ሀገራችን ኢትዮጵያ በለውጥ ሂደት ውስጥ ትገኛለች። እነዚህ ለውጦች መሬትን በነኩ ትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች የተደገፉ ናቸው። ለምሳሌ ሀገሪቱ በአፍሪካ በግዙፍነቱ ተወዳዳሪ የሌለውንና የብዙዎችን ቀልብ እየሳበ ያለውን የህዳሴ የሀይል ማመንጫ ግድብ እየገነባች ነው። የምርምርና የልማት ስራዎችን የሚያግዙ ሁለት ሳተላይቶችን አምጥቃለች። መላ ሀገሪቱን አረንጓዴ የሚያለብስ ግዙፍ የችግኝ ተከላ ዘመቻ እያከናወነች ነው። በፖለቲካውና በዲሞክራታይዜሽን ዘርፍም እንዲሁ ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች እየተከወኑ ነው።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ከውስጥና ከውጭ ከባድ ፈተናዎች የተጋረጡባት ጊዜ ላይ ትገኛለች። በአንድ በኩል ከህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ግብጽ እና ሱዳን ጸረ-ኢትዮጵያ ጥምረት ፈጥረው ሀገሪቱን ለማተራመስና ያልተገባ ተጽእኖ ለመፍጠር እየተሯሯጡ ነው። በሌላ በኩል በትግራይ ያለውን ሰብአዊ ችግር እና ቀጣዩን ሀገራዊ ምርጫ ምክንያት በማድረግ በአሜሪካ ፊት አውራሪነት የተቀነባበረ ጫና ለማሳረፍና በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ፍላጎትና አዝማሚያ በመታየት ላይ ነው። የሰሞኑ የአሜሪካ የጉዞ ቪዛ ክልከላ የዚሁ ቅጥያ ነው። ከውስጥ ደግሞ ከውጭ ኃይሎች ጋር በማበር ምርጫውን ለማደናቀፍ ላይ ታች የሚሉ ቡድኖች እንዳሉ እየተገለጸ ነው።
ይህም ቢሆን ኢትዮጵያውያን መጪው ምርጫ የራሳቸወ ጉዳይ እንጂ የማንም ጉዳይ ባለመሆኑ የተፈጥሮ ሀብታቸው የሆነውን የአባይ ውሃ የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ ከፍለው እያለሙ በጉጉት የሚጠበቀውንም ምርጫ ለማካሄድ ደፋ ቀና እያሉ ይገኛሉ። በዚህ መሰረት የቅድመ ምርጫ ክንውኖች በመገባድ ላይ እንደሚገኙ ከምርጫ ቦርድ የሚወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ።
ከኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው እስካሁን ወደ 40 ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በመጪው ሰኔ 14 ቀን 2013 በሚካሄደው ምርጫ “ይሰራልናል” እና “ይበጀናል” ለሚሉት እጩ ተወዳዳሪ ድምጻቸውን ለመስጠት ተመዝግበዋል።
በዚህ ምርጫ 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚወዳደሩ ሲሆን፤ 8 ሺ209 እጩዎች ተመዝግበዋል። ከእነዚህ መካከልም 125ቱ በግል የሚወዳደሩ ናቸው። የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅስቀሳና ክርክር ማድረጋቸውንም አጠናክረው ቀጥለዋል።
