በተለያዩ ጊዜያት በኮንትሮባንድ መልክ የሚያዙ መሳሪያዎች መብዛታቸው በኢትዮጵያ ያለው የህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ ስለመምጣቱ ማሳያዎች ናቸው። በተሽከርካሪ ኮፈን ውስጥ በመደበቅ እና በረቀቀ መንገድ የተለያየ ክፍሎቻቸው ተለያይተው ከሚጓጓዙ የጦር መሳሪያዎች ባለፈ በምግብ እህል እና በከሰል ምርቶች ውስጥ ተደብቀው ሊዘዋወሩ ሲሉ በቁጥጥር ስር የዋሉ በርካታ መሳሪያዎች መኖራቸው ታይቷል። የህገወጥ መሳሪያዎቹ በድብቅ ወደህዝብ ቢገቡ ለግጭት መባባስ እና ለወንጀል መበራከት የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ እንደሚሆን አያጠራጥርም።
የፌዴራል መንግስትም የህገወጥ የጦር መሳሪያዎችን ዝውውር ለመግታት በሚል አዋጅ አዘጋጅቶ ወደስራ ገብቷል። እኛም አዋጁ ተፈጻሚ ስለሚሆንበት መንገድ፤ የጦር መሳሪያ ዝውውር ስለሚበረታባቸው የድንበር ቦታዎች፣ በዝውውር ሂደቱ ስለሚሳተፉ አካላት እና ጎረቤት ሀገራት እንዲሁም የቁጥጥር ስራዎቹን በተመለከተ በሰላም ሚኒስቴር የሚኒስትሯ አማካሪ እና የብሔራዊ መግባባትና ማህበራዊ ሀብት ግንባታ ዋና ዳይሬክተር ከሆኑት አቶ ሚናስ ፍሰሃ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፦ በህገወጥ ጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመከላከል የወጣ አዋጅ አለ፤ አዋጁን ምን ያክል ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል?
አቶ ሚናስ፦ ጠቅለል ባለ መልኩ ከወራት በፊት የወጣውን የጦር መሳሪያ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅ ሂደትን ማየት ያስፈልጋል። በቅድሚያ ኢትዮጵያ በታላላቅ ሐይቆችና በአፍሪካ ቀንድ አነስተኛና ቀላል የጦር መሣሪያዎችን ክልከላ ቁጥጥር እንዲሁም ቅነሳ የሚመለከተውን ማህበር መስራች ሀገር ነች።
ከህገወጥ መሳሪያዎች ዝውውር ጋር በተያያዘ 15 አገራት የሚሳተፉበት የናይሮቢ ፕሮቶኮል ተብሎ የሚታወቀውን መመሪያ እ.አ.አ. በ2005 ፈርማለች። በዚህ ፕሮቶኮል መሠረት ደግሞ ፈቃድ ሳይኖር በእጅ የገቡ አነስተኛና ቀላል የጦር መሣሪዎችን የማስወገድ ግዴታ አለባት፡፡ ይሁንና ዓለም አቀፍ ህግ ላይ ፊርማ ከተደረገ በኋላ በሀገር ውስጥ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህጉ መርቀቅ ይኖርበታል፤ ከፕሮቶኮሉ በኋላ ላለፉት 15 ዓመታት ኢትዮጵያ ጉዳዩን በተመለከተ ህግ ሳታረቅ ቆይታለች።
ስለዚህ ይህ ህገወጥ መሳሪያ ዝውውሩ ሰፋ ባለ ሁኔታ በተለይ በምስራቅ አፍሪካ በአደገኛ ሁኔታ እንዲበራከት ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ የህግ ማዕቀፍ አለመኖሩ ነው። ከለውጡ በኋላ ግን መንግስት በ2012 ዓ.ም ጥር ወር ላይ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር አዋጅ አውጥቷል። የሰላም ሚኒስቴር ፖሊሲ ከማዘጋጀት እና ከማስተባበር አኳያ የህግ ማዕቀፎች ወደታች እንዲወርዱ ይሰራል፤ በዚህ የህገወጥ ጦር መሳሪያ ዝውውር ላይ በወጣው ህግ ላይም ሰፊ ስራ አከናውኗል፤ እኔም በዚያ ሂደት ተሳታፊ ነበርኩ።
በዋናነት ግን ህገወጥ የጦር መሳሪያ አዋጁን ተግባራዊ የሚያደርገው እና የጦር መሳሪያዎቹን የሚመዘግበው የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ነው። በየክልሉ የሚገኙ የፖሊስ ቢሮዎች ደግሞ እንደየተዋረዳቸው ህጉን በማስፈጸም ታች ህብረተሰቡ ዘንድ ወርደው እንዲሰሩ ግዴታ አለባቸው። በዚህ ሂደት ሶስት ጉዳዮች ላይ አተኩረን ነበር፤ በመጀመሪያ አሳሳቢ በመሆኑ የህግ ማዕቀፍ የማውጣት ስራ ተካሂዷል።
ከአዋጁ መጽደቅ በኋላ መመሪያና ደንብ እንዲዘጋጁ ተደርጓል። በመቀጠል በጥናት ላይ የተመሰረተ የህገወጥ ጦር መሳሪያ ዝውውር እና ቁጥጥርን ለመግታት የሚያስችል ስራ ማከናወን እና በቂ መረጃ ለመያዝ ነው ትኩረት ያደረግነው። በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን እና ከኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የተለያዩ ጥናቶችን ስንሰራ ቆይተናል። በሶስተኛ ደረጃ በአስገዳጅነት በቴክኖሎጂ የታገዘ የጦር መሳሪያ ምዝገባ በማድረግ አዋጁን ለመተግበር ነው አላማ ያደረግነው።
አዲስ ዘመን፦ መሳሪያ መያዝን ባህል አድርገው ለዘመናት የቆዩ ማህበረሰቦች በኢትዮጵያ አሉ፤ ህጉ በዚህ ረገድ የጦር መሳሪያ መያዝ ልምድ ባላቸው አርብቶ አደርና አርሶአደሮች ላይ በምን መልኩ ነው ተፈጻሚ የሚሆነው?
