በዓልን አስታኮ ለሁለት ቀን የተንበሸበሽንበት ውሃ መምጣት ካቆመ አንድ ወር አለፈው። ለህይወት መሰረት የሆነው ውሃ እንኳን ለወር ለአንድ ቀንም ሲታጣ ነፍስ ያስጨንቃል። የሚጠጣ ብቻ ሳይሆን የሚበላው ምግብ የሚሰራው፣ የሚለበሰው ልብስ እና የሚበላበት ዕቃ የሚታጠበው በውሃ ነው። ውሃን ማጣት ከባድ ነው የሚሉት በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ልዩ ስሙ ባሸዋም ትምህርት ቤት አካባቢ የሚኖሩት ወይዘሮ አማረች አስፋው ናቸው።
እንደ ወይዘሮ አማረች ገለፃ፤ ውሃ እጅግ አስፈላጊ ነው። ይህን እጅግ አስፈላጊ የሆነውን በተፈጥሮ የተገኘውን ውሃ አክሞና አስተካክሎ ወደ የቤቱ የሚያደርሰው ተቋም ምስጋና ይገባዋል። ነገር ግን ከምስጋናው በሻገር ማስተካከል ያለበት ጉዳይ አለ ይላሉ። ባሸዋም ትምህርት ቤት አካባቢ ውሃ ለቀናትና ለሳምንታት ውሃ ሳይመጣ የሚቆይበት ሁኔታ መኖሩን ይናገራሉ።
በተቃራኒው እሳቸው በሚኖሩበት አካባቢ ከመንገዱ ተሻግሮ ላሉ ሰፈሮች በሳምንት ሁለትና ሶስት ቀን ውሃ እንደሚያገኙ ገልጸዋል። ከዋናው መንገድ ወዲህ ያሉ የቅርብ ጎረቤቶቻቸውም በሳምንት በትክክል ያለምንም መቋራረጥ አንድ ወይም ሁለት ቀን ያገኛሉ የሚሉት ወይዘሮ አማረች፤ እነርሱ ግን እኩለ ሌሊት በሳምንት አንድ ቀን ለዛውም ውሃው ስለሚቆራረጥ በበቂ መጠን እያገኙ አለመሆናቸው ቅሬታ የፈጠረባቸው መሆኑን ይገልፃሉ።
‹‹በሳምንት ውሃ ማግኘት ብርቅ ሆኖብናል። ሳምንት ብቻ ሳይሆን ወር ጠብቆ የሚመጣው ውሃ የሚገኘው ሌሊት ለዚያውም በትንሹ እየተቆራረጠ በመሆኑ ለሳምንት የሚሆን በቂ ውሃ ሳንቀዳ ተመልሶ እየሄደ እየተሰቃየን እንገናኛለን›› ይላሉ። ይህ ለአንድ እና ለሁለት ወር በተከታታይ ውሃ የማግኘት ችግር ከሁለት ዓመት በፊትም አጋጥሟቸው እንደነበር አስታውሰው፤ የአካባቢው ሰዎች ተሰባስበው ወደ አዲስ አበባ ከተማ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ቅርንጫፍ ወደ አዲስ ከተማ የውሃና ፍሳሽ ቢሮ በህብረት ሄደው መጠየቃቸውን ያስታውሳሉ።
እንደ ወይዘሮ አማረች ገለፃ፤ የተሰጣቸው ምላሽ እናስተካክላለን ለጊዜው አንድ መሳሪያ (ፓምፕ) ተቃጥሏል የሚል ነበር። ‹‹ታገሱን›› ተብለው በክረምት የተሻለ አገልግሎት አግኝተዋል። ነገር ግን ከሁለት ዓመት ወዲህ ችግሩ አልተፈታም። በተለይ ሚያዚያና ግንቦት ላይ ያለው የውሃ መቆራረጥ ችግር ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም። በተደጋጋሚ የእነርሱ አካባቢ ተለይቶ በፈረቃቸው ቀን ውሃው አይገኝም። ውሃው ቢመጣም የውሃ ግፊት አነስተኛ በመሆኑ የሚወርደው በትንሹ ነው። የውሃ ማጠራቀሚያ ታንከር ያለው ሰውም ውሃ ወደ ታንከሩ አይሄድለትም። በርሜል ያለው ሰውም ውሃውን በጎማ ልቅዳ ብሎ ቢያስብ የውሃው መጠን ጎማ ውስጥ ተገፍቶ በርሜል ጋር አይደርስም። በባልዲ ተመላልሰው በመቅዳት አንድ በርሜል ለመሙላት ሙሉ ሌሊቱን ቁጭ ብለው ማደር ግዴታ እንደሆነባቸው ቅሬታቸውን በምሬት ገልፀው፤ ይህንን ችግር ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጠው የሚመለከተውን አካል ጠይቁልን ብለዋል።
እኛም ወደ አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ወይዘሮ ሰርካለም ጌታቸውን ስለጉዳዩ ጠይቀናል። እንደ ወይዘሮ ሰርካለም ገለፃ፤ ስርጭቱ በሳምንት ሁለት ቀን የሆነበት ምክንያት በእርግጥም የውሃ እጥረት ችግር በመኖሩ ነው። ነገር ግን በቅርቡ በቀን 90ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ ወደ መስመር እንዲገባ ተደርጓል። ይህ ተደራሽ የሚያደርጋቸውና ፈረቃውን የሚያሻሽልባቸው አካባቢዎች አሉ። አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የህብረተሰቡን የውሃ ፍላጎት ለማርካት የሚሰራው ያለ እረፍት ለ24 ሰዓት ነው። በቂ ውሃ ቢሆን ኖሮ እንዲሁ መልቀቅ ቀላል ነው።
