የመገናኛ ብዙሃኖቻችንን ሳስባቸው ሞልቶላ ቸው ግብር የሚያበሉ ደጋሽ ይመስሉኛል። በዓይነ ህሊናችሁ ሳሉት፤ ከዳስ የሞላው እድምተኛ ከቀረበው እየተቋደሰም ከሌሎች እድምተኞች ጋር ሲያወጋና ሲጨዋወት። ደጋሽ በየመሃሉ ብቅ ብለው «ብሉ እንጂ፤ ኧረ እየጠጣችሁ» እያሉ ሲጋብዙ። ደግሞ «ተጫወቱ» ብለው ለወጋቸው ትተዋቸው ወደ ሌላው ሄደው ከቆይታ በኃላም «አፈር ስሆን ይህቺን ብቻ» እያሉ ሲያግደረድሩ። ከራዲዮ አሊያም ቴሌቪዥን ያላችሁን ካሰኛችሁ አንድ ጣቢያ ላይ አድርጋችሁ አዳምጡት(ከትህትና ጋር)። ዜናም በሉት ማህበራዊ ጉዳይ፣ ፖለቲካዊም ሆነ መዝናኛ፣ ስፖርት ወይም የዘፈን ግብዣ፣… የትኛውም መሰናዶ እየተስተናገደ ይሆናል። ታዲያ እያዳመጣችሁ ሳለ ከመሃል ከአማላይ ሽልማቶች ጋር «ጠጡ» የሚል ግብዣ ይቀርብላችኃል (በነጻ ይጠጣ ይመስል)። የእናንተን ባላውቅም ለእኔ ግን አብዛኛው ሰውና የመገናኛ ብዙሃኑ እየተመሳሰሉብኝ ነው።
ምነው ቢሉ መዳረሻቸው አንድ ነዋ፤ መጠጥ። ይህንን ለማረጋገጥ ለምን አንድ ዳሰሳዊ ጥናት አንሰራም፤ ከመተግበራችን በፊት ግን በህሊናችን እንሞክረው። የአንድ ተቋም ሰራተኞች ስራቸውን ጨርሰው ሲወጡ ወደየት ይሄዳሉ የሚለውን እናጣራ። እንበልና 20 ሰራተኞች ካሉት ተቋም ምን ያህሉ፤ ወደ ቤታቸው፣ ወደ ትምህርት ቤቶች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የመዝናኛ ቦታዎች፣… ይሄዳሉ? መቼም ከልምዳችሁ ተነስታችሁ ዋናውንም ባይሆን ተቀራራቢውን ምላሽ መስጠት ትችላላችሁ። እንደ እኔ ከሆነ በዛ የሚሉት በስራ የደከመ አካላቸውን ከቤታቸው ሳይሆን ከመጠጥ ጠርሙስ ነው የሚያሳርፉት።
አንዳንዱማ ልማድ ስለሚሆንበት፤ የጠርሙስ አንገት ካልጨበጠ የኖረም አይመስለው። ኧረ እንዲያውም እስከ ቢራ ሰዓት ትጉህ የነበረው ሰራተኛ የሚበላሸው የመጠጥ ቤትን ደጃፍ ከመርገጡ ነው። ያው ሁሉም ነገር ደረጃ አለው አይደል፤ መጀመሪያ ጠጪው ጽዋውን ያነሳል፤ ከዚያ ጽዋው ሌላ ጽዋ ይጋብዛል፣ ሲደጋገምም መጠጡ ራሱ ጭልጥ አድርጎ ወደ ማይታወቅ ስፍራ ይወስዳል። እናማ የምታስበውን፣ የምትናገረውን፣ የምትሰራውንና የምትሆነውን አታውቅም፤ ከጸጸት ጋር እስኪነጋ ማለት ነው። ግን ከ፦ቱ በኃላ መገኛቸው እዚያው መሸታ ቤት ይሆናል፤ የሚገርመው ነገር እንደሚጎዳቸው እኮ ያውቃሉ፤ ነገር ግን ሱስ ስለሚሆንባቸው የሚያቆሙት መጠጡን ሳይሆን ስለመጥፎነቱ ማሰቡን ነው። የመገናኛ ብዙሃኑም