አቶ መርሻ ገበየሁ በአራዳ ክፍለ ከተማ በወረዳ ስምንት ቀበሌ 17 በአዲሱ 15/16 በሚባለው ፓርላማ አካባቢ ነዋሪ እንደነበሩ ያስታውሳሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ፊት ለፊት ላስቲክ ወጥረው እየኖሩ እንደሆኑ ከዓይናቸው ልውረድ አትወርድም ትንቅንቅ ከገጠሙት ዕንባቸው ጋር እየታገሉ አወጉን፡፡ ቀድሞ ቤተሰብ መሥርተው ለቀጣይ የአገሪቱ ተስፋ የሆኑ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ልጆቻቸውን ካፈሩበት ቤት አፈናቅሎ ጎዳና እንደወጡም አነሱልን፡ ፡ እኛም ጉዳዩን ለማጣራት የሚመለከታቸው አካላትን አነጋግረን ያጠናቀርነውን ዘገባ ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡
ከአንደበታቸው በአራት ኪሎ ፓርላማ ማስፋፊያ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ ተወልደው ማደጋቸውን ያነሳሉ፡፡ በወይዘሮ አበበች አይመና ስም ባለው የቤት ቁጥር 258 ለ29 ዓመታት የተገበረበት መሆኑን የሚናገሩት አቶ መርሻ፤ ወይዘሮ አበበች ደግሞ በዚሁ ቤት ለ80 ዓመታት መኖራቸውን የኋሊት ሄደው ጊዜውን ያሰላሉ፡፡ በ1975 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት በመለየታቸውም ፍርድ ቤቱ ለአቶ መርሻ የአክስታቸውን የወራሽነት መብት ያረጋግጣል፡፡ ከቤቱ ጎን ያለው ተከታይ 359 የቤት ቁጥርም በአባታቸው አቶ ደሳለኝ አይመና ስም የተመዘገበ ነውና ከቤተሰባቸው ጋር ሕይወትን እንደገፉ ያስታውሳሉ፡፡ ሁለቱ የተለያዩ ቤቶች በመሆናቸውም ለየብቻው ተገብሮባቸዋል የሚሉት ቅሬታ አቅራቢው፤ ለችግራቸው ምንጭ ያሉትን መነሻ ያስረዳሉ፡፡ በዚህም 1972 ዓ.ም ከአዋጅ በፊት በወይዘሮ አበበች ስም በቀበሌው ፍርድ ሸንጎ በግል ቤት መኖሪያ የነበረ መሆኑ ተጣርቶ የተሰጠ ማስረጃ በቤት ቁጥር 358 ማህደር ውስጥ በክፍለ ከተማው መዝገብ ቤት የሚገኝ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን የት እንደገባ ሳይታወቅ ጠፍቷል፡፡
ከተቋሙ የሚገኘው ማስረጃቸው መጥፋት ባሻገርም ቤታቸው እንደተቃጠለና ይህም በአጋጣሚ ሳይሆን ሆነ ተብሎ የተፈፀመ ደባ መሆኑን እንደማሳያ ይሆናል ይላሉ፡፡ አቶ መርሻ፤ ከነቤተሰባቸው ዘመድ ለመጠየቅ ከወጡበት ሲመለሱ ተቃጥሎ የአመድ ክምር ብቻ ይጠብቃቸዋል፡ በጊዜው እሳት አደጋ ቢደርስም ዳሩ ግን ማዳን ባለመቻሉ ለዓመታት ያፈሩት ንብረትና አስፈላጊ ማስረጃዎቻቸውንም ያጠፋባቸዋል፡ ፡ ባጋጠማቸው ውርጅብኝ ኀዘን የጎዳው ቤተሰባቸውን ይዘው የአባታቸው በሆነው የቤት ቁጥር 359 በጊዜያዊነት ቢጠጉም ሰኔ 3 ቀን 2009 ዓ.