አሁን ያለንበት ወቅት ላይ ያለ ትውልድ ወደፊት ሳይሆን ወደ ኋላ በድሮ ለመኖር ያሰበ ትውልድ ይመስላል። አዋቂ ነን ባዮች ሳይቀር በዘረኝነት ኋላቀር አስተሳሰብ ወደ ኋላ መሄድ ከጀመሩ ቆይተዋል። ሀገራችን ላይ ያለው የዘረኝነት በሽታ ከኮረና በላይ የከፋና የጽኑ ህሙማን ቦታ የሞላበት ይመስለኛል። በየጊዜው የሚከሰቱ ችግሮች ድሮን ከመኖር ይመስላል። ሀገራችን ላይ እንዳሉ ችግሮችማ ጭራሽ አሁን ያለንበትን ዓመተ ምህረት ላይ ገና አልደረስንም። ብዙ ዓመታትን ወደ ኋላ ሄደን ድሮ ላይ ነው ያለነው። ቀደምት ኢትዮጵውያን አስደናቂና አስደማሚ ስራዎችን ሰርተዋል። በዘረኝነት ሳይሆን በአንድነት የጥቁሮች መኩሪያ የሆነች ሀገርን አስረክበውናል። እነዚህ ሁሉ መልካም ነገሮች ናቸው። አሁን ወደ ኋላ ሄደን በዘር መከፋፈል ትክክል አይደለም። የኢትዮጵያውያንን መልካም እሴቶች የሚያደበዝዝ ነው። አሁንን መኖር እንዴት ሰው ያቅተዋል? በነገራችን ላይ አንድ ሰው ሊለካ የሚገባው ባስተሳሰቡ ነው። የመኖር፣ አሳቡን በነፃነት የመግለጽ፣ ሰርቶ የመለወጥ መብት ሊኖረው ይገባል።
አንተ ትክክል መሆንህን ለማወቅ ወይም ትክክል አለመሆንህን ለማወቅ የህሊናህ እና የድርጊትህ እንጂ የሌሎች ሰዎች ድርጊት አያሻህም። ውስጣዊ ማንነቱ የተከፋፈለ ግለሰብ በአብሮነት የማይስማማ ማህበረሰብን ይፈጥራል። የሰው ተግባር ከአስተሳሰቡ ይመነጫል። አንድ ሰው ሃሳቡን በጤናማ መልኩ መግራት ካልቻለ ከክፋት መውጣት አይችልም። የሌሎችን ሃሳብ ማዳመጥ ካልቻለ እሱም አዳማጭ ያጣል ማለት ነው። ለሀገር የሚጠቅም ሳይሆን ለጊዜያዊ ጥቅም ብሎ ሀገርን፣ ህዝብን የሚበድል ለጥቂት ሰዎች ብሎ ብዙሃንን የሚጎዳ ተግባር ላይ ይሰማራል። ይህ ደግሞ አደገኛና አንድነታችንን የሚሸረሽር ነው። ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር ናት ከዘረኝነትና፣ ከክልልና፣ ከሰፈር አስተሳሰብ ወጥተን እንደ ሀገር ጤናማ የሆኑ ተግባራት ላይ ብንሰማራ ጥሩ ነው።
የውጭ አለማት (ሀገራት) የሚያውቁን ኢትዮጵያ በሚለው ታላቅ ስም ነው። በሌሎች ሀገራት ታላቅ ከበሬታን እንዲሰጠን መጀመሪያ ውስጣዊ አንድነታችን ላይ መጠንከር እና ለኢትዮጵያዊነት ትልቅ ቦታ ልንሰጥ ይገባል። ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ ኢትዮጵያዊ መፈናቀል የለበትም። ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ ኢትዮጵዊ እርስ በርስ በዘረኝነት መገዳደል የለበትም።