የየዝግጅታቸው መዳረሻ የአልኮል መጠጦች ማስታወቂያ ነው። ጥሩ ጥሩውን ሲያቀብሉንና መረጃ ሲያስኮመኩሙን ቆይተውም አይደል መዝጊያቸውን «ጠጡ» የሚያደርጉት(ለዚያውም ከእነ ቤተሰባችን በምንከታተላቸው ጣቢያዎች)። እናሳ አይመሳ ሰሉም? አሁን እንኳን የብዙዎቻችን ፍላጎት የተሟላ ይመስለኛል (ለተወሰነ ሰዓት ጠጡ አትበሏቸው ተብለዋላ)። አዋጁን እንደ አዲስ ልነግራችሁ ፈልጌ አይደለም፤ በዚህ ላይ የታዘብኩትን ላካፍላችሁ በሚል እሳቤ እንጂ።
ከሰሞኑ ለስራ ጉዳይ ጥቂት ኪሎ ሜትሮችን አቆራርጬ ነበር፤ ታዲያ በጉዟችንም ሆነ በመልሱ ከመኪናችን ውስጥ የደራ ክርክር ሲደረግበት የቆየው ጉዳይ አዋጁ ነበር። ለእኔ የሚገርም ለሆነብኝ ተቃውሞ እንደ መከራከሪያ ሲነሳ የነበረው ደግሞ፤ የመገናኛ ብዙሃኑ እና የስፖርት ክለቦች (ብሔራዊ ቡድንን ጨምሮ) በስፖንሰር እጥረት ሊዳከሙ እንደሚችሉ እንዲሁም ተጠቃሚው ስለ ራሱ ያውቃልና ነጋሪ አያሻውም የሚል ነው። ግን ግን ማስታወቂያው ለተወሰነ ሰዓት አይተላለፍ በመባሉ ይህ ሁሉ ነገር ከተወራ እንዲያውም አልኮል የተባለ ነገር እንዳይሸጥ የሚያደርግ ህግ ቢወጣ ምን ሊኮን ይሆን? እንዴት ይህንን ዓይነት ጉዳይ ተቃውሞ ሊነሳበትና የክርክር አጀንዳ ሊሆን እንደቻለ ግን አሁንም ድረስ ሊገባኝ አልቻለም።
ስለ መዳከም የተነሳው እውነትነት ያለው ቢሆንም ትውልድን ከማዳን የበለጠ ሊሆን ግን አይችልም። ሰካራም ትውልድ ፈጥረን ሃገሪቷን ለማን ልናስረክብስ ነው? የማስታወቂያ ማጀቢያዎችን ሲዘምሩ («… ሳብ ግጥም» የሚሉ ህጻናት አልገጠማችሁ ይሆን?) የሚውሉና ማስታወቂያውን ቃል በቃል የሚሸመድዱ ህጻናትና ታዳጊዎችን የተመለከተ ለዚህ መደራደሪያ ያቀርባል ተብሎም አይጠበቅም። «እኛም ካልጠጣን» ብለው የሚያለቅሱ እና የተቀዳውንም ሰው «አየን፤ አላየን» ብለው የሚጨልጡም እኮ አሉ። የቀረበለትን ከማግበስበስ ባለፈ «የቱ ይጠቅማል፤ የትኛውስ ይጎዳል?» የሚለውን የመለየት አቅምም ሆነ ፍላጎት ያለው ትውልድ ገና አልተፈጠረም። ለዚህም ነው የአስገዳጅ አዋጅ አስፈላጊነት፤ «ተጠቃሚው ለራሱ ይወቅበት» የሚል ፍርጃ ግን ኃላፊነት የጎደለው ነው። እናማ ወገን በቆርኪ ልክ ማሰባችንን ትተን እይታችንን ማስፋት እንልመድ። አንድን ነገር «ተከለከልኩ» ብሎ ከማላዘንም ሌላ አማራጭ መፈለግ ጉብዝናችንን የሚለካ ይሆናል።
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2011
ብርሃን ፈይሳ