አቶ ሚናስ፦ ህጉ ባህልን መሰረት አድርጎ ተፈጻሚ የሚሆንበትን አሰራር ይዟል። ኢትዮጵያ ውስጥ ከልጅነታቸው ጀምሮ መሳሪያ የመታጠቅ ባህል ያለባቸው አካባቢዎች አሉ። መሳሪያ መያዝን ልክ እንደመለያ ምልክት አድርገው የሚቆጥሩም የማህበረሰብ ክፍሎች አሉ።
ባህል እና ልምድ ስላላቸው መሳሪያ የሚታጠቁ ማህበረሰቦች ዘንድ ግን ችግሮች ሳይፈጠሩ ለዘመናት ተቻችለው መኖር ችለዋል። ስለዚህ የዚህ አይነት ማህበረሰቦች የጦር መሳሪያ እንዲይዙ ይፈቅዳል ህጉ፤ ነገር ግን መሳሪያ ሲይዙ ከስንት ዓመት ጀምሮ መሆን አለበት፤ ቁጥሩም ከአንድ በላይ መሆን የለበትም የሚለውን እና ሌሎች መስፈርቶች ተካተዋል።
ከዚህ ቀደም መሳሪያ ይዞ ሰዎችን አጥቅቶ ያውቃል? ወይስ አያውቅም፤ ጠጥቶ መሳሪያ ይይዛል፤ የጸብ አጫሪነት ባህሪይ ወይም ግጭት ቀስቃሽ ባህሪ አለው ወይ? የሚለውም ተጣርቶ መሳሪያ እንዲይዝ ይፈቀድለታል።የአደገኛ ዕፅ ወይም የመጠጥ ሱስ የሌለበት፣ በሙሉ ወይም በከፊል በፍርድ ወይም በሕግ መሳሪያ የመያዝ ችሎታውን ያላጣ፣ የአዕምሮው ሁኔታ የተስተካከለ እና አላስፈላጊ የኃይል አጠቃቀም ባህሪ የሌለው መሆኑ በማህበረሰቡ አሊያም በተቆጣጣሪው ተቋም የታመነበት ሊሆን ይገባል።
ዋናው መታወቅ ያለበት ጉዳይ ግን መስፈርቶቹን እስካሟላ ድረስ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ መሳሪያ ቢይዝ ህጉ አይከለክለውም። ይህ ህግ ወጣ ሲባል ሁሉም ቤት ያለው መሳሪያ የሚወሰድ እና ባዶ እጃቸውን የሚቀሩ የሚመስላቸው ይኖራሉ። የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ህጉ መሳሪያ መጠቀም መብትህ ነው፤ ግን አስመዝግበህ ተጠቀም የሚለው ላይ ያተኮረ ነው። መመዝገቡ የአገር ደህንነት ቁጥጥር ላይ ጠቀሜታ አለው፤ ባለቤቱም በአንድ አጋጣሚ መሳሪያው ከእጁ ቢወጣ መልሶ ለማግኘትም ሆነ ወንጀል ቢሰራበት ባለንብረቱን ለመከላከል የሚረዳ ነው።
በየትኛውም ማህበረሰብ ቢሆን ግን አንድ ሰው አምስት መሳሪያ ሊኖረው ይችላል፤ በህጉ መሰረት ግን አንዱን ብቻ አስመዝግቦ መጠቀም እንደሚችል በግልጽ ተቀምጧል። ስለዚህ ባህልን መሰረት አድርገው መሳሪያ የሚይዙ ማህበረሰቦችም እስካስመዘገቡ ድረስ በአካባቢያቸው ባህልና አኗኗር መሰረት መሳሪያቸውን እንዲጠቀሙበት የሚከለክል ጉዳይ የለባቸውም።
አዲስ ዘመን፦ ሰዎች የጦር መሳሪያቸውን በአቅራቢያቸው በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ማስመዝገብ ይፈልጉና ሊወረስብን ይችላል የሚል ስጋት ሊያድርባቸው ይችላል፤ በዚህ ምክንያት ሰዎች መሳሪያቸውን ያለማስመዝገብ አዝማሚያ ሊያሳዩ አይችሉም?