የ2013 ሀገራዊ ምርጫ ለኢትዮጵያ የህልውና ጥያቄ የሆነውን የዲሞከራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት በጠንካራ መሰረት ላይ ቆሞ እንዲቀጥል ለማድረግ ፣ ሀገራችን ካለችበት አስቸጋሪ ሁኔታ ወደ ተሻለ የተረጋጋ ሀገራዊ ሁኔታ ለመቀየር እንዲሁም ህዝባዊ ቅቡልነት ያለው መንግሥት ለመመስረት መልካም አጋጣሚ ከመፍጠር አንጻር እጅግ ከፍተኛ የሆነ ሀገራዊና ታሪካዊ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሎ ጠንካራ እምነት ተጥሎበታል። በመሆኑም ዜጎች ይህን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በሀገራቸው የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ ለመወሰን ራሳቸውን ዝግጁ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው የብዙዎች ስምምነት ነው።
ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገትና ልማት የህዝብ ተሳትፎ እጅግ አስፈላጊ ነው። በጋራ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት የህዝብ ተሳትፎ ከግሪኩ ፈላስፋ ከፕሌቶ ዘመን የዴሞክራሲ ጽንሰ ሃሳብ ጋር ቁርኝት አለው። ይህ ዘመን ያልሻረው ጽንሰ ሀሳብ አሁንም እንደ የሀገሩ ተጨባጭ ፖለቲካዊ ሁኔታ በተለያየ መልክ ይተገበራል። በዲሞክራሲ ስርዓታቸው ዳብረዋል በሚባሉት ምእራባዊያን ሀገራትም ይሁን የዲሞክራሲ ምህዳሩ ገና ለጋ በሆነባቸው ኢትዮጵያን በመሳሰሉ ሀገራት ከፖለቲካ አንፃር የህዝብ ተሳትፎ ተብሎ የሚወሰደው በዋናነት የዜጎች የፖለቲካ ምርጫ ተሳትፎ ነው።
ስለዚህ በምርጫ ወቅት የመራጮች ቁጥር መብዛትና ማነስ እንደ ቁልፍ የተሳትፎ መገለጫ (indicator) ተደርጎ ይወሰዳል። ከዚህ አኳያ በርካታ አምባገነን መንግስታት የመራጮች ቁጠር ማነስ የማስመሰል ድራማቸውን ሊያጋልጥብን ብለው ይሰጋሉ። በዚህም ምክንያት ህዝቡን በመደለል፣ በማስፈራራት አልያም በማስገደድ የመራጩን ቁጥር ለማብዛት ሲጥሩ ይታያል። ይህም ምርጫው በአለም ማህበረሰብ ዘንድ ትክከለኛ እና ህጋዊ ነው ተብሎ እውቅና ያሰጠዋል ከሚል እሳቤ ይመነጫል።
ይህ እኛ ጋርም ከዚህ በፊት የተካሄዱት አምስት ተከታታይ ምርጫዎች አይነተኛ መገለጫ ነበር ማለት ይቻላል። የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በሀገራችን የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እንዲኖርና በየአምስት ዓመቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ምርጫ እንዲካሄድ ደንግጓል። በዚህ ድንጋጌ መሠረት እስካሁን የዘንድሮውን ሳንቆጥር አምስት ተከታታይ ምርጫዎች ተካሂደዋል።
ይሁን እንጂ ሁሉም ምርጫዎች ህገ መንግስቱ በሚፈቅደውና በሚያዘው መሰረት የተከናወኑ አልነበሩም። ለዚህ ማሳያው ምርጫውን በበላይነት የሚያስፈጽሙ ነጻና ገለልተኛ ተቋማት ያልነበሩበትና አብሮም ለገዢው ፓርቲ የሚያደሉበት፣ የአንድ ፓርቲ የበላይነት የነገሰበት፣ መራጩ ህብረተሰብ የሚፈልገውን ትቶ የማይፈልገውን ፓርቲ እና እጩ እንዲመርጥ ጫናና ተጽእኖ የሚደረግበት፣ ሂደቱ በብዙ ማጭበርበር እና ውዝግቦች የተሞላ ብሎም በምርጫ ስም አፈናና የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚፈጸምባቸው ሂደቶች የነበሩ መሆኑ ነው።
