ያደግኩበት ሰፈር ይናፍቀኛል፤ አያቶቼ ዘንድ ነው ያደግኩት:: የአንደኛ ደረጃ ትምህርቴንም በዚያው ነው የጨርስኩት:: አያት እጅ ያደገ ብዙ ነፃነት አለው:: ነፃነቱ ነበረኝ፤ የሚያወቅ ያውቀዋል:: በሰፈሩ እንደልብ ተጫውቼበታለሁ:: ሁሉም ለአያቶቼና ለእዚህ ሰፍር ልዩ ግምት እንዲኖረኝ አርገዋል::
የትምህርት ቤት ጉዳይ ነው ከአያቶቼና ካደግሁበት ሰፈር የለያየን:: ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት እናት እና አባቴ ወደአሉበት ሩቅ ሰፈር መሄዴ:: እንዲያም ሆኖ ወደዚህ ሰፈር እመላለስ ነበር:: ቢያንስ በወር አንዴ ብቅ እልበት ነበር። አጋጣሚው ደግሞ በየወሩ ከሚሰባሰቡት አብሮ አደግ ጓደኞቼ ቀላቅሎኛል:: ያኔ ታዲያ የማይነሳ የማይጣል የለም:: የልጅነት ታሪካችን ተወርቶ አያልቅም:: ምሽት ነው የሚያፋተን ::
ሌላ ሶስተኛ ምክንያትም አለ:: ከሶስት ዓመት በፊት በበጋ በአቧራ፣ ዝናብ ጠብ ሲል በጎርፍ ሲጥለቀለጥ ፣ በጭቃ ሲላቁጥ የኖረው ሰፈራችን ሲገነባለት የቆየው አዲስ መንገድ መጠናቀቅ ነው:: የዚህ መንገድ ግንባታ ሲጀመር ወደ አካባቢው እንደፊቱ እንዳልመላለስ አርጎኛል:: ከአያቶቼ ጋር በተለያዩ ማህበራዊ አጋጣሚዎች በሌሎች ስፍራዎች የምንገናኝ ቢሆንም፤ አካባቢውን ካየሁት ግን ወደ ሁለት ዓመት አካባቢ ሆኖኛል::
አሁን የሰፈራችን መንገድ ቀን ወጥቶለታል:: ከሶስት አመት በፊት ነው መንገዱ በአስፋልት መገንባት የጀመረው፤ ይህን ተከትሎ ብዙ ለውጦች እንዳሉ በተለይ ከአብሮ አደግ ጓደኞቼ እሰማ ነበርና ግንባታው የደረሰበትን ሁኔታ ማየት ሶስተኛው ምክንያት ሆኗል።
በስፍራው ስደርስ ባየሁት ሁሉ ተደስትኩ:: የሚገርም መንገድ ተገንብቷል:: እንደማንኛውም የከተማችንም ሆነ የሀገራችን የመሰረተ ልማት ግንባታ የዚህ መንገድ ግንባታ ቢጓተትም የጥራት መጓደል ቢታይበትም አሁን የሚታየው ግን ያስደስታል:: ምጡን እርሺው ልጁን አንሺው አይደል አባባሉስ:: ለመጠናቀቅ መቃረቡ በእጅጉ አስደሰተኝ፤ ሁላችንም ተደስተናል።
እንደ ተጀመረ አካባቢ አይቸዋለሁ:: ወቅቱም ክረምት ነበር:: ግንባታው ሲካሄድ ለተመለከተ ያልቃል ብሎ ለመገመት ያስቸግራል:: በሀገራችን ግንባታ ጀምሮ ትቶ መውጣት የተለመደ መሆኑ ሲታሰብ፣ ግንባታቸው ተጀምሮ ዓመታትን ያስቆጠሩ የመንገድ ፕሮጀክቶች በርካታ መሆናቸው ሲታሰብ፣ ይህም የመንገድ ፕሮጀክት ከችግር ነጻ ይሆናል ተብሎ አይገመትም:: በተቋራጭ አቅም ውስንነት ወይም በወሰን ማስከበር ችግር፣ አልያም በበጀት እጥረት ሳቢያ ቢያቆሙት የማን ያለህ ይባል ነበር:: ችግሮች አጋጥመው መጓተቱ ቀጥሎ ቢሆን ከመጥበሻ የወደቀ ስጋ ሆነን ነበር። ሲንጨረጨሩ መኖር:: እረ ተመስገን ነው::