ም ስፍራው ለልማት ፈራሽ ነበርና ይፈርስባቸዋል፡፡ ጉዳዩን ደብዛውን ለማጥፋት ታስቦ የተደረገ ተግባር እንደሆነ የሚናገሩት አቶ መርሻ አቤቱታቸው በክፍለ ከተማው ቅሬታ ሰሚ ዘንድ እየታየ የነበረ ቢሆንም ሰኔ 3 ቀን 2009 ዓ.ም ተጠግተው ይገኙ የነበሩበት ቤት ቁጥር 359 መፍረሱን ተከትሎ የአቶ ደሳለኝ አይመና እና ወይዘሮ አበበች አይመና ወንድምና እህት የሆኑትን ግለሰቦች ቤት በመቀላቀል በአንድ ተስተናገዱ የሚል ምላሽ ከአስተዳደሩ ይሰጣቸዋል፡
፡ ሙሉ ማስረጃ እያላቸውም ፍትሕ እንደተነፈጉ ይገልፃሉ፡፡ የአባታቸው ቤት ሲፈርስ በልጅነታቸው ካገኙት ውጪ ምንም ዓይነት አገልግሎት ባያገኙም አስተዳደሩ ግን እንዳገኙ አድርጎ ማቅረቡ ብሎም 358 የቤት ቁጥር የ359 አካል የሆነ ሰርቪስ ቤት ነው በሚል መግለጹ ለችግር ዳርጓቸዋል፡ ፡ የቤት ቁጥሩ እንዳልነበር የተሠራው ሴራም ምናልባትም ቤቱን አየር በአየር ለሌላ ግለሰብ እንዲጠቀም አድርገውበት ይሆናል በማለት ስጋትና ጥርጣሬያቸውን ይገልፃሉ፡ ፡ ከእርሳቸው ያደመጥነውን ቅሬታ ካደመጥን በኋላም በእጃቸው የያዙትን ሰነድ ማገላበጥ ጀመርን፡፡ ሰነዶች የአንድ ሰው ነዋሪነት ማረጋገጫ አንዱ መታወቂያ ነውና በ23/01/1994 ዓ.ም ለአቶ መርሻ የተሰጠ መታወቂያ ግልባጭ ከሰነዶቹ ቀድሞ ተመለከትን። መታወቂያው እንደሚያመላክተው በወረዳ 14 ቀበሌ 17 የቤት ቁጥር 358 ነዋሪነታቸውን ያረጋግጣል፡ ፡ ከሰነድ ማስረጃዎቹ መካከል በወይዘሮ አበበች አይመና ስም በ105 ሜትር ካሬ የተከፈለ የቦታ ግብር ደረሰኝና በአቶ ደሳለኝ አይመና ስም ደግሞ በ132 ሜትር ካሬ በ24/3/55 ዓ.ም የተከፈለበት የቦታ ግብር ደረሰኝ ይገኛል፡፡
በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ሐምሌ 25 ቀን 2004 ዓ.ም የወጣ ዕትም ላይም በጉዳዩ ላይ የተሠራ ዘገባም ተያይዟል፡፡ በ19/2/05 ዓ.ም ደግሞ በክፍለ ከተማው ወረዳ ስምንት አስተዳደር ያቀረቡትን አቤቱታ ተከትሎ ምላሽ የተሰጠበት ቅጽ ይታያል፡፡ በቅጹ ሰፍሮ እንደሚገኘው፤ ቅሬታ የቀረበው በ7/02/05 ዓ.ም ነው፡፡ አቤቱታ አቅራቢው የቤት ቁጥር 358 ላይ ከ50 ዓመት በላይ መኖራቸውን በመግለጽ ቤቱ በወይዘሮ አበበች አይመና ስም እንደሚገኝ ሰፍሮ ይገኛል፡ ፡ ቅሬታውን በመቀበል ለማጥራት በተደረገው ሂደትም የተደረሰባቸው ግኝቶች ተቀምጠዋል፡ ፡ በዚህም ቅሬታውን ለመፍታት ያልተሟላ መረጃ መቅረቡን ያትታል፡፡
