ባለፈው ዓመት አሊቨር ሮቢንሰን የተባለ የሲ.ኤን.ኤን ጋዜጠኛ «ኢትዮጵያን ልዩ የሚያደርጓት አስር ነገሮች» በሚል ርዕስ አንድ ፅሁፍ አስነብቦ ነበር፡፡ ታዲያ ሚስተር ሮቢንሰን «ኢትዮጵያን ልዩ የሚያደርጓት» ብሎ ከዘረዘሯቸው ነጥቦች መካከል «በዓለም ላይ ምርጥ የሚባሉ የኢጣሊያ ምግብ ቤቶች» እና «የጣሊያን የቡና አፈላል ሥርዓት» መሆናቸው በግሌ በጣም አስገርሞኝ ነበር፡፡ በእርግጥም ጽሁፉ ፍጹም ኢትዮጵያን የማይገልፅና በተቃራኒው የተለመደውን የነጮች «የበላይ ነን» አባዜ በታላቅዋ አገር ላይም ለመጫን የሚሞክር በማር የተጠቀለለ መርዝ በመሆኑ ከመገረምም ባለፈ በዚሁ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ መዝናኛ አምድ ላይ «ሲ.ኤን.ኤንን ታዘብኩት» በሚል ርዕስ የመልስ ምት ጽፌ ነበር፡፡ በወቅቱ ለሴ.ኤን.ኤኑ ጋዜጠኛ በጻፍኩት ጽሁፍ ውስጥ አሁን ካነሳሁት ርዕሰ ጉዳይ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ መልዕክት አስፍሬ ነበር፡፡ እንደሚከተለው ይነበባል፡- «…ለካ አጂሬ የጣሊያን ምግብ ቤት፣ የጣሊያን ቡና አፈላል ወዘተ እያለ የሚዘላብደው እውነትም የኢትዮጵያ መለያ ነገሮች ሆነው ሳይሆን» ጣሊያኖች በኢትዮጵያ የነበራቸውን የሥልጣንና የንብረት ይዞታ የሚያረጋግጡ ስለሆኑ የነጮችን ሌጋሲ የሚያስታውሱ ስለሆኑ ነው»፡፡ ካልሆነማ የጣሊያን ምግብ ቤት፣ የጣሊያን ቡና አፈላል ለእኛ ምናችን ነው? እንዴትስ የኢትዮጵያ መለያ ሊሆን ይችላል?» ሚስተር ሮቢንሰን እንደሚታወቀው እኛ ኢትዮጵያውያን ስለራሳችን መናገር አንወድም፡፡ አንተው እንድንናገር ካደረከን ዘንዳ ግን እስኪ የሚከተለውን እንንገርህ፡፡ በአፍሪካ አህጉር ከሚገኙ አርባ የሚደርሱ የሳር ዝርያዎች መካከል ወደ ሰላሳ የሚጠጉት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚበቅሉ ናቸው፡፡ አስር ያህሉ ደግሞ ከኢትዮጵያ ውጪ የትም የማይገኙ ብርቅየ የኢትዮጵያ ብቻ ስጦታዎች ናቸው፡፡ በዓለም ላይ ከሚገኙ 277 ትልልቅና መለስተኛ ጡት አጥቢ የዱር እንስሳት መካከል ሰላሳ አንዱ እንደዚሁ ከኢትዮጵያ ውጭ በየትኛውም ዓለማት የማይገኙ ዝርያዎች ናቸው፡፡ በተመሳሳይ በዓለም ላይ ከሚገኙ ከ 9 ሺህ 100 በላይ የአዕዋፍ ዝርያዎች መካከል 862ቱ የሚገኙት በኢትዮጵያ ሲሆን፤ ወደ ሰላሳ የሚጠጉት ደግሞ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በዓለም ላይ ከሚኖሩ 201 ዓይነት የተሳቢ እንስሳት ዝርያዎች መካከል አስሩ፣ በየብስና በውሃ ውስጥ ከሚኖሩ 63 የእንስሳት ዝርያዎች መካከል ሰላሳዎቹ፣ ከ324 ቢራቢሮ ዝርያዎች መካከል ሰባቱ እንዲሁም ከ150 የዓሣ ዝርያዎች መካከል አራቱ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ናቸው፡፡ ሌላም አለ፡፡ በዓለም ላይ ከ6500 እስከ 7000 የሚደርሱ የዕፅዋት ዓይነቶች እንዳሉ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ታዲያ ከእነዚህ መካከል አስራ ሁለት በመቶ የሚሆኑት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ኢትዮጵያ ውስጥ ወደ ሁለት መቶ የሚጠጉ የሰብል ዝርያዎች ይገኛሉ፡፡ ታዲያ በዓለም ላይ ለግብርና ምርት