«ጉዳይዎን እንደ እርስዎ በመሆን ላይ ታች ብለን እናስፈጽማለን። ለስራዎ አጋርና አማካሪ የሚያስፈልግዎ ከሆነም ቀን ከሌት ሰርተን የስኬትን ቁልፍ እናስጨብጥዎታለን»፤ እንዲህ ዓይነት ማስታወቂያዎች አዲስ አይደሉም። ገንዘብ በመክፈል ብቻም በተለያዩ ምክንያቶች እኛ መፈጸም ያልቻልናቸውን ጉዳዮች ያለሃሳብ መከወን የሚቻልበት ጊዜ ላይ ቆመናል። በየዕለቱ ፍጥነቷ እየጨመረ በመጣው ምድራችን ኑሮን ለመግፋት ፉክክር ከመግጠም ባሻገር አማራጭ የለም።
ለስራ የሚሰጠው ሰዓት ከፍተኛ በመሆኑም፤ ቤተሰብን ለመምራት፣ የአገልግሎት ሂሳብ ለመክፈል፣ ፍጆታን ለማሟላት፣ ለማህበራዊ ጉዳይ እና ሌሎች ስራዎችን ለመከወን ግብ ግብ ውስጥ መግባታችንንም እያንዳንዳችን ራሳችንን መታዘብ በቂ ነው። ታዲያ ጊዜን ለመቆጠብና እጅግ አስፈላጊ ለሆነው ጉዳይ ቅድሚያ ለመስጠት ሌሎቹን ስራዎች በአደራ ለሌሎች መስጠት አስፈላጊ ነው። የሰው ልጅ በምድር ሲኖር ከሚያስተናግዳቸው ተፍጥሯዊ ባህሪያት መካከል አንዱ ፍቅር ነው። ፍቅር እንደየ አፍቃሪው በተለያየ ሁኔታ ሊከሰት ይችላል፤ እንደ አመጣጡ ለመመለስም የአፍቃሪው ወይም ተፈቃሪው ባህሪው ወሳኝ ነው። አንዳንዱ ደፋር በግልጽ ተናግሮና አሳምኖ አሊያም በተለያየ ሁኔታ ስሜቱን ገልጦ የሚወደውን ሰው ከእጁ ያስገባል። ሌላው ደግሞ በአይናፋርነት መናገር ባለመቻሉ ሲማቅቅና እንደሚመኘው ፍቅሩን በጊዜ ለማጣጣም አይችልም። መቼም እዚያ ስለ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እዚህ ደግሞ ስለ ፍቅር የምታወሪው ምን አገናኝቷቸው ነው ሳትሉኝ አልቀራችሁም።
ሁለቱን ጉዳዮች ያገናኛቸው የሰሞኑ የኦዲቲ ሴንትራል ዘገባ ነው። ነገሩ ግራ አጋቢ ቢሆንም ለአንዳንዶች ግን እፎይታን የሚሰጥ አገልጋይ ተቋም በጃፓን በስራ ላይ ውሏል(ለግልጋሎቱ ግን ገንዘብዎን ሆጨጭ ማድረግዎ የግድ ነው)። «ኮኩናቪ» ሁለት የጃፓን ቃላት በጥምረት የፈጠሩት ቃል ሲሆን፤ «በፍቅር ግራ መጋባት» የሚለውን ፍቺ ይሰጣል። ይህንን ትርጓሜ ይዞ የተመሰረተው ኮኩናቪ የተሰኘው ተቋምም፤ አፍቃሪን ከተፈቃሪ የማገናኘት (የተቀደሰ ተግባር ነው መቼም) አገልግሎት ይሰጣል። ጃፓናዊያኑ አፍቃሪዎች በፍቅር የተንበረከኩለት ተፈቃሪ ፊት ደርሰው ስሜታቸውን መግለጥ ከተሳናቸው፤ የሚጠበቅባቸው 260 ዶላር ብቻ መክፈል ነው። ኮኩናቪም እሳት በላሱት ሰራተኞቹ የፍቅር መልዕክቶችን በመላክ፣ ደብዳቤዎችን በመጻፍ እንዲሁም የተፈቃሪዋን/ውን ልብ ለማሸነፍ የሚችሉ ነገሮችን ይከውናል፤ ከተፈቃሪ ለሚሰጥ ምላሽም አፍቃሪውን ወክሎ መልስ ይሰጣል።
ገንዘቡን ወደ 530 ዶላር ማሳደግ ከቻሉም ከመልዕክት ልውውጡ በተጓዳኝ አፍቃሪው አይነጥላውን ገፎ ደፋር እንዲሆን የሚረዳው ምክር በባለሙያዎች ይሰጠዋል። እንዲህ ዓይነቱ ስራ ሲከናወንም መረጃዎችን በመመልከት ያሉት ለውጦች ይመዘናሉ፤ በዚህም ስራው ስኬታማ መሆኑ ታይቷል። አገልግሎቱን ያገኙ አፍቃሪዎችም በተቋሙ ይፋዊ ማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ ጭምር በድፍረት ስኬታቸውን በመመስከርም አረጋግጠዋል። «እርዳታቸውን ፈልጌ ወደ ኮኩናቪ በማምራቴ ደስተኛ ነኝ፤ ምክንያቱም በፍቅር ግራ መጋባቴ በስኬት አልፏል። በስራቸውም እጅግ ተደንቄያለሁ» ስትል አስተያየቷን የሰጠችው የ23 ዓመቷ ወጣት ናት። በዚህ ወቅትም አገልግሎቱን ለማግኘት ወደ ተቋሙ የሚያመሩ ሰዎች ቁጥር እያደገም ነው ተብሏል። በጃፓን መሰል አገልግሎት ሰጪዎች እየተስፋፉ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም የስራ መልቀቂያ ለማስገባት የአለቃቸውን ዓይን ለማየት ለሚፈሩ ሰዎች አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም መኖሩን ድረ ገጹ ዘግቦ ነበር። ኮኩናቪ ግን በመገናኛ ብዙሃን ራሱን ሲያስተዋውቅ «ጭንቀትዎ ጭንቀታችን፤ ፍቅርዎም ፍቅራችን ነው» የሚል አይመስላችሁም?
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2011
ብርሃን ፈይሳ