የሰው ልጅ አንዱ በሌላው ላይ ጥገኛ ነው። እንደ ሰው ልጅ በአለማችን አንዱ ከሌላው ፈላጊ የሆነ ፍጡር አይገኝም። አንድ ሰው በጫካ አለያም በዋሻ ተገልሎና ፍራፍሬ እየተመገበ ከዱሩ ሳይወጣ የሚኖር ካልሆነ በስተቀር በከተማ ወይም በመንደር ኑሮ መስርቶ ያለ ሌሎች እገዛ ፈፅሞ መኖር አይችልም። ማኅበራዊ ህይወት ከውልደት እስከ ሞት የሚኖር እና ቀጣይነት ያለው ሂደት ሲሆን በትምህርት፣ ልምድና ከሌሎች ሰዎች ጋር በሚኖረን ማህበራዊ መስተጋብር የሚዳብር ነው:: የሰው ልጅ ስለራሱ እና ስለሚኖርበት ማኅበረሰብ የሚኖረውን ዕውቀት በተለያየ መልኩ፤ ማለትም የአካባቢውን ቋንቋ በመማር፤ አካባቢያዊ ሁኔታውን በመመልከት፤ እንዲሁም ማኅበራዊ ክሂሎትን በማዳበር፣ እያሳደገ ይሄዳል:: የዚህ የማኅበራዊ ህይወትና መስተጋብር ክሂሎት በአግባቡ በማዳበር ለተሟላ ስብዕና እና ሁለንተናዊ ዕድገት ወሳኝነት አለው::
አገር መውደድ ማለት ጥልቅ ትርጉም አለው:: አገር ማለት ህዝብ፤ ህዝብም ማለት አገር ነው። አገርና ህዝብ የማይነጣጠሉ፤ አንዱ ካለአንዱ ትርጉም የማይኖረው፤ እጅግ የተቆራኙ ነገሮች ናቸው። አገር መውደድ ማለት ህዝብን መውደድ፣ ህዝብን ማገልገል፣ ለህዝብ መሞት፣ ለህዝብ መጎዳት ወዘተ ማለት ነው። አዎ አገር ወዳድ ዜጋ ማለት ራሱን ለብዙሃኑ ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ፣ ብዙሃኑም ስለአንዱ የሚገዳቸው ማለት ነው። ይህ ነው የአገር ፍቅር፤ ይህ ነው የህዝብ ፍቅር ማለት።
አረጋውያን አገራቸውን ለማቅናት ደፋ ቀና ብለው የደከሙ በመሆናቸው ያልተቋረጠ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል:: በመሆኑም በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ አካባቢዎች እነሱን የሚደግፉ ማህበራት በመበራከት ላይ ናቸው:: እነዚህ ማህበራት አረጋውያኑን ከመደገፍ ባሻገር የህክምናና ሌሎች አገልግሎቶችን እያሟሉላቸው ነው:: እንደ’ነዚህ አይነት ስራዎች በመንግስት ደረጃ የሚደገፉ ካልሆነ የታሰበላቸውን ግብ መምታት አይችሉም:: ለዛሬ በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኘውን “የሀበሻ አረጋውያን መርጃ ማዕከል”ን እንመለከታለን::
ማዕከሉ የተመሰረተው በቅርብ ቢሆንም በርካታ ስራዎችን አከናውኗል:: ከአረጋውያን በተጨማሪ ከሴቶችና ህፃናት ጋር በተያያዘ የአዕምሮ ህሙማን ላይ ስራዎችን ያከናውናል:: የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ማዕከሉን ከመደገፍ ይልቅ እንቅፋት እየፈጠረ መሆኑ ይነገራል:: ከሀበሻ አረጋውያን መርጃ ማዕከል መስራችና ስራ አስኪያጅ አቶ ዮርዳኖስ ፈቃዱ ጋር ከአጠቃላይ የማዕከሉ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ቆይታ አድርገናል:: መልካም ንባብ::
ማህበሩ አመሰራረትና ያከናወናቸው ተግባራት
“ሀበሻ አረጋውያን መርጃ ማዕከል” በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኙ አቅመ-ደካማ አረጋውያንን ለመርዳት በማሰብ ህጋዊ እውቅና ለማግኘት ሰኔ 8 ቀን 2008 ዓ.ም ተመሰረተ:: ማዕከሉ ስራውን ሲጀምር አምስት አረጋውያንን በመደገፍ ነበር:: አሁን ስድስት ዓመት የሞላው ሲሆን 670 አረጋውያንን እየደገፈ ይገኛል::