በተመሳሳይ በማጥራት ሂደቱ ኮሚቴው መረጃዎችን ከሚመለከተው ጽህፈት ቤት ያላገኘ በመሆኑ አስተዳደራዊ ውሳኔ ቢሰጥበት ሲል ወስኗል በማለት መፍትሔ ያመላክታል፡፡ በቅጹ ላይ አቤቱታው ትክክለኛ ካልሆነ ይብራራ በሚለው ስፍራም ቅሬታ በቀረበበት ቤት ላይ የተሟላ መረጃ አለመገኘቱ ሰፍሯል፡፡ በቀን 19/03/05 ዓ.ም የመዝገብ ቁጥር 1361/05 የወጣ የፍርድ ቤት ውሳኔና ትዕዛዝ ያረፈበት ሰነድ ሌላው ያገኘነው ሰነድ ነው፡፡
በዚህም አመልካች አቶ መርሻ በ17/03/2005 ዓ.ም በቃለ መሐላ አስደግፈው ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት አቤቱታ የወላጅ አባታቸው እህት ወይዘሮ አበበች አይመና ገብረየስ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት የቤት ቁጥር 358 ውስጥ ሲኖሩ ሰኔ ሦስት ቀን 1975 ዓ.ም ማረፋቸውን ያትታል፡፡ በዚህም አመልካች አባታቸውን በመተካት የሟች አበበች አይመና ገብረየስ ወራሽ መሆናቸው እንዲረጋገጥላቸው ማስረጃ መጠየቃቸውን አስፍሯል፡፡ ፍርድ ቤቱም የአመልካችን አቤቱታ በቃለ መሐላ ተረጋግጦ የቀረበ መሆኑን በመረዳቱ አመልካች አባታቸውን ተክተው በፍ/ብ/ህ/ ቁ845/2/ መሠረት የሟች ወራሽ መሆናቸውን እንዳረጋገጠላቸው በውሳኔው ላይ ይነበባል፡፡ በቁጥር አ/ክ/ከ/5/መ/06/3159/01 በቀን 29/05/2006 ዓ.ም ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን አራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ የላከው ደብዳቤ ይገኛል፡፡
በደብዳቤው እንደተገለጸው፤ አቶ መርሻ በ27/05/06 ዓ.ም ባቀረቡት ማመልከቻ የመኖሪያ ቤታቸው በእሳት የተቃጠለባቸው ስለመሆኑ ማስረጃ ጠይቀዋል፡፡ መምሪያውም ግለሰቡ የመኖሪያ ቤታቸው አራዳ ክፍለ ከተማ በቀድሞ ቀበሌ 17 በአሁኑ ወረዳ ስምንት ልዩ መጠሪያው ባሻ ወልዴ ችሎት የቤት ቁጥር 358 የሆነው በ18/09/05 ዓ.ም በተነሳው እሳት ቃጠሎ መኖሪያ ቤታቸው የተቃጠለባቸው መሆኑን ገልጿል፡፡ በ09/5/2011 ዓ.ም መዝገብ ቁጥር ዕንባ/ ዘ9-አመ/869/1 የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ለአራዳ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ጽህፈት ቤት የላከው ደብዳቤ ቅሬታ ሌላው ሰነድ ነው፡፡ በዚህም ቅሬታ አቅራቢው በክፍለ ከተማው ወረዳ 08 የቤት ቁጥር 358 ነዋሪ የነበሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የቤት ቁጥር 358 ማህደር መጥፋት የተነሳ ቤቱ ለልማት ሲነሳ የካሳና ምትክ ጥያቄ ምላሽ ማግኘት አለመቻላቸውንና የአስተዳደር በደል እንደደረሰባቸው አቤቱታቸውን ለተቋሙ ማቅረባቸውን ያትታል፡፡