አቶ ሚናስ፦ አንድ ሰው የያዘው የጦር መሳሪያ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ከተወሰደበት ህጉ በሚያስቀምጠው አሰራር መሰረት ቅሬታውን አቅርቦ ማስመለስ ይችላል። ይግባኝ ሰሚ ቦርድ አለ፤ በዚያ በኩል ችግራቸውን አስረድተው መፍትሄ የሚያገኙበት አካሄድ አለ። በዚህ አካሄድ የተጠያቂነት አሰራርም አለ። ጥቂት ሰዎች በተለያየ ምክንያት መሳሪያቸው ስለተወሰደባቸው ግን ሁሉም በሀገር ደረጃ ይወሰድበታል ብሎ ማሰብም አይገባም። አላስመዘግብም ብሎ የሚቀመጥ እንደሚኖር ሁሉ ህጋዊነቱን ይዞ የሚገለገልበትም አለ፤ ቁጥሩን አሁን ላይ መናገር ባልችልም በህጋዊ መንገድ መሳሪያቸውን አስመዝግበው እየተጠቀሙበት የሚገኙ ዜጎች በርካታ ናቸው።
ፍርድ ቤት ላይ እንኳን የሚቀርቡ በርካታ ክሶችን ብናይ አንድ ግለሰብ የጦር መሳሪያው ሳያስመዘግብ ይቆይና ከጠፋበት በኋላም ሳያስመዘግብ በዚያው ይቀራል። በኋላ ላይ ወንጀል ተሰርቶበታል ተብሎ ቤቱ ድረስ ተፈልጎ መጥሪያ ይሰጠዋል። ይህንን አይነት ችግሮችን ለመከላከል እና ማስረጃ ለመያዝ ደግሞ እያንዳንዱ የጦር መሳሪያ ያለው ሰው ያለስጋት ማስመዝገብ ይኖርበታል።
በተቆጣጣሪ ባለሥልጣን የሚሰጠው ፈቃድ የጦር መሳሪያ ለመታጠቅ ፈቃድ የተሰጠው ሰው ሙሉ ስምና ፎቶ፣ አድራሻ፣ የትውልድ ቀን፣ የጦር መሳሪያውን አይነት፣ የውል ቁጥር፣ የተተኳሽ (ጥይት) ብዛት፣ ፈቃዱን የሰጠው ባለስልጣን ስም፣ ፈቃዱ የተሰጠበት ቀን እና ፈቃዱ የሚያበቃበት ቀን ይሰፍርበታል።
መረጃዎቹ ሰዎች መሳሪያቸውን በህጋዊ መንገድ አስመዝግበው እንዲይዙ እንጂ እንዲወረስባቸው የሚያደርጉ ባለመሆናቸው ከስጋት ነጻ መሆን አለባቸው። አገልግሎቱን የሚሰጡ የጸጥታ አካላትም ይህንን ተረድተው አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ እስከታችኛው እርከን ድረስ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና ህጉን የማስተዋወቁ ሁኔታ እየተሰራበት ነው። ስለዚህ መሳሪያዬ ይወሰድብኛል ከሚል ስጋት ተላቀው ነጻ በሆነ መንፈስ ባለንብረቶች መሳሪያቸውን ማስመዝገብ ይኖርባቸዋል።
አዲስ ዘመን፦ አዋጁ በሚገባው መንገድ ህዝብ ዘንድ ደርሷል የሚል እምነት አላችሁ?
