ሀገር በመልካም ሀሳብ የምትፈጠር የመልካም አንደበቶች ነጸብራቅ ናት። ትውልድ በመልካም አስተሳሰብ የሚፈጠር የመልካም እይታ ውጤት ነው። አሁን ላይ ብዙዎቻችን ምን አገባኝ፣ አይመለከተኝም በሚሉ አፍራሽ አመለካከቶች ተከበን የምንኖርበት ጊዜ ላይ ነን። በራሳችን ላይ ካልደረሰ የማያመን፣ የእኛ የሆነ ነገር ካልሆነ እጃችንን አጣጥፈን የምንታይባቸው በርካታ አጋጣሚዎች አሉ። ኢትዮጵያዊ ቀለማችንን የሚያደበዝዙ ሁኔታዎችን እያየን ዝም የምንል፣ ሀገርና ህዝብን የሚጎዱ ድርጊቶችን እየሰማን ምላሽ የማንሰጥ ፣ ከማህበረሰባችን ባህልና ስርአት ውጪ የሆኑ ጎጂ ሁኔታዎችን እያየንና እየሰማን በዝምታ የምናልፍ ብዙዎች ነን።
የሀገር ህመም ከዚህ ነው የሚጀምረው። እኚህ አመለካከቶች የድህነታችን መንገድ ጠራጊዎችና በር ከፋቾች ሆነው ከጥንት እስከዛሬ አብረውን ኖረዋል። ትውልድ የሚገነባው በመንግስት ብቻ የሚመስለን ብዙዎች ነን። ሀገራችንን የምንገነባው ከአስተሳሰባችንና ከአመለካከታችን በምናዋጣው ግለሰባዊ ተሳትፎ ነው። በተስፋ የተሞላ ራዕይ ያለው ትውልድ የምንገነባው ዛሬ ላይ በምንሆነው የህይወት ልምዳችን ተነስተን ነው። ከምን አገባኝነት ወጥተን ሀላፊነት የሚሸከሙ ታማኝ ትከሻዎች ያስፈልጉናል። በሚያገባን ነገር ላይ አያገባኝም እያልን፣ የእኛን እውቀትና እገዛ በሚጠይቁ ማህበራዊም ሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የነቃ ተሳትፎ ሳናደርግ ትልቅ ሀገርና ህዝብ ለመፍጠር የምናደርገው ትግል ውጤት ያመጣል ተብሎ አይታሰብም። ጠንካራዋ ኢትዮጵያ ያለችው በጠንካራ የያገባል ስሜት ውስጥ ነው። ብርቱና ስልጡን ህዝብ የሚፈጠረው በብርቱውና በስልጡኑ እኛ በኩል ነው። ለራሳችን ሀላፊነት ሳይሰማን የምንፈጥረው ጠንካራ ሀገርና ትውልድ የለም። መጀመሪያ ራሳችንን እንስራ። መጀመሪያ ራሳችንን ጠቃሚ ዜጋ እናድርግ። መጀመሪያ በሀገር ጉዳይ ላይ ያገባኛል የሚልን አመለካከት እንፍጠር። ትውልድ እኮ በእኛ በኩል የሚመጣ ነው።
እኛ የአባቶቻችን ልጆች እንደሆንን ሁሉ የእኛም ልጆች አዲስ ትውልድ ሆነው ነገ ላይ ይፈጠራሉ። በአዲሱ ትውልድ ላይ አዲስ አስተሳሰብን የምንፈጥረው ደግሞ ዛሬ ላይ እኛ የአዲስ አስተሳሰብ ባለቤት መሆን ስንችል ብቻ ነው። ኢትዮጵያ ሀገራችን የአንድና የሁለት ሰዎች የምትመስለን ብዙዎች ነን። ለምንም ነገር ራሳችንን አግለን የቆምን ሞልተናል። ምንም ነገር ላይ እኔ አይመለከተኝም የምንል አለን። እውነቱ ግን ይሄ አይደለም። እውነቱ ኢትዮጵያ የጋራችን መሆኗ እና በማንኛውም የሀገራችን ጉዳይ ላይ በንቃት የመሳተፍ መብት እንዳለን ማወቁ ነው። እኛ ካላገባን በጋራ ጉዳያችን ላይ በጋራ የመወሰን መብታችንን ተጠቅመን አዎንታዊ ለውጥ ካላመጣን በእኛ ጉዳይ የሚገባ ሌላ ሀይል አይኖርም። ዛሬ ላለችው ነገም ለምትፈጠረው አዲሲቷ ኢትዮጵያ እናስፈልጋለን። ማስፈለግ ብቻ አይደለም አለኝታዎቿም ነን። ከአያገባኝም ወጥታችሁ ለልጆቻችሁ የምትሆንን ምቹ ሀገር ፍጠሩ። የኔ ጉዳይ አይደለም ከሚል አፍራሽ አመለካከት ወጥተን ለሁላችን የምትሆንን የጋራ ምድር እንገንባ።
አሁን ላይ በብዙ ነገራቸው የተሳካላቸው ሀገራት በህዝቦቻቸው የነቃ ተሳትፎ የተገነቡ ናቸው። ስልጣኔዎቻቸውም ከምን አገባኝነት ወጥተው በይመለከተኛል እሳቤ በተባበረ ክንድ የገነቧቸው ናቸው። እኔና እናንተም ከምን አገባኝነት መውጣት ይኖርብናል። ምናገባኝነት ሀገር አፍራሽ ከሆኑ አመለካከቶች አንዱ ነው። ምን አገባኝነት ሀገር ለማፍረስ ጦርና ጎራዴ ከታጠቁት እኩል ነው። ለሀገራችን መጨነቅ አለብን። ላለውና ለሚመጣው ትውልድ ተቆርቋሪነት ሊሰማን ይገባል። ያጠፋን ለህግ በማቅረብ፣ ከአጥፊዎች ጋር ባለመተባበር አጋርነታችንን ማሳየት እንችላለን። ጀርባ ከመስጠትና ከመሸሽ ይልቅ ሁሉም የማህበረሰብ ጉዳይ የኔ ጉዳይ ነው ብሎ በመነሳት ለሀገራችን ያለንን ቁርጠኝነት ማረጋገጥ እንችላለን። ባለንበት፣ በቆምንበት በተሰማራንበት የህይወት መስክ ሁሉ በትብብርና በሀላፊነት ስሜት በመንቀሳቀስ አጋርነታችንን ማሳየት እንችላለን።
ከዚህ በላይ ሀገርና ህዝባችንን መጉዳት የለብንም። ከማይጠቅመን ነገር መውጣት አለብን። ምን ጨነቀኝ.. ምን አገባኝ..አይመለከተኝም የሚሉት ሰይፈ ነበልባል አንደበቶች አሁን ላይ ሀገር እያወደሙ ያሉ አጥፊ ሀይሎች ናቸው። ለምንም ነገር ያገባናል። በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው፣ በማህበረሰባዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ያለው ነገር ሁሉ ከእኛ ለእኛ በእኛ ስለሆነ ያገባናል። እንዲስተካከል የምንፈልገው ነገር ካለ በህጋዊ መንገድ ድምጻችንን በማሰማት እንዲስተካከል ማድረግ እንችላለን። ራሳችንን ከሀላፊነት በማራቅ የምናጣው እንጂ የምናገኘው ትርፍ የለም። ሀገሬን ከጥንት እስከዛሬ ያወደማት ይሄ አስተሳሰብ ነው። ትውልዱን የእንግዴ ልጅ አድርጎ ያስቀረው ይሄ አስተሳሰብ ነው። በድህነትና በኋላ ቀርነት እንድንጠራ ያደረገን ይሄ እይታችን ነው። እስኪ ራሳችሁን ጠይቁ…መተኪያ በሌላት በሀገራችን ጉዳይ ሀላፊነት ካልተሰማን ሌላ በምን ላይ ሊሰማን ነው? ከአብራካችን በበቀለ ከአብራኩ በበቀልን ህዝብና ርስት ካላገባን በምን ላይ ሊያገባን ነው? ሀገር የሁላችንም እኩል ሀላፊነት የሚንጸባረቅባት የጋራ ንብረት ናት።
ማህበረሰብ የሁላችንን የጋራ ተሳትፎ የሚጠይቅ የአንድነት ውጤት ነው። እድገት ልማት ስልጣኔ የሚመጡት ሀላፊነት ለመቀበል በተዘጋጁ ማህበረሰብ ነው። ለሀላፊነት ባልተዘጋጀ ማህበረሰብ ዘንድ እድገት የለም። ሀገራዊም ሆነ ግለሰባዊ ለውጣችን ያለው በልበ ሙሉነታችን ውስጥ ነው። ሀገር ሲፈርስ እያየን ዝም ካልን፣ ባህል ሲበረዝ፣ ታሪክ ሲወድም እየሰማን ጆሮ ዳባ ልበስ ካልን አደራ በል ትውልዶች ነን። በሰፈር በመንደር፣ በማህበራዊ አገልግሎቶች ህገ ወጥ ድርጊቶችን እያየን ለመከላከል ካልሞከርን ተባባሪዎች ነን። ሀገርና ህዝብን ሊጎዱ የሚችሉ እንደ ሙስናና ሌብነት ያሉ ነውረኛ ድርጊቶችን እያየንና እየሰማን የማንደነግጥ ከሆንን ለሀገርና ትውልድ ከማይራሩ ሀላፊነት ከማይሰማቸው ውስጥ ነን ማለት ነው። የአንድ ዜጋ ምርጥ ባህሪ የሚለካው ለሀገሩና ለህዝቡ ከሚያሳየው የወገንተኝነት ስሜት ነው። በስራና በትጋት ለሀገራችሁ እንደምታስፈልጉና ወሳኝ እንደሆናችሁ ማሰብ ስትችሉ ያኔ የእውነት ታማኝ ዜጋ ትሆናላችሁ። ዜግነት የሚለካው በተግባር ነው። ባለንበት የስራ መስክ ሀገርና ህዝብ የሚጠቅምን በጎ ተግባር በማከናወን ሀላፊነታችንን መወጣት ይኖርብናል።
ካለ ስራ ካለ መልካም ተግባር መወለድ ወይም በዛ ሀገር ውስጥ መኖር ብቻውን ዜጋ አያስብልም። ሀገርን የሚጎዱ ማናቸውንም ድርጊቶች በያገባኛል መንፈስ ማውገዝና መከላከል አንዱና ዋነኛው የዜግነት ግዴታችን ነው። የአለም ስልጣኔዎች ሁሉ በግለሰቦች የተባበረ ክንድ የመጡ ናቸው። ሀገራቸውን በተዐምር ወይም ደግሞ በአስማት ሀይል ያደረጉ ሀገራት የሉም። የሁሉም ሀገራት ታሪክ የሚጀምረው ሀላፊነት የሚሰማውን ትውልድ ከመፍጠር ነው። የእኛም ሀገር ታሪክ ከዚህ እንዲጀምር እሻለሁ። መጀመሪያ ለራሳችን እውነት እንሁን። ሀገር ስትኖር እንደሆነ እኛ የምንኖረው ማሰብ አለብን። ሀገራችን የመጀመሪያዋም የመጨረሻዋም የልዕልናችን ጥግ ናት ። ለዚች አንድ እውነታችን ደግሞ ከሀሳባችን መካከል ምርጥ የሆነውም መርጠን መስጠት አለብን። ሀገራችን ጥላችን ናት። ከጥላችን እንዳንወጣ ከክብራችን