ዘመናዊ ስፖርቶች በኢትዮጵያ መታወቅና መዘውተር ከጀመሩ አንድ ምዕተ ዓመት የሚጠጋ እድሜ ማስቆጠራቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ። ይሁንና ከረጅም እድሜያቸው ጋር ሲነፃፀር እድገታቸውና ለህብረተሰቡ እያበረከቱ ያለው ፋይዳ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ይገለጻል። ለዚህም የስፖርቱ ዘርፍ የአደረጃጀትና አመራር፤ የአቅም ውስንነት ማለትም የሠለጠነ የሰው ኃይል፤ ዘመናዊና ሳይንሳዊ ሥልጠናና ማዕከላት፤ የስፖርት ፋሲሊቲ ግብዓትና የፋይናንስ እጥረት እንዲሁም የአመለካከትና አቅጣጫ ችግሮች በዋና ዋና ምክንያትነት ይጠቀሳሉ። የአገሪቱ ስፖርት ልማት የትኩረት አቅጣጫም ሰፊውን የህብረተሰብ ክፍል በስፖርት በማሳተፍ ምርጥ ስፖርተኞችን ማፍራትን ታሳቢ ያደረገ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ በተለያየ መንገድ በራሳቸው ጥረት ብቅ ያሉትን በማሰባሰብ በውድድር ስፖርቶች ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴ ማካሄድን ምርጫው ያደረገ ነው።
ምርጥና ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የሚያስችል ሰፊ መሰረት ስላልነበረውም ውጤቱ በየጊዜው ብልጭ ድርግም ሲል ቆይቷል። ለዚህም ህብረተሰቡ በስፖርት የሚያደርገው ተሳትፎ ውስን መሆን፤ የትምህርት ቤቶች ስፖርት መዳከም፤ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ትጥቅና መሳሪያዎች በበቂ ሁኔታ አለመኖር፤የሠለጠኑ ባለሙያዎች የሥልጠና ሥርዓትና ማዕከላት አለመኖር በምክንያትነት ይጠቀሳሉ። እነዚህን የአገሪቱ ስፖርት ልማት ሁነኛ ችግሮች ለማስወገድና በአዲስ አስተሳሰብና አቅጣጫ ለመምራትም የዘርፉን አደረጃጀት የተጠናከረ፤ በፖሊሲ አቅጣጫ የሚመራና የህዝብ መሰረት ያለው ለማድረግ ፖሊሲ ተቀርጿል።
ፖሊሲውም የትኩረት አቅጣጫዎች ተቀምጠውለት፤ የማስፈፀሚያ ስልቶች ተዘጋጅተውለትና አስፈፃሚ አካላት ተዋቅረውለት ሥራ ላይ ከዋለ ሁለት አስርት ዓመታትን አስቆጥሯል። በእነዚህ ሁለት አስርት ዓመታትም ምንም እንኳን ሙሉ በሙሉ ውጤታማ አፈፃፀም አልነበረውም ብሎ መናገር ባያስደፍርም ስኬታማ ውጤት አምጥቷል ማለት ፈፅሞ አይቻልም። አፈፃፀሙ በተለይ በአትሌቲክሱ ውጤታማ ከመሆን ውጪ በእግር ኳሱ ማሳየት አልቻለም። እንደሚታወቀው እግር ኳስ እጅግ ተወዳጅ ስፖርት ከሆነባቸው አገራት አንዷ ኢትዮጵያ ናት። ዜጎቿም ለእግር ኳስ ያላቸው ፍቅርና ክብር እጅጉን የላቀና ከመዝናኛነቱም አልፎ ከዕለት ኑሯቸው ጋር የተቆራኘ ነው። አገሪቱ የክለባቸውን ጨዋታ ለመታደም የምሽትና የሌት ብርድ የቀን ሃሩር ሳይበግራቸው በስታዲየም በሮች ፊት ለፊት ረዥም ሰልፎችን ከሚሰለፉት ደጋፊዎች ባሻገር የምርጥ ተጫዎቾች ባለቤትም ነች።