ማህበሩ ከተመሰረተ በኋላ አላማ ብሎ የያዛቸውን ስራዎች ወደ ተግባር መለወጥ ጀምረ:: የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማንን ከወደቁበት ያነሳል:: ከተለያዩ ቦታዎች የመጡትን አረጋውያን መጠለያ በመስጠት፣ ምግብ፣ አልባሳት፣ ህክምና እንዲሁም ሲሞቱም ስርዓተ ቀብራቸው በስርዓት እንደየሀይማኖታቸው እንዲከወን ያደርጋል:: አንዳንድ ጊዜ ወጣት የሆኑ አዕምሮ ህሙማን ከዳኑ በኋላ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የማገናኘት ስራንም ይሰራል::
ሌላው ደግሞ በጎዳና ላይ ወድቀው የሚገኙና ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ህፃናት ወደ ማዕከሉ እንዲገቡ የሚደረግ ሲሆን፤ ዛሬ በደረሰባቸው ጥቃት የአዕምሮ መታወክ የሚያጋጥማቸው ወደ ሌሎች ማዕከላት እንዲሄዱ አይደረግም:: ማዕከሉ ህፃናቱ ለብቻቸው ሆነው የሚያገግሙበት ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል:: የተወሰኑትን እንዲማሩ የማድረግ ስራ ተጀምሯል:: ወጣት የአዕምሮ ታማሚዎች በተለይ ከዩኒቨርሲቲ በሱስና በሌሎች ምክንያቶች የአዕምሮ ህመምተኛ ሆነው ያቋረጡ ልጆች ድነው ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ እየተደረገ ነው::
ለአረጋውያን በሶስት አይነት መንገድ ድጋፍ የሚደረግላቸው ሲሆን የመጀመሪያው በቋሚነት ድጋፍ የሚደረግላቸው ናቸው:: በቋሚነት የሚደገፉት ምንም አይነት መጠለያ የሌላቸው፣ የራሳቸው ገቢና የጤና ችግር ያለባቸው በማዕከል ውስጥ እንዲኖሩ ይደረጋል:: ሁለተኛው ደግሞ አቅም ያላቸው ማዕከሉ ድረስ መምጣት የሚችሉትን ያካትታል:: እነዚህ አረጋውያን መጠለያ ኖሯቸው ግን ህክምናና የመመገቢያ ገቢ የሌላቸው ናቸው:: እነዚህ አረጋውያን ተመላላሽ ተደጋፊዎች ይባላሉ:: አረጋውያኑ ወደ ማዕከሉ በመምጣት ይውላሉ፤ ይመገባሉ፤ ይታጠባሉ እንዲሁም የህክምና አገልግሎት ያገኛሉ:: ነገር ግን ለእነዚህ አረጋውያን ከኮሮና ወረርሽኝ በኋላ የሚደረገው ድጋፍ ቀንሷል::
ሶስተኛው ደግሞ ቤት ለቤት በመሄድ የሚደረግ ድጋፍ ነው:: አረጋውያኑን በሚኖሩበት ቤት ድረስ በመሄድ የሚሰጥ አገልግሎት ሲሆን ጧሪ የሌላቸውን፣ በተለያዩ ህመም ውስጥ የሚገኙትን እንዲሁም ገቢ የሌላቸውን በጎ ፈቃደኞችን በመመደብ ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል:: ማዕከሉ አረጋውያኑን በዚህ አይነት መንገድ እየደገፈ ይገኛል:: ሌላው ደግሞ በማህበረሰብ ግንዛቤ ዙሪያ ስራዎች እየተከናወኑ የመሆኑ ጉዳይ ነው:: የማህበረሰብ ግንዛቤ ሲባል ከሚረዳው ሰው ይልቅ ድጋፍ የሚደርገው ሰው ይበልጥ ተጠቃሚ የሚሆንበት አገልግሎት ነው::