እንዳንሸሽ በተባበረ ክንድ የቆመች ሀገር እንገንባ። እውቀት ማለት ፊደል መቁጠር አይደለም፣ እውቀት ማለት ዶክትሬትና ፕሮፌሰርነት አይደለም። እውቀት ማለት መጀመሪያ ላይ ቆሞ መጨረሻን ማሰብ ነው። እውቀት ማለት ዛሬ ላይ ሆኖ ነገን አሻቅቦ ማየት ነው። እውቀት ማለት ለሀገርና ህዝብ ተገን ሆኖ መቆም ነው። እውቀት ማለት ውለታ መመለስ ነው። ችግር ፈጣሪ ሳይሆን ችግር ፈቺ ሆኖ መገኘት ነው። እውቀት ማለት ባህልና ስርዐትን ማክበር ነው። ለአባቶች ስርዐት ማጎንበስ ነው። እውቀት ማለት በሀላፊነት፣ በያገባኛል፣ በይመለከተኛል በነዚህ ሁሉ ውስጥ መቆም ማለት ነው።
የልዕልና ጥግ በሆነች ሀገር ላይ ቆሞ አያገባኝም ማለት እውቀት አይደለም። ነገን የተሻለ ለማድረግ በሚውተረተር ድሀ ህዝብ መሀል ተፈጥሮ በእኔ ላይ ካልደረሰ አይመለከተኝም ማለት የመጨረሻው የጭካኔ ማሳያ ነው። ብዙ ተስፋንና ብዙ ራዕይን ሰንቃ ወደ ፊት ለመሄድ በምትውተረተር ሀገር ላይ ዜጋ ሆኖ እየኖረ መጥፎን ነገር እንዳላዩ ማለፍ ከነውርም ነውር ሆኖ ነው የሚታየኝ።
የእስካሁኖቹ ችግሮቻችን ባልተግባቡ ነፍሶቻችን የተፈጠሩ ይመስለኛል። አይደለም ከሌላው ጋር ከራሳችንም ጋር ያልተግባባን ብዙዎች ነን። ሀገር ማለት ትርጉሙ የጠፋን ሞልተናል። ከዛሬነት ወጥተን ነገን ማየት የማንችል ሆነን የምንኖር አለን። ከዛሬ ቀጥሎ ያለውን ነገ አርቆ ማየት ያስፈልጋል። የሀገራችን መኖር የህዝባችን በጋራ መቆም የህልውናችን አንዱ ማረጋገጫ እንደሆነ ሊገባን ይገባል። ወጥተን ስለገባን፣ ተኝተን ስለተነሳን ብቻ ሳይሆን በእውቀቱ፣ በክህሎቱ የተሻለ ነገን የሚፈጥር አዲስ ትውልድ በመፍጠር ላይም ልንተጋ ይገባል እላለሁ። አንዱ እየሰራ ሌላው በሚያፈርስበት፣ አንዱ እየተከለ ሌላው በሚነቅልበት ሀገር ላይ ተስፋ የለም። አንዱ ያገባኛል እያለ ሌላ አይመለከተኝም በሚልባት ሀገር ላይ ልማት የለም። መልካም ነገሮች የጋራ ውጤቶች ናቸው። በአንድ ሀገር ላይ ያሉ ማህበራዊ ከፍታዎች በዜጎች የበረቱ ትከሻዎች የተደገፉ ናቸው። በአንድ ሀገር ላይ ያሉ አሁናዊም ሆኑ ነጋዊ የድል ታሪኮች ዜጎች በአንድነት የሚጽፏቸው የጋራ ውጤቶቻቸው ናቸው። የብዙ ሺ አመት ታሪክ ባላት ሀገር ላይ አያገባኝም ማለት ሀገር ከመካድ ጋር አንድ ነው ብዬ አስባለው። ታሪካችን ባህላችን በጋራ የሚጠበቅ፣ በጋራ የሚለማ እንጂ በአንድ ወገን ብቻ የሚዘከር አይደለም። ሀገራችን የጋራችን እንደሆነች ሁሉ ታሪካችንም፣ ጀብደኝነታችንም እንከናችንም የጋራችን ነው የሚሆነው።
ታሪክ ያወቀ ከጠቢብ ይበልጣል። በአዛውንቶች ልብ ውስጥ ያለችው ጥንታዊቷ ሀገር ኢትዮጵያ በሀገር ጉዳይ ወደ ኋላ በማይሉ፣ ታሪክ በሚያውቁ፣ ባህልና ስርዐት በሚያከብሩ ኢትዮጵያዊያን የቆመች ነበረች። እኛም ጽኑ በሆነ የሀገር ፍቅር መልካም ሀገርና ህዝብ መገንባት ይኖርብናል። ማንም የሚመጣልን የለም እኛ ለእኛ በቂዎች ነን..ኧረ እንዳውም ከበቂም በላይ ለሌሎች መትረፍ የምንችልም ነን። ሀገር ለመገንባት የሚያስችለን መዶሻና ምስማሩ በእጃችን ነው። ለሀገራችን ምርጡን ሀሳብ እናዋጣ። አያገባኝም እያልን፣ ዳር ይዘን በመቆም የምናመጣው ለውጥ የለም። በምናየው በምንሰማው በማንኛውም ነገር ላይ ያገባናል። በሀገራችን ጉዳይ ላይ እኛ ካላገባን ታዲያ ማነው የሚያገባው? እኛ ካልተመለከተን ማነው የሚመለከተው? እኔና እናንተ ተቆጥረን እኮ ነው መንግስት ህዝብ…ህዝብ መንግስት የተባለው። አትሸወዱ እኔና እናንተ ነን መንግስት። ካለ እኔና እናንተ መንግስት የለም።
ብዙዎቻችን በሀገራችን ጉዳይ ላይ አያገባኝም በሚል እሳቤ እንደ ሁለተኛ ዜጋ የምንኖር ነን። በዚህ እሳቤ ውስጥ የሚኖሩ በርካታ ሰዎችን አውቃለው። የምትፈልጓት ኢትዮጵያ በእኔና በእናንተ አሁን ውስጥ ነው ያለችው። አሁናችሁ ውስጥ አሉታዊ እሳቤን አውጡ። በሀገራችሁ ጉዳይ ላይ በምንም ነገር ያገባችኋል። ምን አገባኝ እያልን፣ አይመለከተኝም እያልን የምንፈጥረው ሀገራዊ በረከት የለም። አሁን ላይ በብዙዎቻችን ዘንድ ምን አገባኝ..አይመለከተኝም የሚሉ ሀገር አፍራሽና ትውልድ አውዳሚ ነውረኛ ቃላት አሉ። አሁን ላይ ብዙ ነገራችን ስህተት እየሆነ የመጣው ምን አገባኝ በሚሉ አንደበቶች ነው። ለሀገራችን ያገባናል። ለወገናችን ይመለከተናል። ለትውልዱ ሀላፊነት አለብን። ለሚመጣው…በሚመጣው…ለሚሆነው በሚሆነው ሁሉ ሀላፊነት አለብን። በስራችን፣ በኑሯችን የሚሆነው ነገር ሁሉ ጉዳያችን ነው። አዲሷ ኢትዮጵያ በእናንተ ውስጥ ናት። አዲሱ ትውልድ በእናንተ አስተሳሰብ ውስጥ ነው። ከእውቀታችሁ፣ ከልምዳችሁ፣ ከሰውነታችሁ ውስጥ ለሀገርና ትውልድ የሚበጀውን መልካሙን ሀሳብ አፍልቁ። መኖራችሁ ለሌሎች እሴት እንዲሆን ወደ ሌሎች ብርሀንን አብሩ። የሀገራችሁን የተስፋ ብርሀን ለማጨለም ለመጥፎ የሚተጉትን እያያችሁ ምን አገባኝ አትበሉ። ምን አገባኝ ሀገር አውዳሚ ከባድ መሳሪያ ነውና። ቸር ሰንብቱ አበቃሁ።
ዘለዓለም የሳጥን ወርቅ (የእፀ ሳቤቅ አባት)
አዲስ ዘመን ሰኔ 1/2013