አቶ ሚናስ፦ የህገወጥ መሳሪያ አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጁን ታች ድረስ ወርዶ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ድረስ እንዲያውቀው ለማድረግ ሰፊ ስራ ይጠይቃል። በአሁኑ ወቅትም በመገናኛ ብዙሃን በየአካባቢው የጸጥታ ቢሮዎች፣ በሰላም ሚኒስቴር በኩል እና በተለያዩ ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካላት በኩል ለማስተዋወቅ ሰፊ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
አዋጁን መመልከት ከተቻለ እንግዲህ በሰላማዊ ሰልፍ ወይም አድማ በሚደረግባቸው፣በምርጫ ወይም በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሚወሰኑ ቦታዎች፣ በሕዝብ መዝናኛ ስፍራዎች፣ በትምህርት ቤቶችና በሃይማኖት ቦታዎች በጤና ተቋማት አካባቢ እና ሌሎች የሕዝብ አገልግሎት መስጫ ቦታዎች ላይ የጦር መሳሪያ ይዞ መገኘት ተከልክሏል።
ይህን እና መሰል ጉዳዮችን ከከተማ እስከ ገጠሩ በሚገኙ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች በተከታታይነት መከናወን አለባቸው። ለዚህም መገናኛ ብዙሃን ትልቅ እገዛ ማድረግ አለባቸው። እስካሁኑ ባለው ሂደት በጎ ውጤቶች ቢገኙም እንደሀገር ከሚፈለገው ውጤት አንጻር ግን ይበልጥ አዋጁን ማስተዋወቅ እንደሚገባ ምንም ጥርጥር የለውም።
አዲስ ዘመን፦ በአብዛኛው በግለሰቦች ደረጃ ያለው የህገ ወጥ ጦር መሳሪያ መጠን በትክክል ካለመታወቁ ጋር ተያይዞ የጦር መሳሪያ ምዝገባውን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ ምን አይነት ጥረት ተደረገ?
አቶ ሚናስ፦ ቀደም ብሎም በቴክኖሎጂ የታገዘ አይሁን እንጂ የጦር መሳሪያ ምዝገባ ይካሄዳል። በምዝገባዎቹ ግን ሰርቀህም ይሁን ከየትም ብታመጣው እስካስመዘገብክ ድረስ መጠቀምን የሚፈቅድ አሰራር ነው የነበረው። በሁለተኛ ደረጃ መሳሪያው ከጠፋና ወንጀል ቢሰራበት ፈልጎ ለማግኘት እና ማን ወንጀሉን እንደፈጸመው ለማወቅ ይከብድ ነበር።
ሁለቱን ጉዳዮች አቻችሎ ለመሄድ ለአንድ ሰው አንድ መሳሪያ ብቻ በመፍቀድ እያንዳንዱ የመሳሪያው ይዘት እና ቁጥር እንዲሁም ዝርዝር ጉዳዮች የተካተቱበት በቴክኖሎጂ የተደገፈ ምዝገባ ይከናወናል። በኋላ ቢጠፋ እና ወንጀል ቢፈጸምበት እንኳን በቀላሉ ለመለየት እድል የሚሰጥ ኮምፒውተራይዝድ መረጃ አያያዝ ለመተግበር ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።
ለፌዴራልና ለክልል ፖሊስ ኮሚሽን ባለሙያዎችን በቴክኖሎጂው ዙሪያ እንዴት ምዝገባ ይከናወናል፤ መሳሪያው ምን አይነት አዳዲስ ነገሮችን ይዟል በሚሉ ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በተደጋጋሚ ስልጠና ሰጥተናል። አሁን ላይ በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የመጀመሪያው ሰርቨር ላይ አርኤስፒኤስ የተባለ የጦር መሳሪያ መመዝገቢያ የኮምፒውተር መተግበሪያ ተጭኗል።
ለዚህም ቴክኖሎጂ የአሰልጣኞች ስልጠና እና ባለሙያ ዝግጅት እየተካሄደ በመሆኑ ስራው ሲያልቅ ወደትግበራ ይገባል። የምዝገባ ጉዳይ ዝርዝር ነገር በፌዴራል ፖሊስ በኩል የሚከናወን ሲሆን ሰላም ሚኒስቴር ደረጃ ደግሞ ስራውን በማስተባበር ላይ እንገኛለን። ፌዴራል ፖሊስ በቴክኖሎጂው አማካኝነት በመላ ሀገሪቷ የሚገኙ የጦር መሳሪያዎችን መዝግቦ ሲያጠናቅቅ ያን ጊዜ የተደራጀ መረጃ ማግኘት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፦ ወንጀልን ከመከላከል ጋር በተያያዘ በተለይ በድንበር አካባቢ የህገወጥ ጦር መሳሪያዎች ቁጥጥር የሚደረገው በምን መንገድ ነው?
