ከ37 ቀናት በኋላ ኢትዮጵያ አንድ ትልቅ ኩነት እንደምታስተናግድ ይታወቃል፡፡ ይህም ኩነት ለአገሪቱ የወደፊት እቅድም ሆነ የልማት ስራ ዋና መሰረት መሆኑ ይታመናል፡፡ በመሆኑም በዚህ ሊሰበሰብ የሚገባው ትክከለኛ መረጃ ይታወቅ ዘንድ ተቆጣሪው፣ ቆጣሪውም ሆነ ተቆጣጣሪው አካል ትልቅ ኃላፊነት ይጠብቃቸዋል ፡፡
መንግሥት ቆጠራውን ለማካሄድ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን እየገለጸ ሲሆን፣የተለያዩ አካላትም ኩነቱን አስመልክቶ አስተያየቶችን እየሰነዘሩ ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኞች ቆጠራውን አስመልክቶ ማብራሪያ እንዲሰጡን ከኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተርና የህዝብ ቆጠራ ኮሚሽን ፀሐፊ አቶ ቢራቱ ይገዙ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡ መልካም ንባብ ይሁንልዎ፡፡
አዲስ ዘመን፡- መጋቢት ወር መጨረሻ ላይ መካሄድ የሚጀምረው የህዝብና ቤት ቆጠራ ዝግጅት ምን መልክ አለው?
አቶ ቢራቱ፡- ለአራተኛው የህዝብና ቤት ቆጠራ በአሁኑ ወቅት ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ ከቀደምት ሦስቱ ቆጠራዎች በተሻለ ሁኔታ ቆጠራውን ለማካሄድ በተጨማሪም ውጤቱም የበለጠ ጥራት ያለውና በህዝብም ዘንድ ተዓማኒ እንዲሆን እየተሰራ ነው፡፡ ተደራሽነቱም ሁሉም ቦታ የሆነና መረጃ አሰባሰቡም ላይ አንድም ሰው ሳይቆጠር እንዳይታለፍ በማድረግ በኩልም ታስቦበታል፡፡ ውጤቱ በትክክል ለኢትዮጵያውን እንዲዳረስ ታቅዶ ነው ዝግጅት እየተደረገ የሚገኘው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በማህበራዊ ሚዲያ እንዲሁም በአንዳንድ የመገናኛ ብዙሃንም ጭምር ቆጠራው በትክክል እንደማይካሄድ ከወዲሁ እንደ ስጋት እየተነገረ ነውና በእዚህ ላይ ምን አስተያየት አልዎት?
አቶ ቢራቱ፡- ዝግጅት እየተደረገ ያለው በጥቅሉ ቆጠራውን ስኬታማ በሚያደርግ መልክ ነው፡፡ ምክንያቱም እስካሁን ያደረግናቸው የቴክኒክ ዝግጅቶች ከሞላ ጎደል በመስክም ፍተሻ ስናደርግ በተሻለ ደረጃ ላይ እንደምንገኝ አመላክተዋል፡፡ ለምሳሌ ቆጠራው የሚካሄደው ሙሉ ለሙሉ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ነው፡፡ መረጃ አሰባሰቡ በታብሌት ነው፡፡ በመሆኑም የሚኖረን ሙሉ መረጃ ዲጂታል ነው፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ ለጥራት ቁጥጥር ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡
በቆጠራ ላይ ደግሞ ይከሰታሉ ተብሎ የሚጠበቁትን አላስፈላጊ ነገሮች ለምሳሌ ቁጥር የማብዛት አሊያም የመቀነስ ነገሮችን የምንቆጣጠርበትንም ስርዓት ዘርግተናል። በተለይ የቆጠራ ካርታ በተሰራ ጊዜ በቆጠራው ወቅት ህዝቡ ሳይቆጠር እንዳይቀር እንዲሁም ዳግመኛ እንዳይቆጠር አንድ የቆጠራውን ሥራ የሚያካሂድ ሰው ተከልሎ የሚሰጠው በካርታ (በጂ.ፒ.ኤስ) ስራውንም የተመጣጠነ ለማድረግ እንዲረዳ በአጭሩ በገጠር ከ100 እስከ 150 ቤተሰቦችን፣ በከተማ ደግሞ ከ150 እስከ 200 ቤተሰቦችን የያዘች የቀበሌ ክፋይ መሬት ናት፡፡ ስለዚህ ካርታው በተሰራ ጊዜ አስፈላጊው መረጃ ሁሉ እንዲሰበሰብ የሚያስችል አሰራር ዘርግተናል፡፡ ይህ በመሆኑም ቆጠራው ሲካሄድም ከዚህ ጋር ፍተሻ የሚደረግ በመሆኑ ጥራት ላይ ችግር እንደማይፈጠርና አስተማማኝነቱም የበለጠ እንዲሆን ሥራ ተሰርቷል ማለት ይቻላል፡፡