በማንኛውም ጊዜ እርዳታ ከሚደረግለት ሰው ይልቅ ድጋፍ አድራጊ ተጠቃሚ የሚሆንበት መንገድ ብዙ ነው:: እርዳታ የሚደረግለት ሰው አጥቶ ተቸግሮ በመሆኑ አዕምሮ ላይ ከባድ ጫና ይፈጥራል:: ድጋፍ አድራጊው ጤነኛ ሆኖ የተረፈው ነገር ስለበዛለት የሚያደርገው በመሆኑ እርካታን ያገኛል:: ማህበረሰቡም መረዳት ላይ የሚያሳየው ጥሩ ያልሆነ ስሜት ይስተዋላል:: ነገር ግን ማንኛውም ሰው መሰጥት የሚችላቸው ብዙ ነገሮች እንዳሉት ማወቅ አለበት:: በአዲስ አበባ ውስጥ ወድቀው ድጋፍ የሚፈልጉት አብዛኛዎቹ ከክፍለ ሀገራት የሚመጡ ወገኖች ናቸው:: ይህ የሚሆንበት ምክንያት በአካባቢያቸው የሚደግፋቸው ሰው ሲያጡ በስደት ወደ ከተማ ስለሚመጡ ነው:: በመጥፎ ነገሮች ላይ ሁሉም ሰው ሲተባበር ይታያል:: ነገር ግን ጥሩ ነገር ለማድረግ ድጋፍና ትብብር የሚያደርገው ቁጥሩ አናሳ ነው:: በየትኛውም ሃይማኖት ውስጥ የሚገኝ ሰው በቅን ልቦና የተቸገሩ ሰዎችን ሊደግፍ ይገባል:: ይህ ባለመደረጉ በጎ አድራጎት ማህበራት በድጋፍ እጦት እየተዘጉ ናቸው::
ማህበሩን ያጋጠሙ ችግሮች
የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር ለ”ሀበሻ አረጋውያን መርጃ ማዕከል” ምንም አይነት ድጋፍ አያደርግም:: የከተማ አስተዳደሩ ማህበሩን ከመደገፍ ይልቅ የተለያዩ ጫናዎችን እየፈጠረበት ይገኛል:: ምንክንያቱ ባይታወቅም ከተማ አስተዳደሩ የማዕከሉን ስራ ካለመረዳት የመነጨ እንቅፋት እየፈጠረ ይገኛል:: ማንም ሰው በጎ ነገር ለማድረግ ቀስቃሽ አያስልገውም:: ሁሉም በጎ የሚያደርጉ ማህበራት በአግባቡ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል:: መገናኛ ብዙኃን ለሁሉም በጎ አድራጎት ማህበራት እኩል የሆነ ሽፋን አለመስጠት ስራዎች ለህብረተሰቡ እንዳይዳረስ አድርጓል:: ይህ ሁሉ ችግር አሁንም አልተፈታም።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ችግረኞችን መደገፍ የራሱ ስራ መሆኑን ባለ መረዳትም ይሁን ሌላ ለጊዜው ባይታወቅም፤ በራሳቸው ፈቃድ የሚሰሩ ወጣቶች ላይ ተፅዕኖ እየፈጠረ ይገኛል:: በከተማዎች ላይ የሚገነቡ ማናቸውም ነገሮች የከተማው ቅርስ በመሆናቸው ይጠበቃሉ:: ነገር ግን የከተማ አስተዳደሩ ለበጎ አድራጎት ማህበሩ ምንም አይነት ድጋፍ አያደርግም:: የአካባቢው ነዋሪ ቅን አሳቢ ቢሆንም የከተማ አስተዳደሩ እያደረሰ ባለው ተፅዕኖ የመሸሽ ሁኔታዎች አሉ:: በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ “ሀበሻ የአረጋውያን መርጃ ማዕከል” ምንም አይነት መልዕክት እንዲያስተላልፍ አይፈቀድለትም::
የከተማ አስተዳደሩ ተቃራኒ በሆኑ ጉዳዮች ለሁለት በመከፈሉ ማዕከሉ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዳያገኝ አድርጎታል:: የማዕከሉን ስራ የተመለከቱ አመራሮች ድጋፋቸውን ሲያሳዩ ነገር ግን ማዕከሉ እየሰራ ያለውን ስራ ሳይመለከቱ ‘ማዕከሉ መፍረስና መበተን አለበት’ ብለው ይናገራሉ:: አመራሮቹ አረጋውያኑን ሰብስቦ መጦር ብቻ ሳይሆን ትልቅ ደረጃ ማብቃት ይገባል በማለት እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን እያጣጣሉ ናቸው:: አረጋውያን ሂወታቸው እስካለ ድረስ ይጦራሉ እንጂ ለቁም ነገር ማብቃት እንደማይቻል ባለማወቃቸው ችግር እየፈጠሩ ነው::
