በዘመናት ውስጥ ትውልድ ሄዶ ትውልድ ይተካል።በአንድ ክፍለ ዘመን ውስጥ አራት ትውልድ ሄዶ አራት ትውልድ ይተካል።የቀዳሚው ትውልድ አሻራ ለቀጣዩ ትውልድ ትልቅ ድል እና ትርፍ ይዞ ሲመጣ፤ አንዳንዱ ትውልድ ደግሞ ለቀጣዩ ትውልድ ዕዳን አውርሶ ያልፋል።
ኢትዮጵያ እንደ አገር ከተመሰረተችበት ጊዜ ጀምሮ የተለያየ ትውልድ አልፎ የተለያየ ትውልድ ተተክቷል።መቼም የማይረሳ ለመላው ኢትዮጵያውያን የኩራት ምንጭ በመሆን ዘላለም ሲወደስ የሚኖረው፤ ጣሊያንን ያንበረከከው ለመላው አፍሪካውያን ምሳሌ የሆነው የነፃነት ፈንጣቂው ትውልድ፤ ፋሺስት ጣሊያንን ድል የነሳው ትውልድን ሳይጠቅሱ ማለፍ የማይታሰብ ነው።
በ1888 ዓ.ም የነበረው ትውልድ ጣሊያንን ድል በማድረጉ መላው ኢትዮጵያውያን ከትልቅ የማንነት ቀውስ መዳን ችለናል።ቋንቋችን አልጠፋም።ማንነታችን በነበረበት በራሳችን፤ በአባቶቻችን ምስል እንደተቀረጸ እንዲቀመጥ አግዞናል።እውነት ነው፤ ኢትዮጵያዊ ኩሩ በህልውናው የሚመጣን የማይታገስ እልኸኛ ሆኖ አሁንም ድረስ አለ።
ከአድዋ ድል በኋላ የቀጠለው እስከ አሁንም እየተሸጋገረ ዛሬ ላይ የደረሰው ትውልድ ምንም እንኳ ያ ትውልድ ያስቀመጠለትን አሻራ ተንተርሶ ድንበሩን በጠላት ባያስደፍርም፤ አገር ጠንክራ በኢኮኖሚም በልጽጋ በዕድገት ጎዳና ላይ እንድትራመድ ማድረግ አልቻለም።በእርግጥም በዛ ወቅትም የከፋ እና አገርን ለማፈራረስ ጫፍ የደረሰ የውስጥ ሽኩቻ ባይኖርም እዚና እዚያ መዋጋት መቋሰል የተለመደ ነበር።ያ በውስጥ የነበረው ትርምስ አሁንም ድረስ እንደቀጠለ፤ አገር እያሳረረ ውስጧን እየነፈረ ዛሬም ድረስ አለ።
ያደጉት አገራት ኢትዮጵያ የሄደችባቸውን በሴራ የመጠላለፍ ፖለቲካን በፍጥነት አልፈው ዴሞክራሲን ከመገንባት ባሻገር ኢኮኖሚያቸውን አሻግረው ህዝባቸውን አበልጽገዋል።
በኢትዮጵያ ግን አርቆ አሳቢነት ጠፍቶ አንዱ ተነስቶ ለስልጣን ሲል ሌላውን ሲፈጅ፤ አገር ዛሬ ላይ ደርሳለች።በተለያዩ የመንግስታት ዘመን አገር ብለው ስለአገር የቆሙ ሰዎችን በየዘመኑ የነበሩ መንግስታት ፈጅተዋቸዋል።በዚህ ሳቢያ ጦርነት አብቅቶ ኢኮኖሚን ከማሳደግ ይልቅ ያለውን የተገነባውን በማፍረስ በድህነት መማቀቅ የአገሪቱ መለያ ሆኗል።
ምንም እንኳ ለውጭ ወራሪ አንድነቱን በማሳየት በህብረት ድል የሚነሳ ቢሆንም፤ ህዝቡ ከውስጥ
ለለውጥ ለሚነሱ መንግስታት በመገዛት አገርን የማሳደግ ዝንባሌው አነስተኛ ነው።አርቆ አሳቢ የሆኑ መሪዎች ስልጣን ላይ ወጥተው ተረጋግተው አገር መምራት እና ዴሞክራሲ ማስፈን የሚችሉበት ዕድል ጠባብ ሆኖ ቆይቷል።አርቆ አሳቢ መንግስታት በሰበብ አስባቡ እንቅፋት እንዲገጥማቸው እየተደረገ በምትካቸቸው ጨካኝና እነባገነን መሪዎች በትረስልጣን እንዲይዙ ሲደረግ ቆይቷል።በዚህ የመንግስታ ስሪት ምክንያት ስልጣኑን የያዙ መንግስታትም ህዝብ ለማዳመጥ ጆሯቸውን የከፈቱ ባለመሆናቸው፤ በገጠርም ሆነ በከተማ ያለው ህብረተሰብ በድህነት እንዲማቅቅ አስገደዶታል።
የመንግስታቱ አካሄድ ያልተገባ መሆኑን በመረዳት ለመምከር፤ ለመገሰጽ፤ መንገድ ለማስያዝ የሞከሩ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ተምረው ለአገራቸው ትልቅ ነገር ማበርከት የሚችሉ ሰዎች ‹‹አርፋችሁ ቁጭ በሉ›› እየተባሉ አርፈው ቁጭ ለማለት ተገድደዋል።‹‹ተለይታ በቅላ የታየች በቆሎ አንድም ለወፍ አንድም ለወንጭፍ›› እንደሚባለው የተለየ ሃሳብ የሚያነሱ ምሁራን በሙሉ በንጉሱ ዘመንም ሆነ በደርግ ዘመን እንዲሁም በኢህአዴግ ዘመን እየተለቀሙ ንፋስ እንዳረገፈው ቅጠል ተረፍርፈዋል።
ስለዚህ የአድዋ ድል ለኢትዮጵያ ኩራት ሆኖ ሁልጊዜም የአሸናፊነት መንፈስን ማስረጽ ቢችልም፤ የመንግስታት ምሁራንን የመማገድ ጦስ ድህነታችንን እያሰፋው ዓለም በቴክኖሎጂ ላይ ተመስርቶ ኢኮኖሚውን ሲገነባ አርሰን መብላት አቅቶን በምግብ እጦት እየተሰቃየን እንገኛለን።በጦርነት ካሸነፍናቸው እና ከረታናቸው በጀግንነታችን ካንበረከክናቸው ነጮች እንደገና በውርደት ተንበርክከን ምጽዋት ለመለመን ተገድደናል።
ትውልድ በትውልድ ሲተካ ጥንካሬ እና ሀብትን ሳይሆን ስንፍና እና ዝርፍያን በመልመድ ወንድም ወንድሙን በክፋት መበደል ብቻ ሳይሆን፤ ብቸኛ መኩሪያችን የሆነች አገራችንን አሳልፎ እስከመስጠት የደረሰ ክህደት ውስጥ ገብተናል።የዜጎች ስብዕና የተዛባ እንዲሆን አገር እንድትፈርስ ለሚፈልጉ ጠላቶች በር ከፍተናል።እርስ በእርስ እየተናናቅን፣ እየተበላላን ማፈሪያ ትውልዶች ለመሆን ጫፍ ደርሰናል።እኛ በፈጠርነው ቀደዳ በመግባትም የአባቶቻችን የነጻነት ተጋድሎ ተረስቶ አንዘዛችሁ የሚሉ የውጭ መንግስታት በርክተዋል።
ምንም መካድ የማይቻለው የትናንቶቹ መሪዎች የዛሬዎቹን ወጣቶች የሀገር አሳቢና ተቆርቋሪ እንዳይሆኑ አድርገው ለመቅረጽ ሞክረዋል።የዛሬዎቹ ወጣቶች የወደፊቱን ትውልድ በምን መልክ እንቀርጸው ይሆን ? ዛሬ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ነን።አድዋን ድል እንደነሱት በታሪክ እንደሚዘከሩት ምርጥ ትውልድ ወይም ተወቃሽ ትውልድ ለመባል የተወሰኑ ምናልባትም ከወራት ያነሰ ጊዜ ቀርቶናል።
