በአማራ ክልል በርካታ የከበሩና ከፊል የከበሩ የማዕድን ሀብቶች የሚገኙ ቢሆንም ለውጪ ገበያ የሚቀርቡት ግን በአብዛኛው ወርቅና ኦፓል ናቸው። ወርቅ በብሄራዊ ባንክ በኩል ለውጪ ገበያ ሲቀርብ ኦፓል ደግሞ በህጋዊ ላኪዎች በኩል በማዕድንና ነዳጅ ሚንስቴር አልፎ ለውጪ ገበያ ይቀርባል። በዘንድሮ በጀት አመት የክልሉ የዘጠኝ ወር አፈፃፀም ከሁለቱ ማእድናት የውጪ ንግድ ከ5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል።
የአማራ ክልል የማዕድን ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ የማዕድን ስራዎች ፍቃድ አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ታዬ እንደሚሉት በዘንድሮው በጀት አመት የዘጠኝ ወር አፈፃፀም 6 ሺ 453 ኪሎግራም ጥሬ ኦፓል ወደ ውጪ ሀገር ለመላክ ታቅዶ በህጋዊ ደረጃ የይለፍ ፍቃድ ተሰጥቶ 3 ሺ 676 ነጥብ 35 ኪሎግራም ለማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ቀርቧል። ከዚህም 4 ነጥብ 38 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 1 ነጥብ 314 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ተሰብስቧል።
በሌላ በኩል ደግሞ በእደ ጥበብ ሞያተኞች እሴት የተጨመረባቸው 273 ኪሎግራም የኦፓል ምርቶችን ወደ ውጪ ሀገር ለመላክ እቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም 72 ኪሎግራም ኦፓል ብቻ ለውጪ ገበያ ቀርቧል። በገንዘብ ደረጃም 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 1 ነጥብ 104 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ተሰብስቧል። በአጠቃላይም በዘጠኝ ወሩ አፈፃፅም ከኦፓል ማእድን የወጪ ንግድ ከ 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር መሰብሰብ ተችሏል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ የዘንድሮው የክልሉ ማእድን ዘርፍ የወጪ ንግድ አፈፃፀም ከአምናው ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ሆኖ ተመዝግቧል። በህገወጥ መንገድ የሚላኩ የኦፓል ምርቶች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር ጠበቅ ቢልና ኦፓል በህጋዊ መንገድ ወደ ውጪ ሀገር ቢላክ ደግሞ አፈፃፀሙ ከዚህም በላይ ከፍ እንደሚል ይታሰባል ። በተመሳሳይ በእደ-ጥብብ ሞያ ለሚሰማሩ ሰዎች ተጨማሪ የስራ እድል በመፍጠር ቢቻልና የኦፓል ምርት ላይ እሴት በመጨመር ለውጪ ገበያ የሚቀርቡበት ሁኔታ ቢመቻች ከማዕድኑ ሰፋ ያለ ገቢ ማግኘት ይቻላል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ማዕድኑ በቴክኖሎጂ ታግዞ ቢመረት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ይበልጥ ያድጋል።
