘት እና ስለስራዎቻቸው መረጃ እንዲለዋወጡ በማድረግ አንዱ የገነባውን አንዱ እንዳያፈርስ እና ኪሳራ እንዳያስከትል የምናደርገውን ጥረት በሰፊው እንቀጥልበታለን።
አዲስ ዘመን፦ ስለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
አቶ አልማው፦ እኔም ከልብ አመሰግናለሁ።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2013