በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ አቅመ ደካማዎችን ለመደገፍ ከተመሰረቱ ማህበራት መካከል በአማራ ክልል ዳንግላ ከተማ የሚገኘው የአጉንታ ማርያም በጎ አድራጎት ማህበር አንዱ ነው፡፡ ማህበሩ ከተመሰረተ ጀምሮ በአካባቢው የሚገኙ አቅም የሌላቸውን አረጋውያንና ተማሪዎችን በቻለው አቅም እየደገፈ ይገኛል፡፡ ስለማህበሩ አመሰራረትና የስራ እንቅስቃሴ ከአቶ ወንድወሰን አሰፋ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
የማህበሩ አመሰራረት
የአጉንታ ማርያም በጎ አድራጎት ማህበር ትናንታቸውን ለወገን እና ለሀገር ለገበሩ አረጋውያን ወላጅች እና የነገ የሀገር ተስፋዎች የሆኑት ህጻናት የሚያጋጥማቸውን ማህበረ ኢኮኖሚያዊ የመኖር እና የመማር ጥልቅ ፈተናዎች በማቃለል እንዲሁም በመፍታት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት በሚሹ ጥቂት ወጣቶች እና አዋቂዎች በዳንግላ ከተማ በሚያዝያ 2006 ዓ.ም. ተመሰረተ። ይህ በጎ አድራጎት ማህበር እንዲመሰረት መሰረት የጣለው በወቅቱ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በስፋት የሚከበረው የፋሲካ በዓል ማግስት የተከናወነው ተግባር ነበር። በጊዜው ጥቂት ወጣቶች ሰብሰብ ብለው ለሃይማኖት አባቶች የበግ እርድ በማድረግ ለማግደፍ ተስማምተው የገንዘብ መዋጮ ይጀምራሉ።
በዕለቱ ከመዋጮ በተገኘው ገንዘብ አባቶችን ለማግደፍ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች በሙሉ ተሟልተው ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ሌሊት ከተፈጸመ በኋላ አባቶች በተዘጋጀላቸው አዳራሽ ታድመው ምግብ እና መጠጥ ቀርቦ የማግደፍ ሥርዓቱ ተካሄደ፤ በእለቱ የታደሙትን ተስተናጋጅ የሃይማኖት አባቶችን እና አስተናጋጆችን በሀሴት ሞልቶ በታላቅ የአባቶች ምርቃትም ተጠናቀቀ።
እነዚህ ደግ ወጣቶች ጠዋት ተሰባስበው ስለነበረው ሂደት እያወሩ ከዝግጅቱ የተረፈ ጥቂት ገንዘብ ምን ይደረግ? የሚል ውይይት ይጀመራሉ። “ለአቅመ ደካማ ወላጆቻችን የበዓል መዋያ እንስጣቸው” የሚል ሃሳብም ይነሳል። ጊዜ ሳያጠፉ እርዳታው የሚያስፈልጋቸውን አረጋውያን ለይተው አስር ለሚሆኑ አቅመ ደካማ አረጋውያን ወላጆች ለእያንዳንዳቸው ሁለት መቶ ብር እንዲሰጥ አደረጉ፡፡ ወጣቹ የብዙዎቹን የአረጋውያን ኦና ጓዳ እና ጉስቁልና አይተው አዘኑ፡፡ የአረጋውያኑን ችግር ለመፍታትም ሌላ ከፍ ያለ ተጨማሪ ውይይት ተደረገ። በተለያዩ ችግሮች ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን ለመርዳት ተቋማዊ ድጋፍን እና የጋራ ትብብር ያስፈልጋል የሚል ውሳኔ ሃሳብ ላይ ደረሱ። በዚህ ሂደት ማህበሩ ከጥቂት ውጣ ውረድ በኋላ በአቶ ታደሰ ቢተው እና በወይዘሮ የሺ ገላው በጎ ፈቃድና ፊት አውራሪነት እንዲሁም በወጣቶች ከፍተኛ ትብብር በ2006 ዓ.ም. ህጋዊ ሰውነት አገኘ።