ተቋሙም የቀረበለትን አቤቱታ መርምሮ ተገቢውን የመፍትሔ ሃሳብ ውሳኔ ለመስጠት ያስችለው ዘንድ የተጠቀሰውን የቤት ቁጥር ማህደር በተመለከተ የነበረውን ሁኔታ የሚያስረዳ ምላሽ ከበቂ ማብራሪያና ማስረጃ ጋር በማያያዝ እንዲላክለት ይጠይቃል፡፡ ከቅሬታ አቅራቢው ያገኘናቸውን ሰነዶች ከተመለከትንና ቃላቸውን ከሰጡን በኋላ የሚመለከተው የመንግሥት አካልስ በጉዳዩ ላይ ምን ምላሽ ይሰጣል? ስንል ወደ አራዳ ክፍለ ከተማ አቀናን፡፡ በአራዳ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት ተገኝተንም የሚመለከታቸው አካላት ምላሽና የሰነድ ማስረጃዎችን ለመመልከት ቻልን፡፡
ክፍለ ከተማው በክፍለ ከተማው የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት ተገኝተን በቅድሚያ ቅሬታ የቀረበበት ቤት በ1988፣ 1997 እንዲሁም 2003 ዓ.ም በተነሳው የአየር ፎቶ (ጂአይኤስ) ብሎም ከዛ በኋላም ይህን መሬት ተወርዶ ከባለቤትነት ጋር ለማመሳከር በተሠራው ሥራ ይታያል ወይ? በሚል በቅድሚያ አጣርተናል፡፡ በዚህም ቤቱ በሦስቱም ጊዜያት በተሠራው ሥራ ያለ ቢሆንም ነገር ግን የሚታየው 359 የቤት ቁጥር ማለትም በአቶ ደሳለኝ አይመና ስም በተመዘገበ ቤት ቁጥር ስር ሆኖ 359 ሰርቪስ በሚል እንደሚገኝ ያመላክታል፡፡ ከዚህ በተቋሙ ከሚታየው ማስረጃ በተጨማሪ ሌሎች የሰነድ ማስረጃዎችንም ጽህፈት ቤቱ እንድንመለከት ረድቶናል፡፡ ከሰነዶቹ መካከል አንዱ የሆነው በቁጥር አ/ክ/ከ/ አስ/መ/ል/ማ/566/05 በቀን 18/10/2005 ዓ.ም የክፍለ ከተማው የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት ለክፍለ ከተማው መሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽሕፈት ቤት የላከው ደብዳቤ አንዱ ነው፡፡
በደብዳቤው ሰፍሮ እንደሚታየው፤ የስምንት ጽህፈት ቤት የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት የመረጃ እርማት የሚደረግባቸው ፋይሎችን ተመልክቷል፡፡ በዕለቱ በተደረገው ስብሰባም አንዱ የታየው ማህደር በአቶ ደሳለኝ አይመና ስም የሚገኘውና በቀድሞ ወረዳ 14 ቀበሌ 17 የቤት ቁጥር 359 የሚገኘው ቤት ነበር፡፡ ጉዳዩም በጂአይኤስ የሚያሳየው ሙሉ በሙሉ በቤት ቁጥር 359 ብቻ ሲሆን፣ በመሬት ላይ ግን ግቢው በሁለት ተከፍሎ ሁለት የተለያየ ቤት ማለትም 358 እና 359 በሚል መከፈሉን ያሳያል፡፡ በመሆኑም መረጃቸው በቂ መሆኑ ታይቶ በሁለት አልያም በአንድ ቤት መስተናገድ እንዲችሉ ፕሮሰስ ካውንስሉ አጣርቶ እንዲወስን መቅረቡን ያትታል፡፡ የቀረቡት ማስረጃዎችም፤ የቦታ ኪራይ የቤት ግብር ውሳኔ ማስታወቂያ በቀን 4/2/74 ዓ.