መንግስት መሰብሰብ የሚገባውን ያህል ገቢ እንዳይሰበስብ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል የታክስ ማጭበርበር፣ ስወራና የኮንትሮባንድ ፍሰት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ ድርጊቶች ህጋዊ ግብር ከፋይ ነጋዴዎችንም ከንግድ ውድድር ሜዳ ውጪ ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡ ንግድና ኢንቨስትመንትንም በማዳከም በአገራዊ ልማት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳርፋሉ፡፡
ይህን ችግር ለማስወገድና ሁሉም በአግባቡ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣ ለማድረግ የገቢዎች ሚኒስቴር የተለያዩ መርሃ ግብሮችን ቀርፆ ወደ ስራ መሰማራቱ ይታወቃል፡፡ ‹‹ግዴታዬን እወጣለሁ፤መብቴን እጠይቃለሁ›› በሚል መሪ ሐሳብ ለአንድ ዓመት የሚቆይ የታክስ ንቅናቄ ይፋ ማድረጉም እሙን ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኞች ከኢፌዴሪ የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
በሚኒስቴሩ ሰራተኞች ላይ የተከናወነው ተግባር ስኬታማነት
መስሪያ ቤቱ፤የገቢዎች ዘርፍ ችግር ምንድን ነው? ለምንድን ነው ውጤታማ መሆን ያልተቻለው? መፈታት የሚገባው ችግርስ አለ ወይ? የሚሉ ትልልቅ አጀንዳዎች ነበሩት፡፡ ይህንን መሰረት በማድረግም እቅድ ተነደፈ፡፡ እነዚህ ስራዎች ካልተሰሩ በስተቀር እቅዱ ሊሳካ እንደማይችል ታምኖበታል፡፡ ጎን ለጎንም የግብር ስብሰባውን በማካሄድ በሌላ በኩል የፊዚካል ስራዎች መዋቅርን በድጋሚ በማጥናት የማደራጀት ስራ ተሰርቷል፡፡ ይህ በሁለት ምክንያት ነው የተደረገው፡፡ አንዱ ምክንያት ጉሙሩክ ኮሚሽን ተጠሪ መስሪያ ቤት ሆኖ እንዲወጣ የተወሰነ በመሆኑ ሲሆን፣ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ አደረጃጀቱ ራሱ እና ሰራተኛው ይጠቁም የነበረው በየጊዜው ውይይት ሲደረግበት የነበረ ለስራ እና ለውጤታማነት አመቺ ያልሆኑ ነገሮች የነበሩት በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህም ይህ እንዲጠና እና እንደገና እስከታች ጣቢያ ድረስ እንዲዋቀር ተደርጓል፡፡ ስራው እስከ ታክስ ማዕከላት እንዲዘልቅ ተደርጓል፡፡ ክልል ቅርንጫፍ ድረስ ያሉትንም እንደገና የማዋቀር ስራ ተካሂዷል፡፡
መዋቅሩ ከፀደቀ በኋላ ሰራተኛውን መልሶ በአዲሱ መዋቅር መሰረት የመደልደል ስራ ተከናውኗል፡፡ ሰራተኛውን የመደልደሉ ተግባር ራሱን የቻለ ህግና ስርዓት ያስፈልገው ነበር፡፡ ይህ ከመተግበሩ በፊት መርሁ ምን መሆን መቻል አለበት የሚለውንም ለማየት ተሞክሯል፡፡
አንዳንዱ ዘንድ አላስፈላጊ የስራ መርሆዎች ተቀምጠው ረጅም የስራ ልምድ የሚጠይቁ፣ ነገር ግን ደግሞ በስራ ውጤታማነት ላይ በመካከለኛ ልምድ ሊሰራ የሚችል አዳዲስ ሰራተኞችን እንዲሁም ወጣቶችን ወደፊት እንዲወጡ የማይጋብዝ አይነት የስራ መስፈርት አመላመሎችን ማስተዋል ተችሏል፡፡ የሰራ መዘርዝርም ለማየት ተሞክሯል፡፡