በሳምንት አንድ ጊዜ ብቻ ውሃ የሚገኘው ደግሞ በአካባቢው የውሃ እጥረት በመኖሩ ረዥም ርቀት ተገፍቶ ቦታው ስለማይደርስ ነው። በተጠየቀበት ማለትም በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ባሸዋም ትምህርት ቤት፣ ከጀነራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ጀርባ እና አስኮ አካባቢ ያለውን ሁኔታ አጣርተን እውነት በወር ውሃ የማይገኝ ከሆነ ችግሩን የሚያቃልሉ መሆኑን ተናግረዋል።
ከ10 ሜትር ርቀት በላይ ባለው የውሃ ማጠራቀሚያ ታንከር ላይ ውሃው እንዲደርስ ግፊት ማድረግ የተቋሙ ግዴታ አይደለም የሚሉት ወይዘሮ ሰርካለም፤ ሰዎች የውሃ አቅም ማነስ መኖሩን መገንዘብ አለባቸው ይላሉ። ይህንን ችግር ለማቃለል እየተሰራ ነው ፤ ለምሳሌ በቅርቡ ከአቃቂ ክፍለ ከተማ 90ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ ገብቷል። ይህ ወደ ሥርጭት እንዲሄድ ለማድረግና ችግሩ ወደ ከፋበት ቦታ እንዲደርስ ጥረት የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል።
ተቋሙ ህብረተሰቡን ለማገልገል ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል። አሁንም ችግሩ አለ። በተባለበት አካባቢ የውሃ መቆራረጡ የከፍ ከሆነ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት በማሳወቅ ቦታው ላይ ያለውን ችግር አይቶ የሚፈታ ይሆናል በማለት መልስ ሰጥተዋል።
ከጎዳና ወዲህና ወዲያ ውሃ እያለ እኛ አካባቢ ግን ውሃ የለም በሚል ለቀረበው ሃሳብም፤ ወይዘሮ ሰርካለም ሲመልሱ ሰዎች የውሃ ፍሰትን ጉዳይ ስለማይረዱ የሚቀርብ ጥያቄ መሆኑን ይገልፃሉ። ከአካባቢያቸው ከተቆፈረ ጉድጓድ የሚያገኙ ሰዎች አሉ። ጉድጓዱ ቅርባቸው ቢሆንም እንኳ ውሃው ቁልቁል ስለሚሄድ ከቁልቁለት ሲሞላ እየተገፋ ወደ ላይ ሲመለስ እነርሱ ጋር ይደርሳል። በዚህ ጊዜ ሃይል ላይኖረው ይችላል። ከፍ ያሉ ቦታዎች ላይ ብዙ ጊዜ እጥረት ያጋጥማል። ምክንያቱ ደግሞ የውሃ ግፊት ማነስ ነው በማለት የችግሩን ምንጭ ያስረዳሉ።
አንዳንዴ በቅርብ ያለ አካባቢ ከሌላ ቦታ ውሃ እንዲያገኝ የሚደረግበት ሁኔታ መኖሩንም በማውሳት፤ ለምሳሌ ዘውዲቱ አካባቢ ያለውን ሁኔታ በመጥቀስ ያስረዳሉ። በአንዱ ጎዳና በኩል የሚያገኙት ከለገዳዲ የውሃ ማጠራቀሚያ ጣቢያ ሲሆን ሌላው አቅጣጫ ያሉት ደግሞ ከአቃቂ የጉድጓድ ውሃ ያገኛሉ። ከለገዳዲ በኩል ያለው ቀጥታ ስለሚሄድ የመብራት መቆራረጥ ቢኖርም ውሃ ሁልጊዜ ይገኛል። ከአቃቂ የሚገኘው ግን በግፊት የሚገኝ በመሆኑ የኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥ ሲያጋጥም አብሮ ውሃው ይቋረጣል። ስለዚህ ሁልጊዜ ‹‹ሌላ ሰፈር በቅርብ ርቀት ውሃ አለ። እኛ ግን ውሃ የለንም›› የሚል ተደጋጋሚ ጥያቄ ይቀርባል። እነዚህ ሰፈሮች ከለገዳዲ ውሃ ያግኙ ከተባለ ደግሞ በጣም ትልቅ ገንዘብ ያስፈልጋል። ስለዚህ ሰዎች እነዚህን ጉዳዮች ሊረዱ እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
እንደ ወይዘሮ ሰርካለም ገለፃ፤ መጪው ጊዜ የተሻለ ይሆናል። ምክንያቱም የለገዳዲ ሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ በቀጣይ ዓመት ይጠናቀቃል። ሌሎችም የሚጠናቀቁ ሥራዎች ስለሚኖሩ ችግሩ ይቃለላል። አንድ ፓምፕ ከተቃጠለ ወጥቶ ተጠግኖ ሥራ እስኪሚጀምር አሥራ አምስት ቀን ይፈጃል። በዚህ ጊዜ ችግሩ ሊያጋጥም ስለሚችል ዘላቂ መፍትሄ እስኪሰጥ ድረስ ችግሩን መገንዘብ ያስፈልጋል ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።
በዚህ ገፅ ላይ አንባቢያን በሚፈልጉት ጉዳይ ላይ ጥያቄ የሚያቀርቡበት እና እኛም የሚመለከተውን አካል መልስ ጠይቀን የምናስነ ብብበት ሲሆን፤ ማንኛውም ሰው በስልክ ቁጥር 0111264326 በመደወል ጥያቄ እና አስተያየት ማቅረብ ይቻላል።
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2013