ይከሰታሉ ተብለው ከሚጠበቁትም ችግሮች ለመላቀቅና ችግሩን በተቻለ መጠን ሁሉ ለመፍታት በሚያስችል መልኩ ነው ዝግጅት ያደረግነው፡፡ አሁን ከላይ እስከታች ባለው አደረጃጀት ቆጠራው የተሻለ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የተሳካ እንደሚሆንም ይታመናል፡፡
የህዝብ ቆጠራውን በበላይነት የሚመራው የህዝብ ቆጠራ ኮሚሽንም ከፌዴራል ጀምሮ በክልልም ከዚያም ባሉ አደረጃጀቶች እስከ ታች ድረስ እየተደራጀ ስለሆነ ይህን በበላይነትና በባለቤትነትም ጭምር የመምራት ኃላፊነት ወስደዋልና በመስራት ላይ ናቸው፡፡ ስለዚህም የተሳካ ይሆናል፡፡
ያጋጥማሉ ተብለው የሚጠበቁት ጉዳዮች ደግሞ እየተለዩ ስለሆነ ለምሳሌ አልፎ አልፎ ግጭት ያለባቸው ቦታዎች ጎን ለጎን በመለየት ያን አካባቢ በምን መልክ መቁጠር እንደሚቻልም ከሚመለከታቸው የመስተዳደር አካላት ጋርና የጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ላይ ነን፡፡፡፡
ቆጠራውን ሙሉ ለሙሉ በታብሌት እናደርገዋለን ስንል ይከሰታሉ ተብለው ከሚጠበቁት መካከል አንዱ የመብራት መቆራረጥ አንዱ ነው፡፡ ይህን ሰጋት ለማስወገድ ኃይል የምንሞላበት በጸሐይ ኃይል የሚሰራ መሳሪያ በማቅረብ የኃይል ችግር እንዳያጋጥመን እናደርጋለን፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኔትዎርክ ችግር ለመፍታትም መረጃው ተሰብስቦ ኔትዎርክ ወዳለበት ወጣ በማለት መረጃውን የማስተላፍ ሥራ ይሰራል፡፡ ይህን የሚያስተባብሩም አሉ፡፡ በመሆኑም በእኛ በኩል በሚሳካ መንገድ ነው ዝግጅታችንን እያጠናከርን ያለነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በቆጠራው በኩል ሊያጋጥም ይችላል ተብሎ የተገመተው ሌላው ችግር የቴክኒክ ሲሆን፣ለዚህም መፍትሄ መቀመጡን አመላክተዋል፤ ከቴክኒክ ችግር ባሻገር ሌሎች ችግሮች ቢያጋጥሙስ ምን አይነት ዝግጅት አድርጋችኋል?
አቶ ቢራቱ፡- አገሪቱ የብሄር ብሄረሰቦች አገር ከመሆኗም በተጨማሪ የተለያዩ ኃይማኖቶችም የሚካሄዱባት ናት፤የተለያየ ባህልም ያላት አገር እንደመሆኗ የህዝብ እና ቤቶች ቆጠራ ሲካሄድ አንዳድ ቦታ ላይ ሰውን መቆጠር በራሱ እንደ መልካም የማይታይበት ሁኔታ አለ፡፡ ስለዚህ በእንደዛ አይነት አካባቢዎች ከህዝቡ ጋር ማለትም ከጎሳና ከኃይማኖት መሪዎች ጋርና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ጋር በመሰራት ማሳመን ይጠበቃል ፡፡ለህዝቡ መረጃው ጠቃሚ ስለመሆኑ በማሳወቅ መቆጠር ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ማስገንዘብና በፍላጎትም እንዲቆጠር እንዲሁም ትክክለኛ መረጃ እንዲሰጥ እየሰራን ነው፡፡