በደብረ ብርሃን እንቅስቃሴ እያደረጉ የሚገኙ ኢንቨስተሮች ወደ ማዕከሉ መጥተው ድጋፍ እንዳደርጉ የመከልከል ስራዎች የሚያከናውኑ አመራሮች አሉ:: ድጋፍ ‹‹እኛ ነን እንጂ እናንተ መሰብሰብ አትችሉም›› እስከመባል ተደርሷል:: የምግብ ብቻም አይደለም፤ የዳይፐር ሳይቀር እጥረቶች አሉ:: ለአረጋውያኑ የተሰጠ የአንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ከተማ አስተዳደሩ ኮሚቴ አዋቅሮ ለመውሰድ ሲንቀሳቀስ ነበር:: ነገር ግን ያንን ማድረግ እንደማይችሉ እየታወቀ ግን በህገወጥ መንገድ ለመውሰድ ሲንቀሳቀሱ ነበር:: በዚህም አረጋውያኑ ድጋፍ እንዳያገኙ እገዳ ተጣለባቸው:: ህብረተሰቡ በመገናኛ ብዙሀን በኩል በጎ አድራጎት ማህበራትን አስመልክቶ ማብራሪያዎች ካልወጡ ድጋፍ ለማድረግ አይነሳሳም:: ይህ ብቻም አይደለም፣ አጠገባቸው በጎ የሚሰሩ ማህበራት እያለ ሁሉ በህዝቡ በኩል መደገፍ ያለመፈለግ ሁኔታዎች አሉ::
ቀጣይ የማህበሩ እቅዶች
በቀጣይ ማህበሩ የራሱ ማዕከል ገንብቶ ከልመና የሚላቀቅባቸውን መንገዶች እየቀየሰ ይገኛል:: ለምሳሌ በግ ለማደለብ፣ የላም ተዋፅኦን በማምረት በአካባቢው ሊሚገኙ ተረጂዎች ለመስጠት፣ ዶሮና እንቁላል እንዲሁም የአትክልት እርሻ አዘጋጅቶ እየተንቀሳቀሰ ነው:: በአትክልት እርሻ ሞዴል በጎ አድራጎት መሆን የሚችልበት ሁኔታም ታስቦበት እየተሰራ ነው:: በማዕከሉ ግቢ ውስጥ የጓሮ አትክልት እየተተከለ ይገኛል::
ሌላው ማዕከሉ ስራዎችን ለማከናወን የሚያደርጋቸውን የለጋሽ ሰዎችን እጅ መጠበቅ ለማቆም እቅዶች አሉት:: ማንም ሰው ድጋፍ እንዲያደርግ መለመን የለበትም:: በአገሪቱ የሚገኙ በጎ አድራጎት ማህበራት በአንድነት ቢታቀፉና ችግርም ሆነ ጥሩ ነገር ለመለዋወጥ እገዛ ያደርጋል:: በአዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች ድጋፍ ለማድረግ ቀና ናቸው:: በሌሎች ቦታዎች ላይ የሚገኙ በጎ አድራጊ ማህበራትም ሊደገፉ ይገባል:: ህብረተሰቡም በጎ ስራ እንዲያከናውን የአመለካከት ስራዎች ለመስራት ማዕከሉ እቅድ አለው::
የማዕከሉ ዋነኛ አላማ ድጋፍ የሚያደርጉ ሰዎችን ማፍራት ነው:: የሰውን ችግር ተረድቶ ባለው አቅም ድጋፍ የሚያደርጉ ሰዎችን ማብዛት ያስፈልጋል:: መልካም የሰራ ሰው ከስሮ አያውቅም:: ማዕከሉ በበጎ ሰዎች እየተደገፈ የሚንቀሳቀስ ሲሆን ህብረተሰቡም ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥረት እየተደረገ ይገኛል:: ሁሉም ለአገሩ እንዲኖርና እንዲሰራ ለማድረግ ከፍተኛ ስራዎች ያስፈልጋሉ:: ማዕከሉ አቅም የሌላቸውን አረጋውያንን ይዞ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን፤ በራሳቸው መመገብ፣ መንቀሳቀስና መፀዳዳት የማይችሉትንም በሚችለው አቅም እያገዘ ይገኛል።
ማዕከሉ መቶ አካባቢ አባላትን ያቀፈ ሲሆን አባላቱ ድጋፍ በሚያስፈልግበት ጊዜ ከኪሳቸው ገንዘብ ይሰጣሉ:: ድጋፍ ለማግኘት ብዙ ስራዎችን ያከናወናሉ:: አንድ ሰው በአመት 365 ብር እንዲሰጥ እንቅስቃሴ እየተደረገ ሲሆን ድጋፍ አድራጊዎች በባንክ አካውንት እንዲያስገቡ ይደረጋል:: ገንዘብ የሚሰጡ ሰዎች በደረሰኝ ድጋፍ የሚያደርጉ ከሆነ ለታለመለት አላማ እንዲውል ይደረጋል:: ለተረጂ የሚደረጉ ድጋፎችን ለራስ ማዋል በጥብቅ መወገዝ ያለበት ጉዳይ ሲሆን ድጋፍ አድራጊዎች ህጋዊ በሆነ መንገድ ገንዘብ መስጠት ይጠበቅባቸዋል
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ሰኔ 4/2013