ዲስከቨሪ መፅሄትን ዋቢ አድርጎ የኤኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በገፁ ያሰፈረው መረጃ እንደሚያሳየው፤ የከተማ ኑሮ ለሰው ልጆች ከተዋወቀ ስድስት ሺህ ዓመታትን አስቆጥሯል። ሌላው ዓለም ኑሮውን በገጠር እና በአነስተኛ መንደሮች መግፋት ሲቀጥልም የመጀመሪያዎቹ ከተሞች በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን መሰብሰብ ችለው ነበር። ዛሬ ይህ ተቀይሯል፤ አራት ቢሊዮን የሚሆነው የዓለማችን ህዝብ (ከግማሽ በላይ የሆነው) ከተሞችን ቤቴ ይላል።
ዛሬ ከስድስት ሺህ ዓመታት በኋላ ከተሞች የማይገኙበት የምድራችን ክፍል አይገኝም። ግን ‹‹የመጀመሪያው ከተማ የት ተመሰረተ›› ብሎ የመጀመሪያ የከተሞች አመሰራረትና አኗኗር በመካከለኛው ምስራቅ ሜሶፖታሚያ እንደተጀመረ በማውሳት ስለ ከተሞች አመሰራረትና የግንባታ ጥበብና ዕድገት ያትታትል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በርካታ የዓለማችን ክፍሎች ከተማ እና ከተሜነትን ተዋውቀው ኑሯቸውን እያዘመኑ እንደሆነም ይነገራል። በዛሬው እትማችን ደግሞ የእኛዋን ሃዋሳ ከተማ አሁናዊ ገፅ እና እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን እንቃኛለን።
ሃዋሳ ከተማ ግማሽ ክፍለ ዘመን ያስቆጠረች ውብ የብሄረሰቦች መናኸሪያ ናት። ብዙዎች ሊዝናኑባት የሚመኟት፤ ብዙዎች የሚያደንቋት ሁሌ ሙሽራ ሁሌ አዲስ ሁሌ ውብ የሆነች ከተማ ናት። በአሁኑ ወቅት ከ500 ሺህ በላይ ዜጎች እንደሚኖሩባት የከተማዋ አሃዛዊ መረጃዎች ይጠቁማሉ። የሐዋሣ ከተማ በ1952 ዓ.ም በቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን የተመሠረተች ሲሆን፤ አመሠራረቷ ከአካባቢው ልምላሜ ጋር ተያይዞ ከተማዋን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እና የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ልማት ለመዘርጋት ታሣቢ ያደረገ እንደነበረ የተለያዩ የታሪክ መረጃዎች ያስረዳሉ።
ሐዋሳ ከተማ ስያሜዋን ያገኘችው ከሀዋሣ ሐይቅ ሲሆን፤ ቃሉም ከሲዳምኛ ቋንቋ የተገኘ ነው። ‹‹ሀዋሣ›› ማለት ‹‹ሰፊ የውሃ አካል› ማለት ሲሆን፤ ከተማዋ ይህንን አሁን የምትጠራበትን ስያሜ ከማግኘቷ በፊት ‹አዳሬ› እየተባለች ትጠራ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ሲያስረዱ ይህም በሲዳምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ዘንድ ‹የግጦሽ ቦታ› ማለት ነው። አቀማመጧም ከተማዋ በ70’ 03’’ ላቲቲዮድ እና 80’29” ሎንግዮቲዮድ ምሥራቅ ትገኛለች። ከአዲስ አበባ በ275 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኝ ስትሆን የአየር ንብረቷም ወይና ደጋ ነው። የተፈጥሮ ገፀ በረከቷ የሆነው የሐዋሳ ሀይቅ በከተማዋ በክረምትም ሆነ በበጋ ምንም ዓይነት ምቾት የሚነሳ ሙቀትም ሆነ ቅዝቃዜ የማይታይባት ከተማ ያደረጋት መሆኑ ይነገርላታል።