ሌሎች ተንቀሳቃሽ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች አሉ፤ ለምሳሌ አርብቶ አደር አካባቢ አስቀድመን ከክልሎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ግንኙነት እያደረግን፡፡በመሆኑም በወቅቱ በተቻለ መጠን ተንቀሳቃሽ የሆነውን የአርብቶ አደር ማህበረሰብ በቆጠራው ሰሞን ውስን ጊዜ በመሆኑ ወደመደበኛ መኖሪያቸው ወደሆነው አካባቢ መልሶ በማምጣት የሚቀጠሩበትን ስርዓት ለማበጀት በመነጋገር ላይ እንገኛለን፡፡ ይህን እያደረግን ያለነው በተለይ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ከአፋር፣ ከደቡብ፣ ከኦሮሚያ እንዲሁም ከሱማሌ ክልሎች ጋር ነው፡፡ እንዲሁም ከሌሎች ጋር በዚሁ አግባብ እየሰራን ነው፡፡
ሌላው በአሁኑ ወቅት የእኛ ስጋት በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚለቀቁት ውዥንብሮች ናቸው፡፡የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ማለት የህዝቡን ቁጥር በፆታና በዕድሜ መረጃውን ሰብስቦ እና አቀነባብሮ ውጤቱን ማቅረብ ነው፡፡ይህም በጣም ብዙ ፋይዳ አለው፡፡ለምሳሌ በአንድ አካባቢ የጤና ጣቢያዎችን እንዲሁም የትምህርት ተቋማትንም ሆነ ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለህዝብ ለማድረስ የህዝብ ቁጥርን በትትክል ማወቅ ወሳኝ ነው፡፡
በህዝብ ቆጠራ ወቅት የሚሰበሰቡት መረጃዎች ወደ 80 ያህል ናቸው፡፡ ይህም መረጃ ለወደፊቱ ለአገሪቱ የልማት እቅድም ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ በዚህም መንግሥት የአጭርም ሆነ የረጅም ጊዜ ዕቅድ ለማዘጋጀት ይጠቅማል፡፡
ይሁንና በተለያየ መልክ ከዚህ ውጭ በመውጣት ጫፍ ከነካ ብሄረተኝነት ወይም ጫፍ ከነኩ ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በማገኛኘት ውዥንብር ሊነሳ ይችላል፡፡ ስለዚህ በእኛ በኩል ማድረግ ያለብን ከመገናኛ ብዙኃን ጋር በመስራት ትክክለኛውን መረጃ መስጠት ነው፡፡ እያንዳንዱ ጥያቄ የራሱ የሆነ መረጃ ሰጪ የመሆኑን ያህል ህዝቡ ተገንዝቦ መረጃውን መስጠት ይጠበቅበታል፡፡
የህዘብ ቁጥር መረጃ የሚያገለግለው ለመንግሥት ብቻ አይደለም፡፡ ለሲቪል ማኅበረሰብ፣ መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች፣ ለህዝቡ ለራሱም ነው፡፡ በተለያየ አደረጃጀት ለሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችም ጭምር ነው፤ ምክንያቱም ሁሉን ነገር የሚሰሩት የህዝቡን ቁጥር መሰረት በማድረግ ነውና ፡፡የህዝቡን ቁጥር በስብጥር ደረጃ መታወቁ ይጠቅማል፡፡ስለዚህም የተዛባ መረጃ የሚለቁ አካላት ይህን ቢገነዘቡ መልካም ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሰላም በታጣባቸው አካባቢዎች ከቀያቸው ተፈናቅለው በተለያየ አካባቢ ተጠልለው ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች አሉና እንዴት ነው የምታስተናግዷቸው?
አቶ ቢራቱ፡- ኮሚሽኑ ውይይት ካደረገባቸው ትልቁ ነጥብ ውስጥ የህዝብና ቤት ቆጠራውን ለማካሄድ አመቺ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ጉዳይ ተጠቃሽ ነው፡፡ ሁለተኛው መቼ ቢካሄድ ነው የሚሻለው የሚለውን ገምግሟል፡፡በዚህም አምና በነበረው ችግር ምክንያት ቆጠራው ተላልፏል፤ በዚህ ዓመት ግን መተላለፍ የለበትም፤ምክንያቱም መረጃዎች በጣም እየተፈለጉ ነው፡፡ለቀጣይ ስራም የግድ ይላል፡፡ ስለዚህ አልፎ አልፎ ችግሮች ቢያጋጥሙም እነዛን ችግሮች ለመፍታት በዚህ ዓመት ቆጠራው መካሄድ አለበት የሚል ውሳኔ ላይ ተደርሷል፡፡ በዚህም ሁኔታ መቼ የሚለው ላይ ከክልሎች ጋር በመምከር መጋቢት መጨረሻ ላይ እንዲሆን ከስምምነት ላይ ተደረሰ፡፡
ይሁንና ችግሮች የሉም ማለት አይደለም፡፡ የጠቀስሺው የህዝብ መፈናቀል አለ፤አልፎ አልፎም አንዳንድ ቦታዎች የፀጥታ ችግርም አለ፡፡ ስለዚህ የሚመለከታቸው የክልልና የፌዴራል መንግሥት ችግሩ ያለባቸው ቦታዎች ላይ እንዲሰሩ አቅጣጫ የተሰጠ ሲሆን፣ቢቻል በታቸለ መጠን የተፈናቀለው ህዝብ ወደ ቀዬው ተመልሶ መደበኛ ህይወቱን ይመራል በሚል ደረጃ ማመቻቸት ነው፡፡ የጸጥታ አካላትም ከክልሎች ጋር በመሆን ችግር የሚከሰትባቸው ሁኔታዎችን በተቻለ መጠን የመቀነስ ሥራ ላይ እንዲሰማሩ በመንግሥት የተቀመጠ አቅጣጫ አለ፡፡ በአሁኑ ወቅት የነበሩ ችግሮች እየተቀረፉ ሲሆን፣ አልፎ አልፎ ብልጭ ድርግም የሚሉ ቢኖሩም ባለን መረጃ መሰረት እየተቀረፉ ነው፡፡ይህ ከተከናወነ ሁሉም ቦታ ቆጠራው ተደራሽ የሚሆን ሲሆን አልፎ አልፎ ግን ችግር የሚኖር ከሆነ እንኳ ቆጠራው መካሄድ አለበትና በተቻለ መጠን ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በመተባበር መስራት ያስፈልጋል፡፡
ተፈናቃዮች ወደቦታቸው የሚመለሱበት ሁኔታ ካልተመቻቸ ደግሞ ባሉበት ቦታ እንዲቆጠሩ ይደረጋል፡፡ምክንያቱም አንድም ሰው ሳይቆጠር አይቀርምና፤ ከየት እንደመጡ የሚያሳይ መረጃ ጭምር አብሮ ይሰበሰባል፡፡
በዩኒቨርሲቲ ያሉ ተማሪዎች ደግሞ እዛው ባሉበት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ነው የሚቆጠሩት፡፡ በወይኒ ቤት ውስጥ ያሉ ታራሚዎችም እዛው ባሉበት እንዲቆጠሩ ይደረጋል፡፡ በህዳሴ ግድብ ያሉም እዛው ባሉበት፣ በአረጋውያን መጦሪያና በህፃናት ማሳደጊያም ያሉ እንዲሁ እዛው ባሉበት እንዲቆጠሩ ይደረጋል፡፡ ቤት አልባ ሰዎችም እንዲሁ የሚያድሩበት ቦታ በመሄድ ይቆጠራሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በቆጠራው የሚሳተፉ አካላት እነማን ናቸው? ምንስ ያህል ይሆናሉ? በቂ ስልጠናስ ወስደዋል?
አቶ ቢራቱ፡- በመጀመሪያ ከሰራነው ሥራ ውስጥ የቆጠራ ቦታዎችን በካርታ መሸንሸን ነው፡፡ በአንድ ቆጠራ ቦታ ደግሞ የሚያስፈልገው አንድ ቆጣሪ ነው፡፡ በተመሰሳይ ደግሞ ቆጣሪዎቹ በትክክል ስለመስራታቸው የሚያረጋግጥ አንድ ተቆጣጣሪ አለ፡፡ በዚህ ቆጠራ ላይ በዋናነት የሚሳተፉ በእኛ አጠራር ቆጣሪዎችና ተቆጣጣሪዎች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ በዚህ መሰረት ከ150 ሺ በላይ የሚገመት የቆጠራ ቦታ ካርታ አዘጋጅተናል፡፡ በመሆኑም በዚሁ ቁጥር የሚገመት የሰው ኃይል ለቆጠራው ይሰማራል ማለት ነው፡፡