ክልጅነት ጀምሮ በየመንደሩ ባዶ እግራቸውን ኳስ የሚጫወቱ፤ በልበ ሙሉነት እርሳቸውን ለስፖርቱ ፍቅር አሳልፈው የሰጡ፤ ለእግር ኳስ ፍቅር የሚታመኑ ተጫዋቾች ሀብታምም ነች። በዚህ መልክ እግር ኳስ በፍቅር በሚወደድባት አገር የአገሪቱ እግር ኳስ ልማት ሲነፃፀር ግን እዚህ ግባ ተብሎ የሚወራ ታሪክና ውጤት የለውም። የእግር ኳስ ልማት አጀንዳም ፈር ሳይዝና በእቅድ፣ በሥልጠናና በባለሙያ መደገፍ አቅቶት በእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ብቻ ባለበት እየረገጠ ዓመታትን ማሳለፉንም የዘርፉ ባለሙያዎቹ ይመሰክራሉ። ከሰሞኑ ታዲያ ይህን የአገሪቱን እግር ኳስ ልማት ከተኛበት የሚቀሰቅስ ተግባር እውን ሆኗል። የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ ለምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ እግር ኳስ የሚውለውን ክፍለ አህጉራዊ ልማት ቢሮ በአዲስ አበባ ከፍቶ አስመርቋል። በሥነ ሥርዓቱ ላይም የስፖርት ኮሚሽነር ርስቱ ይርዳው፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው እንዲሁም የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን አባል ሀገራት ተወካዮችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተውበታል። የአዲስ አበባ የፊፋ ክፍለ አህጉራዊ የልማት ቢሮ በሴኔጋልና በደቡብ አፍሪካ ከከፈታቸው ክፍለ አህጉራዊ ቢሮዎች ቀጥሎ ሦስተኛው ሲሆን፤ ቢሮው ካሉት የሥራ ክፍሎች በተጨማሪ የእግር ኳስ ልማት ኃላፊ፣ የፕሮጀክት አስተባባሪ፣ የቴክኒክ፣ የዳኞች እንዲሁም የፋይናንስና ሥነ ምግባር ኦፊሰሮች ክፍሎችንም አካቷል። ከአንድ ዓመት በፊት ሊከፈት ታቅዶ በተለያዩ ምክንያቶች እውን ሳይሆን የቆየው ይህ ቢሮ፤ የቀጠናው እግር ኳስ አባል አገራት ከፊፋ ጋር በቅርበት በመስራት የእግር ኳስ ልማት ስትራቴጂዎቻቸውንና ግቦቻቸውን እንዲያሳኩ ማድረግ ዋነኛው ዓላማው ያደረገ ነው።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ መሰል አህጉራዊ ቢሮዎች በኢትዮጵያ መከፈት ለአገሪቱ እግር ኳስ ልማት ምን አስተዋፆኦ ያደርጋል? ከዚህ ተጠቃሚ ለመሆንስ ምን ተግባራት መከናወን አለባቸው? የሚሉትን ጥያቄዎች በማንሳት ባለሙያዎችን አነጋግሯል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምሀር ረዳት ፕሮፌሰር ወንድሙ ታደሰ እንደሚገልፁት፤ የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን (ፊፋ) ዋነኛ ተልዕኮ የእግር ኳስ ልማት ነው። ፊፋ የሚከተለው የስፖርት ልማት ፕሮግራም በታዳጊዎች ላይ መሰረቱን ያደርጋል፤ በእድሜ የተከፋፈለ የልማት ሥልጠና ሥርዓት ይከተላል። ይህን ዓላማ የሚያስፈፅሙለትም የየአህጉሪቱ ብሄራዊ ፌዴሬሽኖች ናቸው። የአንድ አገር የስፖርት ልማትም እንደ እድገት ደረጃው በዚህ አግባብ መራመድና መሥራት አለበት። ከዚህ ውጪ ውጤታማ መሆን አይቻለውም። «ይህ በሆነበት እኛ የምንከተለው የእግር ኳስ ልማት የለም፤ አለ ከተባለውም፤የት ነው ያለው» ሲሉ የሚጠይቁት ረዳት ፐሮፌሰር ወንድሙ፤ ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት በ1987 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ልማትን የሚመለከቱ ጥናቶች ቢሠሩም፣ ዛሬም ድረስ በዚህ ላይ ተመስርቶ የሚሠራ የለም›› ይላሉ። «የአገሪቱ ስፖርት ፖሊሲ የስፖርት ልማትን ለማገዝ የተቀመረ ቢሆንም፤ ፖሊሲውን በአግባቡ የሚያስፈፅም፤ ካልሆነም እንዴት ነው ተግባራዊ የሚደረገው ብሎ የሚጠይቅ የለም፤ በዚህም ምክንያት በአገሪቱ የስፖርት ልማት አልተሠራበትም»ይላሉ። እንደ ረዳት ፐሮፌሰሩ ገለፃ፤ በአገሪቱ የስፖርት ልማት አጀንዳ ተዘርግቶ የተሠራ ሥራ የለም። የስፖርት ልማት አስፈፃሚዎችም ቢሆኑ ቢሮ ተቀምጠው የሚሠሩ ናቸው።
በስፖርት ልማት ታዳጊዎች እየሠለጠኑ ነው ቢባልም፣ ታች ተወርዶ ሲቃኝ ተጨባጭ ውጤት አይታይም። ስፖርት አካዳሚዎችን የሚመግቡ ማዕከላት ከክልል እስክ ወረዳ ድረስ የሉም። ብሄራዊ አካዳሚውን የሚቀላቀሉትም ቢሆኑ በስፖርት ልማት አጀንዳ ተቀርፀው የመጡ አይደሉም። ይልቅስ በየክልሉ በሚካሄዱ ውድድሮች ላይ ተመርጠው የሚቀላቀሉ ናቸው። በአገሪቱ የስፖርት ልማት አጀንዳ ተዘርግቶ ባለመሠራቱም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወቅታዊ ሁኔታ፤ ክለቦቻችን በአግባቡ ማዋቀር አለመቻላችን የአገሪቱ እግር ኳስ በተለይ የፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብርም በሳይንሳዊ ቀመር ሳይሆን በግምት የሚሠራባት መሆኑን መመልከት በተጨማሪነት በቂ ምስክር ይሰጣል።
«ይህ በሆነበት የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ ለምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ እግር ኳስ የሚውለውን ክፍለ አህጉራዊ ልማት ቢሮ መክፈቱ አቅጣጫዎችን ለማመላከት፤ በተለይም የአገሪቱን የስፖርት ፖሊሲ ተከትለን እንድንጓዝ ከፍተኛ እገዛ ይኖረዋል»የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ከዚህም ባሻገር የገንዘብ ድጋፍ በተለይም ለተጨዋች፤ ለአሠልጣኝ ለክለቦች የቴክኒክ ድጋፍ ለማግኘት ሁነኛ ፋይዳ እንዳለው ያመላክታሉ። ይህን መልካም እድል ለመጠቀም ቀድሞ መገኘት እንደሚያስፈልግ የሚያስገነዝቡት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤«ቢሮውን ዓይን ዓይኑን ማየት ሳይሆን እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ማቀድ፤ ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የታዳጊዎች ልማት አጀንዳን መዘጋጀትና በጊዜ ቀመር የተዋቀረ እቅድ በመንደፍ መድረስ የሚፈለግበት ደረጃ ማስቀመጥ የግድ ይላል›› ሲሉም ይጠቁማሉ።
በአገሪቱ የስፖርት ፖሊሲ ላይ የስፖርት ልማት አጃንዳዎች በአግባቡ የተመላከቱ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ለውጥ ማምጣት ከተፈለገ የፖሊሲውን የልማት አጀንዳዎች በመቃኘት ይህን ለማስፈፀም መጣር እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባሉ። አስፈፃሚ አካላትን በሚመለክትም «በኢትዮጵያ የስፖርት ልማት አጀንዳ የማነው» የሚለው የታወቀ አልመሰለኝም የሚሉት ረዳት ፐሮፌሰሩ፤ የስፖርት ልማት አጀንዳ ቁጥር አንድ የመንግሥት ስለመሆኑ ይገልፃሉ። እንደ ረዳት ፐሮፌሰሩ ገለፃ፣ መንግሥት በስፖርቱ ልማት በሚኖረው ተሳትፎ ላይ የአመለካከት ችግሮች ይስተዋላሉ። የተማረውም ያልተማረው መንግሥት ስፖርት አካባቢ መድረስ የለበትም ሲሉ ይደመጣል። ይሁንና ለአብነት የስፖርት ማዘውተሪያ፤ ስታዲየም፣ አካዳሚ፣ ጅምናዚየም የሚገነባው በፌዴሬሽኖች ሳይሆን በመንግሥት ነው። ይህ እንደመሆኑ መንግሥት በስፖርት ልማት ዋነኛ ባለድርሻ ነው።
ይህ እንደመሆኑም መንግሥት የበኩሉን ኃላፊነት ይበልጥ መወጣት ይኖርበታል። የኮተቤ ሜትሮ ፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህር አቶ ሲያምረኝ በርሄ፤ ኢትዮጵያ የስፖርት ልማት ፖሊሲ እንዳላት ጠቅሰው፤ ይህን በማስፈፀም ረገድ በተለይ በእግር ኳሱ ልማት ምንም አለመሥራቱን ይስማሙበታል። እንደ አቶ ሲያምረኝ ገለፃ፤ በእግር ኳስ ልማት ታዳጊዎችን በመስፈርት በመመልመልና አሠልጣኞችን በማሠልጠን የማሠልጠኛ መመሪያ በማዘጋጀት ከሳይንስ ጋር ለመጓዝ ተሞክሯል። ይሁንና ስፖርቱን በበላይነት ከሚመሩ አስፈፃሚዎች ትኩረት አለመስጠትና የእግር ኳስ ልማቱን የውድድር ሥራ አድርጎ ብቻ ከማሰብ በመነጨ የአመለካከት ችግር የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አልተቻለም። ከታዳጊዎች በተጓዳኝ በወጣቶች ደረጃም የተከናወነ ተግባር የለም። ይህ በሆነበት ውጤት መጠበቅ የማይታሰብ ነው። ለዚህም ውጤቱ በቂ ምስክር ይሰጣል።
ይህ በሆነበት ፊፋ አህጉራዊ ቢሮውን በአዲስ አበባ የመክፈቱ አንድ ምክንያት«የአገሪቱ ስፖርት ልማት በተለይም እግር ኳሱን በበላይነት የሚመሩ አካላት መንግሥትን ጨምሮ ተኝታችኋል ተነሱ የሚል ደውል የሚያሰማ ነው» የሚሉት አቶ ሲያምረኝ፤ ዓላማውም ማነቃቃት፤ ማበረታታትና አገሪቱ ያላትን እምቅ አቅም እንድትጠቀም መቀስቀስ መሆኑን ነው ያመላከቱት። ከዚህ በተጓዷኝ «ኢትዮጵያ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ካፍ መስራችነትም ሆነ በዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር ፊፋ አባልነት ለስፖርቱ እድገት ካበረከተችው አስተዋፅኦ አኳያ ለአገሪቱ እውቅና እንደመስጠት እረዳዋለሁ» የሚሉት አቶ ሲያምረኝ፤ እርምጃውም አገሪቱ ያላትን እምቅ አቅም ከግምት ያስገባ መሆኑንም ይገልፃሉ።