ምርጫ ማለት ህዝብ ከቀረቡለት አማራጮች ውስጥ ይሆነኛል ወይም ይጠቅመኛል የሚለውንና የሚፈልገውን ካለምንም ተጽእኖ በነጻነት መምረጥ ሲችል ነው። ከዚህ በተጨማሪም በውድድር ሜዳው በርካታ ሀሳቦች ቀርበው አብላጫው ህዝብ የመረጣቸው ሀሳቦች ማሸነፍ ሲችሉ ነጻ ምርጫ ተካሄደ ማለት እንችላለን። ይሁንና ባለፉት ምርጫዎች ይህ እውን ሆኖ ለማየት አልታደልንም። የተወሰኑ ፖለቲካ ውስጥ ህዝብን ለማገልገል ሳይሆን የራሳቸውን ጥቅም በማስላት የገቡ ግለሰቦችና ካድሬዎች በዚህም በዛም ብለው አሸነፍን ብለው የሚያውጁበት «እቃ እቃ » ከሚባለው ጨዋታ ጋር የሚመሳሰሉ ምርጫዎች ነበሩ። ስለ ዲሞክራሲ፣ ስለ ፍትሀዊና ነጻ ምርጫ፣ ስለ ህዝባዊ መንግስት፣ ስለ ህገ መንግስት የበላይነት…ወዘተ የሚነገሩት በሙሉ ከእውነትነታቸው ይልቅ የምዕራባውያንን ድጋፍ ለማግኘት ጥቅም ላይ የሚውል የማወናበጃ ስልቶች ነበሩ።
በአጭሩ ከዚህ በፊት ለሀያ ሰባት አመታት ሲሄዱ የነበሩት ምርጫዎች ህዝቡን መጠቀሚያ በማድረግ ለህውሓት መራሹ መንግስት ህጋዊነትና ቅቡልነት በማላበስ አገዛዙን ለማስቀጠል ሲደረጉ የነበሩ የይስሙላ ምርጫ ወይም በፈረንጆቹ አነጋገር (Fake Election) ነበሩ። ምንም እንኳን ”ትእይንቱ” ሂዶ ሂዶ በአሳዛኝ ሁኔታ የተደመደመ ቢሆንም፣ አገዛዙ የህዝቦችን ድምጽ በማፈን የስልጣን ዘመኑን ለ 27 አመታት ማስቀጠል የቻለበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር።
ሁላችንም እንደምንረዳው ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተግባር እውን የሚሆኑት እና መንግስት የሚዋቀረው በሌላ ሳይሆን በህዝብ ተሳትፎ ነው። የህዝብ ተሳትፎ መገለጫዎች ከሚባሉት ውስጥ ደግሞ አንዱና ዋናው ዜጎች ይወክለኛል የሚሉትንና ሀገርን የሚያስተዳድሩ ብቁ እጩዎችን ለስልጣን ለማብቃት ድምጽ የሚሰጡበት ሂደት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከወራት በፊት በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክታቸው “… ኢትዮጵያ ውስጥም ከምርጫ በስተቀር የሚሸጋገር፣ የሚደራደር መንግሥት አይፈጠርም። ማንም ሰው ሥልጣን መያዝ የሚችለው በምርጫ ብቻ ነው…ከዚህ ውጪ ያሉ ሃሳቦች ሁሉ ቅዠቶች ናቸው፤ አይሆኑም ” በማለት አስረግጠው የተናገሩት ከዚሁ መሰረተ ሀሳብ በመነሳት ይመስለኛል።
ዜጎች በመንግሥታት የፖሊሲና የስትራቴጂ ውሳኔዎች ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር ከሚጠቀሙባቸው ወሳኝ ነጥቦች መካከል አንዱ ድምፅ ነው የሚባለው በዚህ ምክንያት ነው። መብቱን ተጠቅሞ ይወክሉኛል ብሎ የሚያስባቸውን እጩዎችን ለመምረጥ ዝግጁ የሆነ ዜጋ በምርጫ ዋዜማ ለውድድር በሚቀርቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ ወሳኝ አካል እንደሚታይ ሁሉ፣ የመንግሥትን አስተዳደር ተረክበው ስልጣን ላይ በሚቀመጡበት ሰዓት ደግሞ ግልጽነት፣ ሀላፊነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ውጤታማ ስራ መስራት የግድ ይጠበቅባቸዋል።
