
በ1999 ዓ.ም የተደረገው የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ውጤት እንደሚያሳየው በአገራችን የከተማ ነዋሪው ሕዝብ ብዛት 11ነጥብ9 ሚሊዮን ሲሆን፣ ይህም ከጠቅላላው የሀገሪቱ ህዝብ 16ነጥብ1 በመቶ ነው፡፡ የዓለም ባንክ በ2008 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት ደግሞ ቁጥሩ ከ20 ሚሊዮን በላይ መሆኑን ያመላክታል፡፡ ይህ የአከታተም ደረጃ አሁን ካለው ከአፍሪካ አማካኝ 37 በመቶ እንዲሁም ከታዳጊ ሀገራት አማካይ 41 በመቶ ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ነው፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያ ባለፉት አስር ዓመታት የከተማ ነዋሪዎች ቁጥር ፈጣን እድገት እያሳየ መሆኑን ነው፡፡ በአገራችን የከተማ ነዋሪ አማካይ ዓመታዊ የእድገት ምጣኔ ከ4 በመቶ በላይ ሲሆን፣ ይህም በዓለም ላይ ከፍተኛ የከተማ ነዋሪ የእድገት ምጣኔ አላቸው ከሚባሉ አገራት አንዱ እንድንሆን ያደርገናል፡፡ ለዚህ ፈጣን የከተሞች የህዝብ እድገት ከተፈጥሮ የህዝብ እድገቱ በተጨማሪ ከገጠር ወደ ከተማ የሚፈልሰው ህዝብም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በመሆኑም ከተሞቻችን ከዚህ ዕድገት ጋር የሚመጣጠን ኢንቨስትመንት፣ የሥራ ዕድልና የመሰረተ – ልማት አቅርቦት ማስፋፋት ይጠበቅባቸዋል፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአብዛኛው በግብርናው ዘርፍ ላይ ተመስርቶ የቆየ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በከተሞች ኢንቨስትመንት እየተስፋፋ ይገኛል፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በየቦታው መገንባትም ለከተሞች እድገት የራሱን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ይጠበቃል፡፡ ከዚህ አንጻር ከተሞች ለጠቅላላው የአገር ውስጥ ምርት (GDP) የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ የሚጠቀስ ነው፡፡ በተጨማሪም የከተሞች ኢኮኖሚ በየዓመቱም ፈጣን ዕድገት እያሳየ ነው፡፡ በሀገር ደረጃ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ለተያዘው ከፍተኛ የእድገት ግብ መሳካት ከተሞች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዲኖራቸው ኢኮኖሚያዊ ምርታማነታቸውን በማሳደግ የተጀመረውን ሰፊ መሠረት ያለው እድገት የማስቀጠል ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል፡ ፡ በተጨማሪም ኢኮኖሚው ማሳየት የጀመረው መዋቅራዊ ለውጥ ዳር እንዲደርስና በዚህም ኢንዱስትሪው በኢኮኖሚው ውስጥ ቁልፍ ሚና እንዲጫወት ለማስቻል በከተሞች የሚካሄዱ ኢንቨስትመንቶችን ማበረታታት ይገባል፡፡
የከተሞች ነባራዊ ሁኔታ ሲዳሰስ ግልፅ ሆኖ የሚወጣው ችግር ሥራ አጥነት ነው፡፡ በእርግጥ ይህን ችግር ለመቅረፍ መንግሥት ከፍተኛ ርብርብ ሲያደርግ ቆይቷል፤ አሁንም እያደረገ ነው፡፡ በተለይ ወጣቶችን እና ሴቶችን ማዕከል ያደረጉ የተለያዩ የሥራ ፈጠራ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ አበረታች ውጤት ተገኝቷል፡፡ ለምሳሌ በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ልማት ፕሮግራም አማካይነት ብቻ ባለፉት ስድስት ወራት ከስድስት መቶ ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡ የከተሞች መሠረተ-ልማት ለማስፋፋት ከፍተኛ ትርጉም የሚሰጣቸው ተግባራት የተከናወኑ ቢሆንም አሁንም የከተሞች የመሠረተ ልማት አቅርቦትና ጥራት ዝቅተኛ ነው፡፡ መሠረተ-ልማትን የማስተዳደር አቅም ውስን መሆንም የከተሞች ሌላው ፈተና ነው፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመፍታትም ከተሞች እነዚህን አገልግሎቶች ለነዋሪዎቻቸው በሚፈለገው መጠን ማቅረብ የሚያስችላቸው የፋይናንስና የማስተዳደር አቅም እንዲፈጥሩ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ ለከተማ ነዋሪዎች ኑሮ መሻሻል መሠረታዊ ከሆኑት ፍላጎቶች መካከል ሌላው መሰረታዊ ጉዳይ የመኖሪያ ቤት ነው፡፡ የከተማ ቤት ልማት ለረጅም ጊዜ ተገቢው ትኩረት ሳያገኝ የቆየ በመሆኑ በከተሞች ከፍተኛ የሆነ የቤት እጥረት ይታያል፡፡