አጠቃላይ መመሪያዎቹን በመከለስ ሊያሰራ ይችላል የተባለውን በማፅደቅ፤ ሰራተኛውም ለራሱ ይወክለኛል የሚለውን ሰው እንዲመረጥ በማድረግና በማናጅመንቱም በመወሰን ከዳይሬክተር እስከ ጣቢያ ማዕከል ድረስ ያለው ሰራተኛ በዚህ መሰረት መልሶ እንዲደለደል ተደርጓል፡፡
ይህን መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት በጣም ወሳኝ ነው፡፡ በጥቅሉ በዚህ ሂደት ውስጥ ያለፈው ከ7ሺ780 በላይ ሰራተኛ በላይ ነው፡፡ ይህን ያህል ሰራተኛ በኢትዮጵያ ቢሮክራሲ ታሪክ እንደ አዲስ መመደብና መደልደል ስልትን ይጠይቃል፡፡ ምክንያት ቢባል ደግሞ አንድን ሰው በአዲስ መልክ መደልደል ቀርቶ ከቦታ ቦታ እንኳ እንዲቀየር ሲደረግ ብዙ ቅሬታ ይቀርባል፡፡
ሚኒስቴሩ ግን በረሃ በሚባሉት ጣቢያዎች ያሉትን ጨምሮ የማቀያየር ስራ ሰርቷል፤ በዚህም በረሃ ያሉትን አምጥቷል፤ ሌሎችን ደግሞ ወደ በረሃ ልኳል፡፡ በክልሎች ላይም እንዲሁ ከፍና ዝቅ የማድረግ ስራ ተፈፅሟል፡፡ ይህም ስራን ማዕከል ባደረገ መንገድ ብቻ ነው የተተገበረው፡፡ በዚህም 99 በመቶ በሚባል ደረጃ ውጤታማ መሆን ተችሏል፡፡
በእጅ ያለ አቅምን ማወቅ
ሌሎች ከዚህ ጋር ተያይዞ የተከናወኑት ተግባሮች ግብር በትክክል የማይሰበሰበው ለምንድን ነው? ከምንስ ነው አሁን መሰብሰብ የሚገባው? ባለፈው ሁለተኛው ሩብ ዓመት ሶስት ወራት፤ ገና ነጋዴውን በማሳመን እና ረጅም መንገዶች በመሄድ ከሆነ ግብሩ የሚሰበሰበው ገቢው መቼ ይሰበሰባል ? የሚሉትን ለመመለስም በእጅ ያለውን አቅም እና ወደ ገንዘብ ያልተቀየሩ ብዙ ነገሮችን መመልከት ውስጥ ተገብቷል፡፡
በዚህም መጀመሪያ ማየት የተቻለው ውዝፍ ግብር ነው፡፡ ከውዝፍ ብቻ ወደ ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ ተችሏል፡፡ ከኦዲት ጋር ተያይዞ ያለው ጉዳይ ሲታይ ደግሞ ሁሉንም ኦዲት ማድረግ ትክከል አይደለም፡፡ ኦዲት መደረግ ያለበት የስጋት መሰረት የሚባል አለ፡፡ ማለትም በተጋላጭነታቸው፣ በፋይላቸው ውስጥ የተለያዩ ማጭበርበሪያ ደረሰኝ የሚያስገቡ ወይም ደግሞ በሚደረገው ክትትል የንግድ እንቅስቃሴያቸው ውስጥ ደረሰኝ እንደማይቆርጡ በማየት ኦዲት የሚደረጉትን ቅደም ተከተል በማስያዝ በያዙት ገንዘብ ትልቅነትም ጭምር ለአገር ያለውን ጠቀሜታ ቅድሚያ በመስጠት የኦዲት ስራ ተሰርቷል፡፡
በእንዲህ አይነት መንገድ ከ2ሺ400 በላይ ትልልቅ ድርጅቶችን ወይም ደግሞ ፋይሎችን በዚህ ጊዜ ውስጥ ኦዲት በማድረግ የታክስ መጭበርበሩ እና ግብር ስወራው የቱ ላይ የተሰራው ? የሚለውን መለየት ተችሏል፡፡