በተጨማሪ ደግሞ ከ37 ሺ በላይ የመቆጣጠሪያ ቦታዎች ተዘጋጅተዋል፡፡ በእያንዳንዱ የመቆጣጠሪያ ቦታም አንድ ተቆጣጣሪ ይመደባል፡፡ በአጠቃለይ ከአነዚህ ጋር ተደምሮ ከ190 ሺ በላይ የሰው ኃይል በቆጠራው ይሰማራል፡፡
እነዚህ ሰራተኞች በተለያየ ደረጃ ስልጠና ይሰጣቸዋል፡፡ ስልጠናውም የሚሰጠው በአራት ደረጃ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ዋናው መስሪያ ቤት ያሉ ሰራተኞች መጠይቁን ያዘጋጁና የቴክኒክ ስራውን ይነድፋሉ፤ እነዚህ ሰራተኞች በዚህ ውስጥ ተሳትፎ ያላቸው ሰራተኞችን የሚያሰለጠኑ ሲሆኑ፣ ቅድሚያ የሚሰጠው ይኸው የአሰልጣኞች ስልጠና ነው፡፡ ይህ ስልጠናም ተሰጥቷል፡፡ በዚህም 130 ሰልጣኞች ናቸው የሰለጠኑት፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ወደ 400 የሚሆኑ ለ12 ቀናት ያህል የአሰልጣኞች ስልጠና ነው እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡ እነዚህም ታብሌቱን እንዴት መጠቀም እንደሚቻል የሚያሰለጥኑ ፡፡
ይህ ስልጠና ካርታ እንዴት እንደሚካለልና ቆጠራው እንዴት እንደሚካሄድ በተግባር የሚከናወን ነው ፡፡ በቀጣይ ደግሞ በክልል ደረጃ የአሰልጣኞች ስልጠና ይኖራል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ እስከ ዘጠና ሺ ለሚጠጉ የአሰልጣኞች ስልጠና የሚሰጥ ይሆናል፡፡
በመጨረሻ መጋቢት አጋማሽ አካባቢ ወደ ቆጠራው የሚሰማሩትን ወደ 180 ሺ የሚገመቱትን አካላት ወደ 180 ሺ በሚሆነው አካባቢ ስልጠና ይሰጣቸዋል፡፡ ይህም ስልጠና ታብሌቱን በተገቢው መንገድ መጠቀም መቻል አለመቻሉን ለማረጋገጥ የሚሰጥ ስልጠና ነው፡፡
በዚህ ስልጠና ፈተና ይሰጣል፡፡ይህም ስልጠና በተግባር የሚታገዝ ነው፡፡ ስልጠናው ሲካሄድ ተጠባባቂዎችም አብረው እንዲሰለጥኑ ይደረጋል፡፡ ከመጀመሪያም ሲመለመሉ እነዚህ ተጠባባቂዎች አብረው የተመለመሉ ናቸው፡፡ በመሆኑም ፈተናውን የወደቀ ቆጣሪ በቆጠራው አይሰማራም፡፡
ቆጠራ በአስር ቀን ውስጥ ይጠናቀቃል፡፡ ይህ መረጃ ደግሞ መከናወን ያለበት ኃላፊነት ባለው አካል እንደመሆኑ ኃላፊነት የሚሰጠውም አካል ጉዳዩን በአግባቡ የማይወጣ ከሆነ ተጠያቂ ይሆናል፡፡ በመሆኑም ምልመላው የሚካሄደው ከመንግሥት ሰራተኞች መካከል ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል በዋናነት የሚሳተፉት ከመምህራን መካከል የተመለመሉ ናቸው፡፡
ቀጥሎ ደግሞ ከግብርና ሰራተኞችና ከጤና ኤክስቴንሽን መካከል የተመለመሉ ናቸው በቆጠራው የሚሳተፉት፡፡ በምልመላው ቴክኖሎጂ መጠቀም የሚችሉት ናቸው የሚካተቱት፡፡በዕድሜ ደረጃ ሲታይ ደግሞ ወጣቶችና ጎልማሶች ናቸው የሚሆኑት፡፡ በተጨማሪም በስነ ምግባራቸው ምስጉን የሆኑና በስራቸውም ትጉህ የሆኑ ሰራተኞች ናቸው፡፡የአካባቢውን ቋንቋ የሚያውቅ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ምልመላውም ላይ ትክክል ስለመሆኑ ግምገማ ይካሄዳል፡፡ በመጨረሻም ወደ ሥራ ከመሰማራታቸው በፊት ትክክለኛ ሥራ ለመስራት ቃለ መሃላ እንዲፈፅሙ ይደረጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለቆጠራው የተመደበው በጀት ምን ያህል ነው? በማንስ የተበጀተ ነው? ቆጠራውስ የሚካሄደው በስንት ቋንቋ ነው?
