“ ምድርም ሁሉ በአንድ ቋንቋና በአንድ ንግግር ነበረች። ከምሥራቅም ተነሥተው በሄዱ ጊዜ በሰናዖር ምድር አንድ ሜዳ አገኙ ፤ በዚያም ተቀመጡ ። እርስ በርሳቸውም፦ ኑ ፥ ጡብ እንሥራ ፥ በእሳትም እንተኵሰው ተባባሉ ። ጡቡም እንደ ድንጋይ ሆነላቸው ፤ የምድርም ዝፍት እንደ ጭቃ ሆነችላቸው ። እንዲህም፦ ኑ ለእኛ ከተማና ራሱ ወደ ሰማይ የሚደርስ ግንብ እንሥራ ፤ በምድር ላይ ሳንበተንም ስማችንን እናስጠራው አሉ ። እግዚአብሔርም የአዳም ልጆች የሠሩትን ከተማና ግንብ ለማየት ወረደ ።
እግዚአብሔርም አለ፦ እነሆ ፥ እነርሱ አንድ ወገን ናቸው፥ ለሁሉም አንድ ቋንቋ አላቸው ፤ ይህንም ለማድረግ ጀመሩ ፤ አሁንም ያሰቡትን ሁሉ ለመሥራት አይከለከሉም። ኑ፥ እንውረድ ፤ አንዱ የአንዱን ነገር እንዳይሰማው ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው ። እግዚአብሔርም ከዚያ በምድር ሁሉ ላይ በተናቸው ፤ ከተማይቱንም መሥራት ተው። ስለዚህም ስምዋ ባቢሎን ተባለ ፥ እግዚአብሔር በዚያ የምድርን ቋንቋ ሁሉ ደባልቋልና ፤ ከዚያም እግዚአብሔር በምድር ሁሉ ላይ እነርሱን በትኖአቸዋል ። “ (ዘፍጥረት 11÷ 1_9)
ዘረ አዳም ሁሉ አንድ ቋንቋ ነበር የሚናገረው ። አንድ ቋንቋ መናገሩ በቀላሉ ለመግባባት ረድቶታል ። ይህ መግባባት ደግሞ በፈጣሪው ላይ በክፋት እንዲዶልት ስላደረገው ፈጣሪ ተንኮሉን ተመልክቶ ቋንቋውን ደበላለቀው ። ለያየው ። እንዳይግባባ አደረገው ። በምድር ላይ በተነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር የተለያዩ ቋንቋዎች በምድር ላይ የተስፋፉት እንዲህ ነው ። በኢትዮጵያ ከጎሳና ነገድ ብዛት አኳያ እንኳ ቢታይ ወደ 74 የሚጠጉ ወይም የሚያንሱ ቋንቋዎች ይነገራሉ ። በዚህ ላይ ዘረ ፣ ማንነት ፣ ጥላቻ፣ ልዩነት ፣ ሴራ፣ ሀሰተኛ ትርክት ፣ ወዘተረፈ በአናቱ ተጨምሮበት ቋንቋችን ይብሱን ተደበላለቀ ።
የሚያግባባን ነገር ጠፋ ። ተለያየን። ሆድና ጀርባ ሆን ። በአንድ ጥላ ስር የሚያሰባስበን ፤ የሚያገናኘንና የሚያግባባን ታሪክ ፣ ጀግና ፣ ምልዕክት ፣ ባህል ፣ ወግ ፣ ማንነት ፣ አስተሳሰብ፣ ወዘተረፈ አጣን ። ወይም የሚያግባባንን ሁሉ ሆን ብለን ጣልን ። የሚያገናኘን ድልድይ ሰበርን ። ሌላው ይቅርና እንደ አባቶቻችንና እናቶቻችን የሀገራችንና የሉዓላዊነታችን መደፈር ፣ መጠቃትና መወረር ያግባባን አያግባባን እርግጠኛ መሆን ከማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል ። ቀፎው እንደ ተነካ ንብ በአንድ ሊያስነሳን የሚችል ነገር ሳስብ በቀላሉ ማግኘት ይቸግረኛል ።
አሸባሪው ህወሓት በሰሜን ዕዝና በሀገራችን ትውልድም ዘመንም ይቅር የማይለው ክህደት በፈፀመ ማግስት ተፈጥሮ የነበረው እልህና ቁጭት የፈጠረው አንድነት ዛሬ በስፍራው ላይ ስለመገኘቱ እርግጠኛ እንዳልሆን የሚያደርጉ ምልክቶችን እያየሁ ነው ። ሱዳን ድንበራችንን ስትወር ፣ ግብጽ በታላቁ ህዳሴ ግድብ የተነሳ ያዙኝ ልቀቁኝ ስትል ፣ የአሸባሪው ህወሓት ርዝራዥና ጭፍራ በሀሰተኛ መረጃ ገጽታችንን ሲያጠለሽ ፣ አሜሪካ ፍርደ ገምድል ማዕቀብ ስትጥልብን ፣ ወዘተረፈ እየተመለከትን የአባቶቻችን አትንኩኝ ባይነትና ጀግንነት በእኛ በልኩ ሲገለጥ ስላልተመለከትሁ ታዲያ በምን ተግባብተን ነው በአንድነት ልንቆም የምንችለው የሚል ስጋትና ፍርሃት አደረብኝ ።