“ያማረ ነገ የሚፈጠረው ዛሬ በምትሰራው ነገር እንጂ፤ ነገ በምታደርገው አይደለም!” (ሮበርት ኢዮሳዲ) እውነት ነው። የተሻለን ነገር ለመስራት ነገ እያልን ሳናደርገው እንቀራለን። የምንመኘውን በጎ ነገር ለሀገር ይጠቅማል የምንለውን በቀጠሮ ከመጠበቅ ለምን ከአሁን አንጀምርም? ታላቁ ሰው ኔልሰን ማንዴላ ስለ ኢትዮጵያ ይሄን ብለው ነበር። “ኢትዮጵያ ሁሌም በአእምሮዬ የተለየ ቦታ ያላት ሲሆን ኢትዮጵያን የመጎብኘት ህልሜ ፈረንሳይ፣ እንግላንድና፣ አሜሪካ አንድ ላይ ተደማምረው ከማደርገው ጉዞ የበለጠ ይማርከኛል። ግርማዊነታቸውን ማግኘት በራሱ ከታሪክ ጋር እንደመጨባበጥ ያህል ነው።”
ምን ያህል ኢትዮጵያ የኛ ብቻ ሳይሆን የጥቁር ህዝቦች መከበሪያ የሆነች ሀገር እንዳለችን በደንብ ብንረዳ በውስጥ አንድነታችን ላይ ፈጽሞ አንደራደርም ከሚከፋፍሉን ነገሮች ይልቅ አንድ የሚያደርጉን ተግባራቶች ላይ መተባበር አለብን።
የምርጫ ተፎካካሪዎች ሁሌም ምርጫ በመጣ ቁጥር ከገዢው ፓርቲ ጀምሮ እስከ ተፎካካሪ ፓርቲ ‹‹ለኢትዮጵያ ይሄን አደርጋለሁ›› እያሉ የተለያዩ ቃል ይገባሉ። እያሰባችሁ ያለውን ለሀገር የሚጠቅም ተግባር ለምን ከአሁን አትጀምሩትም ወይስ ምርጫ ካልደረሰ መልካም ነገር አይኖርም ማለት ነው? የምታስቡት መልካም ሃሳብ ግዴታ ለስልጣን ብቻ መሆን የለበትም። ሀገራችን ውስጥ ፓርቲዎች ይወዳደራሉ። የሁሉም ሃሳብ የተለያየ ነው። ነገር ግን ሌሎቹ ፓርቲዎች ንቁ ተሳትፎ ሲያደርጉ አይስተዋልም። በጣት የሚቆጠሩ ብቻ ፓርቲዎች በየአካባቢው ምረጡኝ ሲሉ ይስተዋላሉ። ለምን ሁሉም ፓርቲዎች ከነሱ እኩል መራመድ አልቻሉም? ዴሞክራሲ የሚገነባው በእኩልነት የመፎካከር መንፈስ ነው። ክርክር በሌሎች ሃሳቦች ወይም ድርጊቶች ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር ዓላማዎችን የመፍጠር ትክክለኛ ሂደት ማድረግ ነው። የምርጫ ክርክርሮች ላይ የሚስተዋሉ ጉድለቶች ለሚነሱት ሃሳቦች አሳማኝና ጠንካራ መልስ አለመስጠት የፓርቲ ተወካይ ክርክር ላይ አለመገኘት ሰዓት አጠቃቀም ሃሳቦችን በተገቢ ሁኔታ አለመቋጨት ሊስተካከሉ የሚገባቸው ችግሮች ናቸው።