ከዚህ በተቃራኒ በምርጫ አለመሳተፍ/አለመምረጥ/ ማለት ባልመረጡት አካል መተዳደርን ያስከትላል። የህዝብን ችግርና ፍላጎት ያላገናዘቡ ፖሊሲዎችና የስትራቴጂ ውሳኔዎችን ተግባራዊ እንዲሆኑም በማድረግ ህዝቡን ለምሬትና ለብሶት ሊዳርጉት ይችላሉ። ባስ ሲል ደግሞ የህዝብ ድምጽ ተጭበርብሯል የሚሉ ቡድኖች ሰላማዊ ያልሆኑ የትግል ስልቶችን እንዲከተሉ ሊያደርጋቸው ይችላል። የትግል ስልቱ ተገቢ ነበር/አይደለም የሚለውን የመከራከሪያ ሀሳብ ለጊዜው ወደጎን ትተን ከምርጫ 1997 በኋላ የ «ግንቦት ሰባት» ንቅናቄን ወደዚህ አይነቱ ትግል እንዲገባ ያስገደደው ዋናው ምክንያት በወቅቱ የነበረው ገዢ ፓርቲ የመራጮችን ድምጽ በጸጋ አልቀበልም በማለቱ መሆኑ የሚያከራክር ጉዳይ አይመስለኝም። ዞሮ ዞሮ ህዝብ ያልመረጠው፣ በህዝብ ይሁንታን ያላገኘና ስልጣኑን የማጭበርበርና በህገወጥ መንገዶችን በመጠቀም ያገኘ ፓርቲና መንግስት ሀገር ቢመራ ትርፉ ኪሳራ ነው የሚሆነው። ያለፉት ሰላሳ አመታት የ ”ዲሞክራሲ“ ተሞክሯችን የሚያረጋግጥልን ይሄንኑ ሀቅ ነው።
በመሆኑም ማንኛውም ዕድሜው የሚፈቅድለትና በህግ አግባብ የመምረጥ እና መመረጥ መብቱ ያልተገፈፈ ሰው የሚሰጠው ድምፅ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ልብ ማለት ያስፈልጋል። በኮተቤ ሜትሮ ፖሊታን ዩንቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር የሆኑት ዶክተር አየነው ብርሀኑ እንደሚናገሩት ዜጎች በምርጫ ድምጻቸውን የሚሰጡበት መሰረታዊ ምክንያት የህዝቡን ጥቅምና ፍላጎት ማሟላት ለቻሉት ፓርቲዎችና አመራሮች ሚና እውቅና በመስጠት ለተጨማሪ አመታት በስልጣን እንዲቆዩ ማስቻል አንዱ ሲሆን፣ ሌላው የህዘቡን ጥያቄና ፍላጎት ማሟላት ያልቻሉትን ፓርቲዎችና አመራሮች ከስልጣን በማውረድ ለሚቀጥሉት ተመራጮች ሀላፊነት ለመስጠትና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም ጥሩ የዕድገትና ብልፅግና ፖሊሲና አሰራር ዘርግቶ ለአገር ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጥ፣ በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ ፖሊሲ የአገሩን ህዝብ ጥቅም የሚጠብቅ፣ ለማናቸውም ብሄራዊ ተግዳሮቶች እጅ የማይሰጥ፣ በትክክለኛ የፖለቲካ አስተሳሰብ የሚመራ፣ የህዝብ ጥቅም ግድ የሚሰጠው፣ እውነተኛ እኩልነትን የሚያረጋግጥ፣ ለሆዱ ሳይሆን ለህሊናው የሚያድር፣ የሚዘርፍ ሳይሆን ህዝቡን ከችግርና ከድህነት ለመላቀቅ የሚጥር፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ችግር አላቆ ትንሳዔዋን ዕውን የሚያደርግ፣ …ወዘተ መንግስት ለመመስረት በምርጫ መሳተፍ ጠቀሜታ አለው።
ነገር ግን አሁን ባለው ተጨባጭ የሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ አብዛኛው ማህበረሰብ በምርጫ የመሳተፍን ጠቀሜታ በአግባቡ ተረድቶ ራሱን የሂደቱ አካል ከማድረግ አንጻር ገና ብዙ እንደሚቀረው አፍ ሞልቶ መናገር ይቻላል። ለዚህ “ ፖለቲካ እና ኤሌክትሪክን በሩቁ ” እየተባባልን ያደግንበት ኋላ ቀር የፖለቲካ ባህላችን እንዳለ ሆኖ፣ ባለፉት አመታት ያለፍንባቸው ኢ-ፍትሀዊና የተጭበረበሩ የምርጫ ሂደቶች አብዛኛው ማህበረሰብ “በምርጫው ብንሳተፍም ያን ያህል ለውጥ አናመጣም ” የሚል አስተሳሰበ እንዲያዳብር ትልቅ አስተዋጽኦ ማደረጉ አይካድም። በርግጥ ስለመራጭነት መብት በቂ ግንዘቤ ስለሌላቸው፣ ምርጫን ምን ምን ፋይዳ እንዳለው በበቂ ሁኔታ ባለመረዳታቸው እና በሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶች በምርጫ የማይሳተፉ በርካታ ዜጎች እንዳሉ ይታወቃል።