ማህበሩ ሰፊ ሀገራዊ ራዕይ ቢኖረውም ሊኖረው ከሚችል የፋይናንስ አቅም አንፃር ጅማሬውን ለጥቂት አረጋውያን ድጋፍ በማድረግ ለመጀመር ወሰነ። በዚህም መሰረት ወጣቶቹ በከተማው በሚገኙ አምስት ቀበሌዎች ውስጥ በአስከፊ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ አረጋውያንን የቀበሌ ሊቀመንበሮችን እና በየቀበሌው ያሉ የሀገር ሽማግሌዎችን በማወያየት እንዲሁም ለተመረጡት አረጋውያን በአካል ቤታቸው ድረስ በመሄድና ቃለመጠይቅ በማድረግ 64 (ስልሳ አራት) አረጋውያን ለይተው ድጋፋቸውን ጀመሩ።
ማህበሩ ያከናወናቸው ተግባራት
ማህበሩ ስራውን መስራት ከጀመረ ከሚያዝያ 2006 ዓ.ም ጀምሮ ከአባላቱ በሚገኝ ወርሃዊ ገቢ የምግብ ዱቄት፣ ዘይት፣ ልዩ ልዩ የአልባሳት፣ የንፅህና ቁሳቁስ፣ የህክምና ድጋፍ እና የመጠለያ እድሳት በማድረግ በርካታ ዘመን ተሻጋሪ አሻራዎችን እያስቀመጠ እና በማስቀመጥ ላይ ነው። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በርካታ ኩንታል የምግብ ዱቄቶችን፤ በርካታ ሊትር ዘይቶችን፤ የንጽህና መጠበቂያ ሳሙናዎችን ለሁሉም አረጋውያን አድርሷል። በዓመት ውስጥ ሶስት ጊዜ የበሬ፣ የበግ እና የፍየል እርድ በመፈፀም፣ የበዓል ዝግጅት በማድረግ አረጋውያኑን በአንድ ቦታ በክብር ሰብስበው ያበላሉ፤ ያጠጣሉ፤ ቅርጫ ስጋ ይሰጣሉ። በዚህ ቀን አረጋውያኑ ከሁሉም የሚልቀውን የአብሮነት ፍቅር እና ክብካቤያቸውን ያገኛሉ። እርስ በርስ ይጨዋወታሉ። የህይወታቸውን አስደሳች ቀናቶች ከበጎ አድራጊ ልጆቻቸው ጋር ያሳልፋሉ።
በማህበሩ ድጋፍ የተደረገላቸው አንድ አረጋዊት እናት ‹‹ልጆቼ በዚህ እድሜዬ አስከሬኔ ከቤት ይወጣል ብዬ እንጂ እንዲህ በክብር ከወገኔ ጋር በዓል አከብራለሁ፤ ቤቴስኪያን እስማለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር።›› ብለዋል። እንደ እኚህ አረጋዊት እናት ቤታቸውን ዘግተው፣ ቤተክርስቲያን እሚያደርሳቸው አጥተው፣ በራቸውን ዘግተው ሞታቸውን የሚጠባበቁ ወገኖቻችን ይህ እድል እንዲኖራቸው አድርገዋል። ማህበሩ የተለያዩ በጎ አድራጊ ግለሰቦችን በማስተባበር ብርድ ልብስ እና ነጠላን ጨምሮ በርካታ ልዩ ልዩ አልባሳትን በተለያዩ ጊዜያት በመለገስ የአረጋውያንን ገላ ከብርድ እና ከእርዛት ተከላክለዋል። የአረጋውያኑ የጤና ሁኔታቸው ሲታወክ ህክምና እንዲያገኙ የቻሉትን ሁሉ ጥረት አድርገዋል። ከዳንግላ ሆስፒታል ሀኪሞች ጋር በመነጋገር የቤት ለቤት የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ እና ተጨማሪ ምርመራ ሲያስፈልግ በሆስፒታሉ አምቡላንስ በመውሰድ የምርመራ እና የመድሃኒት ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ ችለዋል። ከዚህም ባሻገር ከሆስፒታሉ አመራር ጋር በመነጋገር በማንኛውም ሰዓት ከክፍያ ነፃ የህክምና እርዳታ ማግኘት የሚችሉበትን ዘላቂ እድል አመቻችተዋል። ሁሉም አረጋውያን የጤና መድህን ሽፋን በነጻ እንዲያገኙም አድርገዋል።