ብዙ የተጭበረበረ ደረሰኝም አጋጥሟል፡፡ ከዚህም በመነሳት ሌላ ስራ ተሰርቷል፡፡ ይህ ደረሰኝ ከየት ነው የሚመጣው የሚለው ተጠንቷል፤ ማስተዋል የተቻለውም በቀኝ እጅ በመክፈል በግራ እጅ ደግሞ ተመላሽ የሚያደርግ አካል መኖሩን ነው፡፡ በዚህም መሰረት ወደ 124 የሚሆኑ ድርጅቶች ህገ ወጥ ደረሰኝ የሚያሳትሙ፣ የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያን በመጠቀም በሀሰተኛ ማንነታቸው የሚቸረችሩ እንዳሉ ተደርሶባቸዋል፡፡ ሌሎች ችግሮች መኖራቸውም ታውቋል፡፡
በተከናወኑ ተግባሮች እንዲህ አይነቱ እንቅስቃሴ አልቋል፤ ተገቷል ባይባልም መገታት ደረጃ ላይ ግን ተደርሷል፡፡ በዚሁ መንገድ ትልልቅ ድርጅቶች ላይ ክትትል አድርገናል፤ 40 የሚሆኑ ትልልቅ ድርጅቶች ያለደረሰኝ ሲነግዱ መቆየታቸውን ለመረዳት ተችሏል፡፡ እነሱን ለህግ በማቅረብ ምርመራ እንዲካሄድባቸው ተደርጓል፡፡
በተጨማሪም በግብር ስወራና ማጭበርበር በተጠረጠሩ ወደ 55 በሚሆኑ ድርጅቶች ላይ ልዩ ኦፕሬሽን ተደርጓል፡፡ በእነዚህ ድርጅቶች ላይ ወደ እርምጃ የተወሰደው በኢንተለጀንሱ ስራ እና በሀዝብ ጥቆማ ነው፡፡ ወደ 64 የሚደርሱ ተጠርጣሪዎችም እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል፡፡ በእዚህ አይነት መንገድ በህግ ማስከበሩ በኩል እየተሰራ ነው፡፡
በኮንትሮባንድ ንግድ ላይ የመጣው ለውጥ
ሚኒስቴሩ፣ ከየትኛውም በላይ ለውጥ አመጣሁ የሚለው ኮንትሮባንድ ላይ ነው፡፡ ኮንትሮባንድ ላይ ለውጡን እየገመገመ ያለው በያዘው ገንዘብ ልክ ብቻ ሳይሆን ኮንትሮባንድን የሚይዝ አካል እየበዛ በመምጣቱም ጭምር ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በጉምሩክ ሰራተኞች ዘንድ ከፍተኛ መነቃቃት ተፈጥሯል፡፡ በሰራተኛው ላይ የተካሄደው የመዋቅር ድልድል ሰራተኛው በቁጭት ስራውን እንዲያከናውን አድርጓል፡፡ በሰራተኛው ዘንድ መነቃቃትም ማስተዋል ተችሏልና ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ በተለይ በምስራቁ ክፍል ወደጥቅምት መጨረሻ ውይይት ተካሂዶ ነበር፤ በውይይቱም ከባለድርሻ አካላትም ሆነ ከህዝቡ የተገኘው ግብረ መልስ መልካም የሚባል ነው፡፡
የጥቅም ትስስሩ አሁን ተበጣጥሷል
አጠቃላይ መስሪያ ቤት ውስጥ የተለያየ የሌብነት ትስስር አለ በማለት በውጭ ሲነገር እንደነበር ይታወቃል፤ በሰራተኛውም ዘንድ በተለያዩ ምክንያች ጥፋት ሲታይ እንዳላየ ማለፍ ይታይ ነበር፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ‹‹ብንጮህ አንሰማም፤ እኛው እንደ ወንጀለኛ እየተቆጠርን ስለነበር ቢያንስ አይተን እንዳላየ ማለፍ ይሻላል›› የሚለው አመለካከት ነው፡፡ ወደ ጣቢያዎች ወረድ ሲል አንዳንዶች ‹‹ሌላው እየተጠቀመ…›› የሚል ስሜት ተፈጥሮባቸው እንደነበር ገልፀዋል፡፡ በኮንትሮባንድ ውስጥ ከፍተኛ የሌብነት መረብ ይታይ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ትስስሩ ተበጣጥሷል፡፡
በጥቅሉ ግን ስራው በሚታይበት ወቅት ሊሰራ የሚችል ነው፡፡ በክረምት አካባቢ ፣ጥቅምትና ህዳር በሚታይበት ወቅት አንዱ ፈተና የሆነው ግብር ከፋዩ አካባቢ ያለው እንቅስቃሴ ጤነኛ አለመምሰሉ ነው፡፡ በተለይ በትልልቅ ነጋዴዎች ዘንድ ግብር ላለመክፈል የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ነበሩ፡፡
ከንቅናቄው በፊት በየዘርፉ ውይይት ተጀምሮ ነበር፡፡ በከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ በተለይ በአዲስ አበባ ሶስት ቅርንጫፎች ጠንከር ያሉ ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡ በወቅቱም ጤነኛ የነበረውን በመለየት ወደአጋርነት የማምጣት ስራ ተከናውኗል፡፡
ከግብር ከፋዩ ጋር ጥሩ ግንኙነት ላይ ተደርሷል ከሚል ድምዳሜ የሚያደርስ ነገር ባይኖርም፤ ቢያንስ 80 በመቶ ያህሉን ገንዘብ መሰብሰብ ተችሏል፡፡ ቀደም ሲል አጠቃላይ ኢኮኖሚውን የማቀዝቀዝ፣ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ግብር እንዳይሰበስብ የማድረግ ሁኔታ የታየበት ነበር፡፡
አንዳንዴም ግብር ከፋዩ ግብር ሰብሳቢው ዘንድ በመምጣት ‹‹አልከፍልም፤ ምን ታመጣላችሁ፤ልታስሩኝ ትችላላችሁ፡፡›› የሚል ድፍረት የተቀላቀለበት ሁኔታ የተስተዋለበት ጊዜም ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ያ ሁኔታ የለም፡፡
እንዲያም ሆኖ አሁንም ገቢን ያለማሳወቅ፣ግብር መሰወር፣ ገቢን መቀነስ እንዲሁም መሸሸግ ይስተዋላል፡፡ እንደ ቀድሞው አይን ያወጣ ነገር ግን አይታይም፡፡ ክትትሉና እየተወሰደ ያለው እርምጃ ሁሉም ላይ በጅምላ የሚፈጸም አይደለም፡፡ ጥፋት ያለበት ላይ ያነጣጠረ መሆኑ ግንዛቤ እየተወሰደበት ይገኛል፡፡
የጨለማ ኢኮኖሚ ሲባል
የጨለማ ኢኮኖሚ ወይም ህቡዕ ኢኮኖሚ የተባለው የግብር እና የንግድ ስርዓቱ ተመዝግቦ ያልተገኘበትን ሁኔታ ነው፡፡ ግብር መክፈል ከሚገባው አጠቃላይ ማህበረሰብ ወስጥ እየከፈለ ያለው ከእነ ችግሩም ቢሆን 60 በመቶ ያህሉ ነው፡፡ 40 በመቶ ያህሉ እየከፈለ አይደለም፡፡ ይህንን ነው የጨለማ ኢኮኖሚ አለ ለማለት የተፈለገው፡፡ የንግድ እንቅስቃሴው በትክክል ተመዝግቦ ግብር የማያሳውቅ ከሆነም ምድቡ ከእዚሁ ነው፡፡
ስለዚህ ይህ ኢኮኖሚ ከጨለማ ወደ ብርሃን መውጣት ይኖርበታል፡፡ ወደ ብርሃን ይውጣ ሲባልም ወደ ህግና ስርዓት፣ ወደ ግብር ስርዓት ይግባ ማለት ነው፡፡
የግብር ንቅናቄ
አሁን በተያዘው የታክስ ንቅናቄ ግብር የሁሉም፣ የአገርም ብሄራዊ አጀንዳ መሆን አለበት፡፡ ያለ ግብር መንግስት የለም፡፡ ሰው ኮራ ብሎና አንገቱን ቀና አድርጎ የሚሄድበት ሁኔታ አይታሰብም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ህዝቡ ተመሳሳይ ግንዛቤ መያዝ አለበት፡፡ ግንዛቤው ሲፈጠር ነው ደረሰኝ የሚጠይቅና እንዲሰጠውም ግፊት የሚያደርግ ማህበረሰብ መፍጠር የሚቻለው፡፡ በጎ ተፅዕኖ የሚያሳድረው የማህበረሰቡ ጫና ደግሞ ህገ ወጡን ስርዓት ውስጥ ያስገባዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 12/2011
አስቴር ኤልያስ