ዳሩ ግን እዚህ ስብራትና ቁልቁለት ላይ የተገኘነው በአንድ ጀምበር አይደለም ። ጣሊያን ታሪክን እንደገና ለመጻፍ ፤ የዓድዋውን ውርደት ለመቀልበስ ፤ አሳፋሪውን የሽንፈተ ታሪኩን ለማደስ ፤ የተከናነበውን የቅሌት ሸማ በድል አክሊል ለመተካት ከ40 ዓመታት በላይ ዝግጅት አድርጎ ተዋጊ አውሮፕላንንና ታንክን እንዲሁም የመርዝ ጭስ(ማስተርድ ጋስ) ከዘመናዊ የጦር መሣሪያ ጋር እስካፍንጫው ታጥቆ ፤ የወልወሉን ግጭት ሰበብ አድርጎ ሀገራችንን ወሯል ። ከታላቁ የዓድዋ ድል በኋላ ጦራችን በዘመናዊ መንገድ ባለማደራጀታችንና በመዘናጋታችን በሌላ በኩል “የዓድዋ አስማት” ረክሶብን ማለትም ሕዝብን ለአንድ አላማ ያለ ልዩነት ማነቃነቅና ማሰለፍ አለመቻላችን ሀገራችንን ለጊዜውም ቢሆን ድል እንድትነሳ አድርጓል ። ከአምስት ዓመታት በኋላ ጀግኖች አባቶቻችን በዱር በገደሉ በአርበኝነት ጣሊያንን መቆሚያ መቀመጫ በማሳጣት ነፃነቷ ቢመለስም ። ግርማዊነታቸው እንደ አፄ ምኒልክ ሕዝባቸውን በአንድነት ከጎናቸው ማሰለፍ ላይ ክፍተት ነበረባቸው ።
በአፄ ዮሐንስም ሆነ በአፄ ምኒልክ በአንፃራዊነት የአካባቢው ባላባቶች አምነው እስከገቡላቸውና እስከገበሩ ድረስ በዚያው ይሾሙ ይሸለሙ ነበር ። ጅማ አባ ጅፋርን የወላይታውን ንጉሥ ጦናን በአብነት ማንሳት ይቻላል ። አፄ ኃይለ ሥላሴ ከነገሡ በኋላ ግን ይህ አካሄድ ወጥ አልነበረም። በተወሰኑ ግዛቶች የየአካባቢው ባላባቶች ሲሾሙ በሌሎች ደግሞ ከማዕከላዊ መንግሥት እየተሾሙ ይላኩላቸው ነበር። የየአካባቢው ተወላጅ የሆኑ ባላባቶች በዚህ አካሄድ አኩርፈው ስለነበር ከንጉሡ ጎን ለመቆም ያመነቱ ነበር። ሀገራችን በቀላሉ በፋሽስት ጣሊያን ድል እንድትመታ ካደረጉ በርካታ ምክንያቶች ግንባር ቀደም ሆኖ ሊጠቀስ ይችላል ። አፄ ኃይለሥላሴ መንግሥታቸውን ይዘው ወደ እንግሊዝ በተሰደዱ ጊዜ ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት መንበሩን ከአዲስ አበባ ወደ ጎሬ አዛውሮ ወራሪውን የጣሊያን ፋሽስት ለመፋለም የታለመለትን ያህል ያልተሳካው በዚህ የተነሳ መሆኑን የክቡር ዶክተር ሐዲስ አለማየሁ “ትዝታ”መጽሐፍ ያስቃኘናል ።
ታላቋን ሶማሊያ የመመስረት ቅዠት ሰንቆ ዛድባሪ ኢትዮጵያን ሲወር ለሀገሩ ቀናኢና አትንኩኝ ባዩን ዜጋ ዳር እስከ ዳር ማነቃነቅ ቢቻልም የዓድዋን ያህል ግን አልነበረም። ኤርትራ ባድመንና አካባቢውን በወረረችበት ወቀት የነበረው ሕዝባዊ ምላሽ ተቀራራቢ ቢሆንም የራሱ ገፊ ምክንያቶች ነበሩት ። ላለፉት 27 ዓመታት ዘረኝነት ፣ ጥላቻና ልዩነት መዋቅራዊና ተቋማዊ ሆኖ በመሠበኩ ከፍ ብዬ እንደገለጽሁት ቋንቋችን ይብሱን ድብልቅልቁ ወጥቷል ። ሌላው ይቅርና የሰውነት መለያ በሆነው ሀዘንና ደስታ እንኳ መግባባት አቅቶናል ። ምናለቅሰውና ምንዘፍነው በብሔር ሆኗል ።