ከኦፓል ባሻገር በዚህ የዘጠኝ ወሩ አፈፃፀም ህጋዊ ስራዓቱን በተከተለ መልኩ ከክልሉ 7 ኪሎግራም የወርቅ ማዕድን ለብሄራዊ ባንክ ቀርቧል። በክልሉ በርካታ ቦታዎች ላይ ወርቅ በባህላዊ መንገድ የሚመረት ቢሆንም ህጋዊ ስርዓቱን ተከትሎ ለብሄራዊ ባንክ አይቀርብም። ከዚህ በመነሳትም ኤጀንሲው እቅድ በመንደፍ ወርቅ የሚገኝባቸው ቦታዎች ህጋዊ ስራዓት ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ ለብሄራዊ ባንክ የሚቀርበውን የወርቅ መጠን ለመጨመርና ከዚህ ማእድን የሚገኘውን የውጪ ምንዛሬ ለማሳደግ እየተሰራ ነው ።
ወደ ውጪ ሀገራት ለመላክ በእቅድ ደረጃ የተያዙና በክልሉ በሶስት ወረዳዎች ላይ የሚገኙ የግራናይት ማእድናትም የሚገኙ ሲሆን በዚሁ የግራናይት ማእድን ማምረት ስራ ለተሰማሩ ከመቶ ያላነሱ አልሚዎችም በኤጀንሲው በኩል ፍቃድ ተሰጥቷል። እነዚህ ባለፍቃዶች በቀጣይ ወደ ስራ ቢገቡ በከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ከውጪ ሀገር የሚገባውን የግራናይት ምርት በማስቀረት ምርቱን ወደ ውጪ ሀገርት የመላክ እድል ይኖራል። በማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር በኩል በእቅድ የተያዙና በክልል ያሉ ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት የሚውሉ ሌሎች ማዕድናትም ይገኛሉ።
ዳይሬክተሩ እንደሚገልፁት፤ ከስራ እድል ፈጠራ አኳያም በዘጠኝ ወሩ አፈፃፀም በሶስተኛ ሩብ አመት መጨረሻ በአጠቃላይ በክልሉ በማዕድን ዘርፍ ለ32 ሺ 567 ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር እቅድ ተይዞ ለ27 ሺ 26 ዜጎች ቋሚና ግዚያዊ የስራ እድል ተፍጥሯል። ይህም በመቶኛ ሲሰላ በክልል ደረጃ በተለያዩ የመአድን ዘርፎች 82 ከመቶ የስራ እድል ለዜጎች ተፈጥሯል።
በዘጠኝ ወሩ ውስጥ ከክልሉ የማዕድን ዘርፍ ጋር በተያያዘ እንደ ዋና ችግር የታየው በህገወጥ መልኩ የኦፓልና ወርቅ ማዕድናትን ወደ ውጪ ሀገራት የመላክ ሁኔታ በመሆኑ ይህን ችግር ለመፍታት በተለይ ወርቅ የሚመረትበት አካባቢ ያሉ ማህረሰቦችን ተጠቃሚ በማድረግ፣ ኦፓል አምራቾችም እሴት ጨምረው ለውጪ ገበያ እንዲቀርቡ በማድረግ ህጋዊ ስርዓትን የማስፈን ስራ እየተሰራ ይገኛል። ይህን የሚመሩና የሚመለከታቸው አጋር መስሪያ ቤቶችም ህጋዊ ስራዓት ማስያዝ ይኖርባቸዋል።
ከነዚህ ችግሮች በመነሳትም ኤጀንሲው በኦፓል ማምረቻ አካባቢዎች ላይ የገበያ ማዕከላትን አቋቁሟል። የውስጥ ግብዓትም አመቻችቶ ጨርሷል። ይህም ሁሉም አካላት በአስተማማኝ ሁኔታ ግብይት እንዲፈፅሙ ያስችላል። በአዲስ አበባ እጅግ በወረደ ዋጋ የሚቀርበውን የኦፓል ዋጋም ያስቀረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
እስካሁን ድረስ የኦፓል ዋጋ ገዢው በሚያወጣው ዋጋ ተውስኖ የነበረ በመሆኑ ሻጩ ዋጋውን እንዲያወጣ የማድረግ ስራዎችም ይሰራሉ። በኦፓል ማዕድን ማውጫ አካባቢም እሴት መጨመር እንዲኖር የማድረግ ስራም ይሰራል። በዘርፉ ላሉ ሁሉም አጋር አካላትም ህጋዊ ስርዓቱን የማስረዳትና ጠቀሜታውን የማሳወቅ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ።
በአማራ ክልል ከኦፓል የወጪ ንግድ ከ 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ተገኝቷል፤
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2013