ዞሮ ዞሮ ትናንት የሆነው ነገር ሁሉ ትናንት አልፏል። ዛሬ አዲስ ቀን ነው። ትናንት የነበሩት ምርጫዎች ብዙ ነገር አስተምረውናል። ከዚህ አንጻር ያሁኑ መንግስት (ጠቅላይ ሚንስትሩንም ጨምሮ) ከዚህ በፊት በነበሩ ምርጫዎች የነበሩ ስህተቶችን በማረምና ላሁን የሚሆኑ ትምህርቶችን በመውሰድ መጪው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ፍትሃዊ፣ ነጻና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ከምንጊዜውም በላይ በቁርጠኝነትና በትኩረት እየሰራ እንደሆነ በተደጋጋሚ ገልጿል። ይህ ሲታይ ምንም እንኳን እስካሁን ያለው የቅድመ ምርጫ ሂደት ሙሉ ለሙሉ የተዋጣለት ነው ማለት ባይቻልም ምርጫው ካሁን በፊት ሲካሄዱ ከነበሩት ምርጫዎች የተለየ እንደሚሆን ከወዲሁ ከፍተኛ ግምት ተጥሎበታል። ለብዙዎችም ብሩህ ተስፋን እየፈነጠቀ ነው።
በሌላ በኩል አሁን ባለው የሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ከፊታችን ያለው ሀገራዊ ምርጫ የሚከናወንበት ጊዜ ከወትሮው በተለየ ሀገራችንን ፈትነው ያሉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተግዳሮቶች ያሉበት፤ የውጭ ጣልቃ ገብነትና ጫና የበረታበት፣ የማይጣጣሙ (Polarized) የፖለቲካ እይታዎችና አስተሳሰቦች የሚስተናገዱበት፤ በብዙ ጉዳዮች ላይ ሀገራዊ መግባባት ያልተደረሰበት፤ የህግ የበላይነት መከበር አደጋ ላይ የወደቀበት ፤ ባጠቃላይ የሀገሪቷ ሁለንተናዊ ሁኔታ ከቀደሙት ጊዜያት በተለየ ሁኔታ ውስጥ የሚደረግ ምርጫ ነው።
ስለሆነም ዜጎች ለምርጫው የሚሰጡት ትኩረትና የሚያደርጉት ዝግጅት ከወትሮ በተለየ መልኩ እነዚህን ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት። የሚጠበቅባቸውም ሀላፊነት እጥፍ ድርብ ነው ባይ ነኝ። ወቅቱ እነዚህን ሀላፊነቶች መወጣት ይጠይቃል።
ምንም እንኳን ምርጫው ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች በሙሉ ይፈታል ተብሎ ባይታሰብም ምርጫው ነጻ፣ ፍትሀዊና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ ህዝባዊ መንግስት ከተመሰረት የሀገሪቱንና የህዝቡ ችግር የሚፈታበት ምቹ መደላደል ማበጀት ይቻላል የሚል እምነት አለኝ። ይህ የሚሆነው ደግሞ የሚሆነንንና ያመነውን ፓርቲ መርጠን ወደ ስልጣን በማምጣት ነው። የማንፈልገውን አመራርም የምንታገለው በህገ ወጥ መንገድ ሳይሆን የተሰጠንን መብት ባግባቡ ተጠቅመን በምንሰጠው ድምጽ ብቻ ነው።