አቶ ሚናስ፦ እንደኢትዮጵያ ስናስብ ሀገራችን የቆዳ ስፋቷ ትልቅ ነው፡፡ በተጨማሪ የምንገኝበት ቀጣና በእራሱ ውስብስብ የሆነ የጦር መሳሪያ ዝውውር የሚከናወንበት ነው። ይህን ችግር ለመቆጣጠር የሚያስፈልገው የመሰረተ ልማት እና የሚጠይቀው በጀት ሰፊ ነው። ሁሉንም ቦታ ተቆጣጥሮ ለመሄድ ትልቅ አቅም ይጠይቃልና ቁጥጥር የማይደረግባቸው የድንበር ቦታዎች ይኖራሉ። ከዚህ ባለፈ የጦር መሳሪያ ደላላዎች እና ተባባሪ አካላትም የሚሳተፉበት ወንጀል በመሆኑ ሰፊ የቁጥጥር ሃይል ያስፈልጋል።
እንደሀገር ግን ባለው አቅምም ቢሆን ችግሩን ለመግታት ትልቅ ቁርጠኝነት አለ። ስለዚህ ኢትዮጵያ በምትቆጣጠራቸው የድንበር አካባቢዎች ላይ አስፈላጊው ክትትል ይደረጋል። አንዳንድ ድንበሮች ላይ ቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ስራ ይከናወናል፤ የቦሌ ኤርፖርትን ጨምሮ ሌሎች ኬላዎች ላይ ግን በጉምሩክ ኮሚሽን በኩልም ቁጥጥር ይደረጋል።
ደላሎች እና ተሳታፊ አካላትን ለመግታት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነትን ጨምሮ የፌዴራል ፖሊስ እና ሌሎች የደህንነት እና ጸጥታ አካላት የእራሳቸውን የምርመራ ስራ በማከናወን ወንጀሎችን እያመከኑ ይገኛል። ከዚህ ባለፈ ግን ትልቁን ሚና የሚወጣው ማህበረሰቡ በመሆኑ ህዝብን ያሳተፈ የጥቆማ እና መረጃ ልውውጥ አሰራርን በመከተል ህገወጥ መሳሪያዎች እንዲያዙ ይደረጋል። ልውጥ ሰው ሲያዩ እና አንዳንድ የሚያጠራጥር ነገር ሲከሰት ህብረተሰቡ ይጠቁማል፤ ጥቆማ እና መረጃ የመስጠት ልምዱ ተጠናክሮ መቀጠሉን ማየት ተችሏል።
ይህም የጦር መሳሪያ አዋጁ ከወጣ በኋላ በተሰራው ልክ እንዲተዋወቅ በመደረጉ እና በመጠኑም ቢሆን እስከታች እንዲወርድ በመደረጉ የመጣ ለውጥ ነው። በመንግስት የደህንነት ተቋማት እና በህብረተሰቡ መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠናከር ሲሰራ ቆይቷል፤ በቀጣይም አሳታፊ በሆነ መንገድ የቁጥጥር ስራውን ለማከናወን ጥረት ይደረጋል።
አዲስ ዘመን፦ ሰፊ የህገወጥ መሳሪያ ዝውውር ስጋት የበረታባቸው የድንበር አካባቢዎች የትኞቹ ናቸው?
አቶ ሚናስ፦ ለህገወጥ መሳሪያ ዝውውር የተጋለጡ የድንበር አካባቢዎች በርካታ ናቸው። በተለይ ግን የኢልሚ ትሪያንግል ወይም የኤልሚ ሶስት ማዕዘን ተብሎ የሚጠራው ቦታ ትልቅ ችግር የሚታይበት ነው። ኢልሚ ትሪያንግል የተባለው የድንበር አካባቢ ለህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በከፍተኛ ሁኔታ የተጋለጠ ነው።
ሰፊው የህገወጥ ጦር መሳሪያ የሚዘዋወርበት ቀጣና መሆኑ ይታወቃል። አካባቢው ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳንን እና ኢትዮጵያን የሚያዋስን ስፍራ ነው። የጦር መሳሪያ ዝውውሩ በቤኒሻንጉል እና ጋምቤላ ክልሎች የድንብር አካባቢዎች ላይ ሰፊ እንቅስቃሴ አለው። ከኢልሚ ትሪያንግል በተጨማሪ በኢትዮጵያ እና ኬንያ የድንበር አካባቢዎች ላይም የጦር መሳሪያ ዝውውር ችግር ይታያል።
በአንጻሩ ከሶማሊያ ጋር የሚያዋስነን ድንበር ሰፊ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ በዙሪያው ተመሳሳይ ስጋት አለ። በተለይ ሶማሊያ ለረጅም ጊዜ መንግስት አልባ ሆና የቆየች ሀገር ከመሆኗ ጋር ተያይዞ እንዲሁም አልሸባብ በአካባቢው ያለው እንቅስቃሴ ተዳምሮበት ወደኢትዮጵያ የጦር መሳሪያ ለማስገባት የሚደረጉ ጥረቶች አሉ።
እንደአጠቃላይ ግን በአብዛኛው የኢትዮጵያ የድንበር አካባቢዎች እንደየስጋት መጠኑ ይለያይ እንጂ ችግሩ በስፋት ይስተዋላል። በተጨማሪ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ወቅታዊ በሆነ መልኩ የሚፈጸም ወንጀልም ነው። ወራቶችን ጠብቆ የግጭት ጊዜያትን መሰረት ባደረገ ሁናቴ የጦር መሳሪያ መስመሮችን የመፍጠር እና ለማሰራጨት የመሞከር ሁኔታ ይኖራል። መንግስትም በድንበር አካባቢዎች ያለውን የህገወጥ መሳሪያ እና ኮንትሮባንድ ቁጥጥር ስራዎችን በተደራጀ መልኩ እያከናወነ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፦ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርትን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ላይ የጦር መሳሪያዎች ሲያዙ ይስተዋላል፤ ከነዚህ ወንጀሎች ጀርባ ያለው የመንግስት አስተዳደር እና ባለሃብቶች ያላቸው ተሳትፎ ምን ድረስ ነው?