አቶ ቢራቱ፡- የህዝብ ቆጠራ ጉዳይን ከመጀመራችን በፊት የቆጠራውን ፕሮጀክት ሰነድ አዘጋጅተናል፡፡ በወቅቱ ማለትም ከሁለት ዓመት በፊት ለቆጠራው የተገመተው አጠቃላይ በጀት 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ አብዛኛው የሚውለው በመስክ ለሚሰማሩ ሰራተኞች የውሎ አበል ክፍያ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ለቁሳቁስ መግዢያና ተያያዥ ጉዳይ ነው፡፡
እንዲያም ሆኖ በዛሬ ጊዜና ከሁለት ዓመት በፊት ያለው ተመን እኩል አይደለም፤ ግን እያብቃቃን ለመስራት አስበን ነብር፤በመንግሥት ላይም የተለየ ጫና እንዳይፈጥር እስካሁን ባለው ሁኔታ ተጨማሪ የማፈላለግ ሥራ ስንሰራ ቆይተናል፡፡
በዚህም መጠነኛ እርዳታ አግኝተናል፡፡ ድጋፉ በቁሳቁስ አብዛኛው ደግሞ በቴክኒክ ሲሆን፣ ከአጋዦቹ መካከል ዩ.ኤን.ኤፍ.ኤ፣ ዲ.ኤፍ.አይ.ዲ፣ የአሜሪካና የጣሊያን መንግሥት ይጠቀሳሉ ፡፡ እንዲሁም የዓለም ባንክም ብድር ሰጥቷል፡፡ ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆነውን የሚሸፍነው ግን መንግሥት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ቆጠራው ከተጠናቀቀ በኋላ ይፋ የሚያደርገው ማነው?
አቶ ቢራቱ፡- ቆጠራው እንደተጠናቀቀ ወዲያው ይፋ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ሁሉም መረጃ በግርድፉ ከተሰበሰበ በኋላ ይተላለፋል፡፡ ከተላለፈ በኋላ ይመሳከራል፤ ይፈተሻል፡፡ ቀጥሎም እያንዳንዷ የ150 ሺዋ ቦታ አንድ በአንድ እንድትመሳከር ይደረጋል፡፡ ከዛም የመጣው ጥሬ መረጃ ፋይል እንዲሆን ይደረጋል፡፡ የተተነተነውና የታየም ግድፈት ካለ ተፅፎ የሚፈታበት ስርዓትም ይቀመጥና በመጨረሻ ለትንተና ዝግጁ ሲሆን የውጤት ሰንጠረዦችን የማውጣት ሥራ ይሰራል፡፡ ሰንጠረዦች ከወጡ በኋላ የሚመዘኑ ወይ የሚተነተኑ የዴሞግራፊክ ባህሪያት አሉ፡፡ ለምሳሌ የወንድና ሴት ጥምርታና ሌሎችም ይታዩና እንዲፈተሹ ይደረጋል፡፡ ሪፖርትም አብሮ ይዘጋጃል፡፡ ከተዘጋጀ በኋላ በአዋጁ መሰረት ለህዝብ ቆጠራ ኪሚሽን ከነሪፖርቱ ውጤቱ ይቀርባል፡፡ በውጤቱም ላይ ውይይት ይደረግና ሂደቱን ካለፈ በኋላ ኮሚሽኑ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀርባል፡፡ በመጨረሻ ውጤቱን ተቀብሎ ይፋ የሚያደርገው ምክር ቤቱ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ቆጠራው ከተጠናቀቀ በኋላ ውጤቱ ይፋ የሚሆነው በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ነው?
አቶ ቢራቱ፡- መረጃው ሲመሳከር ሊያጋጥም የሚችል ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ ያን ሂደት ካለፈ ግን ከአራት ወር እስከ ስድስት ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ውጤቱ ይፋ ይሆናል ብለን ነው ያሰብነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ቀደም በተደረገው ቆጠራ‹‹የብሄራችን ቁጥር አንሷል፤ የማነሱም ምክንያት ይህ ነው፤ ያ ነው እየተባለ ይነገራል፡፡ብሄራችን አይወልድም አይዋለድም ያለውስ ማነው፤›› የሚሉ አካላት አሉና ይህ እንዴት ይታያል?
አቶ ቢራቱ፡- መጀመሪያ መታወቅ ያለበት የህዝብ ቆጠራ ማለት ሰው መቁጠር ማለት ነው፡፡ በዚህ ውስጥ የሚጠየቀው እድሜ፣ ፆታ፣ ብሄርና የመሳሰለው መረጃ ነው፡፡ ይሁንና ብሄር ሲጠየቅ እኛ የማንነት ጉዳዮችን የመወሰን ስልጣን የለንም፡፡ ከተዘረዘረው መረጃ አንዱ ብሄር ነውና ባለቤቱ ሲጠየቅ ይመልሳል፤ ቆጣሪው ደግሞ ያሰፍራል፡ ፡ አንተ አማራ፣ ጉራጌ የማለት መብት ቆጣሪው የለውም፡፡ ተቆጣሪው ‹‹እኔ አንድ ብሄር ብቻ ሳይሆን እገሌና እገሌ የሚባለው ብሄር ተወላጅ ነኝ፡፡›› ካለ ሁለቱንም የማስመዝገብ አሊያም የመረጠውን ብሄር ማስመዝገብ ይችላል። ቆጣሪውም ያልተነገረውን ማስፈር አይገባውም፤ ቢያደርግ ደግሞ ተጠያቂ ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ጥቂት የማይባሉ የፖለቲካ አመራሮች እንዲሁም አንዳንድ አካላትም የራሳቸው ብሄር ቁጥር እንዲጨምር የሌላው ደግሞ እንዲቀንስ በመፈለግ የሚያደርጉት ቅስቀሳዎች አሉና ይህን እንደምን ያዩታል?