ም በቤት ቁጥር 358-359 በአቶ ደሳለኝ አይመና ስም ለማስከፈል መጋቢት 6/1968 ዓ.ም ቁጥር 80/1968 በወጣው አዋጅ መሠረት የኪራይ ግምት የተገመተበት የማይክሮ ግብር ከፋዮች ጽህፈት ቤት አቶ ደሳለኝ በቤት ቁጥር 359 ስም የተገበረበት ማህደር፣ የጂአይኤስ መረጃ ላይ የቤት ቁጥር 359 በአቶ ደሳለኝ ስም መሆኑ፣ ውሃና መብራት የገባበት ውል በአቶ ደሳለኝ ስም መሆኑ ይታያል፡፡
ከ1957 እስከ 1958 ዓ.ም በጥቅል የተገበረበት ደረሰኝ፣ የቦታ ኪራይ የግብር ደረሰኝ በ1970 ዓ.ም የተገበረበት በቤት ቁጥር 358-359 እንደሆነና ከ1973 እስከ 1975 ዓ.ም እንዲሁም በ1980 እና 1997 ዓ.ም ውጪ በተከታታይ ዓመታት በቤት ቁጥር 359 በአቶ ደሳለኝ አይመና ስም የተገበረባቸው ደረሰኞች እንዲሁም የቤት ቁጥር 358 በሚል ስጦታ በ1985 ዓ.ም ከአቶ ደሳለኝ አይመና ለአቶ መርሻ ደሳለኝ የተሰጠ የመንደር ውል ማስረጃዎች መቅረባቸው በዕለቱ በተያዘ ቃለጉባዔ ላይ ሰፍሯል፡፡ የቤት ቁጥር 359 ፓርላማ ላይ እየተሠራ ባለው የመልሶ ማልማት ሥራ ምክንያት ሙሉ በሙሉ የሚፈርስ በመሆኑ የጽህፈት ቤቱ የካሳ ግምትና ምትክ ባለሙያዎች ከሰነድ ማስረጃዎች በተጨማሪ በቦታው ወርደው ባረጋገጡት መሠረት የተሰጠ የውሳኔ ሃሳብም በስብሰባው መቅረቡ በቃለጉባዔው ይታያል፡፡ በዚህም በቦታው ላይ ሁለት ነዋሪዎች በተለያየ ቤት የሚኖሩ ቢሆንም ቤቶቹ በጣሪያ የተገናኙና መረጃም ያለው በቤት ቁጥር 359 ነው፡ ፡ ቅሬታ የቀረበበት የቤት ቁጥርም ምንም ዓይነት የግብር ደረሰኝም ሆነ መረጃ የሌለው በመሆኑ በአንድ ቤት እንዲስተናገዱ መወሰኑን ያስረዳል፡፡ በዕለቱ የቀረቡለትን የሰነድ ማስረጃዎች እንዲሁም በቦታው ላይ በመገኘት ባለሙያዎች ያጣሩትን በመመልከትም የክፍለ ከተማው ፕሮሰስ ካውንስል ያሳረፈው ውሳኔ በቃለ ጉባዔው ተቀምጧል፡፡
በዚህም መሠረት 359 በሚል በአንድ ቤት ብቻ እንዲስተናገዱ መወሰኑ መመልከት ችለናል፡፡ በተያዘው በጀት ዓመት በ15/05/ 2011ዓ.ም በቁጥር አ/ክ/ከ/መ/ል/ከ/ማ/ጽ/ ቤት/1359/11 የክፍለ ከተማው የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽህፈት ቤት ለክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጽህፈት ቤት የላከው ደብዳቤ ሌላው ማስረጃ ነው፡፡ ይህ ደብዳቤ የተላከው የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ለአራዳ ክፍለ ከተማ አስተዳደር አቤቱታ በቀረበበት ቤት ላይ በአምስት ቀናት ምላሽ እንዲሰጥ በጠየቀው መሰረት የክፍለ ከተማው ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ምላሽ እንዲሰጥበት በመጠየቃቸው የተሰጠ ነው፡፡ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ለጥያቄው በሰጠው የጽሁፍ ምላሽም በክፍለ ከተማው የተመለከትናቸው የሰነድ ማስረጃዎች ተዘርረው በደብዳቤው ይነበባሉ፡፡ በተጨማሪም የቦታ ኪራይና የቤት ግብር ሒሣብ ማስታወቂያ (ካዳስተር ቢል) የተመዘገበው በቤት ቁጥር 359 በአቶ ደሳለኝ ስም መሆኑ ተገልጧል፡፡
የይዞታ ማረጋገጫ ካርታም በቤት ቁጥር 359 የተመዘገበ መሆኑን በመግለጽም፤ የጽህፈት ቤቱ ባለሙያዎች በቀን 07/10/2005 ዓ.ም በያዙት ቃለጉባዔ እንዳረጋገጡት ግን 359 ሰርቪስ በሚል በጂአይኤስ ላይ የሚታየውን ቤት ግለሰቦቹ 358 እንደሚሉት ማመላከታቸውንም ያስታውሳል፡፡ የክፍለ ከተማው መሬት ልማት ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት የቀረቡትን ማስረጃ ዎች መሠረት አድርጎ በቁጥር አ/ክ/ከ/አስ/መ/ ል/ማ/566/08 በቀን 18/10/2008 ዓ.ም በአንድ ቤት እንዲስተናገዱ ባረፈው ውሳኔ መሠረት የካሳ ክፍያውና ምትክ ቦታው በቤት ቁጥር 359 ተሠርቷል፡፡ በዚህም የካሳ ክፍያና ምትክ ቦታ ላይ ባለይዞታዎቹ የቤቱ ካሳ ግምት ተሠርቶላቸዋል፡፡ በቀን 01/07/2007 ዓ.ም የካሳ መቀበያ ሰርተፍኬትም መቀበላቸው ተካቷል፡፡
ቅሬታ አቅራቢውም ምትክ ቦታ 90 ካሬ ሜትር ተወስኖላቸው በቦሌ ክፍለ ከተማ የፕሎት ቁጥር Relo -24/04 A=90 በቀን 24/01/2009 የምትክ መቀበያ ቅጽና በቀን 16/10/2009 ዓ.ም 11 ሺህ ብር የንብረት ማጓጓዣና የማህበራዊ ስነልቦና ትስስር መቋረጥ ካሳ ክፍያ መውሰዳቸውን ክፍለ ከተማ ለተጠየቀው ጥያቄ ማብራሪያ በሰጠበት ደብዳቤ ያረጋግጣል፡፡ አፅዕኖት በክፍለ ከተማው መሬት ልማትና ማኔጅ መንት ጽህፈት ቤት ተገኝተን ከተመለከትናቸው የሰነድ ማስረጃዎች ጎን ለጎን የቢሮ ኃላፊዎችና ቅሬታቸውን በቅርበት የሚያውቅ ባለሙያ ሃሳባቸውን አካፍለውናል፡ ፡ በዚህም ሊስተካከልና በቀጣይ በከተማዋ በሌሎች አካባቢዎችም በትኩረት ሊሠራበት ይገባል ባሉት ጉዳይ ላይ አስተያየትና ሙያዊ ሃሳባቸውን አካፍለውናል፡፡
የግለሰቡ አቤቱታ በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ የሚገኘውን የመንግሥት የሥራ ኃላፊ ጨምሮ ሦስት ኃላፊዎች በተቀያየሩ ወቅትም እንደ አዲስ የሚነሳ መሆኑን ነው በክፍለ ከተማው የከተማ ማደስ የሥራ ሂደት የካሳ ክፍያና መልሶ ማቋቋም ንዑስ የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ተመስገን አርጋው የሚናገሩት፡፡ ቅሬታ አቅራቢው ካሳም ሆነ ምትክ ቦታ አለመውሰዳቸውን በመግለጽ አለመስተናገዳቸውን ባቀረቡት አቤቱታ ሰነዳቸውን የማጥራት ሥራ መሠራቱንም ያስታውሳሉ፡፡