ሚዲያዎች ገለልተኛ መሆን አለባቸው ሲባል ደግሞ የህዝብ ችግር ላይ ማተኮር አለባቸው ማለት ነው። ሚዲያዎች የህብረተሰቡ ድምጽ መሆን አለባቸው። ሁሉም በእኩልነት ገለልተኛ ሆነው ማስተናገድ አለባቸው ማለት ነው። ለእውነት የሚቆሙና ለሀገር አንድነት የሚሰሩ መሆን አለባቸው። ሚዲያዎች ሁሌ መሰረተ ልማት በተመረቀ ቁጥር ለሚዘጋጁ የደስታ ፕሮግራም በመገኘት ብቻ ዶክመንተሪ ሰርቶ ማሳየትን ብቸኛ አማራጭ ማድረግ የለባቸውም። የመገናኛ ብዙሃን ጨዋነትን በተላበሰ መልኩ ማህበረሰቡ በየጊዜው ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ የሚዲያው ሚና ከፍተኛ አስተዋጽዖ ይኖረዋል። የመፍትሄ ሃሳቦች ላይ የሚሰሩ ሊሆኑም ይገባል እንጂ እራሳቸው ችግር ፈጣሪ መሆን የለበትም። የተሻለ ሃሳቦችን ለማንጸባረቅ ለሁሉም ፍታዊ መሆን አለበት። ነገር ግን አሁንም የህዝብ ሚዲያ የህዝብ ፍላጎት የሚንጸባረቅባቸው ከመሆን ይልቅ ለአንድ ፓርቲ ያደላ የህዝብ ሳይሆን የፓርቲ ድምጽ ነው የሆነው። ይሄ ደግሞ ነፃና ገለልተኛ ነው ብሎ ለመናገር የሚያስችል አይደለም። የሚዘግቡት ዘገባ ሳይቀር ለአንድ ፓርቲ ያደላና ገለልተኛነት የማይታይባቸው ሆነዋል። ይሄ ደግሞ ፈጽሞ የዴሞክራሲ ሥርዓትን ከመገንባት አንጻር ተቃራኒ ነው። አንድ ሚዲያ ገለልተኛ ነው ሚባለው ሁሉንም በእኩልነት ሲያስተናግድ ነው። ገለልተኛነት ማለት ለማንም የማይወግን ማለት ነው። ችግር ሲያገኝ መንግስትንም የሚጠይቅ ማለት ነው።
እንደምናየው ሚዲያዎቻችን የሚያተኩሩት መልካም ገጽታዎች ላይ ብቻ ነው። ደካማ ጎን፣ ስህተት መንግስት ላይ የለም ያለው ማን ነው? ነፃ ሆነው በእኩልነት መስራት አለባቸው። ዘገባዎችን ከተጽእኖ ወጥተው መዘገብ አለባቸው። ለእውነት መስራት አለባቸው። ያኔ ነፃና ገለልተኛ ይሆናሉ።
ሰሞኑን የምርጫ ክርክር እየተካሄደ ነው።ፓርቲዎች የተለያየ ኃሳባቸውን በማንጸባረቅ ላይ ይገኛሉ። ሚዲያዎች የአየር ሰዓት ተሰጥቷቸዋል፤ ፕሮግራሞቻቸውን እያስተዋወቁ ይገኛሉ። ነገር ግን እየተከራከሩ ያሉት ሚዲያዎች በመረጡላቸው ርዕስ ላይ ነው። ይህ እንደ ጅማሬ ጥሩ ቢሆንም የራሳቸውን አጀንዳ ይዘው እንዲመጡ ቢደረግ ግን ጥሩ ነው። ምክንያቱም ማህበረሰቡ ይዘውት በሚመጡት ጠንካራ አጀንዳ ማወዳደርም ስለሚችል ማለት ነው። የሚዲያዎች ሚናም በሃሳብ የበላይነት የማመን እና ማንኛውም የተሻለ ሃሳብ በነጻነት የሚቀርብባቸው መድረኮች መሆን አለባቸው።
በመጨረሻም ሁሉንም እንደ ሀገር የሚጠቅም ነገር አንድነት ነው። ችግሮችን ለመቅረፍ በአብሮነት መስራት ያስፈልጋል። ችግሮችን ለመቅረፍ ከድክመታችን መማር እና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አንድ መሆን አለብን።
ሜላት ጌታቸው
አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2013