መቼም እነዚያ የዓድዋና የካራማራ ጀግኖች፤ ለቲዊተር ዘመቻ ፣ ለድጋፍ ሰለፍ ፣ በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ አትግቡ፣ ግድቡ የእኔ ነው ፣ እጃችሁን ከኢትዮጵያ አንሱ ፣ ወዘተረፈ ለማለት እግራችንን ስንጎትት ከመቃብር ቀና ብለው ቢያዩን ያፍሩብናል ። ስለዚህ ያለልዩነት ልብ ለልብ ሊያግባባን የሚችል አንዳች ተአምራዊ ቋንቋ ያሻናል። ሳንነጋገር በአይን የሚያግባባን የሴሜቲክ ፣ የኩሽቲክ ፣ የኦሞቲክ ፣ ወዘተረፈ ቤተሰብ ያልሆነ ቋንቋ ። ከድምጽ ፣ ከምዕላድና ከቃላት በላይ የገዘፈ ቋንቋ ግድ ይለናል። እንደ አድዋ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ሳይነጋገሩ በጥቅሻ የሚያግባባ ቋንቋ ያስፈልገናል ። ከጎሳም ፣ ከነገድም ፣ ከእምነትም ፣ ከማንነትም ፣ ከቀዬም ፣ ከወንዝም ግዘፍ የነሳ ቋንቋ ።
ለምን ሩቅ ትሔዳላችሁ ይላል መሐመድ ካሳ የጉዞ አድዋ መስራችና አባል አድዋ እኮ ቋንቋ ነው ። ኢትዮጵያውያንን ከሰሜን እስከ ደቡብ ፤ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ያግባባ ። ጎጃምን ፣ ሰላሌን ፣ ትግራይን ፣ ወላይታን፣ ከፋን ፣ ጋሞን፣ ወዘተረፈ ለአንድ ቅዱስ አላማ ያነሳሳ ቋንቋ። በአንድ ድንኳን ያሰባሰበ ፤ በአንድ ምሽግ ያስመሸገ፤ በአንድ ማዕድ ያስቆረሰ፤ በአንድ መቃብር ያገናኘ አድዋ ። ሀገርን፣ ሕዝብን፣ ኢትዮጵያዊነትን ፣ ሉዓላዊነትን ፣ ነፃነትን፣ ጀግንነትን ፣ አርበኝነትን ፣ ሰውነትን ፣ ሰብዓዊነትን፣ እኩልነትን ፣ ጽናትን፣ አልበገርባይነትን ፣ ወዘተረፈ ድምጽ ፣ ምዕላድ ፣ ፊደልና ቃል አድርጎ ያግባባ አድዋ ቋንቋ ነው ። አድዋኛ መነጋገሪያ ፣ መደማመጫና መቀባባያ ፣ ወሰን ፣ ዘርና ሃይማኖት የማያግደው አድዋ ቋንቋ ነው ።
በ1887 ዓ . ም በወርሐ መስከረም በገብያ ቀን ቅዳሜ አፄ ምኒልክ ታሪካዊውን የ “ ወረ ኢሉን “ ክተት አዋጅ ሲያስነገሩ አድዋኛ እጩ ቋንቋ ሆኖ አፍ ፈታ :: “ …አገርንና ሃይማኖት የሚያጠፋ ጠላት ባሕር ተሻግሮ መጥቷል :: እኔም የአገሬ ሰው መድከሙን አይቼ ብታገሰውም ፤ እያለፍ እንደ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር ፤ አሁን ግን በእግዚአብሔር እርዳታ አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም :: ያገሬ ሰው ጉልበት ያለህ ተከተለኝ ፤ ጉልበት የሌለህ በጸሎትህ እርዳኝ ፤ …” አዋጁን ተከትሎ በአፄ ምኒልክ አዝማችነት ፣ ከመላው አገሪቱ በከተቱት መኳንንትና መሳፍንት ባለሟልነት ከ100 ሺህ በላይ ወዶ ገብ የገበሬ ጦር እና 29 ሺ ፈረሰኞች በኢትዮጵያዊ አንድነት ፣ ጀግንነት ፣ ቆራጥነት ፣ አልበገር ባይነት ፤ ዳርድንበሩን ፣ ሉዓላዊነቱን ሊያስከብር ቀፎው እንደተነካ ንብ ወደ ሰሜን በአድዋኛ ቃል ኪዳን አስሮ ተመመ :: ዛሬ አይደለም ወዶ ገብ ደመወዝተኛ ወታደር ለመቅጠር እንኳ ፈተና መሆኑን ጠቅላይ ሚንስትሩ በተለያዩ አጋጠሚዎች ደጋግመው ነግረውናል ።