ውቧ ከተማ ሃዋሳ በርካታ አዋሳኞች ያሏት ሲሆን፤ በውብ መንደሮችና ከተሞች ተጎራብታለች። ሐዋሳ በስተሰሜን ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ወረዳ፣ በስተምስራቅ ከሲዳማ ዞን ወንዶ ገነት ወረዳ፣ በደቡብ ምስራቅ ከሲዳማ ዞን መልጋ ወረዳ፣ በስተደቡብ ከሲዳማ ዞን ሸበዲኖ ወረዳ እና በስተምዕራብ የሐዋሳ ዙሪያ ወረዳ ያዋስኗታል። የሀዋሣ ከተማ አጠቃላይ የቆዳ ሥፋት 15 ሺህ 720 ሄክታር ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 6 ሺህ 465 ሄክታር በማዘጋጃ ቤታዊ ድንበር (area covered by structural plan የተካለለ ነው።
ሐዋሳ በነዋሪዎች አንደበት
ወጣት ዳዊት አንጪሶ የሃይቅ ዳር ክፍለ ከተማ ነዋሪ ሲሆን፤ የወጣቶች መዝናኛ ከፍቶ በርካቶችን እያስተናገደ ይገኛል። እርሱ ዘንድ ወጣቶች እየመጡ ፑል ይጫወታሉ፣ ስለ ኳስ ያወራሉ፣ ይፎካከራሉ። ሃዋሳ ውብ ከተማ ሆና ብዙዎች የሚመጡባት ናት። ይህ ለእኛም ለሌሎችም ውበት ነው። እንግዶች በመጡ ቁጥር እኛም ገቢያችን እያደገ ነው ይላል።
ዳዊት እንደሚለው፤ ስለ ሐዋሳ ከተማ ውበትና ዕድገት ከሚነገረው በተቃራኒ ደግሞ እይታ የሚገፈትሩ አካባቢና ሰፈሮች አሉ። ለአብነት አሮጌው መናኸሪያ አካባቢ፣ የዱሮ ገበያ፣ ሞኖፖል የመሳሰሉ መንደሮች ይጠቀሳሉ። ወደ ውስጥ ገባ ሲባል አዳዲስ የግንባታ ፕሮጀክቶች የማያውቃቸውና ዝቅተኛ ደረጃ መሟላት ያለባቸው መሰረት ልማቶች እንኳን የሌሉበት የባይተዋር መንደር ናቸው።
ከዚህም በተለየ ለከተማዋ ዕድገት አንዳች
የማይጨነቁ ሰዎች ሰፋፊ ቦታዎች እየተሰጡ መላ ቅጡ የጠፋባቸው መሰረተ ልማቶች እየገነቡበት ለራሳቸውም ጥቅም ብቻ የሚለፉ ሰዎች መኖራቸው ይናገራል። ታዲያ መንግስትም ይህን እያየ ዝምታ መምረጡ አግባብ አለመሆኑን ይኮንናል። በተቃራኒው ደግሞ በርካታ ወጣቶች የመዝናኛ ማዕከል እንኳን ሳይኖራቸው በአልባሌ ቦታ እየዋሉ እንደትውልድ ዕዳ እየተቆጠሩ ስለመሆኑ ይናገራል።
ወይዘሮ ሀዊሴ ባንዳ ሃዋሳ ከተማ መናኸሪያ አካባቢ ነዋሪ ሲሆኑ፤ ከተማችን ውብ የሆነችው በሰዎች ልፋት ሳይሆን ተፈጥሮ በቸራት ፀጋ ነው ይላሉ። ሃዋሳ ካላት አቅም እና ከየአቅጣጫው ከሚመጡባት ቱሪስቶች አኳያ የሚሰበሰበው ገቢ ወዴት ሄደ ብሎ የሚጠይቅ አካል ያለ አይመስለኝም፤ ጠያቂ ቢኖርማ ከተማችን ምንኛ ባደገች ሲሉ ቁጭታቸውን ይገልፃሉ። እኛ ነዋሪዎችንም ግብር ክፈሉ ብሎ ከመወትወት ባለፈ መሰረተ ልማቶችን አያሟሉም ይላሉ። ዋና ዋና መንገዶችን አስፋልት ተገን በማድረግ እንጂ ወደ መንደር ውስጥ መግባት አልተለመደም ሲሉም ይወቅሳሉ።
ሃዋሳ ከተማ ውስጥ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ እንደ ቅንጦት የሚቆጠርባቸው መንደሮች መኖራቸውንና የሚናገሩት ወይዘሮ ሀዊሴ ከልማት ተገልለው የሚኖሩ አካባቢዎች መኖራቸውን ይጠቅሳሉ። የሃዋሳ ገበናን በፍቅር ሐይቅና በመሃል አስፋልቶች ብቻ ማሞጋገስና ሃቁን ማለባበስ ተገቢ እንዳልሆነ በመጠቆም የከተማው አስተዳደር በእኩል ዓይን ሁሉንም ስፍራዎች ማልማትና መሰረተ ልማቶችን ማሟላት እንዳለበት ይናገራሉ። ይህም ብቻ ሳይሆን ወጣቶች መዋያ ቦታ ስለሌላቸው ከተማዋ የስራ አጦችና ሱሰኞች መቆዘሚያ እየሆነች መምጣቷ ሊያሳስብ ይገባል ይላሉ።
የኃላፊዎች አንደበት
ሃዋሳ ከተማ መሰረተ ልማቶችን ማፋጠን፣ ማዘግየት እና ሌሎች በከተማዋ ዕድገት ላይ ሚና ያላቸውን ተግባራት ሁሉ የምትወስነው ከተማዋ ራሷ ናት ይላሉ። ከተማዋ በራሷ ገቢ የምትተዳደር በመሆኑ ብዙ ገቢ በመነጨ ቁጥር ብዙ መሰረተ ልማት ይገነባል፤ ይህ ሳይሆን ሲቀር ደግሞ ነገሮች በተቃራኒው እንደሚሆኑ ይጠቁማሉ። በዚህም የተነሳ የገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱ መዘመንና በየጊዜው አዳዲስና ለነዋሪዎች ምቹ የሆነ አሰራር መዘርጋት ተገቢ መሆኑን ይጠቁማሉ።