በትክክል እንደታሰበው ምርጫው በሰላም ተካሂዶ ህዝቡ የሚፈልገውን መርጦ እንደታለመው በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ መንግስት መመስረት ከተቻለ ትልቅ ድል ነው።የዴሞክራሲ መስመር በዚህ ትውልድ መሰመር ከቻለ፤ መስመሩ በደማቁ ተጽፎ ከቀጠለ ትውልዱ የዘላለም ተሞጋሽ ይሆናል።በተገላቢጦሽ ምርጫው በአግባቡ መካሄድ ካልቻለ አገር ከታመሰ እና ከተተራመሰ ህዝብ ካለቀ ትውልዱ ካለፉት በታሪክ ከሚወቀሱት በላይ ገኖ ተወቃሽ ይሆናል።ለዚህ መፍትሔው ሰላማዊ ምርጫ እንዲካሄድ ከመተባበር ጀምሮ አጠራጣሪ ነገሮችን ለጸጥታ አካል መጠቆም ሲሆን፤ የፀጥታ መዋቅር ውስጥ ያሉ አካላትም ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ አገራዊ ሃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው።ከወዲሁ የሁከትና የረብሻ አታሞ ለሚደልቁ አካላትንም ማሳፈር ከዚህ ትውልድ የሚጠበቅ ነው።
የፌዴራል መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው የክህደት ጥቃት እውን ሊሆን የቻለው በዛው በመከላከያ ውስጥ የነበሩ ከሃዲዎች የጉዳዩ ተባባሪ እና ፈፃሚ በመሆናቸው ነው።በተቃራኒው ለዕውነት እና ለአገሩ የቆመ የመከላከያ ሰራዊት አገር ከመክዳት መሰዋት ይሻለኛል በማለት ራሱን ለመስዋትነት ማዘጋጀቱ ከዚህም በላይ ጥፋት እንዳይከተል አስችሏል።እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚገባው ከማንም እና ከምንም በላይ አገር እና ህዝብ ይበልጣል።አገር ከሌለ ሰው የለም፤ ሰው ከሌለ ስልጣን የለም፤ መገዛት መግዛት፣ ዕድገት፣ ልማት ብሎ ነገር አይታሰብም።
ተወቃሽ ትውልድ ሆኖ ከማለፍ ይልቅ ተሞጋሽ ሆኖ ዘላለም መዘከር የዚህ ትውልድ መለያ መሆን አለበት።በሰላም ምርጫውን እናካሂድ፤ አባቶቻችን በህብረት ጠላትን እንዳንበረከኩት እኛም ለቀጣይ ትውልድ መሰረታዊ የዴሞክራሲ መስመርን እናስምር።በአንድነት ድህነት ላይ በመዝመት ጠንክረን በመስራት የአገራችንን ኢኮኖሚ እናሳድግ።የህዳሴው ግድብ ሁለተኛው የውሃ ሙሊት እንዲከናወን ለሀገራችን ዘብ እንቁም።ልጆቻችን ዕዳ ሳይሆን የዕድገት እርሾ እናስቀምጥላቸው።ልጆቻችን እና የልጅ ልጆቻችን በተሻለች ኢትዮጵያ የተሻለ አየር እየተነፈሱ ህይወታቸውን በቀና ጎዳና ላይ እንዲያራምዱ እያንዳንዳችን ሃላፊነታችንን እንወጣ።ሰላም!
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሰኔ 8/2013