እውነቴን ነው የምላችሁ :: በመንገድ ግንባታ መጓተት ሳቢያ ስንቶች የዘንጀሮ ኑሮ እንደኖሩ የማያውቅ ያለ አይመስለኝም:: በተለይ አዲስ አበቤ:: መውጫ መግቢያ በመጥፋቱ ሳቢያ እየተንጠላጠሉ የሚገቡ የሚወጡ ስንቶች ናቸው::
የመንገድ ግንባታ መጓተት መንገድ ብቻ አያሳጣም:: የመንገድ መብራት ሳያዩ አመታትን መግፋት የግድ ነው:: የመንገድ መብራት ከሌለ ወደሁዋላ መመለስ ይከተላል:: ባትሪ መጠቀም፤ እንደ ዶሮ በጊዜ መስፈር፤ ለሌባ ተላልፎ መሰጠት፣ በተቆፋፈሩ ቦታዎች ውስጥ ገብቶ መሰበር፣ ወዘተ ይከተላል:: የኛ ሰፈር መንገድ ወደ መጠናቀቁ እነዚህ ችግሮች እየተገላገለ ነው ያሰኛል::
ጓደኞቼ ስለመንገዱ ውበትና በሰፈሩ ላይ ስላመጣው ለውጥ በስልክ ነገረውኛል:: እነሱ በስልክ የነገሩኝን ደስታ በምሽት ከቤተሰብ ጋር የእግር ጉዞ በማድረግ ለማጣጣም አስቤ ነበር።
ጓደኞቼ ልክ እንደ ልጅነት ጊዜያችን ለመንገዱ የመንገድ ዳር መብራት መግባቱን የነገሩኝ ሰፈሩ ፓሪስን መሰለልህ ብለው በማነፃፀር ጭምር ነበር። ሰፈሩን አይሁት:: መንገዱም መብራቱም ጥሩ ተሰርተዋል:: መብራትና መንገዱን ይዘው ሰፈሩ ፓሪስን መስሏል ሲሉ በኩሸት የገለጹት ግን እንኳ ይደር:: ለነገሩ እነሱም ለውጡ ከፍተኛ መሆኑን ለመግለጽ ብለው እንጂ ፓሪስ ወዲህ፣ የኛ ሰፈር ወዲያ መሆኑን አጥተውት አይደለም::
መብራቱ ማታ ማታ ተደብቀው የኖሩትን ቤቶች ገበና አውጣው:: የመኖሪያ ቤቶቹን ቆርቆሮ ዝገት አጋልጦ አወጣው:: ዝገቱ ከመብራቱ የሚወጣውን ብርሃን ሳያደበዝዘው ይቀራል ብላችሁ ነው። ለነገሩ ለውጡ ቀጥሎ ነው የሚመጣው::
አዲስ መንገድ ሲወጣ፣ የመንገድ ደረጃ ሲያድግ መንደሮችም አብረው ይለወጣሉ:: ሰዎችም ይለወጣሉ:: በአዲስ አበባ መንገድ የለወጣቸው ሰፈሮች በርካታ ናቸው:: የኛም ሰፈር እንደምትለወጥ እገምታለሁ:: የመንገዱ መሰራት የለውጡ መጀመሪያ ነው:: የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ድርጅቶችና ተቋማት አካባቢውን ይፈልጉታል:: የቦታ፣ የቤት ዋጋ ፣ የቤት ኪራይም ዋጋ ይጨምራል:: የለማን ማን ይጠላል?