አቶ ቢራቱ፡- ኮሚሽኑ ከመንግሥት ጋር በዚህ በኩል እየሰራን ነው፡፡ ይህ በአስር ዓመት አንዴ የሚከናወን ትልቅ አገራዊ ኩነት ከሆነው ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ስራው በቴክኒክ የሚሰራ ነው። ‹‹ይህን ሙላ ያንን ቀንስ፡፡›› የሚል አካል አይኖርም፡፡ ለማንም አካል የሚጠቅመው ደግሞ በትክክል የህዝቡ ቁጥር ሲሰፍር ብቻ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ቆጠራውን የሚያካሂደው አካል ቆጠራውን ማካሄድ ያለበት ባለበት ክልል አሊያም አካባቢ ሳይሆን ወደሌላው በመሄድ ነው፤ ምክንያቱም አድልዎ እንዳይፈፀም ያግዛል የሚሉ አካላት አሉ፡፡ እርስዎ ከላይ እንደጠቀሱት ደግሞ የየአካባቢውን ቋንቋ የሚያውቁ መሆን ስላለባቸው በአካባቢያቸው መሆን እንዳለበት ነውና እዚህ ላይ አስተያየት ቢሰጡበት?
አቶ ቢራቱ፡- ቋንቋውን የሚያውቁ ሲባል የተፈለገው አድልዎ እንዲፈፅሙ ሳይሆን መረጃውን የሚሰጠው አካል ግር ሳይለው በሚያውቀው ቋንቋ መረጃውን እንዲሰጥ ስለተፈለገ ነው፡፡ በትርጉም ይሰራ ቢባል መረጃ ጠያቂውም ሆነ መረጃ ሰጪው የተናገረውን ሐሳብ ተርጓሚው በትክክል ስለመናገሩ መተማመኛ የሚሆን ነገር የለም፡፡ ጥርጣሬም ሊፈጠር ይችላል፡፡ ስለዚህ መረጃ ጠያቂውም ሆነ ሰጪው በትክክል መግባባት በሚችሉበት ቋንቋ መናገር እንዲችሉ በመታሰቡ ነው፡፡ ቆጠራው የሚከናወነው በአምስት ቋንቋዎች ሲሆን፣ ይኸውም አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ትግርኛ፣ ሱማሊኛና አፋርኛ ናቸው፡፡ ቆጣሪዎች ከየወረዳቸውና ከየዞናቸው የሚመለመሉ ስለሆነ የቋንቋ ችግር ያጋጥማል አሊያም አድልዎ ይካሄዳል የሚል ስጋት አይኖርም።
አዲስ ዘመን፡- በአንዳንድ አካባቢዎች እርዳታን ከህዝብ ቁጥር ጋር አያይዘው የህዝቡ ቁጥር ከፍ እንዲል የመፈለግ አዝማሚያ ይታይባቸዋል ይባላልና እንዲህ አይነቱን አመለካከት እንዴት ለማረም ታስቧል?
አቶ ቢራቱ፡- ልክ ነው፤ አንዳንድ ቦታ ከሌሎች ነገሮች ጋር በማገናኘት ቁጥርን የማብዛት አዝማሚያ ይታያል። በዚህ በኩል የምናስቀምጠው ነገር እኛ ቀደም ሲል የሰበሰብናቸው መረጃዎች አሉና ከእሱ ጋር የማመሳከር ሁኔታን እናካሂዳለን። የተለየ ነገር ካጋጠመን በጥልቀት እንዲታይ እናደርጋለን። መረጃው ሲጠየቅም ሌላ ቦታ ያለን አካል የሚያስመዘግቡ እንዳይኖሩ ግንዛቤ በመስጠት ጭምር በማጥራት መሰራት አለበት። ኮሚሽኑም መረጃውን ሲተነትን በቴክኒክ እይታ ከውሳኔ ጋር ለሚመለከተው አካል እናቀርባለን። ኮሚሽኑ የቴክኒክ እይታውን በራሱ መርምሮ መቀበል አሊያም እንደገና እንዲታይ የማድረግ ወይም ደግሞ ውድቅ የማድረግ ስልጣን አለው ። ምክር ቤቱም የቀረበለትን አይቶ እንዲሁ ድጋሚ እንዲታይ የማለት ስልጣን አለው።
አዲስ ዘመን፡- ቆጣሪው ተቆጣሪው የሚሰጠውን መረጃ ብቻ ነው ማስፈር ያለበት ብለዋልና ተቆጣሪው የቤተሰቡን ቁጥር ከፍ አሊያም ዝቅ አድርጎ ቢናገር እውነት ስለመሆኑ ማረጋገጫው ምንድን ነው?