በጣም አስፈላጊ ከሆኑት ከእነዚህ ሁለት መቶ የሰብል ዝርያዎች መካከል ከ38 ያላነሱት አሁንም የመጀመሪያ ወይም ሁለተኛ የዘር መገኛቸው ኢትዮጵያ ነች፡፡ ከእነዚህ መገኛቸው በኢትዮጵያ ብቻ ከሆኑት መካከል ደግሞ እንጀራ ለሚባለው የኢትዮጵያዊያን ልዩ ባህላዊ ምግብ መስሪያ የሚያገለግለው ጤፍ፣ ቡና፣ ዳጉሳ፣ ገብስ፣ እንሰት፣ ኑግ፣ ሰሊጥና ጫትም የተገኙት እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ በተፈጥሮ ብቻ ነው፡፡ ስልጣኔን ቀድመው ለዓለም ያስተማሩ ጥበበኛ ልጆቿ የአዕምሮ ውጤት የሆኑትና ዓለምን ያስደነቁት እነ አክሱም፣ ላሊበላ፣ ፋሲል፣ ጀጎልና ሌሎችም ተዘርዝረው የማያልቁ ቁሳዊ፣ መንፈሳዊና ባህላዊ ሃብቶቿ ሲጨመሩ ደግሞ ኢትዮጵያን ከአድናቆትም በላይ የሆነች እጅን በአፍ የምታስጭን “የማይደረስባት ምስጢር” ያደርጓታል፡፡ እናም አገራችን በተፈጥሮ የተለገሷትንና በዓለም ላይ ተለይታ የምትታወቅባቸውን የእርሷ ብቻ የሆኑ አያሌ ልዩ ስጦታዎች ማወቅና በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ብልህነት ነው፤ የእኛ ብቻ የሆነውን ልዩ ስጦታ እንደሚገባን የብሔራዊ መለያ አድርጎ መጠቀም ደግሞ ስልጡንነት ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ሰሞኑን ይፋ የሆነው የኢትዮጵያን የግብርና ምርቶች ልዩ ጣዕም በዓለም ዙሪያ ለማስተዋወቅ የሚያስችል ዓለም አቀፍ የምርት መለያ ለእኛነታችን ልዩ መገለጫ ለሆኑት ገጽታዎቻችን ፋይዳው የላቀ ነው፡፡ አንድምታውም አንድ ሁለት ተብሎ በቀላሉ ተቆጥሮ የሚያልቅ አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ የግብርና ውጤቶች በዓለም ላይ ተለይተው የሚታወቁበት ልዩ ጣዕማቸው የአገሪቱ ብሔራዊ የንግድና የቱሪዝም መለያ ሆኖ እንዲያገለግል ባለፉት ሦስት ዓመታት ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ በመጨረሻም ጥረቱ ተሳክቶ ይህን የማድረግ ኃላፊነት የተሰጣቸው የኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጄንሲና ቱሪዝም ኢትዮጵያ በጋራ በመሆን “ኢትዮጵያ፡- የጣዕም መገኛ” የሚል ስያሜ ያለው የኢትዮጵያ የግብርና ውጤቶች ዓለም አቀፍ መለያ ከሰሞኑ አስተዋውቀዋል፡፡ የመለያው ስያሜ የተገኘው ከዋናው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የቱሪዝም ማስተዋወቂያ መለያ ምልክት “ኢትዮጵያ፡- ምድረ ቀደምት” ከሚለው ቃል ሲሆን የግብርና ምርቶች ልዩ ጣዕም በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅና ተፈላጊነታቸውን ከፍ በማድረግ ሃገሪቱን ከዘርፉ በእጅጉ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ታምኖበታል፡፡ የመለያው ጥቅም ላይ መዋል የአገሪቱ የግብርና ምርቶች ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲጨመርና የወጭ ንግዱንም በማስፋፋት ረገድ የሚኖረው ፋይዳ መሆኑን የኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር ካሊድ ቦምባ ይናገራሉ፡፡ ይህም ለኢኮኖሚ ዕድገቱ ከሚያበረክተው አስተዋፅኦ በአሻገር ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ስሟ ከፍ ብሎ በበጎ እንዲነሳ መልካም አጋጣሚን የሚፈጥር ነው፡፡ በተጨማሪም መለያው በአነስተኛ ማሳ ላይ የተሰማራውን አርሶ አደር ከሃገር ውስጥና ከዓለም አቀፉ የአቅርቦት ሰንሰለት ጋር ለማስተሳሰር ያግዛል፡፡ “ይህም የሃገሪቱ የግብርና ትራንስፎርሜሽን የህዝቡን የኑሮ ደረጃ በማሻሻል ላይ የተመሰረተ መሆኑን ማሳያ ነው” ይላሉ ዋና ዳይሬክተሩ፡፡ የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሌንሳ መኮንን በበኩላቸው፤ “በቱሪዝምም ሆነ በንግድና ኢንቨስትመንት ለምርቶቻችን ዓለም አቀፍ መለያ ምልክት ሰጥቶ መንቀሳቀሱ ሃገሪቱ የበርካታ አስደናቂ ነገሮች መገኛ መሆኗን ለዓለም ህዝብ ለማስተዋወቅ መንገድ ከፋች ነው” ይላሉ፡፡ በመሆኑም ምርቶቹን ለማስተዋወቅ ጥቅም ላይ የሚውለው አዲሱ ዓለም አቀፍ መለያ ምልክት በሁሉም ዋና ዋና የግብርና ውጤቶች ላይ ቀጣይነት ባለው መንገድ በቋሚነት እንዲያገለግል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች በዓለም ላይ እጅግ ተወዳጅና አስደናቂ ጣዕም ያላቸው ቢሆኑም ዓለም እንዲያውቃቸውና ዕውቅና እንዲሰጣቸው ባለመደረጉ ሃገሪቱ ማግኘት የሚገባትን ያህል ጥቅም ሳታገኝ መቆየቷን የሚያስታውሱት ዋና ዳይሬክተሩ “አሁን ግን ከጣዕማችን የሚገባንን ያህል ለማግኘት ሁላችንም ተባብረን የምንሰራበት ጊዜ ነው” የሚል መልዕክት ያስተላልፋሉ፡፡ “በዓለም አቀፍ ደረጃ በወጭ ንግድ የምንታወቅባቸውን ቡናና ሰሊጥን ጨምሮ በርካታ የግብርና ውጤቶቻችን መገኛቸው ኢትዮጵያ ከመሆኑም በአሻገር በጣዕማቸውም ቁጥር አንድ ተፈላጊ ናቸው” የሚሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ጥራጥሬ ላኪዎች ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ ዮሐንስ ናቸው፡፡ ስለሆነም ይህንን ዕድል በተገቢው መንገድና በበቂ ሁኔታ ለዓለም ማስተዋወቅና ዓለም አቀፍ መለያ እንዲሆን ማድረግ የወጭ ንግዱን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ ይህም በተራው ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የአገሪቱን አርሶ አደር ህይወት በመቀየር አጠቃላይ የአገሪቱን የምጣኔ ሐብት ወደሚፈለገው ኢንዱስትሪያዊ ሽግግር ለማምጣት አቅም የሚፈጥር ይሆናል፡፡ “ኢትዮጵያ፡- የጣዕም መገኛ” የሚለው አዲሱ የኢትዮጵያ የግብርና ውጤቶች ዓለም አቀፍ መለያ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች፣ በጀርመን፣ በቻይናና በግብፅ በተካሄዱ ዓለም አቀፍ የንግድ አውደ ርዕዮች ተሞክሮ በገዥዎችና በጎብኝዎች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትንና ዕውቅናን አግኝቷል፡፡ እኛም ይህ ልዩ ስጦታን በመለያነት የመጠቀምና በተፈጥሮ የተገኘን መልካም ዕድል ለሁለንተናዊ ዕድገት ማዋል ይበል የሚያሰኝ መልካም ጅማሮ ነውና ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል እንላለን፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2011
ይበል ካሳ