ከትላልቆቹ ክልሎች እንኳ በቂ ምልምሎችን ማግኘት ቸግሯል ። ወደ ነገረ አድዋ ስመለስ ፣ ዘመናዊ የጦር መሣሪየ እስካፍንጫው የታጠቀው የጣሊያን ጦር በአድዋኛ በከተተው አፍሪካዊና ኋላቀር በሆነው የገበሬ ጦር መረታቱ ለማመን የሚቸገር መነጋገሪያ ሆነ :: አንዳንድ ምዕራባውያን ፖለቲከኞችና ሚዲያዎች የኢትዮጵያውያንን ጥቁርነት እስከ መካድ ደርሰው ነበር :: የታላቁ የአድዋ ድል የአፄ ምኒልክንና የእቴጌ ጣይቱ ( በርሃነ ዘኢትዮጵያ ) ዝና በመላው ዓለም እንዲናኝ ከማድረጉ ባሻጋር ሀገሪቱን በዓለም አቀፉ የዲፕሎማሲ መድረክ መነጋገሪያ አደረጋት :: ከአፅናፍ አፅናፍ የዓለምን ትኩረት እንድትሰብ አደረጋት :: እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ፣ እንደ አንድ ልብ መካሪ ስትሆን የዓለም መነጋገሪያ ትሆናለህ ። ትከበራለህ ። አንድነትህ ንፋስ ሲገባው ደግሞ አይደለም አሜሪካና ምዕራባውያን ሊያከብሩህና ለትብብር ሊሰለፉልህ ሱዳን ትዳፍርሃለች ።
ዓድዋኛ
ዛሬ ላይ አደጋ የተደቀነበትን ሉዓላዊነታችንንና ነፃነታችን አለማስጠበቅ የትላንቱን አንጸባራቂ የአድዋ ድል ያስገኛቸውን ምርኮዎች ማለትም ጥቁሮች ነጮችን ድል መንሳት እንደሚችሉ ፤ በቅኝ ግዛት ፣ በጭቆና ለሚገኙ የዓለም ሕዝቦች በተለይ ለአሜሪካ ጥቁሮች መነቃቃትን መፍጠሩን ፤ ለማርከስ ጋርቬ ፣ ለኢትዮጵያኒዝም ፣ ለፓን አፍሪካኒዝም ፣ ለኔልሰን ማንዴላ ፣ ለኩዋሚ ንኩሩማህ ፣ ለስቲቭ ቢኮ እና ሌሎች ንቅናቄዎች እርሾ መሆኑን ከወርቃማ የታሪክ መዝገባችን እንዲፋቅ ተባባሪ መሆን ነው :: ለደቡብ አፍሪካ የፀረ አፓርታይድም ሆነ ለሌሎች ለፀረ ቅኝ ግዛት ትግሎች ጉልበት ሆኖ ማገልገሉን ፤ የአረንጓዴ ፣ ቢጫ ፣ ቀይ ባንዲራቸን ከ20 በላይ የአፍሪካና የካሪቢያን አገራት ሰንደቅ በተለያየ ቅርፅ የመገኘቱ ሚስጥር የተመሰጠረበትን ታላቁን አድዋ እንደ ማደብዘዝ ነው ::
አደጋ የተደቀነበትን ነፃነታችንንና ሉዓላዊነታችን ጠብቆና አስከብሮ አለማቆየት የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነትን ፤ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ( አአድ ) ሆነ የዛሬው የአፍሪካ ህብረት ( አህ ) የምስረታ ሀሳብ የአድዋ መንፈስ የበኩር ልጅ የሆነው ፓን አፍሪካኒዝም እንደ መካድ ነው ። በዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር የሆነው ሬይሞንድ ጆናስ የአድዋን ድል ትምህርት ፣ አንድምታ ፣ ጥልቀት ፣ ከፍታ ፣ ንዑድነትና ትርጉም በሚያስደንቅ ሁኔታ እንዲህ ይገልፀዋል ። የሕዝቦች ጥብቅ ትስስር የሚፈጠረው በእያንዳንዱ ሃይማኖት ፣ ማንነት ብሔር ላይ ተመስርቶ ሳይሆን የጋራ ነፃነትን ለመቀዳጀት በሚከፈል መስዋዕትነት ነው :: ይህ አይነቱ መተሳሰር ብቻ ነው የኢትዮጵያ የነፃነት ከፍታ መገለጫ ፤ የአድዋ ትምህርትም ይኸው ነው :: አድዋኛ ማለት እሱ ነው ።
ዓድዋ ትላንት ፣ ዓድዋ ዛሬ ፣ ዓድዋ ነገ !
አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2013