ምንም እንኳ ቅሬታው የቆየ ቢሆንም ዳግም ለማየትም ተሞክሯል፡፡ በወቅቱ እንደ አዲስ ኮሚቴ በማዋቀር ማስረጃዎች ቢጣሩም 358 የቤት ቁጥር በተመለከተ ግን ምንም ዓይነት ካርታም ሆነ የተሟላ ሰነድ አልተገኘም፡፡ ሆኖም ግን በ359 ቤት ላይ የአቶ ደሳለኝ አይመና ልጅ ሆነው ተካተው የምትክ ቦታና ካሳ ክፍያ መስተንግዶ እንዲሰጣቸው መደረጉን ይገልፃሉ፡፡ ይሁን እንጂ ቅሬታቸው ሲጣራ ግለሰቡ የሚያነሱት የቤት ቁጥር ጂአይኤስ ላይ በ359 የተካተተ ቤትን ነው፡፡ በሌሎች አመራርና ባለሙያዎችም ከዚህ ቀደም መስክ ድረስ ተወርዶ የተጣራና ተገቢው ምላሽ የተሰጠበት ነው፡፡ ግለሰቡ እንደተቃጠለባቸው የሚናገ ሩት ቤትም በጽህፈት ቤቱ መብት ያልተ ፈጠረለትና ካርታ የሌለው መሆኑንም አቶ ተመስገን ያስረዳሉ፡፡ ሰነዶቹ ከቤቱ ጋር ቢቃጠሉም እንኳ በጽህፈት ቤቱ እናት ማህደር ውስጥ በቤት ቁጥሩ ማስረጃ ማግኘት ይቻል ነበር፡ ፡ ቤቱ በ359 የቤት ቁጥር ሰርቪስነት ይዞታ አስተዳደርና ሽግግር ጊዜ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት በላከው በጂአይኤስ በሚታየው መሠረት አገልግሎት እንዲገኝም ተደርጓል፡፡
ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴውም በወቅቱ እንደማይገባቸው ማሳወቁንም ያስታውሳሉ፡፡ በወቅቱ የነበረ አመራር ውሳኔ ቢሰጥም አዲስ አመራር ሲቀየር በፈረሰ ቤት ላይ ጥያቄ ማንሳትም ተገቢነት የለውም፡፡ አመራር መቀየሩን ሲሰሙ የተሳሳተ ጥያቄ እያነሱ ወደ ቢሮ የሚጎርፉ ተገልጋዮች መኖራቸውም ትክክል ያልሆነና ወቅቶችን በመጠቀም መንግሥትን ለማሳሳት የሚደረግ ጥረት በመሆኑ ሊታረም ይገባል፡፡ ቅሬታ በተለያየ ጊዜ መምጣቱ ክፋት ባይኖረውም አመራር በተቀየረ ጊዜ ግን የሚመጡ አስተሳሰቦች ለሥራም ፈታኝ ናቸው ይላሉ፡፡ በክፍለ ከተማው የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ልበሎ ኢታይ፤ የቤት ቁጥር 358ን በተመለከተ በጽህፈት ቤቱ በተደጋጋሚ ቅሬታ መምጣቱን ያምናሉ።በ08/09/2005 ዓ.ም ወረዳ ተጠይቆ በሰጠው ማረጋገጫ 358 የቤት ቁጥር በተመለከተ ምንም ማስረጃ አልተገኘም ። ቅሬታቸውን ለማየትም ኮሚቴ ተቋቁሞ እንዲጣራ ተደርጓል፡፡