በ2013 በጀት ዓመት አስር ወራት አንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡንና በዚያው ልክ አዳዲስ ፕሮክቶች መጀመራቸውን ያብራራሉ። በአሁኑ ወቅት በከተማ ውስጥ በ200 ፕሮጀክቶች የተለያዩ የልማት ሥራዎች በመከናወን ላይ ሲሆኑ፤ ከእነዚህም 150 የሚሆኑት ፕሮጀክቶች ደግሞ በዚህ ዓመት ተጠናቀው ለአገልግሎት እና ለታለማላቸው ዓላማ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል። በቀጣይ ቅንጅታዊ አሰራሮች ከተዘረጉና ዜጎች በአግባቡ ኃላፊነታቸውን ከተወጡ ሐዋሳ ከምንጠብቀው በላይ ፈጣን ዕድገት አስመዝግባ እንመለከታለን ባይ ናቸው።
የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ በበኩላቸው፤ ነዋሪዎች የሚያነሷቸውን ሃሳቦች በብዛት ይጋራሉ። ሐዋሳ ሥመ ብዙ፤ ባለቤቷ ብዙ ችግሯ ብዙ ሁሉ ነገሯ ብዙ የሚመኟትም ብዙ በመሆኑ የሚጨነቁላት በርካቶች መሆናቸውን ያምናሉ። በመሆኑም በየጊዜው አዳዲስ እይታዎችና ሥራዎችን የምትፈልግ የብዙሃን የስበት ማዕከል ስለመሆኗ ይጠቁማሉ። በዚህ ዓመትም ለከተማዋ ዕድገት የሚመጥኑ በርካታ ግንባታዎች ሲሰሩ መቆየታቸውንና በአሁኑ ወቅትም ተጠናክሮ መቀጠሉን ይናገራሉ።
እንደረዳት ኘሮፌሰር ፀጋዬ ገለፃ ከሆነ፤ በሐዋሳ ከተማ በስምንት ክፍለ ከተሞች ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል። በተለይም ሀገራዊ የሪፎርም ሥራው ከተጀመረ ሦስት ዓመታት ወዲህም ሐዋሳ የበለጠ እየተመነደገች ነው። ከተማዋ የምትሰበስበው ገቢም እያደገ መሆኑንና በዚያው ልክ መሰረተ ልማቶችን እያሟለች ስለመሆኑ ይጠቁማሉ። በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ በከተማዋ ሁለት ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር የተበጀተላቸው ፕሮጀክቶች ግንባታ ላይ ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ አንድ ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው የተለያዩ መሰረተ ልማቶችተመርቀው ለህዝብ አገልግሎት ክፍት ሆነዋል።
በ2013 በጀት ዓመት በየክፍለ ከተማው የትምህርት ቤት ማስፋፊያ፣ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ መንገድ እና ሌሎችም መሰረተ ልማቶች ተገንብተው የተመረቁ ሲሆን፤ አዳዲስ የመንገድና ሌሎች ኘሮጀክቶችም እየተጀመሩ ነው። ለአብነትም በዚህ ሰሞን በታቦር ክፍለ ከተማ የተመረቁ የመንገድ ኘሮጀክቶች በስምንት መንደር አራት ነጥብ ስድስት ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸውና 25 ሚሊየን ብር ወጪ የተደረገባቸው እንደሆነም ያብራራሉ። ለተለያዩ ህንጻዎችም 26 ሚሊየን ብር የወጣ መሆኑንና በአጠቃላይ በዚህ ክፍለ ከተማ ብቻ 54 ሚሊዮን ብር የተበጀተላቸው ኘሮጀክቶቹ ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነዋል።