አቶ ሚናስ፦ በህገወጥ ዝውውሮች ውስጥ በድንበር አካባቢ በሚገኙ የመንግስት አስተዳደር ውስጥ የሚሰሩ አካላትም ይሁኑ ባለሃብቶች በወንጀሉ አይሳተፉም ልል አልችልም። ከፖለቲካም ሆነ በጥቅም ጉዳይ ከተመሳሳይ ወንጀሎች ጋር የተሳሰሩ ባለሃብቶች ስለሚኖሩ ማንጻትና የማጣራት ስራ በየሂደቱ ይከናወናል።
በተለያየ መልኩ የሚያዙ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎች በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ካሉ ሰዎች ጋር ተቀናጅተው ነው የሚሄዱት። ይህንን መንግስት እያመከነ ይሄዳል። ትልቁ ነገር ግን አብሮም መታየት ያለበት ኢትዮጵያን የነውጥ ቀጣና ለማድረግ እና እንዳትረጋጋ የሚሰሩ ጎረቤት አገራት መኖራቸው ነው።
ስለዚህ ከባለሃብቶችም ሆነ ከመንግስት አስተዳደር ሰዎች ጋር በመመሳጠር የህገወጥ ጦር መሳሪያ ወደሀገር ውስጥ በገፍ እንዲገባ ያደርጋሉ። ይህ አንድም የደህንነት ችግር ለመፍጠር ሲሆን በሌላ በኩል ህዝብ ደህንነቴ አልተጠበቀም እያለ ሀብትና ንብረቱን በመሸጥ መሳሪያዎችን እንዲገዛ ለማድረግ ተንኮሎች ይታሰባሉ።
በዚህ ሂደት ውስጥ ትልቁን ሚና ይጫወታሉ ተብለው የሚጠበቁት የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት የሚባሉት እንደነግብጽ የመሳሰሉ ሀገራት ናቸው። እኛም ይህንን መሰረት አድርገን ከምናጠናው ጥናት አንዱ ተመሳሳይ የመሳሪያ ዝውውሮች የሚደረጉት ከጥቅም አንጻር ነው፤ የደህንነት ስጋት ለመፍጠር እና ሀገር እንዳትረጋጋ ለማድረግ ነው የሚለውን በዝርዝር ሙያዊ ትንተና እንሰጥበታለን።
ከተመሳሳይ የጥናት ውጤቶች ጋር የሚገኙ ማስረጃዎችንም ለቁጥጥር ስራው እየተጠቀምን ተግባራዊ እናደርጋለን። በዚህ ሂደት የሚሳተፉ ባለሃብቶችም ሆኑ የመንግስት አስተዳደር ውስጥ ሆነው ለህገወጥ ዝውውሩ እገዛ የሚያደርጉ አካላትም ተለይተው አስፈላጊው ምርመራ በጸጥታ ኃይሎች በኩል ይከናወንባቸዋል።
ስለዚህ ግለሰቦችም ሆነ በተቋም ደረጃ የህገወጥ ጦር መሳሪያ ዝውውር ላይ ሊሳተፉ ይችላሉ፡፡ ዋናው ነገር ግን ህጉ እና አሰራሩ ስላለ መንግስት ቀድሞ በማምከን ህጋዊውን እርምጃ ይወስዳል። መንግስት አይደለም በህገወጥ ጦር መሳሪያ ዝውውር ጉዳይ ይቅርና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ሁሉም ጋ ተደራሽ ሊሆን አይችልም። ስለዚህ የሲቪክ ማህበራት እና ህዝብ ተሳታፊ ወንጀለኞችን በመለየት ረገድ የእርሳቸው ሚና አላቸውና በሰፊው መተባበር ይኖርባቸዋል።
አዲስ ዘመን፦ ኢትዮጵያ ውስጥ አለመረጋጋት እንዲፈጠር የሚፈልጉ ሀገራት ኢትዮጵያ ውስጥ ከጦር መሳሪያ ጋር በተያያዘ ግጭት ለመፍጠር የሚሰማሩት የትኞቹን አካላት በመጠቀም ነው?