የካርድን ዋጋና ጉልበት በቅጡ መረዳት ስንጀምርና የመምረጥ ባህል ስናዳብር ስልጣኔያችን እና ፖለቲካችን የደረሰበትን ደረጃ በተግባር እያሳየን ሰላማችንን የማረጋገጥ እና የውስጥ ልዩነቶቻችንንም የመፍታት እድል ይኖረናል። የታለመውን እድገትና ብልጽግናም እውን ለማድረግ ሰፊ እድል ይኖረናል። ከዚህ እውነታ በመነሳት በምርጫው መሳተፍ የውዴታ ግዴታ እንደሆነ መታሰብ አለበት። ይህ ሳይሆን ቀርቶ የመምረጥ እድላችንን ሳንጠቀም ካሳለፍን ሌላውን የመውቀስና የማማረር ሞራል ሊኖረን አይችልም። «ለሁሉም ጊዜ አለው» እንዲል ሀገራዊ ብሂሉ ምርጫ በአምስት አመት አንድ ጊዜ የሚገኝ እድል ነው።
ከዚህ አንጻር በእድሉ ተጠቅመን የምንፈልገውን አካል ባንመርጥ ሀላፊነታችንን እንደ መዘንጋት ተደርጎ የሚቆጠር ከመሆኑም በላይ ለትውልዱም እዳ ጥሎ እንደ መሄድ ይቆጠራል። ከዚህም አልፎ በኛ ያለመሳተፍ ምክንያት ፖለቲካዊ ችግሮች የማይፈቱበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ስለሆነም የምርጫ ካርድ ያወጣን ሰዎች በምርጫው እለት በነቂስ ወጥተን እኛን የሚወክሉና ፍላጎታችንን የሚያሟሉ ሰዎች ፍላጎታችንን እንዲያሟሉ ድምጻችንን በመስጠት ሀላፊነታችንን መወጣት ይገባናል።
ሆኖም በምርጫ መሳተፍ ለብቻው የምርጫውን ትክክለኛነት ያረጋግጣል ማለት እንዳልሆነ መገንዘብ ያሻል። የምንሰጠው ደምጽ ትርጉም ያለውና ምክንያታዊ የሚሆነው በእውቀትና በተሟላ መረጃ ላይ የተመሰረተ ሲሆን ነው። በሌላ አነጋገር ዜጎች ከመምረጣቸው በፊት ምክንያታዊ በሆነ መንገድ በሀሳብ የበላይነት ማመን አለባቸው። ይህም ማለት በምርጫው ድምጽ ስለምንሰጠው ፓርቲ አላማና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ስለሚያራምደው ፖለሲ ፣ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉትን ችግሮች በምን አይነት መንገድ ለማስተናገድ እንዳቀደ ፣ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ስላለው አመለካከትና አቋም …ወዘተ መፈተሸ ያስፈልጋል። ከሀሳብ የበላይነት ይልቅ ፓርቲዎችን በብሄር፣ በሀይማኖት፣ በስያሜ በመሳሰሉት መሰረት በማድረግ መምረጥ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። ስለዚህም እያንዳንዳችን ፓርቲዎች ሀገር ለመምራት ያላቸውን አቅምና ችሎታ ፣ ለሀገርና ለህዝቦች አንድነት ያላቸውን አቋምና ተቆርቋሪነት፣ የህዝብ ሀላፊነትን ለመወጣት ስላላቸው ቁርጠኝነት…ወዘተ ግራ ቀኙን ፣ ፊትና ኋላውን አይተንና መርምረን ትክክለኛውንና ለሀገራችን መጻኢ እድል የሚያዋጣውን አማራጭ በማወቅ ኃላፊነታችንን ለመወጣት እንትጋ።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ባሁኑ ሰዓት አነሰም በዛም በለውጥ ጎዳና ላይ እየተጓዘች ትገኛለች። ብዙ ተስፋ ሰጪ ነገሮችንም እያስተዋልን ነው። ስለዚህ ሀገራዊ ለውጡን አስቀጥሎ ያደገች፣ የበለጸገች እና እንደ ወትሮ ሁሉ ነጻነቷ የተጠበቀና የተከበረች ኢትዮጵያን በመፍጠር ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ የሚቻለው ያወጣነውን ካርድ ተጠቅመን በማስተዋል ላይ የተመሰረት ምርጫ በማካሄድ በመሆኑ “ጋን በጠጠር ይደገፋል” እንደሚባለው የራሳችንን ድርሻ እንወጣ ።
ቸር እንሰንብት !
ዳግም መርሻ
አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2013