በዚህም የክፍለ ከተማው መሬት ልማት ማኔጅመንት የነበረው ፕሮሰስ ካውንስል ስምንት የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት የተለያዩ ማስረጃዎች ቀርበው ባረፈው ውሳኔ መሠረት ቅሬታ ምንጭ ተደርጎ የሚነሳው ቤት የቤት ቁጥር 359 አካል በመሆኑ በአንድ ቤት እንዲስተናገዱ አፅድቋል። በተገኘው መረጃ መሰረት በድጋሚ መስተናገድ እንደማይችሉ አቶ ልበሎ ይገልፃሉ፡ ፡ ምክንያቱም በቤት ቁጥር 359 አገልግሎቱን አግኝተው ቦታው ለሚፈለገው ልማት እንዲፈርስ ተደርጓል፡፡ በዚህ መሠረት በድጋሚ አገልግሎት የሚጠየቅበት ምንም ዓይነት ሕጋዊ መሰረት የሌለው ጥያቄ ሲሉም ይኮንኑታል፡ ፡ አገልግሎት ባገኙበት ቤት ላይ ዳግም ጥያቄ ማንሳትም ማጭበርበር በመሆኑ ሊወገዝ ይገባል ባይ ናቸው፡፡
የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ህንፃ ገብረስላሴ ጉዳዩን አስመልክቶ እንደተናገሩት፤ በ1988 ዓ.ም ጀምሮ በተነሳ የአየር ካርታ(ጂአይኤስ) መረጃ መሠረት 358 የሚባል የቤት ቁጥር አይታወቅም፡፡ ግለሰቡ የሚያቀርቡት ቅሬታ ትክክለኛ ቢሆን ኖሮም የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ባይሰራላቸው አልያም ፍትሕ ተጓድሎ ቢሆን ለሦስት ጊዜያት በተጠናቀረው የጂአይኤስ መረጃ ላይ ሊገኝ ይችል እንደነበር ያስረዳሉ፡፡ በአየር ካርታው እንደሚታየውም ያልተካተተና የተተወ የለም፡፡ በዚህም መሠረት ተገቢውን ካሳና ምትክ ቦታ ቢያገኙም አመራር በመቀየሩ ጥያቄው እንደ አዲስ አጀንዳ ተደርጎ ሲቀርብ ይታያል፡፡
ዜጎች በደል ሲደርስባቸውና አገልግሎት ሲጓደልባቸው ጥያቄ ማንሳት እንዳለባቸው ይታመናል፡፡ ጽህፈት ቤቱ ከመረጃ አንፃር ሰነድ አገላብጦ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡ ከዚህ ውጪም ምላሽ የሚሰጥበት አግባብ አይኖርም፡፡ የሰነዱ ማስረጃዎች የሚያመላ ክቱትና ቅሬታ አቅራቢው የሚያነሱት አቤቱታ የሚለያይ ሲሆን በዛው ሰነድ ምላሽ ተሰጥቶ ሌላ አመራር ሲመጣ ዳግም ጥያቄ ሆኖ መቅረቡ አግባብነት የለውም፡ ፡ መንግሥትንም ለተሳሳተ ውሳኔ የሚዳርግ ባለሙያዎችንም ተጠያቂ የሚያደርግ ተግባር መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በዚህ መልኩ በተሳሳተ መረጃ አገልግሎት ቢሰጥም አገልግሎት ሰጪውም ሆነ ተቀባዩን ከተጠያቂነት አያድንምና ይህን መሰል ድርጊት ሊታረም ይገባል ይላሉ፡፡ ያም ሆኖ ግን ከላይ የዘረዘርናቸው ማስረጃዎች ጠለቅ ያለ ምርመራን የሚፈልጉና ውስብስብ በመሆናቸው የሚመለከታቸው አካላት ጉዳዩን በጥልቀት መርምረው ዘላቂ መፍትሄ ሊሰጡ ይገባል እንላለን፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2011
ፍዮሪ ተወልደ