አቶ ሚናስ፦ በተለየ መልኩ ግብጾች በዚህኛው ዘመን ብቻ ሳይሆን ለበርካታ ዘመናትም ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋ ይሰሩ ስለነበረ በኢኮኖሚውም ሆነ በፖለቲካው የተለየ ጫና ሲያደርጉ ኖረዋል። በዋነኛነት የኢትዮጵያ መዳከም ለግብጽ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለው ያስባሉ።
ስለዚህ የትኛውንም ሁኔታ በመጠቀም ችግር ለመፍጠር ይሞክራሉ፤ ከዚህ ውስጥ የህገወጥ ጦር መሳሪያ ዝውውሮችን መደገፍ አንዱ ነው። በተለያየ ጊዜ ስልጣን ላይ የነበሩ እና አፈንግጠው የወጡ ሰዎችን፣ የመብት ጥያቄ የሚያነሱ ግለሰብና ቡድኖችን በመያዝ ለህገወጥ ስራዎች እና ግጭት ቅስቀሳ ያሰማራሉ።
ግብጾች ህገወጥ የጦር መሳሪያ በገፍ በማስገባት ኢትዮጵያ ውስጥ የደህንነት ችግር የሚፈጥሩ ቡድኖችንም ያስታጥቃሉ። በሱዳን በኩል በቅርብ እስከታየው የጸባይ መለወጥ ድረስ ለረጅም ጊዜ በጥሩ ጎረቤትነት የቆየን ነበር። አሁን ባለው አካሄድ የሁለቱ አገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የተጠናከረ ቢሆንም መንግስታቸው ግን የግብጽ የመጋለቢያ ፈረስ ሆኖ ኢትዮጵያን ለማበጣበጥ የሚከናወን ስራ ላይ የሚሳተፍበት እድል ተፈጥሯል። በድንበር አካባቢ መሳሪያ በማስገባት ቡድኖችን ያስታጥቃሉ፤ ይህ ደግሞ ግጭት በመቀስቀስ ኢትዮጵያ ሳትረጋጋ እና ሳትጠነክር እንድትቆም ለማድረግ ታስቦ የሚያደርጉት ነው።
አዲስ ዘመን፦ኢትዮጵያ ውስጥ በሽብርተኝነት የተፈረጀው የሸኔ አባላት እና ሌሎች ታጣቂዎችም በመንግስት ደረጃ ብቻ ሊያዙ የሚገባቸውን የጦር መሳሪያዎች ይዘው በማህበራዊ ሚዲያው ላይ ይታያሉ፤ እንደነዚህ አይነት መሳሪያዎች ምንጫቸው ከየት ነው የሚለውን አጣርታችኋል?
አቶ ሚናስ፦ ያገኘናቸውም አንዳንድ ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያ ውስጥ በህገወጥ መንገድ መገኘት የሌለባቸው መሳሪያዎች በተለይም ከሀገራት እርዳታ ውጪ በግለሰቦች ድጋፍ ሊገኙ የማይችሉ የጦር መሳሪያዎች ተገኝተዋል። ይህን አይነት በፌዴራል ተቋም ብቻ ሊያዙ የሚገባቸው የጦር መሳሪያዎችን የሚይዙ ቡድኖች መገኘታቸውን ስናይ ጉዳዩ ለኢትዮጵያ አዲስ ነገር መሆኑን መገንዘብ እንችላለን።
የእራሱ የሆነ ዝርዝር ጥናት ያስፈልገዋል። ከዚህ ቀደም በገፍ የሚገቡ የጦር መሳሪያዎች ሁሉም ሰው በኪሱ ሊይዛቸው የሚችላቸው የሽጉጥና ሌሎች መሳሪያዎችን ነበር። አሁን ላይ የሚታዩት እንደነሸኔ ያሉ አሸባሪ ቡድኖች የሚታጠቁት ዘመናዊ መሳሪያ ከግብጽ ነው የመጣው፤ አሊያም ከሌላ ሀገር ብሎ ለመናገር የእራሱ የሆነ ጥናት ያስፈልገዋል።
የአንዳንዶቹ የህገወጥ መሳሪያዎች ስሪትና ምንጭ ግን ከቱርክ አካባቢ ሲሆን ይታያል። በዚህ ዝውውር ውስጥ የጦር መሳሪያ ነጋዴዎችና ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋ የሚፈልጉ ግለሰቦች ይኖሩበታል፤ ግለሰቦቹ ኢትዮጵያውያን እና የውጭ አገራት ዜጎችም ሊሆኑ ይችላሉ።
ዓለም በግሎባላይዜሽን መንገድ አብሮ ደህንነቱን የሚጠብቅበት መንገድ ላይ ደርሷል፤ ኢትዮጵያም በጋራ የሀገራትን ደህንነት መጠበቅ ይገባል የሚለውን አምና ጎረቤት ሀገራት በሰላምና በጋራ ስራዎችን እንዲያከናውን ስታስተባብር ቆይታለች። በአንጻሩ አንዳንድ ሀገራት ግን በጎረቤት ሀገር የሚፈጠረው ችግር እነሱ ጋር ተመልሶ የሚመጣ አይመስላቸውም፤ በዚህ ረገድ ግብጽ ኢትዮጵያ ላይ ሰላም እንዳይመጣ ስልምትፈልግ መሳሪያውን አስታጥቃ ሊሆን የሚችልበት እድል ይኖረዋል።