በአንዳንድ ከተሞች ያሉት አብዛኛዎቹ ቤቶችም የተጨናነቁ፣ የተጎሳቆሉ፣ በፕላን ያልተሠሩ፣ የመሠረተ-ልማት ያልተሟላላቸው፣ ለድንገተኛ አደጋዎች የተጋለጡ እና በአጠቃላይም ለኑሮ አመቺ ያልሆኑ ናቸው፡፡ መንግሥት ይህን ችግር ለመፍታትም በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች የቤት ልማት ፕሮግራም ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በዚህ ፕሮግራም አማካይነት መንግሥት በተለይም ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ወጪ ቆጣቢ የሆኑ ቤቶችን በመገንባት የቤት ችግራቸውን ለማቃለል ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በአገራችን የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በዘርፉ የነበሩ ችግሮችን በመለየት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ በከተሞች ያለው የመልካም አስተዳደር ሁኔታም ሌላው መሰረታዊ ፈተና ነው፡፡
በተለይ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በአገራችን ውስጥ ተከስተው ለነበሩ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች የመልካም አስተዳደር ችግር ዋነኛው መነሻ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በመሆኑም መንግሥት እነዚህን ችግሮች ከመሰረቱ ለመፍታት ልዩ ልዩ የመዋቅር ማሻሻያዎችና አሰራሮችን ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል፡ ፡ ያልተማከለ አስተዳደርን በመዘርጋት ቀልጣፋና ውጤታማ መንግሥታዊ አገልግሎቶችን ለማቅረብ፣ ተጠያቂነትንና ግልጽነትን ለማስፈን፣ እንደዚሁም የህዝብ ተሳትፎን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ማሻሻያዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ በአጠቃላይ አገራችን ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማካሄድ በከፍተኛ እንቅስቃሴ ውስጥ ባለበት በአሁኑ ወቅት ከተሞቻችን የሚኖራቸው ሚና የጎላ ነው፡፡ ይህንንም ውጤታማ በሆነ ሁኔታ ለመፈፀም የእርስ በርስ የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበትና ተደጋግፈው የሚያድጉበት የጋራ ፎረም መድረክ ማካሄድ ከጀመሩም ዘጠኝ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
የዘንድሮ የከተሞች ፎረምም በምስራቃዊቷ ከተማ ጅግጅጋ ተካሂዷል፡፡ በፎረሙ ተሳታፊ የሆኑ ከተሞች በእስከዛሬው ሂደታቸው ያስመዘገቧቸውን መልካም ሥራዎች ይዘው የሚቀርቡበት፤ ራሳቸውን የሚያስተዋውቁበትና ለከተማ ነዋሪዎች መረጃ የሚሰጡበት፤ መድረክ ከመሆኑም በላይ እርስ በርስ የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበት ነው። በመሆኑም እያንዳንዱ የከተማ አስተዳደር ያገኘውን ልምድ ከራሱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማዛመድ የተመጣጠነ የከተሞች እድገት እንዲፈጠር ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2011