አቶ ቢራቱ፡- ቆጣሪው መረጃውን ከማስፈሩ በፊት ጥያቄውን ያቀርባል። ተቆጣሪው ሲናገርም የማጥራት ሥራ ይሰራል። ልጆቹ የት እንደሆኑና አብረው ስለመኖር አለመኖራቸውም ጠለቅ ያለ ጥያቄ በመጠየቅ እያጠራ ይሄዳል። እንዳይረሳ የማውጣጣት ተጨማሪም ሰው እንዳይመዘገብ የማጥራት ሥራ በመስራት ነው መረጃውን የሚሰበስበው።
አዲስ ዘመን፡- ሰዎች ደግመው እንዳይመዘገቡ የምትጠቀሙት እንደ ጣት አሻራ አይነት የመለያ ዘዴ ይኖር ይሆን?
አቶ ቢራቱ፡- እስከማውቀው ጊዜ ድረስ የትም አገር ቆጠራ ሲቆጠር አሻራ አሊያም አይንና መሰል መለያዎች ሲወሰድ አላስተዋልኩም። ምክንያቱም የአንድን ቤተሰብ ሁሉ በአንድ ላይ ለማግኘት ምናልባት ወር ሁለት ወር ሊፈጅ ይችላል። እንደሚታወቀው ደግሞ ቆጠራ የሚካሄደው በአጭር ጊዜ ውስጥ ነው። በአንድ ወቅት ስለኖረ ሰው ነው የሚካሄደው። አንዳንድ አገሮች የተለየ መታወቂያ ይኖራቸዋል። እኛ ደግሞ እንዳለመታደል ሆኖ እሱ የለንም። በቀጣይ ጊዜ እሱ ሲኖር የተሻለ ያደርገዋል። አሁን ግን እኛ በስልጠና ጊዜ ትልቅ ትኩረት የምንሰጠው ‹‹የቤተሰብ አባል እነማን ናቸው? በምን ይገለፃል?›› በሚለው ላይ ነው። ለምሳሌ በአንድ ቤት ውስጥ በደባልነት የሚኖሩና የየራሳቸውን ምግብ አዘጋጅተው የሚመገቡ ከሆኑ እንደ ሁለት ቤተሰብ ነው የምንቆጥራቸው። በመሆኑም ያልሽውን አይነት ቴክኖሎጂ እስካሁን በአፍሪካ ውስጥም አልተደረገም። አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር ምን ያህል ይሆናል ተብሎ ነው በኤጀንሲው በኩል የተተነበየው?
አቶ ቢራቱ፡- ብዙ ጊዜ የወሊድ፣ የጤናና የመከተም ሁኔታ እንደ ግብዓትነት በመከተል ቀደም ሲል የተሰራው ትንበያ ወደ 98 ሚሊዮን ነው። ተቆጥሮ ሲመጣ ግን ጭማሬም ቅናሽም ሊያሳይ ይችላል።
አዲስ ዘመን፡- ቆጠራው የሚመለከተው ኢትዮጵያውያንን ብቻ ነው?
አቶ ቢራቱ፡- በወቅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን፣ ኢትዮጵያውያን ያልሆኑም፣ ስደተኞችም፣ የዲፕሎማቲክ ሰዎችም እንዲሁም በሌላ ሥራ ላይ የተሰማሩ የውጭ አገር ዜጎችም ይቆጠራሉ። በመጨረሻ ውጤቱ ሲገለጽ ኢትዮጵያውያንና የውጭ አገር ዜጎች ተብሎ ለሁለት ተከፍሎ ይገለጻል። በመሆኑም በኢትዮጵያ መልካምድር ክልል ውስጥ ነዋሪ የሆነ ሰው ሁሉ ይቆጠራል ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ እናመሰግናለን።
አቶ ቢራቱ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን የካቲት 12/2011
አስቴር ኤልያስ