በምስራቅ ክፍለ ከተማ ደግሞ አንድ ነጥብ ሰባት ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የጥርብ ጌጠኛ የድንጋይ ንጣፍ መንገድ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኗል። እነዚህን የመሰረተ ልማት ግንባታ ሥራዎችም ዘጠኝ ሚሊዩን ብር በላይ ወጪ መደረጉንም ጠቁመዋል።
በመናኸሪያ ክፍለ ከተማ ሰባት ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የጥርብ ጌጠኛ የድንጋይ ንጣፍ መንገድ ግንባታን ከ38 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ህብረተሰቡ እንዲገለገልበት መደረጉን ይናገራሉ። በተያያዘም የመናኸሪያ እና ምስራቅ ክፍለ ከተሞችን የሚያገናኘው ከየሺ እስከ መካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ያለውን ሁለት ነጥብ ሁለት ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን መንገድ በአስፋልት ለመገንባት የሚያስችል ሥራ መጀመሩንና ይህም ህብረተሰቡ ለረጅም ጊዜ ሲያነሳው የነበረ ጥያቄ መሆኑን ከንቲባው ያስታውሳሉ። አጠቃላይ ለመንገድ ግንባታ ከተማ አስተዳደሩ 100 ሚሊዮን ብር በጅቶ እየሰራ ይገኛል።
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ደግሞ ሦስት ኘሮጀክቶች በዚህ ዓመት መገንባታቸውንና ከእነዚህም ውስጥ የዳካ የወጣቶች ስብዕና ልማት ማዕከል እና የቱሪስት መረጃ ማዕከል ለሃዋሳ እድገትና የቱሪስት ፍሰት ለሚታይባት ከተማ ዘርፈ ብዙ ትርጉም እንዳለው ተናግረዋል። ለሶስቱ ፕሮጀክቶች ደግሞ 30 ሚሊየን ብር ወጪ ተደርጓል። ከተማዋን ከመገንባት ጎን ለጎንም ለከተማዋ እና ለከተሜነቱ የሚመጥኑ ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ እንደሆነ ይጠቁማሉ። በዚህም ለበርካታ ወጣቶች መልካም ስብዕና መገንባትና ሀገራዊ ኃላፊት መወጣት ብሎም ወደ ከተማዋ ለሚመጡ ቱሪስቶች አስፈላጊውን መረጃ ከማቅረብ አኳያ ፋይዳው የጎላ እንደሆነም ምክትል ከንቲባው ያብራራሉ።
‹‹ከተማዋ ውብና ማራኪ ሆና እንድትቀጥል ብሎም ለሀገር በሚበጅ መንገድ ተገንብታ ሀገራችን እንደሀገር ተጠናክራ እንድትቀጥል ዜጎች ትልቅ ሚና አላቸው። ኘሮጀክቶች በፍጥነት ተጠናቀው አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ የተቻለው የኘሮጀክት አስተዳደር ሥርዓቱ የፈጠነ እንዲሆን በመደረጉ ነው›› የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ፤ ሁሉንም የከተማዋን አካባቢዎች በእኩል ፍጥነት ለማልማትና ለማስዋብ እየተሰራ መሆኑን ያብራራሉ።
ይሁንና ከገንዘብ አቅም ውስንነትና ፕሮጀክቶች በፍጥነት የማጠናቀቅ ልምድ ማነስ የተነሳ ቅሬታዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ታሳቢ የሚደረጉ መሆናቸውን በመጠቆም በተቻለ መጠን የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማርካት ሌት ተቀን እንሰራለን ይላሉ። በቀጣይም ለህዝብ ምላሽ የሚሰጡ አዳዲስ የመሰረተ ልማት ማስፋፋትና ማደስ ኘሮጀክቶች የሚጀመሩ መሆኑን ከንቲባው ገልፀው፤ የፈጠነና የተረጋጋ ልማት እንዲኖር ሁሉም ሀገራዊ ግዴታውን ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2013