በዛሬው የእሁድ ገፅ የስፖርት አምዳችን አፍሪካ ውስጥ በቀዳሚነት መነጋገሪያ ስለሆኑ የሳምንቱ የእግር ኳስ ዜናዎች ይዳስሳል። በተለይ በዚህ ሳምንት በዋናነት ትኩረት ስበው ከነበሩ መነጋገሪያ እግር ኳሳዊ አጀንዳዎች መካከል የብዙኃኑን ቀልብ ይዞ የነበረው የቀድሞው የናይጄሪያ የተከላካይ መስመር ተጫዋች ታይዎ ኦንጆቤ ዜና እረፍት ነበር ።
ናይጄሪያ
ለናይጄሪያ የእግር ኳስ ብሄራዊ ቡድን ለበርካታ ዓመታት በተከላካይ መስመር ተሰልፎ ተጫውቷል። ኢንተርናሽናል ተጫዋች ታይዎ ኦንጆቤ። በፕሮፌሽናል ተጫዋችነቱ አገራቸውን ካስጠሩት ጎራ የሚመደብ ነው። በዚህ ብቻ አያበቃም ኳስ ጨዋታ ይብቃኝ ብሎ ጫማውን ከሰቀለ በኋላ በናይጄሪያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ውስጥ በዋና ፀሐፊነት ለዓመታት ሠርቷል። ከድል እስከ ሽንፈት፤ ከመልካም ጊዜዎች ፈተና እስከበዛባቸው ቀናቶች ለሚወዳት አገሩ በሙያው ደፋ ቀና ብሏል። ሰሞኑን ግን የቢቢሲ የአፍሪካ ስፖርት ድረ ገፅ በደቡብ ምዕራቧ የናይጄሪያ ግዛት ኢባዳን አንድ መጥፎ ዜና ይዞ ብቅ ብሏል። ታይዋን በ65 ዓመቱ ይህችን ምድር መሰናበቱን አስነብቧል። የቀድሞው የእግር ኳስ ጠበብት ድንገት ባጋጠመው ህመም በሆስፒታል እና በመኖሪያ ቤቱ ህክምናውን ሲከታተል ቆይቶ በመጨረሻ በሞት ተሸንፏል። ኦንጆቤ በዋና ፀሐፊነት የናይጄሪያን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከማገልገሉ አስቀድሞ ለፕሬዚዳንትነት ሁለት ጊዜ ተወዳድሮ በባላጋራዎቹ ሽንፈት ገጥሞት ነበር። ይሁን እንጅ በአገሩ ስፖርት ላይ ቁልፍ ቦታ የሆኑ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ በመቀመጥ አገልግሏል።
ካሜሮን
ይህኛው የአፍሪካ ዜና ደግሞ ወደ ካሜሮን ይወስደናል። በተለይም በጉብዝናው ዘመን ዓይኖች ሁሉ ከርሱ ላይ ወደማይነሱት፣ ግብ አዳኙ፣ የአራት ጊዜ የአፍሪካ ኮኮብ ተጫዋች ወደሆነው ሳሙኤል ኢቶ ይዞን ይጓዛል። እንደሚታወቀው ይህ ምትሃተኛ አፍሪካዊ ኮኮብ የእግር ኳስ ዘመኑን ሳይጨርስ ዝቅተኛ ሊግ ወዳላቸው የአረብ አገራት እየተዘዋወረ በመጫወት ላይ ይገኛል። ከቱርክ ክለብ ተዘዋውሮ ወደ ኳታር ከመጣ በኋላ ኳታር ኤስ ሲ ለተባለ ክለብ በመጫወት ላይ ይገኛል። ክለቡ ከሁለት ጨዋታዎች በላይ በጉዳት ምክንያት ሳይሰለፍ ቀርቷል። በዓመቱ መጨረሻ ላይም ከዚህ ቡድን ጋር ያለው ኮንትራት ይጠናቀቃል። ቢቢሲ አፍሪካ ስፖርት ድረ ገፅ ሰሞኑን በማስታወቂያ ሥራ በሳውዝ አፍሪካ በማከናወን ላይ የሚገኘውን ሳሙኤል ኢቶን ስለ ወደፊት የእግር ኳስ ህይወቱ አነጋግሮት ነበር። በዚህም አሁን ከሚገኝበት ክለብ ጋር ያለው የኮንትራት ውል በዓመቱ መረሻ ቢጠናቀቅም እግር ኳስ የማቆም ሃሳብ እንደሌለው ገልጿል። የ37 ዓመቱ ጎልማሳ ኢቶ «በኳታር ደስተኛ ነኝ በዚህ እድሜዬ የመጫወት እድል ማግኘቴ መልካም ነው። በተጓዳኝ ትምህርትም እየተከታተልኩ ነው። ከፍላጎቴ ጋር ስለማይጋጭም አሁን ላይ እግር ኳስ የማቆም ሃሳብ የለኝም ኳታር ተመችቶኛል» በማለት የዓመቱ መጨረሻ ላይ ጫማ የመስቀል ሃሳብ እንደሌለው አሳውቋል። ኢቶ ከሰጠው አስተያየት መረዳት የሚቻለው በቅርቡ ጫማ የመስቀል ፍላጎት እንደሌለው ነው። በተለይ አሁንም ድረስ ጥሩ ብቃት ላይ እገኛለሁ ብሎ ያስባል። ለዚህም ነው አቋሜ ሲገድበኝ ብቻ ነው ለማቆም የምገደደው ሲል አስተያየቱን የሰጠው። ለተጨማሪ አንድ ዓመት በዚያው በኳታር እንደሚቆይ ማረጋገጫ ሰጥቷል። «እግር ኳስ ለኔ ሁሉም ነገሬ ነው እስከቻልኩት ለመጫወት እሞክራለሁ። ሆኖም ግን ሁኔታዎች ከገደቡኝ ለማቆም እገደዳለሁ» በማለት አስተያየቱን የሰጠው የቀድሞው የባርሴሎና የፊት መስመር ኮኮብ ሳሙኤል ኢቶ በእንግሊዝ እንዲሁም በበርካታ የዓለም አገራት በሚገኙ ክለቦች የመጫወት እድል ማግኘቱ የእግር ኳስ ህይወቱን እንዳሰመረለት ይናገራል። በተለይ ረጅሙን ጊዜ በስፔኑ ባርሴሎና ክለብ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2004 እስከ 2009 መቆየት ችሏል። በዚህም ከምትሃተኛው ሮናልዲንሆ ጎቾ ጋር የቡድን አጋር ሆኖ ሦስት የላሊጋ እና ሁለት የአውሮፓ ሻምፒዮና ዋንጫዎችን በስኬት ታሪክ መዝገቡ ላይ አስቀርጿል። ኢቶ በአፍሪካ ዋንጫ 18 ጎሎችን አስቆጥሯል። ለአገሩ ካሜሮንም 54 ጎሎችን በማግባት ክብረ ወሰኑን በእጁ አስገብቷል። ከዚህም ሌላ በ2000 እና በ2002 የአፍሪካ ዋንጫንም አንስቷል።
አይቮሪ ኮስት-ኢትዮጵያ
አይቮሪኮስታዊው የቀድሞ የቼልሲ እና የዝሆኖቹ ኮኮብ ዲዲዬ ድሮግባ በአፍሪካ የቢዝነስ እና ጤና ፎረም ጋባዥነት በአዲስ አበባ ተገኝቶ ነበር። አዲስ አበባ በሚ ገኘው ሀያት ሆቴል በመገኘት አፍሪካ ውስጥ በማህበራዊ እና ጤና ዘርፎች እየሠራ የሚገኘውን ሥራ ማበረታታቱን ሶከር ኢትዮጵያ በድረ ገፁ አስነብቧል። ተጫዋቹ ከአድናቂዎቹ ጋርም ተገናኝቷል። ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣ በቅድሚያ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ጋር ተወያይቷል ያለው ድረ ገፁ የገጠመው አቀባበል ፍፁም ያልጠበቀው እንደሆነ መናገሩን አስነብቧል። «እዚህ ስመጣ የመጀመርያዬ ነው። ነገር ግን እጅግ ብዙ አፍቃሪ እንዳለኝ ተረድቻለሁ» በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል። «አፍሪካ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ የመደመጥ እና የመታየት እድል አላት» በማለት ተስፋውን ተናግሯል። «በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተበታተኑ ልጆቿ አቅማቸውን አጎልብተው፣ ተምረው፣ ሰልጥነው እና ሰርተው ተመልሰዋል። አሁን በጋራ ሆነን አፍሪካን ተባብረን አይዞሽ ልንላት እና ልንገነባት ይገባል» የሚል ጠንካራ አመለካከቱን አንፀባርቋል። ‹‹በጋራ ከሆንን የማንችለው ነገር የለም›› በማለት አብሮ የመሥራት አስፈላጊነትን ገልጿል። ከእግር ኳስ ራሱን ካገለለ በኋላ ራሱ ባቋቋመው ፋውንዴሽን አማካኝነት በትምህርት እና ጤና ላይ አተኩሮ እየሠራ እንደሆነ የተናገረው ድሮግባ በሀገሩ ትምህርት ቤት ከፍቶ ሙሉ ለሙሉ የዲጂታል የትምህርት አሰጣጥ ተግባራዊ እንዲሆን አስችሏል። ከዚህ በተጨማሪም የእናቶች እና ህፃናት ጤና ላይ ትኩረት አድርጎ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነም ገልጿል። ወደፊትም በትምህርት እና ጤና ላይ ይበልጥ አተኩሮ መሥራት እንደሚፈልግ የገለፀው ድሮግባ ሁሉንም ነገር ማድረግ የሚቻለው እንደ አንድ ሆኖ በትብብር በመሥራት እንደሆነ ተናግሯል።
የፊፋ እግርኳስ ልማት
ሶከር ኢትዮጵያ በድረ ገፁ እንዳስነበበው የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ የበላይ አስተዳዳሪ ፊፋ በ2016 ለጀመረው ‹‹ፊፋ ፎርዋርድ›› የእግርኳስ ልማት ማስፈፀሚያነት በተለያዩ የዓለማችን ሀገራት ፅህፈት ቤቶችን መክፈቱን ቀጥሏል። 10ኛው ቢሮውንም በአዲስ አበባ ከፍቷል። የምስራቅ አፍሪካን የእግርኳስ ልማት እንቅስቃሴ ለመከታተል ያለመው ይህ የክፍለ አህጉር ፅህፈት ቤት ከደቡብ አፍሪካ እና ሴኔጋል በመቀጠል በአፍሪካ ሦስተኛውነው። ቦሌ አካባቢ ፍሬንድሺፕ ሞል ጀርባ በሚገኘው አፎሚ ህንፃ ላይ ይገኛል። በኪራይ የተገኘው ይህ ቢሮም ሙሉ ወጪው በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ይሆናል። የቢሮውን መከፈት በማስመልከት ባለፈው ሰኞ ቀትር ላይ በተዘጋጀው የማብሰሪያ መርሐ ግብር ላይ የፊፋው ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ፣ የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ሒሩት ካሳው፣ የፊፋ ዋና ፀሐፊ ፋትማ ሳሞራ፣ የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ርስቱ ይርዳው፣ የካሬብያን እና አፍሪካ እግር ኳስ ልማት ዳይሬክተር ቬሮን ሞሴንጎ-ኦምባ እንዲሁም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ ጂራ ተሳትፈዋል። በመርሐ ግብሩ መጠናቀቂያ ላይም የካፍ ፕሬዚዳንት አህመድ አህመድ ተገኝተዋል። የቢሮውን መከፈት የሚያበስረው ሪባን በጂያኒ ኢንፋንቲኖ እና ዶክተር ሒሩት ካሳው ከተቆረጠ በኋላ በቬርን ሞሴንጎ-ኦምባ አማካኝነት በተጀመረው መርሐ ግብር የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ ጂራ ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር የፅህፈት ቤቱን መከፈት ፋይዳ ገልፀዋል። ‹‹እንኳን ወደ ሁለተኛ ቤታችሁ እና ወደ አፍሪካዋ ዋና ከተማ አዲስ አበባ እንዲሁም የአፍሪካ እግር ኳስ አባት ይድነቃቸው ተሰማ ሀገር ኢትዮጵያ በሰላም መጣችሁ። ወደ አመራርነት ከመጣን 7 ወራት ባስቆጠርንበት በዚህ ወቅት በሀገራችን፣ በዞናችን እና በአህጉራችን የእግር ኳስ ልማት ላይ ለመሥራት ጥሩ እድል ላይ እንገኛለን። የዚህ ቢሮ መከፈትም የምናልመው የረጅም ጊዜ እቅድን ለማሳካት ከማገዙ በተጨማሪ ፊፋ ይበልጥ ወደ እኛ ቅርብ እንዲሆን የሚያደርግ ነው። መንግሥታችን የኪራይ ወጪውን በመሸፈን ለቢሮው መከፈት ትልቁን ሚና ተጫውቷል። ለዚህም መንግሥታችንን በተለይም የስፖርት ኮሚሽን እና ኮሚሽነሩ ርስቱ ይርዳውን ማመስገን እፈልጋለሁ›› በማለት መልካም የሥራ ጊዜን ተመኝተው ንግግራቸውን ቋጭተዋል። በመቀጠል ንግግር ያደረጉት የፊፋ ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ አዲስ አበባ በመገኘታቸው እና ቢሮውን በመመረቃቸው ደስታቸውን ገልፀዋል።
አያይዘውም በአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ተገኝተው ንግግር ስለማድረጋቸው እና ስለተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድም ገለፃ አድርገዋል። ‹‹ትላንት በአፍሪካ መሪዎች ፊት ንግግር አድርጌ ነበር። ስለ እግር ኳስ ኃያልነት ገልጫለሁ። እንዴት እግር ኳስ አንድነትን እንደሚፈጥር፣ ከባቢን እንደሚቀይር ተናግሬያለሁ›› ያሉት ፕሬዚዳንት ጂያኒ ከአፍሪካ ኅብረት ጋርም ካፍን ባካተተ መልኩ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል። ዋና ዋና ነጥቦቹም በአንደኝነት መልካም አስተዳደርን ማስፈን እና ሙስናን መታገል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሲሆን፣ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አሳሳቢ የሆነው ጉዳይ ሙስና መሆኑ ተገልጿል። ይህንን መታገል እና ለማስቆም መሞከር ይኖርብናል ብለዋል። ሁለተኛው የሚያተኩረው የስታዲየሞች ፀጥታ እና ደህንነት ላይ በመሆኑ «ሰዎች ከዚህ በኋላ እግርኳስ ለመከታተል ወጥተው መሞት የለባቸውም» የሚል አቋም ተይዟል። ሶስተኛው እና ዋናው ነጥብ ደግሞ እግር ኳስን በትምህርት ቤቶች ማስፋፋት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ነው። ፊፋ በዓለማችን የሚገኙ ትምህርት ቤቶች እና 700 ሚሊዮን ህፃናትን ማዳረስ ይፈልጋል። ለዚህም 11 ሚሊዮን ኳሶችን እያከፋፈለ ይገኛል። በእግር ኳስ አማካኝነት ትምርህት እንዲያገኙ 100 ሚሊዮን ዶላር ፈሰስ ተደርጓል።
አዲስ ዘመን የካቲት 10/2011
ዳግም ከበደ