እላያቸው ላይ የዘመሙ እና እየፈረሱ የነበሩ የአረጋውያን ጎጆዎችን አድሰዋል። እንጨት ቆርጠው፤ አፈር ቆፍረው፤ ጭቃ አቡክተው የአረጋውያን ወላጆቻቸውን ጎጆ አድሰው ከዝናብ፣ ከብርድ እና ከአውሬ ተከላክለዋል። ከአረጋውያን በተጨማሪ ከ30 ያላነሱ ደጋፊ ለሌላቸው ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁሶች ድጋፍ አድርገዋል። ለልጆቹ ዩኒፎርም፣ ደብተርና እስክርቢቶ በመለገስ የነገ ተስፋቸውን አለምልመዋል፤ የመማር ፍላጎታቸውን ጨምረዋል።
የማህበሩ የስፖርት ቡድን ተቋቁሞ በወጣቶች እና በከተማው ህብረተሰብ ላይ በጎ ተጽዕኖዎችን ፈጥሯል። በማህበሩ ስም የሚጠራው የእግር ኳስ ቡድን በርካታ ዋንጫዎችን አንስቷል። የከተማውን ስፖርት አነቃቅቷል፤ እንዲሁም ማህበሩን በተለያዩ ቦታዎች በስፋት ለማስተዋወቅ ተችሏል። ከተማዋ ውስጥ ጉልህ አስተዋፆ ያበረከቱ ቅን ልቦችን እውቅና በመስጠት ብዙ ደጋጎችን ለማፍራት ጥረት በማድረግ ላይ ነው። ለአብነት የቀድሞው የዳንግላ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ርዕሰ መምህር ለነበሩት ለአቶ መርሻ ወልደ ገብርኤል ለትውልዱ ላበረከቱት አስተዋጽኦ እንዲሁም የዳንግላ ሆስፒታል ሀኪሞች ለአረጋውያን ወላጆቻችን ላበረከቱት ጉልህ የህክምና ድጋፍ እና እንክብካቤ የማህበሩን የክብር የእውቅና ሽልማት አግኝተዋል።
ማህበሩ የአረጋውያኑን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ከዳንግላ ከተማ አስተዳደር በተቀበለው የስድስት ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ለአረጋውያን መጠለያና ሁሉን አቀፍ ማዕከል በመገንባት ላይ ነው። ይህ ማዕከል በሀገሪቱ በአስከፊ ሁኔታ የሚኖሩ አረጋውያንን በአንድ ጥላ ስር በማኖር ተገቢ የሆነ ድጋፍ እንዲያገኙ፤ አረጋውያኑን በማዕከሉ የተለያዩ ስራዎችን እንዲሰሩ ሁኔታዎችን በማመቻቸት አምራች የህብረተሰብ ክፍል እንዲሆኑ፤ ወላጆቻቸውን በተለያየ ምክንያት ያጡ ህጻናት እና ታዳጊዎች የመማር እና የማህበረሰቡን እንክብካቤ የማግኘት እድል እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡
ማንኛውም የማህበረሰብ ክፍል አረጋውያኑን በቀላሉ በአንድ ቦታ መጎብኘት፣ ማጫወት እና መንከባከብ እንዲችል፤ ልዩ ልዩ ማህበራዊ ክንዋኔዎችን፤ ለምሳሌ የልደት፣ የሙት ዓመት፣ ብሄራዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላትን፣ ሰርግ፣ መልስ ወዘተ ከአረጋውያኑ ጋር በቀላሉ ለማክበር፤ ማዕከሉን ለሚያስተዳድሩ የህብረተሰብ ክፍሎች የስራ ዕድል ለመፍጠር፤ በተማሪዎች ስነምግባር ላይ በጎነትን ከማስረጽ አንጻር ተማሪዎች በበጎ አድራጎት ክበብ ተደራጅተው እንዲሁም በትምህርት ቤት ደረጃ አረጋውያኑን እንዲጠይቁ እና እንዲንከባከቡ በማድረግ የትውልድ ሰብዕና የሚቀረጽበት ትልቅ ተቋም ለማድረግ የሚያስችል ርዕይ የታጨቀበት፤ የቅን ልቦች አሻራ ያረፈበት ህያው የሰብዓዊነት ማዕከል ነው። ማህበሩ በከተማው ውስጥ ላደረገው እና እያደረገ ላለው የላቀ የበጎ ስራ አስተዋፅኦ ከህብረተሰቡ እና ከመንግስት አካላት ልዩ ልዩ የአድናቆት እና የምስክር ወረቀቶችን ማግኘት ችሏል።
ማህበሩን ያጋጠሙት ችግሮች