አዲስ ዘመን፦ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለይ በከተሞች አካባቢ ፈንጂዎች ተጥለው ይገኛሉ፤ መሳሪያዎቹ ፈንድተው በንጹሃን ላይ ጉዳት አድርሰዋል፤ ችግሩን ለመከላከል የቤት ለቤት አሰሳ ያስፈልጋል የሚሉ አካላት አሉ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ ሚናስ፦ ትልቁ ለውጥ የሚመጣው ያልተፈቀዱ ፈንጂ እና ትላልቅ መሳሪያዎች ካሉ ሰዎች በእራሳቸው ፈቃድ ለፖሊስ ማስረከብ ሲችሉ ነው። አሁን ላይ በፍቃዳችሁ አስመዝግቡ ሲባል የተሰጠው የጊዜ ገደብ አለ። ከጊዜ ገደብ ውጪ ላስመዝግብ ብሎ የሚመጣ ካለ ሲገኝበት ተጠያቂ መሆኑ አይቀርምና በወቅቱ ማስመዝገብ ይገባዋል።
በተጨማሪ ደግሞ በየአካባቢው የሚኖረው ማህበረሰብ ከየአካባቢው የፖሊስ ቢሮ ጋር ሰላሙን የሚጠቅብ አካሄድ አለው። በአካባቢው የተለየ ነገር ያየ ሰው በሚሰጠው ጥቆማ አማካኝነት ፖሊስ ተጨማሪ ፍተሻ እና ምርመራ ያደርጋል። እንደየአስፈላጊነቱ የደህንነት ጉዳዮች በሚነሱበት እና መረጃዎች በተገኙበት ወቅት ደግሞ ቤት ለቤት አሊያም በተመረጠ ቦታ ፍተሻ ሊደረግ ይችላል። እስከአሁን በሚከናወኑ ድንገተኛ አሰሳዎች ህገወጥ የጦር መሳሪያዎች ሲገኙ አይተናል፤ ወደፊትም አሰሳው ይቀጥላል።
አዲስ ዘመን፦ ከጦር መሳሪያ ዝውውር ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ ወንጀሎች መረባቸው በተለያዩ ሀገራት የተዘረጉ ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ ከየትኞቹ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራችሁ ነው?
አቶ ሚናስ፦ ከአፍሪካ ህብረት ፣ ከምስራቅ አፍሪካና ትላልቅ ሐይቆች ቀጣናዊ የአነስተኛ መሳሪያዎች ቁጥጥር (RECSA) ከአሜሪካ አፍሪካ (አፍሪኮም) የጸጥታ ትብብር ፣ ከኢንተር ፖል እና ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመግታት እየሰራን ይገኛል።
የህገወጥ ጦር መሳሪያ ችግር ኢትዮጵያን ብቻ የሚያሳስባት ጉዳት ሳይሆን የዓለም ሀገራትንም የሚያሳስባቸው ጉዳይ ነው። በተለያዩ ሀገራት ጋር መረጃ በመለዋወጥ እና የጋራ ስራዎችን በማከናወን ወንጀልን ለመከላከል ጥረት ይደረጋል። እንደሰላም ሚኒስቴር ከአህጉራዊው አፍሪፖልም ሆነ ከዓለም አቀፉ ኢንተር ፖል ጋር ስልጠናዎችን በማከናወን ረገድ ጠንካራ ግንኙነት አለ።
የህገወጥ ጦር መሳሪያ ወንጀል ምንጭ፣ ሂደት እና መዳረሻ ለመለየት የሚያስችሉ ስራዎች ላይ ከዓለም አቀፍ ተቋማቱ ጋር በትብብር እየሰራን ነው። በዚህ ሂደት የሚሳተፉ ወንጀለኞች ሲገኙም በማጋለጥ እና ለህግ በማቅረብ ረገድ ከኢንተርፖልም ጋር በሰፊው እየተሰራበት ነው።
ከምንም በላይ ግን የአቅም ግንባታ ስራዎች ላይ ዓለም አቀፍ ስልጠናዎች ይሰጣሉ። ኢትዮጵያም ሉአላዊነቷን ጠብቃ የወንጀል መከላከል ስራ ከሚያከናውኑ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በከፍተኛ ጥንቃቄ መረጃ በመለዋወጥም ሆነ ባለሙያ በመገንባት ረገድ እየሰራች ትገኛለች።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
አቶ ሚናስ፦ እኔም ከልብ ነው የማመሰግነው።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2013