«አገሪቱ ያላትን እምቅ አቅም ለመጠቀም የተወሰኑ ማስተካከያዎችና ድጋፎች ከተደረጉ ኢትዮጵያ በእግር ኳስ ስፖርት ከታወቁ አገራት ተርታ መሰለፍ እንደምትችል የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ» የሚሉ አቶ ሲያምረኝ፤ በዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር /ፊፋ/ አህጉራዊ ቢሮውን በመዲናዋ መክፈትም ተቋሙ በአገሪቱ ላይ የፀና እምነት እንዳለው ምስክር የሚሰጥ መሆኑንም እንደሚያስገነዝብ ይጠቅሳሉ። በአህጉራዊው ቢሮ መከፈትም፤ የሥልጠና የማማከርና ሌሎች ድጋፎችን ለማግኘት እድል የሚሰጥ በመሆኑም አገሪቱ ይህን መልካም አጋጣሚ ሳይውል ሳያድር መጠቀም እንዳለባት የሚያስገነዝቡት አቶ ሲያመረኝ፤ ይህን «ከአገሪቱ ለውጥ ጋር የመጣ መልካም እድል በቀላሉ ከማሳልፍ ይልቅ ከፌዴሬሽን ጀምሮ ትምህርት ሚኒስቴርም በትምህርት ቤቶች እንዲሁም ሌሎችን ባለድርሻ አካላት ተገቢውን ጥረት ማድረግ አለባቸው ነው»ያሉት። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ፤ የክፍለ አህጉራዊው ቢሮ መከፈት ተቋሙ ከኢትዮጵያ፣ ከምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ አባል አገራት ጋር ያለውን ቀረቤታ ይበልጥ ለማሳደግ በእግር ኳስ ልማት የተሻሉ ሥራዎች እንዲሠሩ መልካም አጋጣሚን እንደሚፈጥር ያረጋግጣሉ።
ፌዴሬሽኑ በአሁኑ ወቅት በአገሪቷ እግር ኳስ ውስጥ ያሉ ችግሮችን በመለየትና ጥናት በማድረግ ላይ መሆኑን ያስገነዘቡት ፕሬዚዳንቱ፤ የተቋሙ ቢሮ በመዲናዋ መኖርም በጅምር ላይ ያሉ የእግር ኳስ ልማት ሥራዎችን ዳር ለማድረስ አንድ እርምጃ ስለመሆኑ ነው ያስረዱት። በምርቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር ፊፋ ፕሬዚዳንት ጂያን ኢንፋንቲኖ እንደገለጹት፤ ተቋሙ የዓለም እግር ኳስ እድገት የተሟላ እንዲሆን የአፍሪካን እግር ኳስ ማሳደግ ወሳኝ ነው፤ ለዚህም ፊፋ ከአፍሪካ ጋር በትብብር እየሠራ ነው። እ.ኤ.አ በ2016 ፊፋ በጀመረው «የፊፋ ፎርዋርድ የልማት መርሃ ግብር» እግር ኳስ በመላው ዓለም እንዲያድግ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል። አዲስ አበባ የተከፈተው ለምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ እግር ኳስ የሚውለው ክፍለ አህጉራዊ ልማት ቢሮም የእዚሁ ሥራ አንዱ ማሳያ ነው። የአፍሪካ አገራት ላለፉት ሁለት ዓመታት የቀረጿቸው የእግር ልማት ፕሮጀክቶች ለአህጉሪቷ የእግር ኳስ እድገት ወሳኝ ሚና እንደሚኖራቸው ያመላከቱት ፕሬዚዳንቱ፤ ተቋማቸውም ለፕሮጀክቶቹ ስኬት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡ ከቢሮው መከፈት በተጓዳኝ ተቋማቸው በአፍሪካ እግር ኳስ ውስጥ ያለውን ሙስና ለመዋጋት፣ በስታዲየሞች ጸጥታና ደህንነት እንዲሁም በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እግር ኳስን ለማስፋፋት የሚያስችል የጋራ ስምምነት ከአፍሪካ ህብረት ጋር መፈራረሙን አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 12/2011
ታምራት ተስፋዬ