ማህበሩ የአረጋውያን እና ህፃናት መኖሪያ ማዕከሉን ለመገንባት አለመቻል፣ በቂ የቤት አስቤዛ ማቅረብ አለመቻል፣ የፈራረሱ ጎጆዎችን ለማደስ መቸገር፣ በመንግስት በኩል የሚደረግ ቋሚ የበጀት ድጋፍ አለመኖር እንዲሁም የበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ተሳትፎ አናሳ መሆን ተደጋጋሚ ችግሮች ናቸው። በተጨማሪም ለተማሪዎች በቂ የትምህርት ግብዓት ማሟላት አለመቻል፣ በኮቪድ-19 ምክንያት የገቢ ማሰባሰቢያ ስራዎችን ማድረግ አለመቻል፣ አረጋውያኑን በተበታተነ ቦታ በመሆናቸው አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ መቸገር፣ አረጋውያኑ ታመው ወደ ህክምና ሲሄዱ አስታማሚ አለመኖር፣ ከአባላት የሚሰበሰበው ወርሃዊ መዋጮ አናሳ መሆን፣ ረጂ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ድርጅቶችን ድጋፍ በፍጥነት ማግኘት አለመቻል፣ የአባላት ቁጥር አናሳ መሆን እንዲሁም ከሰራተኞች አኳያ የሰው ሃይል ማሟላት አለመቻል ተጠቃሽ ናቸው።
ለማህበሩ መመስረት አስተዋጽኦ ያደረጉ
በዚህ ማህበር ታሪክ ውስጥ አቶ ታደሰ ቢተው እና ወይዘሮ የሺ ገላው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉ በጎ አድራጊዎች ናቸው፡፡ አቶ ታደሰ ቢተው ከማህበሩ ምስረታ (2006 ዓ/ም) ጀምሮ ህይወታቸው እስካለፈበት ዋዜማ (2010 ዓ.ም.) ድረስ ጊዜያቸውን ያለስስት በመስጠት ያገለገሉ አንፀባራቂ ቅን ልብ ያላቸው ደግ አባት ነበሩ። አቶ ታደሰ ቢተው ህጋዊ የማህበሩን ፍቃድ ከማውጣት ጀምረው፤ ድጋፍ የሚደረግላቸውን አረጋውያን በየቀበሌው ዞረው መርጠው፤ ከአባላት እና ከደጋፊዎች ገንዘብ ለምነው፤ ለአረጋውያን ወላጆቻቸው የምግብ ዱቄት እና ልዩ ልዩ ስጦታዎችን ቤታቸው ድረስ በማቅረብና ማህበሩን በማስተዋል በመምራት ትልቅ አሻራቸውን አስቀምጠው አልፈዋል።
ወይዘሮ የሺ ገላውም ከማህበሩ ምስረታ ጀምሮ ሌላኛው ለዚህ ማህበር ደማቅ አሻራ ያስቀመጡ እናት ናቸው። እሳቸውም ማህበሩ ህጋዊ እውቅና እንዲያገኝ ከአቶ ታደሰ ቢተው እና ከባለራዕይ ወጣቶች ጋር ብዙ ደክመዋል። ለአረጋውያን ወላጆቻችን የሚደረገውን ድጋፍ ተዘዋውረው አድርሰዋል። በዓመት ሶስት ጊዜ የሚደረጉ የበዓል ዝግጅቶች ላይ ምግብ በማብሰል እና በማስተናገድ ጉልህ ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን ተወጥተዋል። እስከ አሁንም ከማስተማር ስራቸው ጎን ለጎን ለማህበሩ ስራ አስፈላጊ በሆኑበት ጊዜ ሁሉ ለአረጋውያን ወላጆች የቻሉትን ያደርጋሉ።
ከአቶ ታደሰ ቢተው ህልፈተ ህይወት በኋላም በከተማው ውስጥ አንቱ የተባሉትና ከውጭ ሁነውም ማህበሩን በተለያየ መንገድ ሲደግፉ የነበሩት አቶ ጌታሁን ብርሃን ማህበሩን በላቀ ማስተዋል እና በጎነት በመምራት ላይ ናቸው። እኚህ አባትም ያለባቸው ማህበራዊ የስራ ጫና ሳይበግራቸው ያለ ምንም ክፍያ ባላቸው ጊዜ ሁሉ አረጋውያን ወላጆችን በመደገፍ ላይ ያሉ ከቅን ልቦና የመነጨ አሻራቸውን በማስቀመጥ ላይ ያሉ አባት ናቸው።
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2013