ወደ አደግሁበት ሰፈር መሄድን ሳስብ ይህ ሁለት ባለ ድመቱን ኤቨሬዲ ባትሪ ድንጋይ እየከተትን ላምባዲና እያበራን አንዳንዴም እሱንም እየተቀባበልን ያደግንበት ሰፈር አዲስ ሆኖ እንደሚጠብቀኝ አልተጠራጠርኩም። በዚህ አይነት ሀሳብ ወስጥ ሆኜ ነበር ለምን ራሴን አላስደስትም ብዬ አመሻሽ ላይ አፈር ፈጭቼ ውሃ ተራጭቼ ወዳደኩባት ሰፈሬ ያቀናሁት። እታችኛው ሰፈር ላይ ደርሻለሁ፤ ይህ ሰፈር ድሮ ቡድን በቡድ ሆነን የምንጋጠምበት ነበር፤ የፀብ ሜዳ መሆኑ ነው:: ወርቃማው የመንገድ ዳር መብራት ከሩቅ እዩኝ እዩኝ እያለን ነው::
በአንድ በኩል የራሴን ደስታ ለማጣጣም በሌላ በኩል ፎቶ አንስቶ ለባህር ማዶ ጓደኞቻችን ዜናውን ለማድረስ ቸኮልኩ። ከስራቸው ደርሼ አንጋጥጬ እያየሁ በስልኬ ምስል ማስቀረቱንም ተያያዝኩት። ጓደኞቼም ተቀላቀለውኛል፤ማውካካት ሆኗል። ብዙ ተጨዋወትን፤ አብረን ለማምሸት ወስነናል፤ በቅድሚያ አያቶቼን ማግኘት እንዳለብኝ ነገሬያቸው ተለያየን።
ይህን ጊዜ ሁሉም በአንድ ድምጽ ቀስ ብለህ ሂድ፤ ጉድጓድ እንዳትገባ አሉኝ። በቅጽበት ከቆምኩበት ሃምሳ ሜትር ወደማይርቀው ቤታችን አይኔን ስወረውር በራችን አካባቢ የተቆለለ አፈር ተመለከትኩ። ምንድን ነው ? አልኳቸው እነሱ ያደረጉት ይመስል ቆጣ ብዩ። በእናንተ በኩል ያለው ለመብራት፣ በነባሪያው / ጓደኛቸው ነው/ ደጅ በኩል ደግሞ የውሃ መስመር ለማስተካከል የተቆፈረ ነው አሉኝ።
ከወር በፊት ችግር እንዳልነበረበት ነገሩኝ፤ ግንባታው ተጠናቆ የእግረኛ መሄጃው ተነጥፎም ነበር። ለአይነ ስውራን በሚል የሚነጠፈው ባለቢጫ ቀለም ጡብ ግንባታም ተካሂዶለት ነበር:: ጡቦቹ ባለ መስመርና ቅርጽ ያላቸው በጣም የሚያምሩ ናቸው:: እንግዲህ ይህ ሁሉ ፈርሷል።
በእርግጥ ደግመው ሊሰሩት ይችላሉ፤ ነገር ግን እስካሁን ባለው ልምድ እንደ መጀመሪያው አሳምረው አርገው ላይሰሩት ይችላሉ። ማን እንደ መጀመሪያ:: ይህ ነው እንግዲህ ፓሪስን … ስንል- ሳሪስን እየሆነብን ያለው:: ወዲያው ወደሁዋላ መመለስ ለምን? ስል ራሴን ጠይቅሁ:: ሳንዋብበት፣ የወጣበትን ያህል ሳያገለግል ሌላ ወጪስ ለምን?
የመሰረተ ልማት ግንባታ የሚያካሂዱ ተቋማት አብረው እየሰሩ ስንባል በስራቸው ግን ተለያይተው የምናያቸው እስከ መቼ ነው? እነዚህ ተቋማት እርስ በእርሳቸው እየተፈራረሱ የሚቀጥሉት እስከ መቼ ነው ? ካልተሳሳትኩ አንድ ወቅት የተቀናጀ የመሰረተ ልማት ኤጀንሲ የሚባል ተቋም መቋቋሙንም አስታውሳለሁ፤ ኤጄንሲው ወዴት ነህ?
ይህን ማስተካካል እንዴት ያቅታል፤ ባለሙያው የኛ፣ ፋይናንሱ የኛ:: ትላልቅ ስራዎች እየተሰሩ፣ ይህን በሽታ ነቅሎ መጣል ለምን አቃተን? “ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም” የሚለውን አገርኛ አባባል ያዙልኝና በፕሮጀክቶች ላይ ጠንካራ ቁጥጥር ማድረግ ከተቻለ አራት አምስት ተቋማትን አቅናጅቶ የመንግስት የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በተሳለጠ መልኩ ማካሄዱ አይገድም:: ያኔ አንዱ የአንዱን ማፍረሱ ይቀራል::
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2013